❐ ቀዳሚ ቃል
ቁርአን ከአምላካችን አላህ (سبحانه وتعالى ) የተሰጠን መለኮታዊ መፅሀፍ በመሆኑ በውስጡ ምንም አይነት የእርስበርስ ግጭት እንደሌለበት እኛ ሙስሊሞች እናምናለን። አንድ “መለኮታዊ” የተሰኘ መፅሀፍ ውስጡ ከእርስ በርስ መጣረስ የፀዳ ሊሆን እንደሚገባ ሁሉም ሰው ይጠብቃል። የእርስ በርስ ግጭት ስንል ከሀሳብ ግጭት ጀምሮ የቁጥር፣ የጊዜ፣ የቦታ ወዘተ ግጭቶችን ያካትታል። መነሻ ላይ የተናገረውን መድረሻ ላይ በተቃራኒ ቃል የሚያፈርስ መፅሀፍ አይደለም የአምላክ ቃል ሊሆን ይቅርና የአስተዋሽ ደራሲ ውጤትም ሊሆን አይችልም።
ከዚህ በመነሳት እኛ ሙስሊሞች መፅሀፍ ቅዱስ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችን ስንሰነዝር ቆይተናል። መፅሀፍ ቅዱስ አያሌ የእርስ በርስ ግጭቶችን በውስጡ አቅፎ የያዘ መፅሀፍ እንደሆነ የሚገልፁ የተለያዩ ድርሳናት በተለያዩ ቋንቋዎች ለዘመናት ሲቀርቡ ኑረዋል። ለሀገራችን አንባቢያን እንዲጠቅም በማሰብም ከዚህ በፊት “ስቲሮት” በሚል ርዕስ መፅሀፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ በቁጥር ከመቶ በላይ የሚሆኑ ግጭቶችን በማጠናቀር በአማርኛ ቋንቋ መጠነኛ መፅሀፍ አዘጋጅቼ ነበር 1 ሌሎች ወንድሞችም በተመሳሳይ በራሳቸው መንገድ ከመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያገኟቸውን የእርስበርስ መጣረሶች በተለያዩ ጊዜያት አስነብበዋል፤ ጠይቀዋል።
ነገር ግን እነዚህን መጣረሶች አስመልክቶ በክርስቲያኖች ዘንድ የተሰጡ ምላሾች እምብዛም የሚባሉ ናቸው። በዚህ ዘርፍ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ጥቂት የክርስቲያን ፀሀፍትን ስራዎች ብንመለከት “ምላሽ” ተብለው የቀረቡ ሀሳቦች ከነ አካቴው ሊያስገርሟችሁ ሁሉ ይችላሉ። የአንዳንዶቹ መልስ “ቢጋጭ ምን ችግር አለው?” ወይንም “የቁጥርና መሠል ግጭት መኖሩ እምነታችን ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ የለውም” የሚሉ “ምላሾች” ነበሩ። ዳንኤል ተሾመ የተሰኘ የክርስቲያን ፀሀፊ “ይኸውና መልሴ” በሚል ርዕስ ምላሽ ለመስጠት በሞከረበት መጽሀፉ ላይ የመፅሀፍ ቅዱስ ስህተቶችን አስመልክቶ የሚከተለውን ይላል፦
” .በአንፃሩ ደግሞ ቅዱሳን ሰዎች በጊዜና በቦታ ውስን ስለሆኑ፣ ሁሉንም አይነት እውቀት ለምሳሌም መልክዓ ምድራዊ፣ ሥነ ቋንቋዊ፣ የሥነ ጹሁፍ፣ ልዩ ልዩ መረጃዎች .. ወዘተ ስለማያውቁ (በከፊል ካልሆነ በቀር) በሥነ ጹሁፋቸው ውስጥ እንደ መረጃ ስሕተት፣ የጊዜ አቆጣጠር መዛባት፣ እንደ ታሪካዊ ቅንብር ያለ ጉድለት ሊኖር ግድ ነው” 2
በሌላ ቦታ እነዚህን የስምና የአሀዝ ግጭቶች አስመልክቶ ፀሀፊው ሲናገርም እንዲህ ይላል፦
“.. ስለዚህ የቦታ፣ የስምና የአሃዛት ልዩነት መከሰቱ እንግዳ ነገር አይደለም፤ ጸሀፊዎቹ የተሰጣቸውን መለኮታዊ መልዕክት በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋና በሥነ ጹሁፍ በኩል ስለሚያስተላልፉ፣ በዚያም ዘመን መረጃዎችን እንደ ልብ የማግኘትም ሆነ ወዲያው የመዘገብ ሁኔታ ስለሌለ፣ እስኪዘገብም ድረስ በትውስታ መልኩ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ስለሚተላለፍ፣ መዘገብ በሚጀመርበት ጊዜ የቦታ፣ የስምና የአሃዛት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል” 3
በተመሳሳይ ዶ/ር ተስፋየ ሮበሌ “የትምህርተ ሥላሴ መሠረታውያን፥ መጽሀፍ ቅዱሳዊ፣ ታሪካዊና ምክንዮአዊ ትንታኔ” በተሰኘው መጽሀፉ ላይም እንዲህ ይላል፦
“..2ኛ ሳሙኤል 10፥18፤ 1ዜና 19፥18 ላይ በ700 እና በ7,000 መካከል ያለው ልዩነት፣ በጥንት ጊዜ ክፍሉ ሲገለበጥ የተፈጠረ ስሕተት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ዐይነቱ የግልበጣ ችግር በወል የሚስተዋለው በእንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ ነው..” 4
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቅል በሆነ መልኩ የመፅሀፍ ቅዱስን ይዘትና የፀሀፊዎችን ማንነት አስመልክቶ ያለውን ግራ መጋባት መምህር ያሬድ ሽፈራው “የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥ” በተሰኘው መፅሀፉ የመጀመሪያው ቅጽ (ቅጽ ፩) ላይ እንደሚከተለው ይገልፀዋል፦
“በዘመናችን አንድ መጽሀፍ የመጽሀፉን ርእስ፣ የጸሀፊውን ስም፣ የተጻፈበትን ቀን፣ የታተመበትን ማተሚያ ቤትና ሀገር እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች መረጃዎችን ስለሚይዝ ስለመፅሀፉ ለመናገር ይቻላል። ሆኖም ቅዱሳን መፅሀፍት በተጻፉበት ወቅት ይህንን ዘመናዊውን የመረጃ አሰጣጥ መንገድ ተከትለው ስላልተፃፉ የተፃፉበትን ጊዜ በርግጠኝነት ለማወቅና በማን እንደተፃፉ ለመረዳት እጅግ አዳጋች ሊሆን ችሏል” 5
በዚህ ዘርፍ ጠቃሚ መልስ የሌላቸውና ተስፋ የቆረጡ አካላት የተሻለ መስሎ የታያቸው አካሄድ በተቃራኒው “ቁርአን ውስጥም ግጭት አለ” የሚል መከራከሪያ በማንሳት ጥያቄውን በአፀፋ ለመመለስ መሞከር ነው። በዚህም “መፅሀፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ቁርአንም ይጋጫልና ብዙ አይገርምም” የሚልን መልዕክት በቀላሉ በማስተላለፍ መልስ የሰጡ የመምሰል ኢ-አመክኗያዊ ብልጠት ነው። የነሱን ለራሳቸው ትተን ያመጡትን ስሁት ንጻሮ/False comparison/ በራሳችን መንገድ እንመልሳለን። ይህንን አስመልክቶ “በእውኑ ቁርአን ይጋጫልን?” የሚለውን ጥያቄ አንስተን በጥልቀት ካየን መልሱ “በፍፁም” የሚል ነው። ይህንን አስመልክቶ ከምንም በፊት እራሱ ቁርአን ማስተማመኛውን እንዲህ ሲል ይሰጠናል፦
أَفَلَا يَتَدَبَّرُونَ الْقُرْآنَ وَلَوْ كَانَ مِنْ عِندِ غَيْرِ اللَّهِ لَوَجَدُوا فِيهِ اخْتِلَافًا كَثِيرًا
ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን መለያየት ባገኙ ነበር፡፡
(ሱረቱ አል-ኒሳእ – 82)
ሙሐመድ ፉዓድ አብዱልባቂ የዚህን የቁርአን መልዕክት አስመልክቶ የምንመረምርበት/የምናረጋግጥበት ሁለት መንገድ አለ ይላል። አንደኛው መንገድ ቁርአንን ሙሉ ለሙሉ በማጥናት የሚጋጩ አንቀፆች እንደሌሉ ማረጋገጥ ነው። ይህኛው መሠረታዊና የሚተገበር ቢሆንም ከሁለተኛው አንጻር ትንሽ አድካሚና ጊዜ የሚወስድ ነው። ሁለተኛው አካሄድ ደግሞ እራሱ ይህንን የቁርአን አንቀፅ ብቻ በመመልከት ረቂቅ በሆነ መልኩ የምናረጋግጥበት ሌላኛው መንገድ ነው።
ስለ ግጭት የሚያወራውን የቁርአን አንቀጽ በዚህ መልኩ መፃፍና አንድ አስገራሚ እውነታ መመልከት እንደምንችል ያብራራል፦
“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ اخْتِلَافًا كَثِيرًا “ኢኽቲላፈን ከሲረን” ባገኙ ነበር፡፡”
ወይንም
“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙ اخْتِلَافًا “ኢኽቲላፈን” ባገኙ ነበር፡፡”
ቃላቶቹን መልሰን ስንሰድራቸው የሚከተለውን አረፍተ ነገር እናገኛለን፦
“ቁርኣንን አያስተነትኑምን ከአላህ ሌላ ዘንድ በነበረ ኖሮ በርሱ ውስጥ ብዙን “ኢኽቲላፈን/” ባገኙ ነበር፡፡”
ይህንን ያስተዋለ ጎበዝ ምክንያታዊ ሰው ቀጥታ የሚያደርገው ተግባር ልዩነትን ለመግለጽ የገባውን “ኢኽቲላፈን” የሚለውን ቃል ትርጉሙን ለጊዜው አቆይቶ ቃሉን ሌጣውን በሙሉ በአረብኛው ቁርአን ውስጥ መፈለግ ነው። ምክንያቱም ቁርአኑ ከአሏህ ባይሆን ኑሮ ብዙ ኢኽቲላፈን የሚለው ቃል ይገኝበት ነበር የሚል ውስጠ ትርጉምም ይወስዳልና።
በዚህም በቀላሉ የቁርአን ባለቤት አንድን ቃል በ”መጠቀም” እና እንዲሁ በ”ማንሳት” መካከል ያለውን ልዩነት ጠንቅቆ የተረዳ እንደሆነ ማወቅ ይችላል። ያ ብልህ ምክንያታዊ ሰውም ኢኽቲላፈን የሚለው ቃል ቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው ብዙ ጊዜ ሳይሆን አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ በቀላሉ ይረዳል ማለት ነው። ይህም ቁርአን ስለልዩነት የሚያወራውን አንድ ቃል ልዩነት እንደሌለ በገለጸበት ኹናቴ ቃሉንም የተጠቀመው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ይረዳል 6
ስለዚህም ቁርአን ከአላህ ሌላ የነበረ ቢሆን ኖሮ በውስጡ ብዙ “ኢኽቲላፈን” ይገኝበት ነበር። ቁርአን ስለፅንሰ ሀሳብ እያወራ ቃል ሲጠቅስም መልዕክቶችን አዝሎ ነው። ምናልባት አንድ ሰው ይህንን ሲመለከት ድንገታዊ ግጥምጥሞሽ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት ሊሰነዝር ይችላል። መልሱ ግን “አይደለም” የሚል ነው። ምክንያቱም እንዲህ አይነት አስደናቂ አንቀፆች በዚህ አንቀፅ ብቻ የተገደቡ አይደሉም። ቁርአንን ያጠና ሰው መሠል አንቀፆችን ያስተውላል..! አንድ እንጨምር፦
“ዋሂዳ وَحِيدًا” ወይንም “አንድ” የሚለው ቃል ቁርአን ውስጥ የተጠቀሰው በሚከተለው አንቀፅ ላይ ነው።
ذَرْنِي وَمَنْ خَلَقْتُ وَحِيدًا
አንድ ኾኖ ከፈጠርኩት ሰው ጋር ተዎኝ (እኔ እበቃሃለሁ)፡፡
(አል ሙደሢር – 11)
ይህ “አንድ” የሚለውን ቃል ትርጉም የሚይዘው “ዋሂዳ وَحِيدًا የተሰኘ ቃል በቁርአን ውስጥ ስንት ጊዜ የተጠቀሰ ይመስልዎታል? መልሱ ቀላል ነው፤ አንድ ጊዜ ብቻ..!
መሠል የቁርአን መልዕክቶች ጥልቀት ባለው መልኩ ጥናት የሚያስፈልጋቸውና ከተራ ትርጉም በዘለለ የግል ጥረትንም የሚጠይቁ ናቸው። ቁርአን ተጋጭቷል በሚል በአላዋቂ ሚሽነሪዎች የሚቀርቡ ሀተታዎችን አስተውሎ ለተመለከተ ሰው አይደለም መሠል ጥናት ውስጥ ሊያልፉ ይቅርና የትርጉም አንቀፆችን እንኳን በአርምሞት እንዳልተመለከቷቸው ይረዳል።
በአንድ መፅሀፍ ውስጥ “በለጠ ወደ አዲስ አበባ ሔደ” የሚል አረፍተ ነገርና በሌላ ቦታ ደግሞ “በለጠ ወደ ጎንደር ሔደ” የሚል ሌላ አረፍተ ነገር ቢያገኙ ለነዚህ ሰዎች ምናልባት ግጭት ተደርጎ ታይቷቸው ሊያስገርሟችሁ ይችላሉ። ለነሱ በለጠ አንዴ አዲስ አበባ ከሔደ ሌላ የትም ቦታ ሊሄድ የማይችል ሚስኪን ግለሰብ ነው። እነሆ ከዚህ በኃላ በሚቀርበው ተከታታይ ፁሁፍ እያንዳንዳቸውን ቁርአን ላይ የሚቀርቡ የግጭት ክሶች በአሏህ ፍቃድ ምላሽ የምንሰጥ ይሆናል። በዚህ ዘርፍ እስካሁን ያለውን ጥያቄ በአላህ ፍቃድ በተቻለ መጠን በዚህ ተከታታይ ፁሁፍ ዘርዝረን የምናጠናቅቀው ይሆናል።
- ማጣቀሻዎች
- ስቲሮት፥ ከ100 በላይ የመጽሀፍ ቅዱስ ግጭቶች – የሕያ ኢብኑ ኑህ ↩︎
- ዳንኤል ተሾመ – “ይኸውና መልሴ” ገጽ 10 ↩︎
- ዳንኤል ተሾመ – “ይኸውና መልሴ” ገጽ 84 ↩︎
- ዶ/ር ተስፋየ ሮበሌ – የትምህርተ ሥላሴ መሠረታውያን፥ መጽሀፍ ቅዱሳዊ፣ ታሪካዊና ምክንዮአዊ ትንታኔ ገጽ 142 ↩︎
- ያሬድ ሽፈራው ፤ የመጽሀፍ ቅዱስ ታሪካዊ አመጣጥ ቅጽ ፩ ገፅ 7 ↩︎
- Muhammad Fu’ad Abd al-Baqi, Al-Muahjam al-Mufahris li al-Fadh al-Qur’anal-Karim, 1997, Dar al-Fikr, Beirut (Lebanon), p. 305. ↩︎


