የማቴዎስ ወንጌል በአዲስ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ ከተመሳሳዮቹ ወንጌላት {Synoptic Gospels} አንዱ ሲሆን በአቀማመጡ ረድፍ የአዲስ ኪዳን የመጀመሪያ መግቢያ ላይ ተሰድሯል።
«መጽሐፉ የጸሐፊውን ማንነት አይገልጽም። በተጨማሪም ጥናቶች መሠረት የጸሐፊው ማንነት አይታወቅም። በቀደምት ትውፊትና የቤተ-ክርስቲያን አባቶች መሠረት የመጽሐፉ ጸሐፊ ሐዋሪያው ቀረጥ ሰብሳቢው “ማቴዎስ” ነው ተብሎ ይታመን ነበር። ነገር ግን ጸሐፊው ማቴዎስ ነው የሚለውን መላምት ትክክል እንዳልሆነና ሊሆንም እንደማይችል ዛሬ ላይ ዘመናዊ አጥኚዎች {Modern Scholars} ውድቅ አድርገውታል።
«ከሙግታቸው ውስጥ አንዱ ነጥብ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ “ማቴዎስ” የተባለው ቀራጩ ከ12ቱ የኢየሱስ ሐዋሪያ የዓይን ምስክር ከሆነ እንዴት ሐዋሪያ ካልሆነውና ኢየሱስን ምንም ከማያውቅ ለታሪኩ ባዕድ ከሆነው ከማርቆስ መረጃ ይገለብጣል? ስለዚህ “ማቴዎስ” ሊሆን አይችልም። ይልቁንስ “ማቴዎስ” የሚለውን ስያሜ ኋላ ላይ በ2ኛው ክፍለ ዘመን በቤተ-ክርስቲያን አባቶች የተጨመረ ባዕድ ስያሜ ብቻ ነው።
«ኢየሱስ ሲናገርበትና ሲያስተምር የነበረው በአረማይክ ቋንቋ ነበር። ሐዋሪያቱም ሆኑ በዘመኑ የነበሩ የገሊላ ነዋሪዎች ጭምር የአረማይክ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ይህ “የ ማቴዎስ ወንጌል” ተብሎ የተሰየመው መጽሐፍ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈው “በግሪክ” ቋንቋ ነበር። የኢየሱስ ሐዋሪያ “ማቴዎስ” አረማይክ ተናጋሪ ከነበር ታዲያ ይህኛው ግሪክኛ ተናጋሪ “ማቴዎስ” ከየት መጣ? ስለዚህ ከመሠረቱ ኢየሱስና ሐዋሪያቱ በአረማይክ ቋንቋ ካስተማሩ በአረማይክ ቋንቋ ምን ብለው አስተምረው እንደነበርም በግልጽ አይታወቅም።
«ስለዚህ የዚህ ወንጌል ጸሐፊ ሊሆን የሚችለው የኢየሱስ ሐዋሪያ ያልሆነ ሌላ የግሪክኛ ቋንቋ ተናጋሪ የአይሁድን ባህል ጠንቅቆ የሚያውቅ አይሁድ የሆነ ክርስቲያን ሰው ነው።
«ይህ ወንጌል ከ70-110 AD በግሪክ ቋንቋ የተጻፈ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ኦርጂናል ጽሑፍ {Manuscript} ደብዛው ጠፍቷል። በስተመጨረሻ በኋላ ላይ በ1930 AD የተገኘው የ “ማቴዎስ ወንጌል” ቀዳማይ {Manuscript} የሚባለው ፓፒረስ 45 {papyrus 45} ሲሆን ይህ ጽሑፍ በ 250 AD ላይ ድጋሚ የተዘጋጀ ነው።
«የዚህ ወንጌል ጸሐፊ 46% ከማርቆስ ወንጌል ገልብጧል ይላሉ። ይህንን የግልበጣ ፐርሰት ጭራሽኑም ከፍ በማድረግ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ማብራሪያ እንዲያውም 91% የሚሆነው የማርቆስ ወንጌል በማቴዎስ ውስጥ ይገኛል» ሲል ያስቀምጣል። በዚህም ድንበር የለሽ የመመሳሰላቸው ምክንያት “የተመሳሳዮቹ ወንጌላት ውዝግብ” ችግር ፈጥሯል።
«ይህን “የመመሳሰላቸውን” ችግር ለመፍታትና የመመሳሰላቸውን ምክንያት ለማስቀመጥ ምሁራን ብዙ አስተያየቶችን አስቀምጠዋል፦
- «የወንጌላቱ ምንጭ ሥነ ቃል ነው። በጥንቱ ዓለም ሥነ ቃሎች ትልቅ ቦታ ስለ ነበራቸው ጸሓፊዎቹ በዚህ ረገድ የጋራ ምንጮችን ተጠቅመዋል፡፡
- «የወንጌላቱ ምንጭ ከእነርሱ በፊት የተጻፈ ወንጌል ነው። አንዳንድ ሰዎች «እነዚህ ወንጌሎች ከመጻፋቸው በፊት አንድ ሌላ ወንጌል ነበር ። ጸሓፊዎቹ ወንጌሎቻቸውን የጻፉት በአንድ ወቅት የነበረውን በኋላ ግን የጠፋውን ወንጌል መሠረት አድርገው ነው» ይላሉ፡፡
- «የወንጌላቱ ምንጭ እዚህም እዚያም ተበታትነው የሚገኙ ጽሑፎች ናቸው፦ አንዳንድ ሰዎች የኢየሱስን ሕይወት የሚተርኩ ልዩ ልዩ ጽሑፎች ስለ ነበሩ ጸሓፊዎቹ እነዚህን ጽሑፎች መሠረት በማድረግ ጽፈዋል» ይላሉ፡፡
- «የወንጌላቱ ምንጭ ጸሓፊዎቹ ራሳቸው ናቸው፦ የተመሳሳዮቹ ወንጌላት ጸሓፊዎች አንዳቸው ከሌላው እየወሰዱ ጽፈዋል ከዚህም የተነሣ ወንጌላቱ ተመሳሳይ ሊሆኑ ችለዋል» ይላሉ፡፡
- «የወንጌላቱ ምንጭ ሁለት ዐበይት ምንጮች ናቸው፦ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ተቀባይነት ባለው አመለካከት መሠረት የወንጌላቱ ምንጭ «የማርቆስ ወንጌል» እና አንድ ሌላ «መላ ምታዊ ምንጭ ነው» ይህ ምንጭ በጀርመን ቋንቋ “ኩዌል” ይባላል፤ ትርጉሙም ምንጭ ማለት ነው። ማቴዎስና ሉቃስ ወንጌላቸውን ሲጽፉ በስፋት የተጠቀሙት እነዚህን ምንጮች ነው::
“ከእነዚህ እይታዎችና መላምቶች የምጨምቀውና የተስማሙበት ጉዳይ ወንጌል ጸሐፊዎቹ “በመንፈስ ቅዱስ” ምሪት ያዘጋጁት “መንፈስ ቅዱስ” ለአንዱ ጸሐፊ የገለጠለትን አውነታ ለሌላኛውም ጸሐፊ በተመሳሳይ ገልጦለት ሳይሆን ጸሐፊያኑ በራሳቸው ጥረት በዘመኑ ያሉ ብጥስጣሽ ምንጮችን አፈላልገውና ያገኙትን ጽፈው እንደገና እርስ በርሳቸው አንዱ ከአንዱ እየገለበጡ የዘገቡት የሰው ታሪክ ብቻ መሆኑን ነው። በዚህ ድርጊታቸው ውስጥ የእግዚአብሔርም ሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሚና የቱም ጋር አልተስተዋለም አልተገለጸም።
«ስለዚህ እነዚህ ወንጌላት በዚህ ታሪካቸው የፈጣሪ ቃል የሚሆኑበት ምንም አይነት ምክንያት ማስረጃም ማቅረብ አይቻልም። እነሱም በዘመናቸው ማንም ሰው ሲጽፍ እንዳዩት በራስ ተነሳሽነት ስሜት መጻፍን ወደዱ እንጂ “የእግዚአብሔርን ቃል” እንጻፍ ብሎ ያሰበ ማንም የለም።
“በኋላ ላይ የመጡ የቤተ-ክርስቲያን አባቶች ክርስትናን ሲመሰርቱ ለራሳቸው ምሥረታ እምነት ተስማሚ ነው ያሉትን ቃል ብቻ ከበርካታ ወንጌሎች ውስጥ 4ቱን ብቻ መርጠው “የእግዚአብሔር ቃል”እስትንፋሰ-እግዚአብሔር” ሲሉ ጸሐፊዎቹ ያላሰቡትን በጸሐፊዎቹ ላይ ቀጥፈዋል። ምናልባትም ዛሬ እነዚያ ጸሐፊያን በግል ጽሑፋቸውና በግል ደብዳቤያቸው ላይ የተመሰረተውን ይህንን የክርስትና አለም ቢያዩ ምን እንደሚሰማቸው ማሰብ ይከብዳል።
© አቡ ማሒራ


