የወንጌላውያን ወጥመዶች -3
(የግለሰቡን የእምነት መሠረት መናድ)
❝..አላማየ ሙስሊሞችን ክርስቲያን ማድረግ አይደለም.❞
ጆርዳናዊው ዳዒ ፕሮፌሰር ኢያድ ቁነይቢ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2002 የገጠማቸውን ክስተት አስመልክቶ ሰፋ ያለ አርቲክል ጽፈው ነበር። በወቅቱ አንድ ወዳጃቸው አንድ በአሜሪካ የሚዘጋጅ መጽሔት ይሰጣቸዋል። የመጽሄቱን ይዘት ሲመለከቱት ግን በጣም ይገረማሉ። መጽሄቱ አንድ የተለያዩ ሚሽነሪዎችን የህይወት ተሞክሮ በተመለከተ ያዘጋጀው ዘገባ ነበር።
በመጽሄቱ ላይ ከተጠየቁ ሚሽነሪዎች መካከል አንዱ እንዲህ ይላል፦
..
❝My goal is not to convert a Muslim,… My goal is to plant a tiny seed that will fester and gnaw and grow, so that eventually they will begin to question their religion. My prayer is that they will become restless sleepers and troubled by what they hear. That’s a horrible thing to wish on someone..❞
ትርጉሙም
❝ አላማዬ ሙስሊምን መቀየር (ክርስቲያን ማድረግ) አይደለም፣ … አላማየ ሀይማኖታቸውን መጠራጠር እንዲጀምሩ የሚያደርግ እየቆየ የሚመረቅዝ የሚከነክናቸውና እያደገ የሚሄድ ትንንሽ ዘር መትከል ነው። ጸሎቴም እንቅልፍ አልባና እረፍት የሌላቸው እንዲሆኑና በሚሰሙት ነገር እንዲጨነቁ ነው። በእርግጥ ለአንድ ሰው ይህንን መመኘት በጣም አሰቃቂ ነገር ነው..❞
የክርስቲያን ሚሽነሪዎች በተለይም የቅርብ ጊዜያት ስራዎቻቸውን ለተመለከተ ሰው ጭንቀታቸው ወደነሱ እምነት እንድትመጣ አይደለም። አንድ ዲኑን በመጠኑ የተረዳ ሰው የነሱ ኩፍር ውስጥ ቁምነገር አለ ብሎ የሚሳብበት ምንም መሠረት እንደሌለ ጠንቅቀው ያውቁታል። ዋነኛ አላማቸው ወደነሱ መሄድ ያልቻለውን ሙስሊም ቢያንስ ባለበት ሀይማኖት ላይ እንዳይቆይ ውዥንብር በመፍጠር ዘደ ኤቲየዝም፣ ኒሂሊዝም ወዘተ እሳቤዎች እንዲሻገር መትጋት ነው።
ሙስሊሙ በእምነቱ ጠንካራ መሆኑ አብዝቶ ምቾት ይነሳቸዋል። ወደነሱ ለማምጣት የሚደረገው ሙከራም ከዱንያዊ ጥቅማጥቅሞች ጋር ያልተያያዘ ካልሆነ በቀር አዳጋች እንደሆነ ያውቁታል። ስለዚህም ጥርጣሬ በመፍጠር በራሱ እምነት ዙሪያ በጥርጣሬ እየዋለለ አእምሮው በዚ እንዲሆን ይፈልጋሉ። ዋነኛ የትኩረት አጀንዳቸው ምዕመኑ ወደነሱ እንዲመጣላቸው ቢሆንም የመጨረሻ ግባቸው ግን ሙስሊሙን ከእምነቱ መነጠል ነው።
በዚህ በኩል በንጽጽሩ አለም ውስጥ በዳዕዋ ስራ ላይ የተሳተፉ ወንድምና እህቶች ትኩረት ሊሰጡበት የሚገባ አንድ አጀንዳ አለ። እሱም በተለያዩ የንጽጽር ጉዳዮች ሲጽፉ አጀንዳ መቅረጽ ያለባቸውና አጥንተው መጻፍ ያለባቸው እነሱ ናቸው። ኩፋሮች የቀደዱትን ቦይ ይዞ መፍሰስ ተገቢ አይደለም። አስፈላጊ ሲሆንና ለዑማው ይጠቅማል ሲባል አጀንዳውን በራስ የጊዜ ሰሌዳና የፍሬሚንግ ልክ በማንሳት ተገቢውን መልስ መስጠት ይቻላል። ከዚያ ውጭ መጽሀፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ አስፈላጊ ስራዎችን ሙስሊሞች እንዳይሰሩ በማሰብ በትርኪ ምርኪ የመልስ መልሶች ለመጥመድ በለፉ ቁጥር ተባባሪ መሆን አያስፈልግም። ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልገው “ምን አይነት ስራ ብሰራ ነው ለክርስቲያን ወገኖቼ መዳን አስተዋጽኦ የማበረክተው?” የሚለው ላይ ብቻ ነው። በዚህ ሒደት ላይ ዋነኛው መሠረታችን መርህ ብቻ ነው። መርህን አጥብቆ የያዘ ሰው የትኛውም ወጀብ አያዘዋውዘውም፤ ስሜታዊ አድርጎም በእልህ መስመር አያስተውም።
ሲጠቃለል
ሙስሊሙን በተመለከተ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ሚሽነሪ ዋነኛ ትኩረቱ የሙስሊሙ መደናገር ነው። በተቻለ መጠን ሙስሊሙ በመልስ ብቻ ተጠምዶ ስለ መጽሀፍ ቅዱስ እንዳያወራና ቢዚ ማድረግም ነው። በዚህ ስራ ላይ ባላንስ ያደረገ አካሔድን መከተል ይኖርበታል። መልስ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሲነሱ በዝርዝር መመለስ በተመሳሳይ ሰአት ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት የነሱ ሀይማኖታዊ መጽሀፍትስ ይዘቱ ምንድን ነው የሚለውን ለምዕመኑ እያቀረቡ በጨዋነት መወያያት ትክክለኛውና አዋጭው መንገድ ነው።


