በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
7. አፍራሽ ተግባራት፡-
ለ. ትንሹ ሺርክ፡-
5. ማሰርና ማንጠልጠል፡-
የሰው አይን በመፍራት፣ ወይም ሊመጣ ከሚችል በሽታ ሰበብ ሆኖ ይከላከላል በማለት በአንገትና በእጅ ላይ የሚታሰሩና የሚንጠለጠሉ ነገሮች ከትንሹ ሺርክ ይመደባሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ሰበብ ከመሆን አልፈው በራሳቸው ኃይል አደጋን ይከላከላሉ፣ የተከሰተን አደጋ ደግሞ ያነሳሉ ብሎ ማመን ደግሞ ትልቁ ሺርክ ውስጥ ይከታል፡፡ አላህ ልጆችን ከሰው አይን ለመከላከል፡ በአንገት ላይ የሚንጠለጠል ሒርዝን ወይም በእጅ የሚጠለቅን ቀለበትና አምባር ሰበብ አላደረገም፡፡ ይህ የሰዎች የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን ነቢያችን (ዐለይሂ ሶላቱ ወሰላም) ሐሰንና ሑሰይንን (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ፡- “አዒዙኩማ ቢከሊማቲላሂ-ታምማህ፣ ሚን-ኩልሊ ሸይጧኒን-ወሃምማህ፣ ወሚን-ኩልሊ ዐይኒን-ላምማህ” በማለት ከአላህ ዘንድ ጥበቃን ይለምኑላቸው ነበር፡፡ ከዛም፡- “አባታችሁ (ነቢ ኢብራሂም ዐለይሂ-ሰላም) ኢስማዒልንና ኢስሐቅን በዚህ ዱዓእ ይጠብቃቸው ነበር” ይሏቸዋል፡፡ (ቡኻሪይ 3371፣ ኢብኑ ማጀህ 3525፣ አቡ ዳዉድ 4737)፡፡ ትርጉሙም፡- (ሙሉ በሆነው በአላህ ቃል፡ ከሰይጣናትና ከገዳይ መርዛማዎች ሁሉ፡ እንዲሁም ከክፉ አይኖች እጠብቃችኋለሁ) ማለት ነው፡፡ እኛም እሳቸውን በመከተል ይህን አስተማማኝ ዱዓእ ማድረግ እያለብን፡ ሰበብ ያልሆነ ነገር ላይ መንጠልጠል አግባብ አይደለም፡፡ ይልቁኑ ሺርክ ላይ የሚከት ስራ እንደሆነ በሌላ ሐዲሥ ተገልጾአል፡-
ዐብደላህ ኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ‹‹ሩቃ፣ ሒርዝ፣ መስተፋቅር ሺርክ ናቸው›› ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡” (አቡ ዳዉድ 3883፣ ኢብኑ ማጀህ 3530፣ አሕመድ 1/381)፡፡
ሩቃ፡- ይህ ማለት ሸሪዓዊ ያልሆነ መንገድን በመከተል በሽተኛን ለማዳን የሚደረጉ ስርአቶች ማለት ነው፡፡ በህመምተኛው ላይ የሚደረገው የሩቃ አይነት ቁርኣን ማንበብ፣ ዱዓእ ማድረግ ከሆነ ይህ የሚበቃና ብሎም የሚወደድ ተግባር ነው፡፡ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሱረቱል ፋቲሓን ‹‹ሩቅያህ›› ብለዋታልና፡፡ ቁርኣን ደግሞ መድሃኒት ነው፡፡ (ሱረቱል ኢስራእ 82)፡፡
ሒርዝ፡- ይህ ማለት ደግሞ በህመምተኛው አንገት ላይ ከሰው አይን ለመጠበቅ ሲባል የሚንጠለጠል ነገር ማለት ነው፡፡ ያ የሚንጠለጠለው ነገር ከቁርኣን የተወሰነ አንቀጾች የተጻፉበት ከሆነ፡ ከፊል የኢስላም ሊቃውንት (ሰለፎች) ሲፈቅዱ፡ ከፊሎቹ ደግሞ አይበቃም ብለዋል፡፡ አንዳንድ ዑለማዎች ይህን ሲያብራሩ እንዲህ ይላሉ፡- ቁርኣን መድሀኒት መሆኑ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ መድሃኒትን ለመጠቀም ደግሞ የራሱ የሆነ አወሳሰድ አለው፡፡ ከተነገረን የአወሳሰድ መንገድ ውጪ መገልገል አይፈቀድልንም፡፡ በቁርኣን መድሀኒትነት ለመጠቀም መፍትሄው፡- በህመምተኛው ላይ መቅራት እንጂ በወረቀት ላይ ጽፎ፡ በክር ቋጥሮ፡ በአንገት ላይ ማሰሩ አይደለም፡፡ በተለይ ይህ ህመምተኛ ቁርኣኑን በአንገቱ ተሸክሞ ሽንት ቤት ይገባል፡፡ ሰውንም በምላሱ ያማል፡፡ ምናልባትም ቁርኣኑ አንገቴ ላይ እስካለ በማለት ቁርኣኑንም ከመቅራት ሊሳነፍ ይችላልና በዚህ መልኩ መጠቀሙ የተሻለ አማራጭ አይደለም ፡፡ እነዚህ ሁሉ የቁርኣንን ቅድስና ይጻረራል፡፡ (አል-ቀውሉል ሙፊድ፡ ዐላ ኪታቢ-ተውሒድ 1/182)፡፡ በተለይ እኛ ደግሞ ሰዎች አንጠልጥሉ ብለው የሰጡንን ነገር ነው እንዲሁ ተቀብለን የምናንጠለጥለው፡፡ ውስጡ የሰፈረው ቁርኣን ይሁን ሌላ እንኳ ከፍቶ ለማየት የሚደፍር የለም፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩ፡ ከአንገት ላይ የተበጠሱ ሒርዞችን ከፍተን ስናያቸው፡ የቀበሌ ራሽን ካርድ የተገኘባቸው ስንት ናቸው? ቤቱ ይቁጠረው፡፡ በመሆኑም እንጠንቀቅ፡፡
መስተፋቅር፡- ይህ ደግሞ ባል ሚስቱን እንዲወዳት፣ እሷም እሱን እንድትወደው ተብሎ፡ ከሁለት አንዳቸው ላይ የሚደረግና የሚንጠለጠል ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሺርክ ነው፡፡ በሁለቱ መሐል ፍቅርንና መዋደድን አላህ እንጂ ሌላ ማንም ሊያመጣ አችልም፡፡
“وَمِنْ آيَاتِهِ أَنْ خَلَقَ لَكُمْ مِنْ أَنْفُسِكُمْ أَزْوَاجًا لِتَسْكُنُوا إِلَيْهَا وَجَعَلَ بَيْنَكُمْ مَوَدَّةً وَرَحْمَةً إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآيَاتٍ لِقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ ” سورة الروم 21
“ለናንተም፣ ከነፍሶቻችሁ (ከጐሶቻችሁ) ሚስቶችን ወደነርሱ ትረኩ ዘንድ መፍጠሩ፤ በመካከላችሁም ፍቅርንና እዝነትን ማድረጉ ከአስደናቂ ምልክቶቹ ነው፤ በዚህ ውስጥ ለሚያስውሉ ሕዝቦች ታምራቶች አሉ።” (ሱረቱ-ሩም 21)፡፡
በመሐከላቸው አለመግባባት ከተፈጠረና ፍቅር ከቀዘቀዘም በሽማግሌና ቀርቦ በመወያየት ይፈታል እንጂ ከድግምት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ነገሮች መፍታት አይገባም፡፡ አላህ ሰበብ ያላደረገውን ሰበብ አድርጎ ለመጠቀም መሞከር ስህተት ነው፡፡
ከዐብዱላህ ኢብኑ ዑከይም (ረሒመሁላህ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “በአንዳች ነገር ላይ (ልቡ) የተንጠለጠለ ሰው፡ ወደሱ እንዲጠጋ ይደረጋል” (አሕመድ 4/211፣ ቲርሚዚይ 2073)፡፡ መመካትና መጠጋት የሚገባን በአላህ ላይ ብቻ ሆኖ ሳለ (ሱረቱ-ጦላቅ 3) በሌላ ነገር ላይ የሚጠጋና ቀልቡ የሚንጠለጠል ሰው፡ እስኪ እሱ ይደርስልህ እንደሆን እየው! በመባል ወደተጠጋው ነገር ይተዋል፡፡ ይህ ትልቅ ክስረት ነው፡፡ አላህ ሁላችንንም ይጠብቀን፡፡ ወንድሞችና እህቶች እስካሁን በመጠኑ በተከታታይ ስንመለከተው የነበረው የ‹‹ላ ኢላሀ ኢለሏህ›› እምነትን አፍራሽ ከሆኑ ተግባራት አንዱ የሆነውን የሺርክን ምነነት ነው፡፡ በቀጣዩ ክፍለ ጊዜ ደግሞ ጌታችን አላህ ፈቃዱ ከሆነ ከሁለተኛው አፍራሽ ተግባር እንጀምራለን ኢንሻአላህ፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


