“ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቷል” የሚለውን ቃል እየደጋገመ እንደሚፎክር ሰባኪ የሚያሳዝነኝ ፍጡር የለም። ግለሰቡ የዚህ እምነቱ “ድንቅነት” ያስገረመበት ምክንያት ኢየሱስን አስመልክቶ ያለው ምልከታ በጥርጣሬ ወጀብ የተመታ ስለሆነ ነው። ከመነሻው ፈጣሪ ሞት የሚባለውንና እራሱ የፈጠረውን ነገር ማሸነፉ ምኑ ነው እንደ ትልቅ ጀብድ የእድሜ ልክ የሰበካ ርዕስ የሚሆነው? ምናልባት በሰባኪው ልቦና ውስጥ የኢየሱስ ቦታ የተደናገረ ደረጃ ካለው (ፍጡር ወይንስ ፈጣሪ የሚለው) ክስተቱን ቢያገዝፈው አይደንቅም። አንድ ፍጡር ሞትን ድል አድርጎ ቢነሳ የምርም ይገርማል፤ በዚህ መሀል በጥርጣሬ ለሚዋልል ሰው የኢየሱስን ከሞት መነሳትን ማመን እንደ ትልቅ ነገር ቢመለከተው ግን አይገርምም።
አንድ ተጨማሪ ነገር
ሞትን ድል ማድረጉ ትልቅ የክርስትና ስኬት ተደርጎ በጳውሎስ መጠቀሱም አስገራሚ ነው። ጳውሎስ ኢየሱስ ባይነሳ ኑሮ ክርስትና ከንቱ እንደነበር ይነግረናል፦
“ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው።”
— 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥14 (አዲሱ መ.ት)
አስቡት አንድ አምላክ እንደሞተ ቢቀር ሊያስጨንቅ የሚገባው የዚህ አጽናፈ አለም ህልውና ነው ወይንስ ከህልውናው ቀጥሎ የሚመጣው ሰበካ ነው? ክርስትና ቫኪውም ላይ አይሰበክም፤ ክርስትና ይሰበክ ዘንድ ምድራችን ልትኖር ይገባል። አምላክ ከሌለ ደግሞ እሱ የለም። ታዲያ ጳውሎስ በትክክል ኢየሱስ አምላክ እንደሆነ ቢያስብ ኑሮ ሞቶ በመቅረቱ ከንቱ የሚሆነው ምን ሊሆን እንደሚችል አይረዳም ነበር ማለት ነው?
ጳውሎስ የዘነጋው ነገር ቢኖር ግን የኢየሱስ ትንሳኤው ሳይሆን ስቅለቱ ነበር ዋጋ ቢሱ..! ኢየሱስ ሊሞትለት የሚገባ ጉዳይ ፈጽሞ አልነበረውም። ምናልባት አይሁዶች እንደሚገድሉት ተጨንቆ እያለቀሰ አምላኩን እንዲያድነው ለምኗል፤ ከዚያ በተረፈ የሚሞትለት ሌላ አላማ አልነበረውም። በሶስተኛው ቀን እንደሚነሳ እያወቀ በተከታዮቹ ላይ ተራ ድራማ መስራት አይጠበቅበትም። ስቅለቱ ከመነሻው አላስፈላጊና ዋጋ ቢስ ነበር፤ አልሐምዱሊላህ አሏህ ﷻ ከግድያቸው አድኖታል፤ ባይሆንና ቢገደል ኑሮ እንኳን ከሱ በፊት የነበሩ ነብያትን እንደገደሉት ሁሉ የሱም ሞት ሌላ ትርጉም የሌለው የአይሁዳውያን ግድያ ይሆን ነበር። በርግጥም ያዳነው አሏህ አሸናፊና ጥበበኛ ነው።
© የሕያ ኢብኑ ኑህ


