(የሕያ ኢብኑ ኑህ እና አቡ ዩስራ)
“ጂሃድ” የሚለዉ ቃል ሲወሳ ብዙ ሰዎች በተለይም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች አስፈሪ ምስል ይደቀንባቸዋል። ከተለያዩ የሚዲያ ምንጮች የሚያገኟቸው የተለያዩ መረጃዎች በዚህ አረዳዳቸው ላይ የራሳቸው ተፅእኖ አላቸው። እነዚህ ሰዎች ስለ ጂሃድ ሲያስቡ ምናልባትም ፊልም ላይ እንደሚያዩት ጺሙ የተንዥረገገ፣ፊቱ የተኮሳተረ፣ በቀኝ እጁ ቁርአን በግራ እጁ ሰይፍ የያዘ ሰዉ በአይነ ህሊናቸዉ ሊመጣባቸዉ ይችላል፡፡ ይህም ሰዉ ከፊት ለፊቱ ያገኘዉን ሁሉ “ትሰልማለህ ወይስ አትሰልምም” በማለት ይጠይቃል “ሰልሜያለዉ” ያለዉን ይተዋል “አልሰልምም” ያለዉን ግን “አሏሁ አክበር” በማለት አንገቱን በሰይፍ ይቀላል ወይም ደግሞ ቦንብ አንግቦ ሰላማዊ ህዝብ የተሰበሰበባቸዉን ቦታዎች በማጋየት ንፀሃንን ሲጨርስ ይታያቸዋል፡፡
ሌሎች ደግሞ ጂሃድ ሲባል ወደ ህሊናቸው የሚመጣው “ቅዱስ ጦርነት” የሚለው ትርጓሜ ነው። ይህም ሌላኛዉ የጂሃድ የተሳሳተ እይታ ነዉ፡፡
እንደመግቢያ ይህንን ካልን ታዲያ ስለ ጂሀድ ፅንሰ ሀሳብ ለመወያየትና አንዳንድ ብዥታዎችን ለማጥራት የሚከተሉትን ነጥቦች መዳሰስ ያሻል።
✔️ ጂሃድ ምንድን ነዉ?
✔️ እስልምና ስለ ሰላም እና የጦርነት ጊዜያት ያለዉ አስተምህሮ ምን ይመስላል?
✔️ እስልምና የጦር መሳሪያ ዉጊያን የሚፈቅደዉ መቼ እና እንዴት ነዉ?
✔️ የጂሃድ አላማዎችስ ምን ምን ናቸዉ?
የጂሃድ ትርጉም
“ጂሃድ” የሚለዉ ቃል በቁርአን ዉስጥ 34 ግዜ ተወስቷል። “ጀ ሐ ደ” ከሚል የአረብኛ ግስ የተገኝ ሲሆን ትርጉሙም “ጥረት አደረገ” “ተበራታ” “አቅሙን አሟጦ ተጠቀመ” ማለት ነዉ፡፡ ቁርአን ዉስጥ የሰፈረበት ሁኔታ ስንመለከት የሚሰጠን መልዕክት ጥሩ ነገርን ለማግኘትና መጥፎ ነገርን (ክፋትን) ለማስወገድ ከሚደረግ ትግልና ጥረት ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጂሃድ በጣም ሰፊ የሆነ ማብራሪያ ያለው አስተምህሮ ሲሆን አብዛኛዉን ግዜ በተለምዶ የምናቀዉ ግን የጂሃድ አንዱ ክፍል የሆነዉን “ቂታል” ወይንም “ውግያን” የተመለከተውን ክፍል ብቻ ነዉ። በዚህም ምክንያት ስለ ጂሃድ ስንሰማ መጀመርያ አእምሮአቸን ዉስጥ የሚመጣዉ በጦርነት የሚደረግ ዉጊያ ብቻ ነዉ፡፡ ነገር ግን ቂታል የጅሀድ አንዱ ክፍል እንጅ እራሱ ብቻውን ጂሃድ አይደለም። ከዚህ በታች ሰፋ አድርገን አናብራራው። ከዛ በፊት ግን ለመግባባት እንዲመች የተወሰኑ ቃላትን በመጠኑ ፍቻቸውን አስቀምጨ ልለፍ፦
✔️ ቂታል ፦ የጠላትን ጥቃት ለመከላከል /ለመመከት/ የመሳሪያ ሀይልን መጠቀም ማለት ነዉ፡፡ በቁርአን ምዕራፍ 2፥190 ተጠቅሷል። ይህ ቃል በቁርአን ወስጥ 67 ጊዜ ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ይህም አይነት ውጊያ ተቀባይነት የሚኖረው “በአላህ መንገድ›› ላይ ብቻ ሲፈፀም ነዉ።
“ቂታል” የጂሃድ (የትግል) አንድ አካል እንጂ ሙሉ በሙሉ ጂሃድን አይተካም፡፡
✔️ ሀርብ ፦ ቁሳዊ ጉልበትን በመጠቀም ተቀናቃኝ ወገኖችን ለማጥቃት የሚደረግ ውጊያ ሲሆን ይዘቱ ከጂሃድ ይለያል፡፡ሀርብ መሠረቱ አለማዊ የሆነ ጽንስ ሃሰብ ነዉ (ሀይማኖታዊ ይዞታ የለዉም)። አብዛኛውን ጊዜ ግልጋሎት ላይ የሚውለውም ተቀናቃኝ ወገንን ለመጨቆንና ለመዝረፍ እንዲሁም ህዝቡን ለመግዛት በሚደረግ ውጊያ ላይ ነው።ይህ ጦርነት ከጦር መሳሪያ ዉጪ ባሉ ባሉ ነገሮችም ሊከናወን ይችላል። ለአብነትም በኢኮኖሚ፤ በሚዲያ ፣በአስተሳሰብ/Ideology/ ወዘተ.. ይህ ቃል ቁርአን ውስጥ 6 ጊዜ ተደጋግሞ ተወስቷል፡፡
✔️ ኢርሃብ (ሽብር)፦ ትርጉሙ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ሽብር መፍጠር የሚል ሲሆን አተረጓጉሙ ላይ ብዙውን ጊዜ ስምምነት የለም። በተለምዶ ሽብርተኛ የሚባለው አካል ለአንደኛው ቡድን ሽብርተኛ ሲሆን ለሌኛው ቡድን ደግም የነፃነት ታጋይ ሁኖ ይገኛል። በጥቅሉ ትርጉሙ ግን ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ነው።
ከላይ በጥቂቱ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ጂሃድ ሰፋ ያለ ትርጉም ያለው አስተምህሮ እንጅ እንዲሁ “ጦር መዞ” ሌላኛዉን ወገን መጨፍጨፍ አይደለም።
የእስልምና ሊቃውንት/ዑለሞች/ ጂሃድን በአራት ይከፍሉታል፦
- ነፍስን መታገል
- ሰይጣንን መታገል
- በዳዬችንና ሐጢያተኞችን መታገል
- ከሃዲያንና መናፍቃንን መታገል
እነዚህ የጂሃድ አይነቶች በውስጣቸዉ የየራሳቸዉ የተለያየ እርከኖች ይዘዋል።
የመጀመርያዉ 4 እርከን ያለው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 2 እርከን አለው። በተመሳሳይ ሶስተኛዉ 4 እርከን ሲኖረው አራተኛው ደግሞ 3 እርከን አሉት፡፡ በአጠቃላይ ድምሩ 13 ይሆናል ማለት ነዉ።
በተለምዶ “ጂሃድ” እየተባለ የሚጠራዉ ሙስሊም ካልሆኑ ሰዎች ጋር የሚደረገዉ የመሳሪያ ግብግብ በአራተኛዉ የጂሃድ አይነት ዉስጥ የሚካተት ሲሆን ንፅፅሮሹ 1/13ኛ ወይንም በፐርሰንት 7.7 ፐርሰንቱን የሚሸፍን ነው። ቀሪዉ 92.3 ፐርሰንቱ ከመሳሪያ ዉጪ የሚደረግ ጂሀድ ሲሆን ‹‹ጂሃድን›› በመሳሪያ ጦርነት ብቻ የሚደረግ ትግል አድርጎ መተርጎም ምን ያህል ስህተት እንደሆነ ያሳየናል፡፡
ስለዚህም ስለመጀመርያዎቹ 3 አይነት ጂሃዶች ከቁርአን አጠር ያሉ ማብራሪያዎችን አይተን ወደ መጨረሻውና ዋና ወደ ሆነዉ “የመሳሪያ ጦርነት” እንገባለን
- ነፍስን መታገል
የሰዉ ልጅ ስጋዊ እና በመንፈሳዊ ስሜቶች ተዳብለው የተገነባ ፍጡር ነዉ። ይህንን የተሰጠውን ነገር ተጠቅሞ ወደ ፈለገዉ አቅጣጫ የመሄድ መብቱ የራሱ እንደመሆኑ መጠን በዚህ መንገድ ላይ ወደ መልካም ለመሄድና ከክፉ ለመራቅ ከውስጡ ጋር የሚያደርገው ትግል ደግሞ አንዱ የህይወት ዑደት ነው። ነፍስ በራሷ ተስተካክላና ተገርታና ቅኑን መንገድ ተመርታ ወደ ከፍታ ትዘልቅ ዘንድ ከራስ ጋር ከፍተኛ ትግል ማደረግ ያስፈልጋል። መልካም ነገሮች ሁሉ ያለጥረት አይገኙምና፡፡( ቁርአን 91፡7-10፣ 29፡69) በዚህ የትግል ሂደት ዉስጥ የሰዉ ልጅ ነፍስ 3 እርከኖችን ታልፋለች፡፡
✔️በክፉ የምታዝ ነፍስ፦ ይህች ነፍስ የምታዘው መጥፎ ወደተባሉ መንገዶች ነው። ይኸውም በዝሙት፣ ሰዎችን በመበደል፣ አስካሪ መጠጥ በመጠጣት ወዘተ የምታዝ አይነት ስትሆን ቁርአን ይህች አይነቷን ነፍስ (ነፍሰ አማራህ) ይላታል፡፡ ታዲያ ይህችን ነፍስ ታግሎ ወደ ቀጣዩ ደረጃ መውስድ ያስፈልጋል። –
‹‹ ነፍስ ሁሉ …በመጥፎ ነገር በእርግጥ አዛዥ ናትና›› ቁርአን 12፡53
✔️ ወቃሽ ነፍስ (ነፍሰን ለዋማህ)፦ በዘመናችን አገላለፅ ‹‹ንቁ ህሊና›› የምንለዉ አይነት ነዉ። የሰዉየዉ የዉስጥ ተቆጣጣሪ ስሜት እንደማለት ነዉ። መጥፎ ተግባራትን ሲፈጽም “ለምን?” እያለች በጥያቄ የምታፋጥጥ ፤የምታስጨንቅ በወቀሳ ማዕበል የምትንጥ ነፍስ ነች። ውስጥን እየገረፈች የምታቃጥል እየቆጠቆጠች እንቅልፍ የምትነሳ ነፍስ ናት። ይህችንም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ አሁንም ትግል ይፈልጋል፡፡
“..( ራሷን )ወቃሽ በሆነች ነፍስም እምላለዉ ( በእርግጥም ትቀሰቀሳላችሁ) ቁርአን 75፡2
✔️ የረጋች ነፍስ( ነፍሰን ሙጥመኢን)፦ ይህች ነፍስ ደግሞ ከፍተኛዉን የስብዕና ደረጃ የደረሰች፤ በሰከነ እምነትና አመለካከት የበለፀገች ነፍስ ናት፡፡
“አንቺ የረካሺዉ ነፍስ ሆይ! ወዳጅ ተወዳጅ ሆነሽ ወደ ጌታሽ ተመለሺ” ቁርአን 89፡27-28
- ሰይጣንን መታገል
እስልምና እንደ አብዛኛው ሰማያዊ ሀይማኖቶች ሁሉ በሰይጣን መኖር ያምናል። ሰይጣን የሰው ልጅ ዋነኛ ጠላት እንደሆነም ያስተምራል። የሰዉ ልጆች ሁሉ አባት ለሆኑት አዳም (ዐ.ሰ) የክብር ስግደት አልሰግድም ብሎ ከአላህ እዝነት መባረሩንም ያስተምራል፡
“እርሱም ለጌታዉ እንዲህ አለ፦”በአሸናፊነትህ ይሁንብኝ በመላ አሳስታቸዋለዉ ከእነርሱ ምርጥ የሆኑት ባሮችህ ሲቀሩ” ቁርአን 38፡82-83
ከዚያን ግዜ ጀምሮ ከሰው ልጅ ጋር ግብግብ ገጥሟል፤ የሰዉን ልጅ መቀመቅ ለመክተት ታጥቆ ተነስቷል፡፡ ጠላት አድርገን እንድንይዘዉም በቁርአን በግልጽ ተነግሮናል ( ቁርአን 35፡6 2፡168-169)
ስለዚህ የሰይጣንን ጠላትነት ተረድቶና የማጥቂያ መንገዱን፣የማታለያ ስልቱን ተገንዝቦ እሱን መታገል (ጂሃድ) ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
- በዳዮችንና ሐጢያተኞችን መታገል
ሶስተኛዉ ጂሃድ በማህበረሰብ ዉስጥ የሚስተዋልን የበደል እና የእኩይ ድርጊትን አዝማሚያ ለማስወገድ የሚደረግ ጥረት ( ጂሃድ) ነዉ፡፡ይህ የጂሃድ አይነት የምንኖርበት ማህበረሰብ በመጥፎ ተግባራት እንዳይበከልና ከውስጥ እንዳይበሰብስ ለመከላከል ታስቦ የሚደረግ ትግል ነው።
ይህም የጂሃድ አይነት የተለያዩ መስኮች አሉት፦
✔️ ግፍንና ግፈኞችን መታገል
ሀያሉ በደካማዉ ላይ፣ ሀብታሙ በድሃዉ ላይ፣ አሰሪዉ በሰራተኛዉ ላይ፣ ባለስልጣናት በህዝባቸዉ ወዘተ ላይ የግፍ በትሮቻቸውን እንዳያሳርፉ የሚደረግ ትግል ሲሆን ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን በተመለከተ እንዲህ ብለዋል “ተከታዮቼ በዳይን “በዳይ” ለማለት ከፈሩ ህልዉና እንደሌላቸዉ ቁጥር ነው” (አህመድ ዘግበዉታል)
እናም እስልምና ግፍና በደልን ለማስወገድ የሚደረግ ጥረትን እንደ አንድ የጅሀድ መስክ ይቆጥረዋል።
✔️ሙንከር መታገል
የሰውን ልጅ የሚጎዱ እና ማህበረሰብን የሚበክሉ ልምዶችና ድርጊቶች ሁሉ በቁርአን ቋንቋ “ሙንከር” ይባላሉ፡፡ ይህም ዝሙትን፣ አስካሪ መጠጥን፣ አደንዛዥ እፅ፣ ሙስናን ወዘተ ያጠቃልላል፡፡ ማህበረሰቡን ከእነዚህ እና ከመሰል በሽታዎች ለማጽዳት አሁንም ትግል/ጅሃድ/ ያስፈልጋል፡፡ ማህበረሰብ በስነ-ምግባር እጦት ሲበሰብስ፤ ወጣቱ አላማ ቢስ ሲሆን፤ አዋቂዉ ሰነፍና እንዝህላል ሲሆን፤ ምሁሩ አስመሳይ ሲሆን፤ መሪዎች ጥቅመኛ ሲሆኑ፤ ማጭበርበርና ዉሽት ከብልጠት በተቃራኒው ሀቀኛ መሆን ከሞኝነት ሲቆጠር አሁንም ትግል ያስፈልጋል። ማህበረሰቡ ‹‹በመልካም የሚያዝ ከክፉ የሚከለክል›› ብዙ ታጋዬች ያስፈልጉታል።
✔️ ቢድዓን /በሀይማኖት ውስጥ የሚጨመር መጤ አስተምህሮ/ መታገል
የሙስሊሙ ህብረተሰብ እምነቱና የአምልኮ ስርአቱ በመጤ እምነቶችና የአምልኮ ስርአቶች (ቢድዓ) ሳይበረዝ መሠረቱንና ይዘቱን ጠብቆ ይቆይ ዘንድ የሚደረግ የጂሃድ ክፍል ነዉ፡፡ ስለዚህ የሙስሊሙ ህብረተሰብ መልካም እሴቶቹና ባህሎቹ እንዲሁም እምነቱና አስተምህሮ እንደተጠበቀ ከውስጥ ሳይበከልና ሳይበሰብስ ይቆይ ዘንድ የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ጂሃድ ይሰኛሉ፡፡
አሁን ዋና አጀንዳችን ወደ ሆነዉ ወደ “አራተኛው” አይነት ጂሃድ እንግባ
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መጀመርያ ስብከታቸውን የጀመሩት በትውልድ ሀገራቸው በመካ ዉስጥ ነበር። በዚህም ወቅት ጥሪያቸዉን ከግለሰብ ጀምረዉ እስከ ማህበረሰብ ድረስ እያንዳንዱን ጎሳ እየጠሩ ሳይቀር ስብከታቸዉን ማድረግ ቀጠሉ። ለዚህ ጥሪያቸው ግን የጠበቃቸዉ ምላሽ እሳቸዉን ዕብድ፣ ደጋሚ፣ ዉሽታም በሚል የማጠልሺያ ስያሜ ጥሪያቸዉን ማንቋሸሽ ነበር ( ቁርዓን 15፥6 እና 38፥4)።
ከዛም በዘለለ አማኞችን ማንገላታትና ማስጨናነቅ ዋነኛ ስራቸዉ ሆነ።በዋናነት ግን ፌዝና ስላቅን እንደማሸማቀቂያ ይጠቀሙበት ነበር (ቁርዓን 68፡51 እና ቁርዓን 83፡29-33) ይህ አልሳካ ሲላቸው ወደ አካላዊ ጥቃት እና ማሰቃየት ገቡ፤ በዚህም በርካታ ሙስሊሞች መከራ እና ችግር እንደሁም ሞት ደረሰባቸዉ፡፡በተለይ የአማር ቢን ያሲር (ረ.ዐ) ቤተሰብ ላይ የደረሰዉ አደጋ የከፋ ነበር፡፡ ሁኔታዎች እየከፉ ሲመጡ ስደት የግድ ሆነ። የመጀመርያውን ስደት ወደ ሀባሻ (የዛሬይቱ ኢትዮጵያ) አደረጉ፡፡ከዛ በፊት ግን የመካ ጣኦታውያ ነብዩ ይህን ጥሪ እንዲያቆሙ የተለያዩ መደራደሪያቸውን ይዘው ቀርበው ነበር። በአንድ ወቅት ወደሳቸው በመምጣት፦
“ሙሀመድ ሆይ! በዚህ ባመጣኸዉ እምነት ሰበብ ማግኘት የምትፈልገዉ ገንዘብ ከሆነ ከሁላችንም የበለጠ ሃብታም እናደረግህ፤ የምትፈልገው ክብር ከሆነ የሁላችንም አለቃ እናድርግህና ያለ ፈቃድህም ምንም ነገር ላለመፈፀም ቃል እንግባ፤ የምትፈልገዉ ንግስና ከሆነም ንጉሳችን እናደረግህ›› የሚል ጥያቄ አቅርበው ነበር።
መጀመሪያውኑ ጭንቀታቸው ይህ ያልነበረው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ግን ምላሻቸው ድንቅ ነበር
“ፀሃይን በቀኝ እጄ ጨረቃን በግራ ቢያኖሩልኝ እንኳ (መልዕክቱ) እስኪሳካ ወይም እኔ እስክሰዋ ድረስ ከጥሪየ ወደኃላ አልልም”
ጣኦታዉያኑ ተስፋ ባለመቁረጥ ሌላ ጊዜ እንዲህ የሚል መደራደሪያም አቅርበው ነበር “ግማሽ አመት የእኛን ግማሽ አመት የአንተን ሀይማኖት እናምልክ” ሲሉ ጥያቄ አቀረቡ። አላህም በቁርአኑ ለዚህ ጥያቄያቸዉ መልስ ሰጣቸው፦
“ለእናንተ ሃይማኖታችሁ አልላችሁ፡፡ ለእኔም ሃይማኖቴ አለኝ” ሱረቱ አል-ካፊሩን – 6
በመጨረሻም በለስ ያልቀናቸዉ እነዚህ ጣኦት አምላኪያን በሙስሊሞቹ ላይ “ማእቀብ” ወደ መጣሉ ተሸጋገሩ፡፡ ስለዚህም ሌላኛዉ ስደት ወደ መዲና ሆነ፡፡ ይህም ስደት ሀብት ንብረትን ጥሎ የሚደረግ ሲሆን አንዳንዱ ሚስቱንና ልጆቹን ሳይቀር ይዞ እንዳይሄድና ግለሰቡ ብቻ ወደ መዲና እንዲሰደድ ተገዶ ነበር፡፡ እስልምና በመካ የዳዕዋ ጊዜያቱ አሰቃቂ ጥቃቶችን የተፈፀመው በሙስሊሞች ላይ ነበር፤ ያኔ ከእስልምና እንዲወጣ እንጂ ወደ እስልምና እንዲገባ የተገደደ የተገረፍ የተሰቃየ ከቶ አንድም አልነበርም፡፡
ሙስሊሞች ከመካ ተሰደዉ ወደ መዲና ሲገቡ የመዲና ህብረተሰብ በእልልታ ተቀበላቸዉ በግዜዉ መዲና ዉስጥ አይሁዶችና አናሳ ጣኦት አምላኪዎች እንደሁም ከመካ ተሰደዉ የመጡ (ሙሃጂሪን) እንዲሁም የመዲና ነዋሪዎች (አንሷር) ነበሩ፡፡ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ህዝባቸዉን አደራጅተው መንግስት መሰረቱ። ከዚያም ሙስሊሞችና ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ሊተዳደሩባቸዉ የሚችሉበት ሰነድ አዘጋጁ። በዚህም ስምምነት መሰረት መዲናና በዙርያዋ የሚገኙ ቀየዎችን ያካተተ የአንድነት መንግስት ተመሰረተ፡፡
ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በመዲና ውስጥ ማስተዳደር ከጀመሩ በኃላ የአናሳዎችን መብት የሚያከብር ህግ አወጡ። ይህም ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን የሚመለከት ሲሆን በእስልምና “ዚሚይ” ይባላሉ፡፡ የቃሉ ትርጉም “የጥበቃ ዋስትና” መኖራቸውን የሚገልፅ ሲሆን እነዚህ የጥበቃ ዋስትና የተሰጣቸው ሰዎች ካሏቸው መብቶች መካከል፦
✔️ የሀይማኖት ነፃነት ፡- ቁርአን ግልፅ በሆነ ቃል እንደሚነግረን “በሃይማኖት ማስገደድ የለም” (ቁርአን 2፡256) በዚህም ሳቢያ እስልምና በሌሎች ሀይማኖቶች ላይ ምንም አይነት የሀይል ተፅዕኖ ማድረግን ይከለክላል። ሰዎች የመረጡትን የሀይማኖት ፍኖት እንዲከተሉ ነፃነት ይሰጣል። የሚገርመው ይህ አንቀፅ የወረደው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መካ በነበሩበትና ሀይል ባልነበራቸው ወቅት ሳይሆን ከተሰደዱ በኃላና መዲና ዉስጥ ጠንካራ መንግሰት ካነፁ በኃላ ነበር። ስለዚህም ከዚህ ቀደም በመካ ጣኦታውያን “አንድ ግዜ ያንተን ሌላ ግዜ የኛን እናምልክ” ተብሎ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ “ለእናንተ ሃይማኖታችሁ ለእኔም ሃይማኖቴ” እንደተባሉት ዛሬ ላይ ደግሞ “በሃይማኖት ማስገደድ የለም የፈለገ ይመን የፈለገ ይካድ” ተብሎ ተደነገገ፡፡ ከዚህም ባለፈ ጂሃድ ከሚደረግባቸዉ አላማዎች ውስጥ አንዱ የአይሁድንና የክርስቲያን የአምልኮ ስፍራዎች ከጥቃት መከላከል እንደሆነም ገለፀ። ለዚህ ቁርአን 22፡39-40 ላይ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፦ “.. አላህ ሰዎችን ከፊላቸዉን በከፊሉ መከላከሉ ባልነበረ ኖሮ ገዳማት ቤተክርስቲያኖች ምኩራቦችም በውስጣቸዉም የአላህ ስም በብዛት የሚወሳባቸዉ መስጊዶችም በተፈረሱ ነበር..”
✔️ በሰላም የመኖር መብት፡- ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሀዲሳቸው እንዲህ ይላሉ፦ “ሙስሊም ያልሆነን ሰላማዊ ወገን የገደለ የጀነትን ሽታ አያገኝም ሽታዋ አርባ አመታት ከሚያስኬድ እርቀት ላይ የሚገኝ ቢሆንም” ( ቡኻሪ እንደዘገቡት) በዚህ ሀዲስ መሠረት አካላቸዉ ከጥቃት ነፍሳቸውም ከግድያ የተጠበቁ ናቸዉ፡፡
✔️ ከውጭ ጥቃት ጥበቃ የማግኘት መብት፦ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መንግስታቸዉ ለሌሎች ሙስሊም ላልሆኑ ወገኖች ከአጥቂ ኃይል የመከላከልን ግዴታ እንዳለበት አዘዋል፡፡
✔️ ከዉስጥ በደል መከላከል፦ ከሙስሊሙ ወገን እነሱ (አናሳዎች) ላይ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዉስጥ የሚኖርና ሙስሊም ያልሆነን የበደለ ወይም መብቱን ያጓደለ ወይም ከአቅሙ በላይ ሃላፊነት የጫነበት ወይም ያለፍቃዱ አንዳች ነገር የወሰደበት በዕለተ ትንሳኤ እኔው እራሴ እሞግተዋለው›› አቡ ዳዉድ ዘግበውታል
በሌላ ዘገባሞ
‹‹ዚሚይን ያወከ ባላንጣዉ እኔ ነኝ እኔ ባላንጣዉ የሆንኩኝ ደግሞ በመጪዉ አለም አሸንፈዋለዉ››
የሚያስደንቀው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ይህን የተናገሩት ከዛሬ 1400 ዓመት በፊት ነዉ፡፡ አይደለም የዛሬ 1400 አመት ይቅርና ዛሬ ላይ እንኩዋን እንዲህ አይነት ፍጹማዊ ድንቅ የሆነ አስተምህሮ የተነገረበት ሀይማኖት እስልምና ዉስጥ እንጂ ሌላ ቦታ የትም አይገኝም፡፡
✔️ የንብረት ዋስትና፦ ይህን በተመለከተ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ከነጅራን ክርስቲያኖች ጋር ያደረጉት ዉል ይህንን ያረጋግጣል፤ እንዲህ ይነበባል፦
“የነጅራንና በዙርያዋ ያሉ ክርስቲያኖች በአላህና በነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የጥበቃ ዋስትና ስር ናቸዉ፡፡ ገንዘባቸው ኃይማኖታቸው ቤተ-አምልኮዎቻቸውና በስሮቻቸዉ ያሉ ንብረቶች ይነሱም ይብዙም የጥበቃ ዋስትና ተስጥቷቸዋል” (ጦበራኒ)
✔️ ሰርቶ የማደር መብት፦ በየትኛዉም የስራ መስክ ተሰማርተው ሃብት የማፍራት ሙሉ መብት ሙስሊም ላልሆኑ ወገኖች ዋስትና ሰጥቷል፡፡
✔️ በፈለጉት ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ክብራቸው ተጠብቆ የመኖር መብት
ይህንን አስመልክቶ ድንቅ ምሳሌዎችን ለማየት ያክል፦
ኸሊፋው ዑመር (ረ.ዐ) በይተል መቅዲስን (እየሩሳሌምን) በተረከቡ ግዜ ለነዋሪዎቹ እንዲህ የሚል ዋስትና ነበር የሰጧቸው።
“በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነዉ፡፡ ይህ መልዕክት የአላህ ባሪያ የሆነዉ የአማኞች መሪ ለእየሩሳሌም ሰዎች የሰጠዉን ዋስትና የያዘ ነው። ለህይወታችሁ፣ ለገንዘባችሁ፣ ለአብያተ ክርስቲያኖቻችሁ፣ ለመስቀሎቻችሁ ለሌሎችም ሃይማኖታዊ ሀብቶቻቸው ዋስትና ሰጥቷል። አብያተ ክርስትያኖቻቸዉ አይነጠቁም፤ አይፈርሱባቸምም ከይዞታቸዉም አይቀነሰም። ከንብረቶቻቸዉ ኢምንት አይቀነስም እምነታቸዉን እንዲቀይሩ አይገደዱም ፤ከመካከላቸዉም አንዱም (በእምነቱ ምክንያት) ጉዳት አይደረስበትም”
ብለዉ ህዝቡን ሰብሰበዉ አዋጅ አስነገሩ፡፡ከዚያም ከፓትሪያርኩ ጋር በመሆን የተቀደሱ ቦታዎችን ጎበኙ። በአንደኛው ቤተክርስትያን ገቢ ውስጥ እያሉ የሰላት ሰአት ደረሰባቸው፤ የዚህን ጊዜ ፓትርያርኩ ዑመርን (ረ.ዐ) ከቤተ-ክርስቲያኗ ዉስጥ እንዲሰግዱ ጋበዟቸዉ። እርሳቸው ግን ግብዣዉን አልተቀበሉም፤ ምክንያታቸዉን ሲገልፁ “እኔ ከቤተ-ክርስቲያኗ ዉስጥ ብሰግድ ተከታዮቼ ከጊዜ በሁዋላ የሙስሊሞች የአምልኮ ቦታ ነዉ በማለት ሊነጥቋዋችሁ ይችላሉ” በሚል ነበር።
የጂሃድ ፅንሰ-ሀሳብ እስልምና ውስጥ የሚገኙ እንዲህ አይነት የመቻቻል ፖሊሲና የፍትህ ስርዐትን ማምጣት ችሏል። ጂሃድ በአሁኑ ሰአት ሚዲያዎች አጠልሽተው የሳሉት አይነት አስፈሪ የጭፍጨፋ አካሄድ ሳይሆን ሰላምና ፍትህን ለማምጣት የሚደረግ ትግል ነው።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።



ብዙ ዕውቀት ያገኘሁበት ጥልቅ ትምህርት ነው ። አመሰግናለሁ ።