«ሉቃስ ማለት የጳውሎስ ተማሪ ጋደኛው የነበረና የሕክምና ሙያ ጭምር የነበረው ሰው ነበር። ጳውሎስም ኾነ ሉቃስ ኢየሱስን አያውቁትም በዘመናቸውም አልተገናኙም። ይሁንና የዚህ የጳውሎስ ጓደኛ የሆነው ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈበትን ዘመን ምሁራን እንደሚያስቀምጡት ከ80-90 AD እንደተዘጋጀ ይናገራሉ። እስከ 110 AD ያደረሱትም አልጠፉም። ይህ የመጀመሪያው ቅጂ {manuscript} ጽሑፍ ደብዛው ጠፍቷል ምኑም የለም። ዛሬ ላይ የዚህ ወንጌል ቀዳማይ ጽሑፍ {Manuscript} አለ የሚባለው በ 250 AD ላይ የተዘጋጀ ፓፒረስ 75 {Papyrus 75} ነው።
«የሉቃስ ወንጌል መጽሐፉ ጸሐፊውን አይናገርም። ግለሰቡን ማወቅ አልተቻለም። ጸሐፊው የጻፈበትንም ሐገር የት እንደሆነና ይህን ደብዳቤ ተቀባዩ ቴዎፍሎስም በየት ሐገር ይኖር እንደነበር ወደ የት እንደተላከ አይታወቅም። ይሁንና የመጽሐፉ ጸሐፊው ማን እንደኾነ በእርግጥ ባይታወቅም «የሉቃስ ወንጌል እና የሐዋሪያት ሥራ» ጸሐፊ እንዲሁ በግምት ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚጠቀሰው አንድ ሰው ነው። እሱም «የጳውሎስ ተማሪ ወይም አብሮት የነበረው ጓደኛው ሉቃስ ሊሆን ይችላል» ይላሉ።
«ይህ ማንነቱ ያልታወቀ ጸሐፊ ይህንን ወንጌል የተባለውን ደብዳቤ የፃፈው “ለወዳጁ ቴዎፍሎስ” እንጂ ልክ ዛሬ ላይ እንደምናዬው ከሁለት ቢሊዮን በላይ ለክርስትናው ዓለም “ቅዱስ ወንጌል” ወይም “የፈጣሪ ቃል” ብለው እንዲያምኑበት አስቦ በፍጹም አልነበረም። እሱም ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም የወንጌላት ጸሐፍት ማናቸውም ቢሆን ጽሑፋቸውን ሲጽፉ “መጽሐፍ ቅዱስ” ይሆናል ብለው አስበውት አልነበረም። ዶ/ር ማኒስ እንደሚለው፦——
“Never came across any of the New Testament writers’ mind that his writing about Christ would become the Christians’ holy book, which Christians read for centuries around the -world”.
« የዶ/ር ቄስ ማኒስ ንግግር በግርድፉ ሲቀመጥ፦—- «ማንኛውም የወንጌል ጸሐፊ ስለ ክርስቶስ ታሪክ ሲፅፍ ክርስቲያኖች የእሱን ወንጌል ወደፊት “መጽሐፍ ቅዱስ” አድርገው እንደሚወስዱትና ለረዥም ምዕተ አመታት የእምነት መጽሐፋቸው አድርገው ያነቡታል ብሎ ያሰበ ጸሐፊ ማንም አልነበረም» ይለናል። {{ -Fake Suspicions about the Bible, Priest Manees A.Noor, PP42}}
«የሉቃስ ወንጌልንም ጸሐፊ ለመረዳት ስናይ ጸሐፊው ማንም ይሁን ማን ብቻ ገና ወንጌሉን መጻፍ ሲጀር ደብዳቤው ለማን እንደኾነና የሚመለከተው አካል ማንን እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ አስፈሮታል። ስለዚህ ደራሲው ተደራሲውን በግልጽ ካሰፈረ በሰው ደብዳቤ ሌላው ሕዝብ በማይመለከተው ማጨብጨብ አያስፈልግም። ጸሐፊው ገና ሲጀምር እንዲህ ይላል፦—-
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
«በእኛ መካከል ስለ ተፈጸሙት ነገሮች ብዙዎች ታሪኩን የተቻላቸውን ያህል ጽፈውት ይገኛል ይህም ታሪክ ከመጀመሪያው አንሥቶ የዐይን ምስክሮችና የቃሉ አገልጋዮች የነበሩት ያስተላለፉልን ነው። ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ፤ እኔም በበኩሌ ሁሉን ከመሠረቱ በጥንቃቄ ከመረመርሁ በኋላ፣ ታሪኩን ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ። ይህንንም የማደርገው የተማርኸው ነገር እውነተኛ መሆኑን እንድታውቅ ነው» {«ሉቃስ 1-4 አዲሱ መ.ት)
«ይህ ያልታወቀ ጸሐፊ በግልጽ እንዳስቀመጠው የጻፈበት ዋና አላማ ለወዳጁ ብቻ መሆኑን አንጽኦት ሰጥቶ “ክቡር ቴዎፍሎስ ሆይ» ሲል የግል አክብሮቱንና ትህትናውን አስቀድሞ ጽፎለታል።
«እንግዲህ እዚህ ላይ ልብ የምንለው ዋናው ነገር ዛሬ ክርስቲያኖች እንደሚሉትና እንደለጠፉበት ጸሐፊው “መንፈስ ቅዱስ ተገልጦልኝ” መንፈስ ቅዱስ አዝዞኝ» “የጻፍኩት የእምነት መጽሐፍ ቅዱስ ነው” ምናምን ብሎ አልተናገረም። እሱ ያስቀመጠው በቀጥታ የግል ስሜቱንና በወቅቱ የተከሰቱ ክስተቶችን እንደዚሁም ከቀደምት አፈታሪኮች የሰማውን ያጠናውን በደንብ ከመረመረ በኋላ ለጠቅላላ እውቀት ለወዳጁ ታሪካዊ ጥናቱን በደብዳቤ መልክ አንተም እወቅ ብሎ ደብዳቤውን ጽፎለታል።
«እሺ! የታለ እናንተ የለጠፋችሁት መንፈስ ቅዱስ? ታሪክን ማጥናት የመንፈስ ቅዱስ ቃል ያሰኛል? አንድ ሰው ስለ ክርስቶስ አባቶች ሲተርቱ የሰማውን መጻፉ የፈጣሪ ቃል ያሰኛልን? የተጻፉ ጽሑፎችን አፈላልጎ ማንበቡና የተረዳውን ታሪክ ለጓደኛው መጻፉ የፈጣሪ ቃል ይሆናልን? ሊሆን አይችልም። ታዲያ ሉቃስ ምን የተለየ ነገር ጻፈ? እሱ ፍጹም ያላሰበውን ነገር በእሱ ላይ መለጠፍ ዕብለትም ጭምር ነው።
«የወንጌሉ ጸሐፊ ራሱ በግልጽ እንደተናገረው ደብዳቤውን ለወዳጁ ቴዎፍሎስ ሲጽፍለት ቀደም ብለው ብዙ የተጻፉ ታሪኮችን መርምሮ አጣርቶ በቅደም ተከተል መዘገቡንና መረጃ ምንጮችን መጠቀሙን በግልጽ አስፍሯል። የታሪክ ምሁራን ሲያስቀምጡ በዋናነት ከተጠቀማቸውም ምንጮች አንዱ የ “ማርቆስን ወንጌል” ሲሆን 41% የሚሆነውን ከማርቆስ ገልብጧል። ከዚህ በተጨማሪም “Q Source” እና “L Source” የተሰኙ የኢየሱስን ንግግሮችና አፈ-ታሪኮች የያዙ ምንጮችን መጠቀሙን ይናገራሉ።
«ይህ ሁሉ ሒደት ሲሆን ክርስቲያኖች የለጠፉት ዋና ጸሐፊው ግን የማያውቀው “መንፈስ ቅዱስ” የት ገባ? ጥያቄያችን የመንፈስ ቅዱስ ሚናው ምኑ ጋር ነው? ይህን ሉቃስ ፍዳውን አይቶ በራሱ ጥረትና ድካም ምንጮችን አይቶ ለወዳጁ ጠቅላላ ታሪካዊ ግንዛቤ እንዲኖረው ሲል የጻፈለትን ደብዳቤ እንዴት “የእግዚአብሔር ቃል” ይባላል??? የእግዚአብሔር ቃል ለመባልና እንዲያ ቢሆን ኖሮ “ትክክለኛ ቃሉን መልአኩ ገብርኤል” ወይም “መንፈስ ቅዱስ” በቀጥታ ወይም በልቡ ላይ ቃሉን ያሰርፅለታል። ጸሐፊው የማንንም ሰው ሰራሽ ጽሑፎችና ብጥስጣሾችን ታማኝነት የሌላቸውን አፈ-ታሪኮች መገልበጥ ማግበስበስ አይጠበቅበትም ነበር።
«ስለዚህ ሉቃስ ይህንን ደብዳቤ እንደማንኛውም ታሪክን ማወቅና ለወዳጁ ማሳወቅ እንደሚወድ ሰው በራሱ ጥረት ጽፎታል። እሱም የሚያምነው የራሱን ጥረትና ድካም እንጂ ዛሬ ክርስቲያኖች እንደሚሉት በ “መንፈስ ቅዱስ”ን ምሪት ሚባል አያውቅም። ይሁንና በዚህ እሳቤ ከሄድን የፈጣሪ ቃል ነው ብትሉ እንኳ የፈጣሪ ቃል መሆን የነበረበት «የሉቃስ ወንጌል” ሳይሆን እነዚያ ቀዳማይ “ሉቃስ በምንጭነት የተጠቀማቸው ዋና ምንጮች” ናቸው።
«ምሳሌ፦- ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ የተለያዩ ምንጮን ተጠቅሚያለሁ። እና ይህንን ስለ ሉቃስ ወንጌል ታሪክ የጻፍኩት የፈጣሪ ቃል ይሆናልን? ወይም እንደምትወዱት አርዕስቱን ብቀይረውና ልክ እንደ ሉቃስ “የኢየሱስን ታሪክ” “ውልደቱን” እድገቱን” ስቅለቱን” ትንሳዔውን” ብጽፍ ኖሮ የፈጣሪ ቃል ሊሆን ይችላልን? በምን ሚዛን? አይችልም ከሆነ ምላሹ ሉቃስም ይህንኑ ብቻ አድርጓል አለቀ።
© አቡ ማሒራ


