“እኛ” እና “ሥላሴ”ን ምን አገናኛቸው?
© ኡስታዝ አቡ ሐይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
” قُلْ هُوَ اللَّهُ أَحَدٌ * اللَّهُ الصَّمَدُ * لَمْ يَلِدْ وَلَمْ يُولَدْ * وَلَمْ يَكُنْ لَهُ كُفُوًا أَحَدٌ ” سورة الإخلاص 4-1
“በል፦ እርሱ አላህ አንድ ነው። አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። አልወለደም፤ አልተወለደምም። ለርሱም አንድም ብጤ የለውም።”
(ሱረቱል ኢኽላስ 1-4)፡፡
በዚህ ምድር ላይ የፈጣሪ አምላካችንን የአላህን ፍጹማዊ አንድነት የሚሰብክ ብቸኛ ሃይማኖት ቢኖር፡ ኢስላም ብቻ ነው ማለት ማጋነን አይሆንም፡፡ የሙስሊሞች እምነትም ብዙ ጊዜ ጎልቶ የሚታየው ‹‹አላህ አንድ ነው!›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ተመራማሪዎች በዙና፡ ቅዱስ ቁርኣንን ሲመረምሩ፡ በውስጡም እንደ ሥላሴ አምላኪዎች የአላህን ሶስትነት የሚመሠክር ጥቅሶች በብዛት እንዳገኙበት ገለጹ!፡፡ ምንድነው የተገኘው ስንላቸው፡- አላህ እራሱን ‹‹እኛ›› ብሎ ነው የሚገልጸው፡፡ እሱ ‹‹አንድ›› ብቻ ከሆነ ለምን ‹‹እኛ›› በማለት በብዙ ቁጥር ይጠቀማል? አሉን፡፡
ወደ ምላሹ ከመግባታችን በፊት፡ ሁለት ነገሮችን መጠቆም እወዳለሁ፡-
1ኛ፡- አላህ በቅዱስ ቁርኣኑ ውስጥ የሱን ማንነት በተመለከተ፡ በአራት መንገዶች ገልጾልናል፡፡ ይህንን ማወቁ ለመልሱ አጋዥ ይሆናል፡፡ እነዚህም መንገዶች፡-
ሀ. የመጀመሪያ መደብ ነጠላ ስያሜ፡- ይህ በእንግሊዘኛው፡ ‹‹First person singular term›› የሚባለው ነው፡፡ በብዙ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ላይ ጌታ አላህ የራሱን ማንነት ሲያስተዋውቀን ‹‹እኔ›› እያለ ይናገራል፡፡ ልምሳሌ ያህል፡-
“ባሮቼን እኔ መሓሪው አዛኙ #እኔው ብቻ መኾኔን ንገራቸው፡፡ ቅጣቴም እርሱ አሳማሚ ቅጣት መኾኑን (ንገራቸው)፡፡”
(ሱረቱል ሒጅር 49-50)፡፡
“ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ መላእክትን ከራእይ ጋር በፈቃዱ ያወርዳል፤ (ከሐዲዎችን በቅጣት) አስጠንቅቁ፤ እነሆ #ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም ፍሩኝም ማለትን (አሳታውቁ በማለት ያወርዳል)።” (ሱረቱ-ነሕል 2)፡፡
“#እኔ አላህ እኔ ነኝ፣ ያለ እኔ አምላክ የለምና ተገዛኝ፤ ሶላትንም (በርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ።” (ሱረቱ ጣሀ 14)፡፡
ለ. የሁለተኛ መደብ ነጠላ ስያሜ፡- ይህ ደግሞ በእንግሊዘኛው፡ ‹‹Second person singular term›› የሚባለው ነው፡፡ በብዙ የቁርኣን ክፍሎች ላይ፡ ጌታ አላህ እኛ እንድንማጸነውና እንድንለምነው እሱን ‹‹አንተ›› እያልን እንድንጠራው፡ እራሱን ‹‹አንተ›› በማለት ያስተዋውቃል፡፡ ለምሳሌ፡-
“…(በሉ)፡- ጌታችን ሆይ! ብንረሳ ወይም ብንስት አትያዘን፤ (አትቅጣን)፡፡ ጌታችን ሆይ! ከባድ ሸክምን ከእኛ በፊት በነበሩት ላይ እንደጫንከው በእኛ ላይ አትጫንብን፡፡ ጌታችን ሆይ! ለኛም በርሱ ችሎታ የሌለንን ነገር አታሸክመን፡፡ ከእኛም ይቅርታ አድርግ ለእኛም ምሕረት አድርግ፡፡ እዘንልንም፤ ዋቢያችን #አንተ ነህና፡፡ በከሓዲዎች ሕዝቦች ላይም እርዳን፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 286)፡፡
“(ሙሐመድ ሆይ!) በል- የንግሥና ባለቤት የሆንክ አላህ ሆይ! ለምትሻዉ ሰዉ ንግሥናን ትሰጣለህ፤ ከምትሻዉም ሰዉ ንግስናን ትገፍፋለህ፤ የምትሻዉንም ሰዉ ታልቃለህ፤ የምትሻዉንም ሰዉ ታዋርዳለህ። መልካም ነገር ሁሉ በእጅህ (በችሎታህ) ነው፤ #አንተ በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነህና።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 26)፡፡
“ሰማያትንና ምድርን የፈጠርክ፣ ሩቁንም ቅርቡም ዐዋቂ የኾንክ አላህ ሆይ! #አንተ በባሮችህ መካከል በዚያ በርሱ ይለያዩበት በነበሩት ነገር ትፈርዳለህ፤ በል።” (ሱረቱ-ዙመር 46)፡፡
ሐ. የሶስተኛ መደብ ነጠላ ስያሜ፡- ይኸኛው በእንግሊዘኛው፡ ‹‹Third person singular term›› የሚባለው ነው፡፡ ሙስሊሞች ስለ አምላካቸው አላህ ሲያስተምሩና ሲሰብኩ፡ የሱን ስሞችና ባሕሪያትን ለሰው ሲያስተዋውቁ፡ ‹‹እሱ›› ጌታችን አላህ ማለት እንዲህ ነው! እያሉ እንዲያስተምሩ፡ በቅዱስ ቁርኣኑ ላይ እራሱን በ‹‹እሱ››ነት ይገልጻል፡፡ ያ ማለት፡- ስለ አላህ፡- እሱ ማለት እንዲህ ነው ብላችሁ ተናገሩ ለማለት እንጂ፡ በቁርኣኑ ላይ ‹‹እሱ›› እያለ ስለ አላህ እየተናገረ ያለው አካል ሌላ አካል ነው ለማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡-
“እንደዚሁ ከበፊትዋ ብዙ ሕዝቦች በእርግጥ ያለፉ ወደ ሆነችው ሕዝብ፥ እነርሱ በአልረሕማን የሚክዱ ሲሆኑ፥ ያንን ወደ አንተ ያወረድነውን ቁርአን በነርሱ ላይ ታነብላቸው ዘንድ ላክንህ፤ #እርሱ (አልረሕማን) ጌታዬ ነው፤ #ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ #በርሱ ላይ ተጠጋሁ፤ መመለሻየም #ወደርሱ ብቻ ነው በላቸው።” (ሱረቱ-ረዕድ 30)፡፡
“#እርሱ ያ የፈጠራችሁ ለናንተም መስሚያና ማያዎችን ልቦችንም ያደረገላችሁ ነው፤ ጥቂትንም አታመሰግኑም በላቸው። እርሱ ያ በምድር ላይ የበተናችሁ ነው፤ ወደርሱም ትሰበሰባላችሁ በላቸው።” (ሱረቱል ሙልክ 23-24)፡፡
“በል፦ #እርሱ አላህ አንድ ነው። አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው። አልወለደም፤ አልተወለደምም። #ለርሱም አንድም ብጤ የለውም።” (ሱረቱል ኢኽላስ 1-4)፡፡
መ. የመጀመሪያ መደብ ብዜት ስያሜ፡- ይኸኛው በእንግሊዘኛው፡ ‹‹ First person Plural term›› የሚባለው ነው፡፡ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በብዛት ጎልቶ የሚታየው ይኸኛው ክፍል ነው፡፡ ጌታችን አላህ፡- ለባሮቹ ደረገውን ውለታ እና መለኮታዊ ክብሩን የሚያመላክቱ ስራዎችን ለመግለጽ እራሱን በ‹‹እኛ››ነት በመግለጽ፡ ‹‹ሰራን›› ‹‹ፈጠርን›› ‹‹አደረግን›› ‹‹ወሰንን››… እያለ ታላቅነትንና ከበሬታን በሚገልጽ የብዙ ቁጥር ስያሜ ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ፡-
“#እኛ በሰዎች መካከል አላህ ባሳወቀህ ልትፈርድ፣ ወደ አንተ መጽሐፉን በውነት አወረድን፤ ለከዳተኞችም ተከራካሪ አትሁን።” (ሱረቱ-ኒሳእ 105)፡፡
“#እኛ ፈጠርናችሁ፤ አታምኑምን?” (ሱረቱል ዋቂዓህ 57)፡፡
“#እኛ በናንተ ላይ መስካሪ መልክተኛን ወደእናንተ ላክን፡፡ ወደ ፈርዖን መልክተኛን እንደላክን።” (ሱረቱል ሙዘሚል 15)፡፡
2ኛ፡- በዐረብኛ ቋንቋ ህግ መሰረት እኛ የሚለው ቃል፡ ሁለት ትርጉሞችን የያዘ ነው፡፡ እነሱም፡-
ሀ. ብዛትን፡- ይህ የመጀመሪያው ትርጉም ነው፡፡ ከብዙዎች ጋር ሆኖ የሚናገር አካል የሚጠቀምበት ቋንቋ ነው፡፡ አሥር ሰዎች አንድ ላይ በመሆን፡- እኛ መስጂድ ነበርን ማለት ይችላሉ፡፡
ለ. ከበሬታን፡- ይህ ደግሞ ተናጋሪው አካል አንድ (ነጠላ) ብቻ ሆኖ ሳለ፡ ነገር ግን ስለ ራሱ ሲናገር፡ እራሱን በማክበርና በማተለቅ እኛ በማለት ይገልጻል፡፡ ይህ አነጋገር ብዙ ጊዜ ንጉሶች የሚጠቀሙበት ነው፡፡ እኛም ከሰዎች ‹ታዲያስ› የሚል ሰላምታ ሲቀርብልን፡ በአብዛኛው የምንመልሰው መልስ ‹አለን› የሚለውን ነው፡፡ አለን ማለታችን ግን ብዛትን ለማመልከት አይደለም፡፡
ታዲያ ጌታችን አላህ ስለ ራሱ ሲናገር ‹‹እኛ›› እያለ መናገሩ፡ የሱን ታላቅነትና ኃያልነት ለመግለጽ እንጂ፡ እሱ ከአንድ በላይ በተለይም ሶስት መሆኑን ለመግለጽ እንዳልሆነ ከዚህ በታች ባሉት መረጃዎች መሰረት ምላሹን ይከታተሉ፡-
- አንድ በመሆኑ፡- ፈጣሪያችን አላህ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በቀጥታ አነጋገር እሱ አንድ ብቻ መሆኑን በ22 የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች ላይ ነግሮናል፡፡ እኛም ከነዚህ አንቀጾች በመነሳት የሱን ፍጹማዊ አንድነት አምነን ተቀብለናል፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-
“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 163)፡፡
“«በምስክርነት ከነገሩ ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ማነው» በላቸው፡፡ (ሌላ መልስ የለምና) «አላህ ነው፡፡ በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ ነው፡፡ ይህም ቁርኣን እናንተንና የደረሰውን ሰው ሁሉ በርሱ ላስፈራራበት ወደኔ ተወረደ፡፡ ከአላህ ጋር ሌሎች አማልክት መኖራቸውን እናንተ ትመሰክራላችሁን» በላቸው፡፡ «እኔ አልመሰክርም» በላቸው፡፡ «እርሱ አንድ አምላክ ብቻ ነው፡፡ እኔም ከምታጋሩት ነገር ንጹሕ ነኝ» በላቸው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 19)፡፡
“እኔ አምላካችሁ አንድ አምላክ ብቻ ነው ማለት፥ ወደኔ የሚወርድልኝ ቢጤያችሁ ሰው ብቻ፤ ነኝ፤ የጌታውንም መገናኘት የሚፈልግ ሰው፤ መልካም ሥራን ይሥራ፤ በጌታውም መገዛት አንድንም አያጋራ፣ በላቸው።” (ሱረቱል ከህፍ 110)፡፡
ታዲያ ጌታችን አላህ እርሱ ‹አንድ› ጌታ ብቻ መሆኑን እንዲህ በግልጽ ከነገረን፡ ተመልሶ የራሱን ማንነት ሲገልጽ ‹እኛ› በማለቱ ለክብር እንጂ ከአንድ በላይ ነው ብለን ማሰብ እንችላለን? - ብዛትን በመቃወሙ፡- አምላካችን አላህ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ከአንድ በላይ አምላክ አለ የሚሉትን ሰዎች አውግዟቸዋል፡፡ ንግግራቸውም የክህደት ንግግር መሆኑን ገልጾልናል፡፡ ለምሳሌ፡-
ሀ. ሁለት አምላክ የሚሉትን፡-
“አላህ አለ፦ ሁለት አማልክትን አትያዙ፤ እርሱ አምላክ ብቻ ነው፤ እኔንም ብቻ ፍሩ።” (ሱረቱ-ነሕል 51)፡፡
ለ. ሶስት ነው የሚሉትን፡-
“…በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ (አማልክት) ሦስት ናቸው አትበሉም፤ ተከልከሉ ለናንተ የተሻለ ይሆናልና፤ አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው…” (ሱረቱ-ኒሳእ 171)፡፡
“እነዚያ አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፤ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ፣ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል።” (ሱረቱል ማኢዳህ 73)፡፡
ሐ. ከሶስት በላይ የሚያመልኩትን፡-
“የእስር ቤት ጓደኞቼ ሆይ! የተለያዩ አምላኮች ይሻላሉን ወይንስ አሸናፊው አንዱ አላህ?” (ሱረቱ ዩሱፍ 39)፡፡
ታዲያ በነዚህ አንቀጾች ላይ፡ ጌታችን አላህ፡ ሁለት፣ ሶስትና ከዛ በላይ አማልክት አሉ በማለት የሚያመልኩት የሃይማኖት አካላትን ካወገዛቸውና፡ ስራቸውም የኩፍር ስራ መሆኑን ከገለጸ፡ እንዴት ስለራሱ ‹‹እኛ›› ብሎ መናገሩን ከአንድ በላይ ነው ለሚለው መረጃ አድርገን ማቅረብ እንችላለን? - ምክንያታዊነቱ፡- ጌታችን አላህ በቅዱስ ቁርኣን ላይ፡ የዚህ ዓለም አስተዳዳሪና አምላክ አንድ እንጂ፡ ከአንድ በላይ ሊሆን እንደማይችል አሳማኝ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡ እሱም፡- ይህን ዓለም የሚመራው ኃይል፡ ሰዎች እንደሚሉት ከአንድ በላይ ቢሆን ኖሮ፡ በመሪዎቹ መሐከል የሀሳብ ልዩነት ይፈጠርና የዚህ ዓለም ስርዓት ቅጥ ያጣ ይሆናል፡፡ የዛኔም የሰማይና የምድር ስርዓት ይናወጣል፡፡ በመሪዎቹ መሐል የርስ በርስ ሹክቻ ይፈጠርና ሁሉም የራሱን ፍጥረት ይዞ ለብቻው ይገለል ነበር፡፡ አንዱ በአንዱም ላይ የበላይ ለመሆን ትግል ይጀመር ነበር በማለት ከአንድ መሪ ውጪ ዓለማችን ስርዓት ሊኖራት እንደማይችል አስረድቶ የሱን አንድነት ይገልጻል፡፡ ቀጣዩን አንቀጽ እንመልከት፡-
“በሁለቱ (በሰማያትና በምድር) ውስጥ ከአላህ ሌላ አማልክት በነበሩ ኖሮ በተበላሹ ነበር፤ የዐርሹ ጌታ አላህም ከሚሉት ሁሉ ጠራ።” (ሱረቱል አንቢያእ 22)፡፡
“አላህ ምንም ልጅን አልያዘም (አልወለደም)፡፡ ከእርሱም ጋር አንድም አምላክ የለም፡፡ ያን ጊዜ (ሌላ አምላክ በነበረ) አምላክ ሁሉ በፈጠረው ነገር በተለየ ነበር፡፡ ከፊላቸውም በከፊሉ ለይ በላቀ ነበር፡፡ አላህ ከሚመጥኑት ሁሉ ጠራ፡፡” (ሱረቱል ሙእሚኑን 91)፡፡
ጌታችን እውነትን ተናገረ! ስድስትና ሰባት ሰው የምትኖርባት አንድ ቤተሰብ እንኳ የምትመራው በአንድ አባወራ ነው፡፡ ትምህርት ቤት የሚተዳደረው በአንድ ዳይሬክተር ነው፡፡ ሀገር የሚመራው በአንድ መሪ ነው፡፡ ታዲያ አጽናፈ ዓለሙን የሚመራው አምላካችን አላህ፡ አንድ እንጂ እንዴት ከአንድ በላይ ነው ተብሎ ይታሰባል? - የአጠቃቀሙ ሁኔታ፡- ጌታችን አላህ በቅዱስ ቁርኣኑ ላይ ስለራሱ ‹‹እኛ›› ብሎ እንደተናገረው ሁሉ፡ እንዲሁም ‹‹እኔ›› በማለትም ይናገራል፡፡ ነገር ግን ‹‹እኛ›› የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት፡ የሰራቸውን ያደረጋቸውን ድርጊቶች በሚገልጽበት ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡ አንድም ቦታ ላይ ስለ አምልኮ በሚናገሩ የቁርኣን አንቀጾች (አየተ-ተውሒድ) ላይ ‹እኛ› ብሎ አልተናገረም፡፡ አላህ፡- ፈጠርናችሁ፣ ሰጠናችሁ፣ አወረድንላችሁ… እንዳለው ሁሉ፡ አምልኮ ላይም፡ ስገዱልን፣ አምልኩን፣ ተገዙን አላለም፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የሚናገረው፡ ፍሩኝ፣ ተገዙኝ፣ ለምኑኝ… በማለት ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚያመላክተው ‹‹እኛነቱን›› የተጠቀመባቸው ስራውን የሚገልጽበት አንቀጽ ላይ ብቻ መሆኑ፡ ታላቅነቱን እንጂ ከአንድ በላይ መሆኑን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-
ሀ. ስለ አምልኮ በሚናገሩ አንቀጾች፡-
“… ዛሬ እነዚያ የካዱት ከሃይማኖታችሁ ተስፋ ቆረጡ ስለዚህ አትፍሩዋቸው ፍሩኝም…” (ሱረቱል ማኢዳህ 3)፡፡
“ጌታችሁም አለ፡- ለምኑኝ እቀበላችኋለሁና…” (ሱረቱ ጋፊር 60)፡፡
“ከለሊቱም ለርሱ ስገድ በረዥም ለሌትም አወድሰው” (ሱረቱል ኢንሳን 26)፡፡
“ይህች (ህግጋት) አንዲት መንገድ ስትሆን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ” (ሱረቱል አንቢያእ 92)፡፡
ለ. ስለ ስራው የሚናገሩ አንቀጾች፡-
“በሰማይም ላይ ቡሩጅችን በእርግጥ አድርገናል…” (ሱረቱል ሒጅር 16)፡፡
“በእርግጥም ከበላያችሁ ሰባትን ሰማያት ፈጠርን ከፍጥረቶቹም ዘንጊዎች አልነበርንም” (ሱረቱል ሙእሚኑን 17)፡፡
“እኛ በጣም ብዙ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ” (ሱረቱል ከውሠር 1)፡፡
“በነዚያም ነፍሶቻቸውን በበደሉት ሰዎች መኖሪያ ውስጥ ተቀመጣችሁ በነሱም እንደት እንደሰራንባቸው ተገለፀላችሁ ለናንተም ምሳሌዎችን ገለጽንላችሁ” (ሱረቱ ኢብራሂም 45)፡፡
“በናንተም ላይ ደመናን አጠለልን በናንተም ላይ (እንደ ነጭ ማር ያለ) መንናን እና ድርጭትን አወረድን…” (ሱረቱል በቀራህ 57)፡፡
ከነዚህና መሰል አንቀጾች በመነሳት፡ የጌታችን ‹‹እኛነት›› የታላቅነትና የክብር መገለጫ መሆኑን እንጂ የብዜት መገለጫ እንዳልሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ - ገደብ አልባ በመሆኑ፡- አምላካችን አላህ ስለራሱ ሲናገር ‹እኛ› ብሎ መጠቀሙን በመያዝ፡ እሱ ከአንድ በላይ (ሥላሴ) ነው ማለት የሚቻል ከሆነ፡ እንግዲውስ እሱ ጌታችን አላህ ‹‹እኛ›› በማለቱ፡ አሥር አምላክ ነው ማ
ለት ይቻላል ማለት ነው? ምክንያቱም ‹እኛ› የሚለው የብዜት ቃል፡ ሶስትን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ብዙ ቁጥርን አመልካች ነው፡፡ ለ3 ማስረጃ የሚሆን ከሆነ ለ33ትም ማስረጃ መሆን ይችላል፡፡ 33ት አምላክ እንዴት ይኖራል? የሚባል ከሆነም፡ 3 አምላክስ እንዴት ይኖራል? በማለት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ ‹እኛ› የሚለው ክብርን አመልካች እንጂ ብዜትን ገላጭ አይደለም የሚል ነው፡፡
- በመጠየቅ፡- አላህ ስለራሱ ‹እኛ› ብሎ መናገሩ የሱን ሶስትነት ‹ስላሴነት› ያስረዳል የሚሉ ከሆነ፡ ቀጥሎ ያለውን አንቀጽ እንዴት ሊያደርጉት ነው? እንዲህ ይላል ጥቅሱ፡-
“…የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው፡፡ በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው…“ (ሱረቱል በቀራህ 87.253)፡፡
በዚህ አንቀጽ ላይ ጌታችን ለዒሳ ‹ሰጠነው› ይላል እንጂ፡ ‹ሰጠሁት› አላለም፡፡ ታዲያ ‹ሰጠነው› በማለቱ፡ እኛነትን ተጠቅሟልና እሱ ‹ሥላሴ› ከሆነ፡ ዒሳ ከሥላሴ ተባሯል ማለት ነው? ምክንያቱም ዒሳ ተቀባይ እንጂ ሰጪዎች ውስጥ አይደለም፡፡ ከሥላሴዎች አንዱ ዒሳ ነው ተብሎ ነው የሚታመነው አይደል? በመሆኑም ጌታችን ስለራሱ ‹እኛ› ማለቱ ታላቅነቱንና ክብሩን ከመግለጽ ውጪ በፍጹም ሥላሴነቱን አይገልጽም፡፡ - ሌሎችም ስለተጠቀሙት፡- በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ አንድ ሆኖ ሳለ ‹እኛ› በማለት ከጌታችን ውጪ ሌላውም ሲጠቀምበት አይተናል፡፡ ታዲያ ያ አካል አንድም ሶስትም ነው ሊባል ነው?
“(ወርደው) ተጓዙም ወጣትንም ልጅ ባገኙና በገደለው ጊዜ ያለ ነፍስ (መግደል) ንጽህን ነፍስ ገደልክን በእርግጥ መጥፎን ነገር ሠራህ አለው…ወጣቱም ልጅማ ወላጆቹ ምእምናን ነበሩ (ቢያድግ) ትንቢትና ክህደትንም የሚያስገድዳቸው መሆኑን ፈራን ጌታቸውም በንጽህነት ከርሱ በላጭን በእዝነትም ከርሱ በጣም ቀራቢን ልጅ ሊለውጥላቸው ፈለግን” (ሱረቱል ከህፍ 74)፡፡
ሙሳ መንገድን እየተጓዘ ሳለ ከኸዲር ጋር ተገናኝተው ሙሳ አብሮት እንዲሄድ በመማጸን አብረው ይጓዛሉ፡፡ ሲጓዙም በመንገድ ወጣትን ልጅ አግኝተው ኸዲር ይገድለዋል የሁኔታው ሚስጥር ያልገባው ሙሳም፡- ምንም ያላጠፋን ነፍስ ትገድላለህን? አለው፡፡ ኸዲርም ፡- ልጁ ከሀዲ ነው፡፡ ወላጀቹ ምእምናን ናቸው ቢያድግ ወላጆቹን ወደ ክህደት እንዳያስገድዳቸው ፈርተን ነው አለው፡፡ የኛ ጥያቄ ኸዲር “ፈራን” ሲል ስንት ነበር? የሚል ነው፡፡
ለማጠቃለል ያህል የጌታችን ‹እኛነት› በምንም አይነት መልኩ የሱን ከአንድ በላይ መሆን የሚያመላክት አይደለም፡፡ ከዛ ይልቅ የሱን ኃያልነት፣ መለኮታዊ ክብሩንና ታላቅነቱን ለማሳየት ነው፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።



ጀዛከላሁ ኸይር ድንቅ ማብራሪያ ነው።አላህ እናንተንም እኛንም ያበርታን ፤ስላሴያውያን ወገኖቻችንንም አላህ እርሱን ብቻ መገዛትን ይችራቸው አሚን
ማሻአላህ ጥሩ የመማሪያና የማስተማሪያ መድረክ ነው
ማሻ አላህ ግሩምና ማራኪ ማብራሪያ ነው በተለይ አሁላይ ሁሉም ሊያነበው ሊማረው ይገባል የአክፍሮት ሀይላትን ትችት ለመመከት ዑማው ቢያንስ መሰረታዊ የሆኑ የዲኑን ትምህርት መቅሰም አለበት በንፅፅርም ዙሪያ የግድ ሁሉም መማር አለበት ብዬ አስባለው።ጀዛኩምላህ ከኸይረን ጀዛ🙏