ነብዩ “ﷺ” የልጅ ልጃቸውን ብልት ስመዋል በሚል በግልቡ ለሚቀርበው ክስ የተሰጠ ማብራሪያ
መግቢያ
የኢንተርኔት አለም የክርስቲያን አቃቤዎች የገቡበት የምዕመን መሸሽ አጣብቂኝ በነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” ስብእና ላይ ጥላሸት ይቀባልናል ብለው ያሰቡትን ማንኛውም ትርክት ከማምጣት ወደ ኃላ እንዳይሉ አድርጓቸዋል። በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ ትርክቶች ውስጥ ነብዩ “ﷺ” የልጅ ልጃቸውን ብልት ስመዋል በሚል የሚነሳው አንደኛው ነው። ዘገባው ሙሉ ለሙሉ ደዒፍ (ደካማ) ቢሆንም ጥቂትም ምዕመን ቢሆን ካደናገረልን በሚል ሲደጋግሙት ሰንብተዋል፣ ስለዚህ ጉዳይ እርግጡን የማያውቁ ሙስሊሞችንም ግራ ለማጋባት ሞክረዋል። ከዚህ በታች ዘገባውን እንገመግማለን።
ዘገባው
የአላህ መልእክተኛ የልጅ ልጃቸውን ሁሴን (አንዳንድ ዘገባዎች ሀሰን ይላሉ) ብልት መሳማቸውን በሚመለከት በክርስቲያኖቹ በኩል የሚቀርበው ሀዲስ የሚከተለው ነው፦
- አል-ሐሰንን ወይም አል-ሑሰይንን (ትንሹን) ብልት እንደሳሙ ተዘግቧል።
- ነብዩ “ﷺ” የሑሰይን (ረ.ዐ) እግራቸውን ለያዩና (ትንሹን) ብልታቸውን ሳሙ።
በዘገባዎቹ ላይ ያሉ እይታዎች
ትረካዎቹ በሚከተሉት ዘጋቢዎች ላይ በአንድም በሌላ መንገድ ይገኛል፦
1/ አል-ጠበራኒ (አል-ጠባራኒ፣ ሙአ’ጃም አል-ከቢር፣ (ካይሮ፥ መክተባ ኢብኑ ተይሚያህ፣ 1994) ሀዲስ 2658፣ 12615።
2/ አል-በይሃቂ (አል-በይሃቂ፣ ሱነን አል-ኩብራ፣ (ቤይሩት፥ ዳር አል-ኩቱብ አል-ኢልሚያ፣ 2003) ሀዲስ 651።
3/ ዲያ አል-መቅዲሲ (አል-መቅዲሲ፣ አል-አሃዲስ አል-ሙኽታራህ፣ (ቤይሩት፥ ዳር አል-ኺድር፣ 2000) ሀዲስ 549
4/ ኢብኑ አቢ ዱንያ (ኢብኑ አቢ ዱንያ፣ አል ናፍቃህ ‘አላ አል-አያል፣ (ደማም፥ ዳር ኢብኑ ቀይም፣ 1990) ሀዲስ 210፣ 211
5/ ተማም አል-ራዚ (አል-ራዚ፣ ተማም፣ አል-ፋዋኢድ፣ (ሪያድ፥ መክታባ አል-ሩሽድ፣ 1412 ሂጅራ) ሐዲስ 610
6/ ኻጢብ አል-ባግዳዲ (አል-ኻጢብ አል-ባግዳዲ፣ ታሪክ አል-ባግዳድ፣ (ቤይሩት፤ ዳር አል-ገርብ አል-ኢስላሚ፣ 2002) ቅጽ 4
7/ ኢብኑ አሳኪር አል-ዲመሽቂ (አል-ደሚሽቂ፣ ኢብኑ አሳኪር፣ ታሪኽ ዲመሽቅ፣ (ቤይሩት፥ ዳር አል-ፈክር፣ ) 14/224።
ከአል-በይሃቂ እና ተማም አል-ራዚ በቀር በቀሪዎቹ የተሰጡት ኢስናድ (የተራኪዎች ሰንሰለት) ቃቡስ ቢን አቢ ዘይባን በተመለከተ ደካማ ዘጋቢ መሆኑን በአንድ ድምጽ ይስማማሉ።
በዚህ ምክንያት አል-ነዋዊ (676 ሂጅራ) እና ኢብኑ ሀጀር (852 ሂጅራ) ይህንን ዘገባ ደኢፍ ብለውታል።
- አል-ነወዊ፣ ኹላሳህ አል-አህካም 1/138
- አል-አስቀላኒ፣ ኢብኑ ሀጀር፣ ተልኺስ አል-ሀቢር 1/352።
በተጨማሪም በአል-ኻጢብ እና ኢብኑ አሳኪር ዘንድ የሚገኙት ሰንሰለቶች ከቃቡስ በተጨማሪ ሙሐመድ ኢብኑ ማዚድ ኢብን አቢ አል-አዝሃር የተባለ ሌላ ተራኪን ያካተተ ነው። ይህ ተራኪ ውሸታም እና ቀጣፊ መሆኑ ደግሞ በሀዲስ ዘገባዎች ጥናት ይታወቃል። አል-ኻጢብ አል ባግዳዲ ይህንን ከጠቀሰ በኃላ እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል፦
“ይህ ሐዲስ በዘጋቢ ሰንሰለቶችም ሆነ በይዘቱ መውዱዕ (የተፈበረከ) ነው”
(አል-ባግዳዲ፣ ታሪኽ አል-ባግዳድ 4/164)
የአል-በይሃቂ ሰንሰለት በተጨማሪም እንደ ሙሐመድ ኢብኑ አቢ ለይላ ያሉ ደካማ ዘጋቢዎችን የያዘ ነው። በተጨማሪም አብዱረህማን ቢን አቢ ለይላ ከነብዩ “ﷺ” በቀጥታ የተናገረውም ግለሰብ ሶሓብይ የነበረ ሰው አልነበረም።
- አል አልባኒ፣ ኢርዋእ አል-ጋሊል፣ (ቤይሩት፡ መክተብ አል-ኢስላሚ፣ 1985) 6/213፣ 1811ኛው ሀዲስ
▣ በዚህ ዙሪያ ያለው ሰሒሕ ሀዲስ የቱ ነው?
በዚህ ዙሪያ ያለው አስተማማኝ ሀዲስ ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” የልጅ ልጃቸው የነበረውን የሀሰን ህጻን ገላ ሆዱ ላይ መሳማቸውን የሚገልጽ ነው።
ዑመይር ብን ኢስሃቅ እንደዘገበው “ከአል-ሐሰን ቢን ዓልይ (ረ.ዐ) ጋር ነበርኩ፣ አቡ ሁረይራን አገኘናቸው። (ለሀሰን)፦ የአላህ መልእክተኛ ሰለላሁ ዓለይሂ ወሰለም ሲስሙህ ያየሁትን (የሰውነትህን ክፍል) አሳየኝ አለው። ሸሚዙን ከፍ አደረገ፣ አቡ ሁረይራ እምብርቱን ሳመው።”
- አህመድ ኢብን ሀንበል፣ አል-ሙስነድ ሐዲስ ቁጥር 7455 ሰሂህ እንደሆነ ገልጸውታል።
- አህመድ ሻኪር በተመሳሳይ ሰሒሕ ምድብ ውስጥ ዘግበውታል
- ወሲዩላህ አባስ በፈዷኢሉ ሰሀባህ ጥራዛቸው ውስጥ ሰሒሕ ምድብ ውስጥ ዘግበውታል (ሐዲስ ቁጥር 1375)
ማጠቃለያ እና መደምደሚያ
ነብዩ “ﷺ” የልጅ ልጃቸውን ብልት እንደሳሙ የሚገልጸው ሐዲስ ደካማ ነው። አንድ አያት የልጅ ልጁ ጋር የሚኖረውን ትስስር ሁሉ በዚህ ደረጃ ወሲባዊ/Sexualize/ ለማድረግ የተከሄደበት ጥረትም የፖርኖግራፊው አለም እንዴት ህሊናችንን እንደተቆጣጠረው የሚጠቁም ነው። ይህ ዘገባ ግን ተኣማኒ ያልሆነ ዘገባ መሆኑ እሙን ነው። በዚህ ዙሪያ ያለው አስተማማኙ ዘገባ ነቢዩ “ﷺ” የልጅ ልጃቸውን አል-ሐሰን ቢን ዓልይ (ረዐ) ሆዳቸውን (እምብርት) መሳማቸውን የሚጠቅሰው ሐዲስ ብቻ ነው።
▣ ይህ ጹሁፍ የኡስታዝ ወቃርን ሰፊ ጥናት መሠረት በማድረግ ለአማርኛ አንባቢ አጥሮ የቀረበ ነው።
(የሕያ ኢብኑ ኑህ)


