ሙስሊሙን ማክፈር – የዘመናዊው አለም የሚሽነሪ እንቅስቃሴ
(የሕያ ኢብኑ ኑህ)
ወቅቱ በ1930 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠርር ነበር፤ የግብፁ አል-አዝሀር ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንግዳ ነገር ተሰማ። በሳሙኤል ዚውመር የተመራው የሚሽነሪ ቡድን ያለምንም ፍርሀት ቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ዘልቆ በመግባት የተለያዩ ፓምፍሌቶችንና ብሮሹሮቹን በተነ።በተግባሩ የአዝሀር ዑለሞች ተቆጡ፤ “ፈጽሞ አይደረግም” በሚል ሀሳብ ያንቀላፉት ሳይቀር ባለማመን ሰመመን ውስጥ ሁነው ድንጋጤ አላወሳቸው። የሁሉም ጥያቄ ግን “እነዚህ አካላት በዚህ ደረጃ እንዴት ደፈሩ?” “በርግጥ የዚህ ተግባር መንስኤ የነሱ ድፍረት ነው ወይንስ የኛ ድክመት?” የሚሉት ነበሩ
እነዚህ ጥያቄዎች የያኔውን የግብፅ ሙስሊም ማህበረሰብ ሰቅዘው ያዙት። ዑመር ሪያድ MUSLIM RESPONSE TO MISSIONARY ACTIVITIES IN EGYPT: WITH A SPECIAL REFERENCE TO THE AL-AZHAR HIGH CORPS OF ‘ULAMÂ (1925 1935) በተሰኘው ስራው እንደገለጸው ይህ የሚሽነሪዎች ተግባር የወቅቱን ሙስሊም ክፉኛ አስቆጥቶት ነበር። በወቅቱ የነበሩ የሚዲያ ውጤቶችም ተግባሩን በሰፊው ዘገቡት። ተግባሩን ምሳሌ በማድረግ የተደቀነውን የሚሽነሪ አደጋ በሰፊው ተነተኑ።
ካርተር “on Spreading Gospel” በተሰኘ ጥናቷ ከገፅ 18-36 ባለው ክፍል እንደገለፀችው ይህ ክስተት የግብፅ ሙስሊሞችን በተለይም የአዝሀር ሙስሊም ሊቃውንትን ለወደፊት እርምጃቸው ያነቃ ነበር። እንደሷ ገለፃ ከሆነ በወቅቱ በግብፅ ብቻ 450 የውጭ ዜግነት ያላቸው ሚስዬናውያን ሲኖሩ 1500 ደግሞ የሀገሬው ተወላጅ ሚስዬናውያን አብረዋቸው ነበሩ። በአጠቃላይ አመታዊ በጀታቸውም ከ$700,000 ዶላር በላይ እንደነበር ታትታለች። (Barbara L. Carter “On spreading Gospel” Pp 20
ሳሙኤል ዙዌመር (1867-1952) በሙስሊሙ አለም በሰራቸው የሚስዮናዊ ስራዎቹ ገናና ስም ያለው አሜሪካዊ ሚሽነሪ ነው። “Apostle to Islam” በተሰኘው ቅፅል ስሙ በሰፊው ይታወቃል፤ “ወደ ሙስሊሙ አለም የተላከ ሀዋርያ” እንደማለት ነው። ተፅእኖው ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከሱ በኃላ የተነሱ ሙስሊም ተኮር የሚስዬናዊ ስራዎች ሳይቀር በሱ ፍኖት ላይ ያረፉ ነበሩ። ከካይሮው ኮንፈረንስ (1906) እስከ ህንዱ ኮንፈረንስ (1911) ፊት አውራሪው እርሱ ነበር።
በህንዱ የ”ለክኖ ኮንፈረንስ” ወቅት 54 የሚሽነሪ ድርጅቶችን የወከሉ 160 ተሳታፊዎች ተገኝተው ነበር። ስብሰባውም ከጃንዋሪ 23-28 በህንድ ሶቦርን ኮሌጅ ግቢ ውስጥ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1911 ነበር የተካሄደው።
የዚህና መሠል ስብሰባዎች አላማና በመጨረሻ የደረሱባቸው ድምዳሜዎች ምንድን ናቸው? ከነዚህ ድምዳሜዎች የምንወስደው ቁምነገርስ ምንድን ነው? የሚሉት ነጥቦች እንደ ሙስሊም ወሳኝ መሰረተ ሀሳቦች ናቸውና ከዚህ በታች በከፊል እዳስሳቸዋለሁ። በዳሰሳየ የማተኩረው ካካሄዷቸው ኮንፈረንሶች ውስጥ እንደ ማሳያ የ1911ዱን በህንድ ተካሂዶ የነበረውን ኮንፈረንስ ለአብነት እየጠቀስኩ ነው።
✔ የኮንፈረንሱ ዋነኛ አላማ
ኮንፈረንሱ በዋነኝነት ሁለት አላማዎችን ያነገበ ሲሆን እነሱም በአጭሩ የሚከተሉት ናቸው፦
1. የእስልምናን ሒደታዊ መስፋፋት መግታት
2. በሙስሊሞች ላይ ድል በመቀዳጀት ወደ ክርስትና መቀየር
«ድል መቀዳጀት» የሚለው ሀሳብ የስነልቦና፣ የአስተሳሰብ/Ideology/ እንዲሁም የፖለቲካ የበላይነትን ያከተተ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ የተንጸባረቀው የአካሄድ መስመርም ጠብ ጫሪ/Aggressive approach/ አካሄድን የተከተለ ነበር። ይህን አካሄድ የተቃወሙ የስብሰባው ተሳታፊዎች የነበሩ ቢሆንም ከመድረክ ጀምሮ ይስተጋባ የነበረው አካሄድ ግን ድምጻቸው አንሶ እንዲዋጡ አድርጓቸዋል።
✔ የኮንፈረንሱ አበይት ድምዳሜዎች
በኮንፈረንሱ ሰፊና ዝርዝር ሀሳቦችን አንስተው ተወያይተዋል። ሙስሊሙን እንዴት እናክፍር? በሚለው ዙሪያ ከሚገጥሟቸው ፈተናዎች ጀምሮ ሊያደርጉ እስካሰቡት ተግባር “ይህ ቀርቷል” በማይባል መልኩ ሀሳቦችና ጥናታዊ ወረቀቶች ቀርበው በሰፊው ተነጋግረዋል። በስተመጨረሻም ከዚህ በታች የሚገኙትን አራት ድምዳሜዎች በማስቀመጥ ኮንፈረንሳቸውን ቋጭተዋል።
1. የሙስሊሙ አንድነት መንፈስ/Pan-Islamism/ የሚሽነሪ ስራው ተግዳሮት/እንቅፋት/ እንደሆነ
2. የክርስቲያን ሚሽነሪዎችን ለሙስሊሙ ዓለም እንዲመቹ አድርጎ ማሰልጠን ወሳኝ ተግባር መሆን እንዳለበት
3. ሙስሊሞችን ትኩረት ያደረጉ የሚሽነሪ የጽህፈት ውጤቶች ተዘጋጅተው የሚበተኑበት መንገድ መመቻቸት እንደሚኖርበት
4. የአስልምናን መስፋፋት ለመግታት የተቀናጀ የክርስቲያኖች ህብረት በፅኑ እንደሚያስፈልግ
እነዚህ አራት ድምዳሜዎች እጅግ መሰረታዊ ዝርዝር ሀሳቦችን በውስጣቸው ያካተቱ ሲሆን አሁን ድረስ ለሚሰሩ የሚሽነሪ ስራዎች እንደ መሰረት/Foundation/ ያገለግላሉ። እስኪ ከዚህ በታች እያንዳንዳቸውን እያነሳን በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክር።
1. የሙስሊሙ አንድነት መንፈስ/Pan-Islamism/
ከስብሰባው ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕስ ውስጥ አንዱ ይህኛው ክፍል ሲሆን በየትኛው መልኩ ሙስሊሙ አንድነቱን መጠበቁ ለሚሽነሪ ስራቸው እንቅፋት እንደሆነ በግልጽ አስቀምጠዋል። ይህንን በመረዳትም ክርስትያኑ በዚህ እንቅስቃሴው ውስጥ የራሱን አንድነት ጠብቆ በጋራ እንዲታገልም አሳስበዋል (Lucknow, 1911: Papers and discussions of Lucknow Missionary conference, p, 10. )
በተመሳሳይ እራሱ ሳሙኤል ዚውመር በመጽሀፉ እንደገለጸው “የሙስሊሙን አንድነት ተጋፍጦ መናድ የሚቻለው የወንጌላውያን አንድነት መረጋገጥ ሲችል ነው። (Zwemer, Samuel. M, lslam a Challenge to Faith, p.240. )
2. ክርስቲያን ሚሽነሪዎችን ማሰልጠን
ሁለተኛው መሰረታዊ ነጥብ ተደርጎ የተወሰደው ክርስቲያን ሚሽነሪዎችን ለሙስሊሙ አለም ምቹ በሆነ መልኩ ማሰልጠንና ማብቃት ላይ መሰራት እንዳለበት ነው። እንደሚታወቀው አብዛኛው ሚሽነሪ ስለ እስልምና ምንም እውቀት ሳይኖረው ከፍ ካለም ውስን እውቀት ይዞ ለአገልግሎት የሚሰማራ ነው። ይህ አነስተኛ እውቀት ያለው ሚሽነሪ ደግሞ ወደ ሙስሊሙ ዓለም ሲመጣ ከአዳኝነት ወደ ታዳኝነት የመለወጥ እድሉም ሰፊ ነው። ለዛም ነው እነ ሳሙኤል ዚውመር “ማሰልጠን” ሲሉ የጠሩት በተግባር ግን “እስልምናን አጥልሽቶ የማሳየት ተግባር” መከወን አለበት ሲሉ የሚገቱት።
ከዚህም በተጨማሪ ሚሽነሪዎች የሙስሊሙን አለም ባህልና ልማድ ጠንቅቀው ማወቅ እንደሚኖርባቸውም ጭምር ተጠቅሷል። ዚውመር ለአብነት የአሳማ ስጋን ምሳሌ በማድረግ «ሚሽነሪዎች ለሙስሊሙ አለም «ሙስሊም» መስለው መቅረብ» እንዳለባቸው ገልጿል። (Lucknow, 1911: Papers and Discussions of Lucknow Missionary conference, pp, 46-59)
3. የሚሽነሪ የጽህፈት ውጤቶች
ሚሽነሪዎች ወደ “ወንጌል አገልግሎት” ከመሰማራታቸው በፊት የሚሄዱበት አካባቢ ህዝቦች የሚናገሩበትን ቋንቋ አስመልክቶ የተዘጋጀ የፁሁፍ ስራዎችን ይዘው መሄድ እንዳለባቸው ተገልጿል። እነዚህ ጹሁፎች ለስራቸው አጋዥ በመሆን ስራ የሚቃልሉላቸው ናቸው። በተጨማሪም ማህበረሰቡን በአፍ መፍቻ ቋንቋው የሚያናገሩ ድርሳናት ናቸውና በቀላሉ ልብ ውስጥ የመስረፅ እድላቸው ሰፊ ነው።
4. የተቀናጀ የወንጌላውያን ህብረት
ኮንፈረንሱ በመጨረሻ ያስቀመጠው ድምዳሜ የወንጌላውያን ህብረት መኖር የእስልምናን መስፋፋት ለመግታት ወሳኝ ተግባር መሆኑን ነው። የተለያዩ የሚሽነሪ ስራዎች በየቦታው የሚሰሩት ስራ የተበታተነ እንደመሆኑ መጠን እንደታሰበው ለውጥ አለማምጣቱን ገልጸው በዚህ ዘርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች በአጠቃላይ በአንድ ህብረት ውስጥ መሆናቸው ጥንካሬን እንደሚያላብሳቸው ጠቅሰዋል። (Lucknow, 1911: Papers and discussions of Lucknow Missionary Conference, p,209.
✔ ሲጠቃለል
ይህ ኮንፈረንስ ከዛሬ መቶ አመት ገደማ በፊት የተካሄደ ቢሆንም የድምዳሜ ነጥቦቹ ግን በዘመነኛ ሚሽነሪ ጓዳዎች ሳይቀር ይሸታሉ። ቦታና ጊዜን መሠረት ካደረጉ መጠነኛ ለውጦች ውጭ ድምዳሜዎቹ አሁን ድረስ የሚሽነሪ “ቀኖናዎች” ናቸው። አሁን ላይ ሙስሊሙ ለዚህ የኩፍር እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጠበት እንደመሆኑ መጠን መለስ ብለን ታሪክን መቃኘታችን መልካም ነው በሚል አጠር አድርጌ ከላይ አስቃኝቻችኃለው። አላህ ሲፈቅድ ደግሞ በሌላ ፁሁፍ እንገናኛለን።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።



Allah melkam ymendachu
We are in dire need of this kind of blogs. I will share this website.
አሰ ወራ ወበ ወንድም የሕያ ኢብኑ ኑህ ብዙ ግዜ የድካምህን ፍሬዎች ስመገብ ኖሬያለሁ አንተንና መሰል ወንድሞችን አላህ ሱወ ሥራችሁን ውጤታማ ፍሪያማ ያድርግላችሁ የምትከትቡበትንም እጃችሁን ጠንካራ ምላሳችሁንስ ስል አንደበታችሁንም በሥነምግባር የተሞላ ርቱዕ ያድርግላችሁ አሚን ያረበል አላሚን ጠንክሩ በርቱ ተስፋ እንዳትቆርጡ በሁሉም ነገር ከጎናችሁ ነን ለማለት ነው ወጀዛኩሙላሁ ኽይረን ወንድማችን ወሰ ወራ ወበ🙏