የማርቆስ ወንጌል
«ከአራቱ ወንጌላት መካከል የመጀመሪያውና በቀዳሚነት እንደተጻፈ የሚታመነው የማርቆስ ወንጌል ነው። ይህ ወንጌል ከ66- 70-4) AD ባሉት ጊዜያት እንደተጻፈ ይገመታል። ምሁራን አራቱም ወንጌላት ጸሐፊያቸው በእርግጠኝነት አይታወቅም ይላሉ። አክለውም ጸሐፊዎቹ የኢየሱስ ሐዋሪያት ወይም የዘመኑ የአይን- ምስክሮችም አይደሉም ይልቁንስ ዛሬ ላይ ያለው ስያሜያቸው በ2ኛው ክፍለ ዘመን ላይ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የተሰየሙ ባዶ ስያሜዎች ናቸው ይላሉ።
«ከእነዚህ አራት ወንጌላት ውስጥ የመጀመሪያውን ወንጌል የማርቆስ ወንጌልን ስንመለከት ጸሐፊው ሐዋሪያ አልነበረም ማንነቱም አይታወቅም። ይሁንና ግን እንዲሁ ግምታቸውን ሲያስቀምጡ “ዮሐንስ የተባለው የኢየሩሳሌሙ ማርቆስ” ነው ይላሉ። ክርስትና ግን ይህን ጸሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ነው ወንጌሉን የጻፈው ብሎ ያምናል። ግን እንዴት? የቱ መንፈስ ቅዱስ? በምን ስሌት መንፈስ ቅዱስ ላይ ይለጠፋል?
«ይህንን ማንንቱ ያልታወቀ ጸሐፊ ተፈብርኮ በተሰጠው ስያሜ “ማርቆስ” እያልን ልንነጋገር ግድ ነው። ስለዚህ ማርቆስ እንዴት ጻፈው? ስንል ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት” ብለው ይመልሳሉ። ግን የመንፈስ ቅዱስ ሚናው መሪነቱ የቱ ጋር ነበር?
“ማርቆስ ወንጌሉን ያዘጋጀው በመንፈስ ቅዱስ መሪነትና የነገረውን እንደሆነ አላስቀመጠም አልገለጸም። ይልቁንም እውነታው ከዚህ ተቃራኒ ሁኖ እናገኘዋለን። በመሠረቱ ሁሉም ወንጌላት ከክርስቶስ ከብዙ አመታት በኋላ በቃል እና በብጥስጣሽ ጽሑፎች ሲተላለፍ የነበረን ዘገባና ትርክት አቀናብረው በማሰካካት ያቀረቡት ዝግጅት ብቻ ነው። ስለዚህ ማርቆስም በዚህ ወንጌል ቅንብር ላይ ብዙ ምንጮችን (Sources) ተጠቅሟል።
“የሚገርመው ደሞ ከሱ ቀጥለው የተጻፉት “የማቴዎስ” እና “የሉቃስ ወንጌል” የማርቆስን ወንጌል እንደ ዋና ምንጭ መጠቀማቸው ነው። ሌሎች ተጨማሪ ምንጮችን በመጠኑ ቢጠቀሙም እንደ ዋና ምንጭ ማርቆስን ተጠቅመውታል። ያ ማለት በቀላል አገላለጽ ወደ ፊት የፈጣሪ ቃል የሚሆንን የእምነት መጽሐፍ አንዱ ከአንዱ ይኮርጁ ነበር ማለት ነው። ለዛም ነው ሦስቱ ወንጌላት በተመሳሳይ ትርክት፣ በተመሳሳይ ቃላት አጠቃቀም፥ ተመሳሳይ ቅደም ተከተል ሳይቀር እጅግ በመመሳሰላቸው ምክንያት «ተመሳሳዮቹ ወንጌላት» (Synoptic Gospels) የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።
«ታዲያ ይህ ሁሉ ሲሆን የመንፈስ ቅዱስ ሚናው የት ገባ? ምን እየጠበቀ ነበር? በክስተቱ ዘመን ያልነበሩ ሰዎች ከዘመናት በኋላ በራሳቸው ጥረት ከቀደምት ሕዝቦች የደረሳቸውን የታሪክ ብጥስጣሽ መረጃ በጽሑፍ አስቀመጡ እንጂ ከዚህ የተለየ ምን ተፈጠረ? ምንም አላደረጉም። መንፈስ ቅዱስ ቢሆን ኖሮ ዋና ተቆጣጣሪው አንዱ ከአንዱ የሚኮርጅበት እድል አይፈጠርም ነበር። ምን ፍለጋ? ምን ጎድሎት አንዱ ከአንዱ ይኮርጃል?
«ለሁሉም ወንጌላውያን በየግላቸው መጻፍ የሚገባቸውን እውነታ እና ታሪክ ለሰው ልጆች እግዚአብሔር ማስተላለፍ የፈለገውን እውነታና ሕግ-ጋት በቀጥታ በነገራቸው ባጻፋቸው ነበር። ማርቆስ የኢሱስን ታሪክ ከተለያዩ ምንጮች አጥንቶ መጻፉ ዛሬ ላይ አንድ የታሪክ አጥኚ ወይም ተመራማሪ የኢየሱስን ታሪክ ቢያጠና እና የጥናቱንም ወጤት ታሪክ በመጽሐፍ ቢያቀርብ በምን ሚዛን ነው የፈጣሪ ቃል የምንለው? ማርቆስስ ከዚህ የተለየ ምን አደረገ?
«የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጸሐፊያቸው የማይታወቁ ወንጌሎችን በሐሰት ማንነት መጠሪያ እንደሰየመችው ሁሉ “በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተጻፉ” የሚለውም እሳቤ ቤተ ክርስቲያኗ መጽሐፍቱን በምእምናን ላይ ለመጫንና በተራው ምእመን ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የፈጠረችው እሳቤ እንጂ የትኛውም ወንጌላዊ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ግንኙነት ያለው አልነበረም።
«ሁሉም ወንጌላዊ ወንጌሉን የጻፈው በራሱ ጥረትና ድካም እንደ ማንኛውም ታሪክን ማጥናትና መጻፍ እንደሚወድ ሰው እንደ ግለሰብ ብቻ ነው። ስለዚህ የማርቆስም ሆነ የሌሎች ወንጌላት በዚህ ይዘታቸውና አወቃቀራቸው ሳሉ የፈጣሪ ቃል ከተሰኙ የትኛውንም የሪሰርች ውጤትን የፈጣሪ ቃል ነው ብሎ ከማመን በምንም መልኩ አይለይም።
© አቡ ማሒራ


