በወንድም ሳላህ
ጌታ አምላካችን ‟ﷻ” በዚህች ዓለም በመለኮታዊው ዛቱ ለማንም አልተገለጠም፣ ዓይኖች እንዲመለከቱትም ፈጽሞ አልፈቀደም። ከሁሉ በላይ የሆነው አሏህ በትንሳኤ ቀን እርሱ በፈቀደው መጠን እንደምናየው ነግሮናል፣ ያለ አንዳች ግርዶ ለባሮቹ እንደሚታይም በተለያዩ ተዓማኒ ትውፊቶቻችን ውስጥ ተዘግቧል። በምድራዊ ሕይወቱ ግን እርሱን በዐይነ-ሥጋው የተመለከተ አንድም ፍጡር የለም። አሏህ ለአንድ ነቢይ ወይም መልዕክተኛ የሚገለጠው በሦስት መንገዶች እንደሆነ በሱረቱል ሹራ 42/51 ላይ ከተናገረ ቡኋለ በገሃድ መገለጥ ግን ተገቢው እንዳልሆነ ገልጿል። ይህ ማለት ታላቁ መልዕክተኛ ነቢዩ ሙሐመድም ቢሆኑ ፈጽሞ በዐይኖቹ የእርሱን ዛት (ህላዌውን) አላዩትም ማለት ነው። ነቢዩ አሏህን አይቷል ብሎ የተናገረ ማንኛውም ሰው ውሸታም ነው።
عَنْ عَائِشَةَ رضى الله عنها قَالَتْ مَنْ حَدَّثَكَ أَنَّ مُحَمَّدًا صلى الله عليه وسلم رَأَى رَبَّهُ فَقَدْ كَذَبَ وَهْوَ يَقُولُ لاَ تُدْرِكُهُ الأَبْصَارُ
ከአዒሻህ (ረ.ዐ) እንደተተረከው፡ እርሷ እንዲህ ብላለች:- ‟ሙሐመድ (ﷺ) ጌታውን አይቷል ብሎ ያወራልህ ማንኛውም ሰው በእርግጥ ዋሽቷል፣ እርሱም ዓይኖች አያገኙትም ይል ነበርና።”
(📚Sahih al-Bukhari,7380: Book 97, Hadith 10)
እራሳቸው ነቢዩ ሙሐመድ ወደ ሰማይ በተጓዙበት ወቅት ጌታህን አይተሃልን ተብሎ በተጠየቁ ጊዜ እንዳላዩት በአንደበታቸው ተናግረዋል:-
عَنْ أَبِي ذَرٍّ، قَالَ سَأَلْتُ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم هَلْ رَأَيْتَ رَبَّكَ قَالَ نُورٌ أَنَّى أَرَاهُ
ከአቡዘር (ረ.ዐ) እንደተላለፈው፡ ‟የአላህ መልዕክተኛን (ﷺ) ጌታህን አይተሃልን?” ብዬ ጠየኳቸው፣ እሳቸውም ‟እርሱ ብርሃን ሆኖ ሳለ እንዴት ልመለከተው እችላለሁ ?” ብለው መለሱ።
(📚Sahih Muslim,178: Book 1, Hadith 348)
አራት ነጥብ ! ታላቁ መልዕክተኛ እራሳቸው አሏህ ብርሃን ነውና፣ ግርዶውም እንዲሁ ብርሃን ሆኖ ሳለ እንዴት አየዋለሁ ብለው ከተናገሩ፣ የምዕመናን እናት የሆነችው አዒሻም ዓይኖች አያዩትም የሚለውን አንቀጽ ከራሳቸው ዋቢ አድርጋ ነቢዩ ጌታውን አይቷል ብሎ ያወራ ማንኛውም ሰው ውሸታም መሆኑን ከገለጸች ማንም ተነስቶ ሌላን ነገር ቢያወራ ፈጽሞ ተቀባይነት አይኖረውም። ታድያስ እውነታው ይህ ከሆነ ! ከሰሞኑ ሙስሊም ባልሆኑ አካላት በተለይ በክርስቲያኖች የሚራገበው ሐዲስ ምንድነው ? የሚለውን አጠር አድርጌ ለመመለስ እሞክራለሁ። ሐዲሱ በብዙ መንገዶች የመጣ ቢሆንም እነርሱ የጠቀሱት ሸይኹል ኢስላም ለጃሕሚያዎች መልስ ከሰጡበት መጽሐፍ ነውና ያንኑ ዘገባ ላስቀምጥላችሁ:-
رأيتُ ربِّي في صورةِ شابٍّ أمرَدَ له وَفرةٌ جعدٌ قططُ في روضةٍ خضراءَ.
‟ጌታዬን በወጣት መልክ፣ ፂም ያሌላው፣ ፀጉራም ሆኖ በአረንጓዴ ስፍራ ውስጥ አየሁት።”
(📗በየኑ ተልቢስ አል-ጀሕሚያህ 7/290)
1- ቀደምት የሐዲስ ሊቃውንት በሪዋያው ደረጃ ወይም በተዓማኒነቱ ዙርያ ተለያይተዋል። ለምሳሌ ኢማሙ አህመድ፣ አጦበራኒ፣ አር-ራዚ፣ ኢብኑ በሻር ወዘተ..ትክክለኝነቱን የሚቀበሉ ምሁራን ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ ዘገባው ተቀባይነት ያሌለው “ደኢፍ” እንደሆነ ከተናገሩት ሊቃውንት መካከል ኢብኑል ጀውዚይ፣ ኢማሙ ዞሀቢይ፣ አስ-ሰበኪይ ወዘተ ይጠቀሳሉ [አል-ሙተናሂያ 1/36፤ ሲየር አዕላም አን-ኑበላዕ 10/113፤ ጠበቃት አሽ-ሻፊዕያህ 2/312]። ታላቁ የዘመናችን ሙሐዲስ ሸይኽ አልባኒይም በተመሳሳይ ተቀባይነት ያሌለው ዘገባ መሆኑን ጽፏል፣ እንዲያውም የመካከለኛው ዘመን የሐዲስ ሊቅ የሆኑት ኢብኑ ዲባዕ አል-ሸይባኒ ደረጃው “ደኢፍ” እንኳ ለመባል ብቁ ያልሆነ “መውዱዕ/Fabrication” እንደሆነ ገልጸዋል [አት-ተመዩዝ: ገፅ 95]።
➳ ታድያስ ራጂሁ (መያዝ ያለበት) የትኛው ነው ? ከተባለ በሙስጠላህ ሚዛን (Hadith terminology) መሰረት “ደኢፍ” ነው የሚለው ያመዝናል። አንድን ዘገባ ውድቅ የሚያደርጉ መስፈርቶች እዚህ ሪዋያ ላይ ይታዩበታልና። ለአሁን ግን በዚሁ ብቻ ላለመቋጨት እንደው ዘገባው ትክክለኛ (Sahih) ይሁን በሚለው እንሂድና እውነት ነቢዩ አሏህ ይህን ይመስላል ብለው እየተናገሩ ነው ወይስ ክርስቲያኖች ሳይረዱት እያራገቡ ነው ? የሚለውን እንመልከት።
2- ሐዲሱ ላይ ነቢዩ አሏህን ያዩት በዐይነ-ሥጋቸው ነው የሚል አንድም ሐረግ የለም። በተቃራኒው ግን ያዩት በሕልም እንደሆነ የሚናገር ተመሳሳይ ሐዲስ ተዘግቧል። እንዲህ ይላል:- رأيت ربِّي في المنامِ في صورةِ شاب ‟ጌታዬን በሕልም በወጣት መልክ አየሁት…።” [መጁሙዕ አል-ዘዋዒድ 7/182]። እራሳቸው ሐዲሱን ያስተላለፉልን ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያህ በዚያው መፅሐፋቸው ሐዲሱ ላይ በሰጡት ማብራርያ የሚከተለውን ብለዋል ❝..ነቢዩ አሏህን እንዳዩት የሚናገሩ እነዚህ ሐዲሳት በአጠቃላይ ስለ ሕልም ዕይታ ነው የሚያወሩት..❞ [በየኑ ተልቢስ አል-ጀሕሚያህ 7/229]። በተመሳሳይ መፅሐፍ ገጽ 194 ላይም ‟..ይህ ኢማሙ አህመድ እንዲወራ ያዘዘው ሐዲስ ስለ ሕልም ዕይታ ነው የሚገልጸው” ሲል ጽፏል። የሐዲሱን ትክክለኝነት የተቀበሉት ምሁራን እንኳ ዘገባው ስለ ዐይነ-ሥጋ እይታ እንደማያወራ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ኢብኑ ተይሚያህ ❝..በዚህች ዓለም ማንም አሏህን በዐይነ-ሥጋው ማየት አይቻለውም..❞ ብሏል፡ [መናሒጅ አስ-ሱናህ 2/313]።
ኢማሙ ዞሀቢይ ❝..ይህ ሪዋያ ትክክል ነው እንኳ ቢባል ስለ ሕልም ዕይታ ነው የሚናገረው..❞ ብለዋል [ሚዛን አል-ኢዕቲዳል 1/594]። አስ-ሲዩጢም ‟..ይህ ሪዋያ ስለ ሕልም ዕይታ የሚናገር ነውና ምንም ችግር የለውም።” ብለው ተናግረዋል [አል-መስኑዓህ 1/34]። አል-ዓጀሉኒም በቀጥታ የሲዩጢን ንግግር ምላሽ አድርገው ተጠቅመዋል [ከሽፍ አል-ኸፋዕ 1/437]። ጥንታዊው የሐዲስ ሊቅ ኢማሙ አዷሪሚይም በተመሳሳይ “وإنما هذه الرؤية كانت في المنام ማለትም ‟ይህ የሕልም ዕይታ ነው” ማለቱ ይታወቃል፡ [ነቅድ አለል ማሪሲይ 2/738]። ስለዚህ ሐዲሱ ተዓማኒ ነው በሚለው መንገድ እንኳ ብንጓዝ ነቢዩ አሏህን በዐይነ-ሥጋቸው ነው ያዩት የሚለውን አያመለክትም። በሕልም ደግሞ ማንም አምላኩን በተለያየ መልክ ሊመለከተው ይችላል። ይህ ማለት ግን አምላክ ያንኑ ያየነውን ነው የሚመስለው ማለት አይደለም።
ሸይኹል ኢስላም በዚሁ ዙርያ የሚከተለውን ተናግረዋል:-
❝የሰው ልጅ ጌታውን በሕልሙ ሊመለከተው፣ ሊያናግረውም ይችላል። ይህ በሕልም ውስጥ ያለ እውነታ ነው። ነገር ግን ተመልካቹ ሰው አሏህ በሕልሙ ያየሁትን ነው የሚመስለው ብሎ በፍጹም ማሰብ የለበትም። ያንቀላፋ ሰው በሕልሙ የሚመለከተው ነገር ከእውነታው ጋር አይመሳሰልምና። ስለዚህ ማንም አሏህን በሕልሙ ቢመለከተው አሏህ ያንን ይመስላል ማለት አይደለም፣ ሰው በተለያየ መልክ አሏህን ማየቱ ጉድለት ወይም ነውርም አይደለም። እርሱ ሰው ከሚያስበው ሁሉ የጠራ ነውና። አምላክን ይቅርና መላእክትንም ሆነ አጋንንትን በሕልም ቢመለከት በእውኑ ግን እነርሱ ያንኑ ይመስላሉ ብሎ ማሰብ የለበትም።”
(📗ኢብኑ ተይሚያህ፤ በየኑ ተልቢስ አል-ጀሕሚያህ 1/325)
3- ሌላኛው ነጥብ “ኢብኑ አባስ ነቢዩ አሏህን አይቷል” ብሏል የሚል ሙግት ነው። በእርግጥ ካFiሮች የጠቀሱትን ጠለቅ ብሎ ያልተመለከተ ሰው ኢብኑ አባስ እንደዚያ ያለ ብሎም ከነቢዩ እና አዒሻ ጋር በጉዳዩ ዙርያ የተለያየ ሊመስለው ይችላል። እውነታውን ስንመለከት ግን ታላቁ ሙሐዲስ እና ሙፈሲር ፈጽሞ ከነቢዩም ሆነ ከአዒሻህ ጋር እንዳልተጋጨ እንረዳለን። እስኪ ሐዲሱን እንመልከት:-
سألْتُ ابنَ عبَّاسٍ: هلْ رأى محمَّدٌ ربَّه؟ قال: نعمْ، دونَه سِترٌ مِن لُؤلؤٍ..
ኢብኑ አባስን ‟ሙሐመድ ጌታውን አይቷልን ?” ብዬ ጠየኹት። እርሱም ‟አዎ ከፊትለፊቱ የዕንቁ መጋረጃ ነበር” ብሎ መለሰ። (አል-ሙንተኺብ ገጽ 232)
ከኢክሪመ በኩል የመጣው ዘገባ ይህ ነው። በዚህ ሐዲስ ላይ ኢብኑ አባስ ነቢዩ ጌታ አሏህን አይቷል ብሎ ሲናገር በፍጹም በዐይነ-ብረቱ ተመልክቶታል እያለን አይደለም። ከፊትለፊቱ የዕንቁ መጋረጃዎች አሉ ማለቱን ልብ በሉ። ታድያ ነቢዩ ጌታውን አይቷል ማለቱ ስለምንድነው ከተባለ እራሱ ኢብኑ አባስ በሰሒህ ሙስሊም 176: መፅሐፍ 1 ሐዲስ 341 ላይ “The Prophet saw Allah with, his heart” በማለት እይታው በልቡና እንጂ በዐይነ-ሥጋ እንዳልሆነ ይገልጻል። ኢብኑ ተይሚያህ እንደሚከተለው ያጠቃልሉታል:-
كُلُّ حَدِيثٍ فِيهِ: أَنَّ مُحَمَّدًا رَأَى رَبَّهُ بِعَيْنِهِ فِي الْأَرْضِ فَهُوَ كَذِبٌ بِاتِّفَاقِ الْمُسْلِمِينَ وَعُلَمَائِهِمْ؛
‟ሙሐመድ (ﷺ) በምድራዊ ሕይወቱ ጌታውን በዐይነ-ሥጋው አይቷል የሚሉ ዘገባዎች በአጠቃላይ በሙስሊሙ እና በሊቃውንቶች ስምምነት መሰረት ውሸት ናቸው።
(📚መጅሙዕ አል-ፈታዋ፤ ቅፅ 3፡ ገጽ 386)
وَلَمْ يَثْبُتْ عَنِ ابْنِ عَبَّاسٍ وَلَا عَنِ الْإِمَامِ أَحْمَدَ وَأَمْثَالِهِمَا أَنَّهُمْ قَالُوا: إنَّ مُحَمَّدًا رَأَى رَبَّهُ بِعَيْنِهِ،
‟ከኢብኑ አባስም ሆነ ከኢማሙ አህመድ ወይም ከመሰሎቻቸው ሙሐመድ በዐይኑ ጌታውን አይቷል የሚል አንድም በትክክል የተረጋገጠ ሪዋያ የለም።
(📚መጅሙዕ አል-ፈታዋ፤ ቅጽ 1፡ ገጽ 176)
○ ማጠቃለያ:- ጌታ አምላካችንን በዓይነ-ሥጋው የተመለከተው አንድም ፍጡር የለም። አሏህን በወጣት መልክ አየሁት የሚለው ዘገባ ጥርጥር ያለበት እንዲያውም ብዙ የሐዲስ ሊቃውንት “ደኢፍ” ያሉት ዘገባ ነው። የተቀበሉት እንኳ እይታው የሕልም እንደሆነ ነው የሚያምኑት (በሌላ ሐዲስም እንደመጣው ምሳሌ) ስለዚህ ተቀባይነት አለው ራሱ ቢባል ነቢዩ አላህን እየገለጹበት ያለ መንገድ ሳይሆን በሕልም ያዩትን ነው የተናገሩት። በሕልም ደግሞ ሁሉም ሰው አምላክን በተለያየ መልክ ሊመለከተው ይችላል። ይህ ማለት አምላክ ለሁሉም ሰው የተያውን ይመስላል ማለት ግን በፍጹም አይደለም።
® Hidaya islamic Center🖊


