ዳዊት ንጉስ ብቻ አልነበረም “ልበ አምላክ” ሳይቀር የተባለለት ፃድቅ ሰው ነበር። መጽሀፍ ቅዱስ በእርግጥ ስለ ዳዊት ሲነግረን አይደለም ጻድቅ ይቅርና ተራ አማኝ እንኳን እንዳይመስለን አድርጎ በሀጥያት አጨማልቆ ነው የገለፀልን። የሰው ሚስት ከጋብቻ ውጭ ማማጋጡ ሳይቀር የተረገዘው ልጅ የባሏ እንደሆነ ለማስመሰል ጦር ሜዳ የነበረውን ባሏን አስመጥቶ ከሷ ጋር እንዲተኛ ሊያግባባው ሞከረ። ባሏ ግን ጓዶቹ ጦርሜዳ ሁነው እሱ ምቾትን እንደማይፈልግ በመግለፅ ራሱን ማቀቡን ገለፀ። መጨረሻ የወሰደው እርምጃ ታዲያ ባሏን እንዲገደል ማድረግ ነበር። ይህ የምነግራችሁ ታሪክ ተራ የልቦለድ ድርሳን ውስጥ ያለ ሳይሆን መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ በ2ኛ ሳሙኤል ምዕራፍ 11 ጀምሮ የተተረከ ታሪክ ነው።
በዚህ መልኩ በህይወቱ ዙሪያ በድፍረት ሀጥያተኛ የሆነ ሰው ለሌላው ሰው ምን ሊያስተምር ነብይ እንደተደረገ ፀሀፊዎቹ ያውቃሉ። ያም ሁኖ ዳዊት እንደ መልካም ሰውም ተደርጎ ተገልፆልናል። እግዚአብሔር ንጉስ ዳዊት ሚስት በማብዛቱም አልከፋውም። እንዴውም በቂ ሚስቶች እያሉህ ለምን የሰው ሚስት አማገጥክ? ያሉት አንሰውብኝ ነው ብትል እኮ እጨምርልህ ነበር ይለዋል።
“የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ #የጌታህንም #ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ #ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ #እጨምርልህ ነበር።”
— 2ኛ ሳሙኤል 12፥8
እግዚአብሔር ለዳዊት ምድራዊ ስሜቶች እጅግ ስስ ሁኖለት ነበር። ሴት ልጅ ማለት ለዳዊት ሲሸመግል እንኳን ማሞቂያ እንድትሆን ከሀገሪቱ ሁሉ ተመርጣ ትመጣለት ነበር። ያውም ለማሞቂያ ማንኛውም ሴት አልነበረም የምትመጣለት ተመርጣ ድንግሏ ነበር የምትመጣው።
“ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፥ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር። ባሪያዎቹም፦ ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለጋለች፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፥ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው አሉት። በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቈንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፥ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ” 1ኛ ነገሥት 1፥1-3
የሴት ልጅ መብት በቀደምት የሮማውያን ስልጣኔ እንዲሁም በቀደምት የፐርሺያኖች አልያም ሌላ ገናና ስልጣኔዎች ውስጥ ከተራ ሸቀጥነት የዘለለ ዋጋ አልነበራትም። ይህ በነዚህ ሰው ሰራሽ ህግጋትን መመሪያ ባደረጉ ባርባርያኖች ዘንድ ቢኖር ብዙ ላይገርም ይችላል። በፈጠራት አምላኳ እኩልነት ስትነፈግና ተራ የወንድ ልጅ የብብት ማሞቂያ ስትደረግ መመልከት ግን ያደክማል።
እነዚህ ትርክቶች በዘመኑ ከነበሩ አምላክን በማያውቁ ነገስታት ታሪኮች አንፃር ብዙም አስገራሚ ላይሆኑ ይችላሉ። በማይለዋወጠው የአምላክ ማንነትና ስርአት ውስጥ ቦታ ተሰጥቶት ተቀምጦ ማየት ግን ያሳፍራል። ስለሴት ልጅ መብት መጽሀፍ ቅዱስን አንስተን የተወሰነ ታሪኮችን ብንመለከት አይደለም ለራሳቸው ለሴት እህቶቻችን ይቅርና እህትና እናት ላለን ለኛ ለወንዶችም የሚረብሹ ታሪኮችን ማየታችን የማይቀር ነው።
ስናጠቃልለው የዳዊት ህይወት በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው ከስህተቱ እንድንማር ነው የሚሉን ክርስቲያኖች መልሳቸው ያስገርማል። ዝሙትና የሰው ሚስት ማማገጥ ጸያፍ መሆኑን ልናውቅ ዘንድ አንድ ነብይ መዘሞትና ሰው መግደል አለበት ማለት ነው? ይህኮ በተፈጥሮ ሳይቀር Innate በሆነው ማንነታችን ልክ እንዳልሆነ የምንረዳው እውነታ ነው። ከዚያ ይልቅ መሰል ታሪኮች ሰውን ለሀጥያት የቀለለ ምልከታ እንዲኖረው ከማገዝ በዘለለ የሚጠቅሙት ፋይዳ አይኖርም። በእግዚአብሔር የተቀባ ሰው አንዲት ሴትን ስትታጠብ እርቃኗን አይቷት ተማርኮ ከዘሞተ ተራው አማኝማ ከዚያም በላይ ቢፈጽም ብዙ አያስገርምም። የእግዚአብሔር ሰው እግዚአብሔርንና ትዕዛዙን በዚያ ደረጃ ከተረሳው የሌላውማ ያን ያክል የሚካበድ አይደለም።
እስልምና እንደሚነግረን ነብዩሏህ ዳውድ عليه السلام በዚህ መሰል ነውሮች ውስጥ የሚዘፈቅ ሰው አልነበረም። ለህዝቦቻቸው መሪና መንገድ አመላካች አብሪ ከዋክብት ይሆኑ ዘንድ ከተመረጡ ነብያቶች መካከል አንዱ ነበሩ። አሏህ ﷻ ስለሱና ስለልጁ ሲናገር እንዲህ ይላል፦
وَلَقَدْ آتَيْنَا دَاوُودَ وَسُلَيْمَانَ عِلْمًا ۖ وَقَالَا الْحَمْدُ لِلَّهِ الَّذِي فَضَّلَنَا عَلَىٰ كَثِيرٍ مِّنْ عِبَادِهِ الْمُؤْمِنِينَ
[ ሱረቱ አል-ነምል – 15 ]
ለዳውድና ለሱለይማንም ዕውቀትን በእርግጥ ሰጠናቸው፡፡ አሉም፡- «ምስጋና ለአላህ ለእዚያ ከምእምናን ባሮቹ በብዙዎቹ ላይ ላበለጠን ይገባው፡፡»
© የሕያ ኢብኑ ኑህ


