በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ውድና ክቡራን ሙስሊም ወንድሞቼና እህቶቼ! በቅድሚያ አሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ፡፡
“የራሷ አርሮባት የሰው ታማስላለች” እንዲሉ ሆነና ነገሩ፡ ቅዱስ ቁርኣን የአላህን ፍፁማዊ አንድነት (በህላዌው፣ በስራው፣ በባሕሪያቱና በአምልኮ) በሰፊው በማስተማር ከአንድ አላህ ውጪ እንደ አምላክ የተያዙና የሚመለኩ አካላትን (በተለይ ሥላሴን) ሲቃወም፡ ይህ ያልተዋጠላቸው የአክፍሮት ኃይላት ቅዱስ ቁርኣንን እንዲህ በለው ይተቻሉ፡- ቁርኣን ሥላሴዎች ብሎ የሚጠቅሳቸው ‹እግዚአብሄርን፣ ኢየሱስን እና ማርያምን› ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስህተት ነው፡፡ እኛ ሥላሴዎች ብለን የምንጠራቸው ‹አብ (እግዚአብሄርን)፣ ወልድ (ኢየሱስን)፣ መንፈስ ቅዱስ (አጽናኙን)› ነው፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ቦታ ማሪያም መግባቷ ስህተት ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ የሚጠቅሱት ቀጣዩን የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ነው፡-
” وَإِذْ قَالَ اللَّهُ يَا عِيسَى ابْنَ مَرْيَمَ أَأَنْتَ قُلْتَ لِلنَّاسِ اتَّخِذُونِي وَأُمِّيَ إِلَهَيْنِ مِنْ دُونِ اللَّهِ قَالَ سُبْحَانَكَ مَا يَكُونُ لِي أَنْ أَقُولَ مَا لَيْسَ لِي بِحَقٍّ إِنْ كُنْتُ قُلْتُهُ فَقَدْ عَلِمْتَهُ تَعْلَمُ مَا فِي نَفْسِي وَلَا أَعْلَمُ مَا فِي نَفْسِكَ إِنَّكَ أَنْتَ عَلَّامُ الْغُيُوبِ ” سورة المائدة 116
“አላህም፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ ፦ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ)፤ ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፤ ግን ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል፡፡ (ሱረቱል ማኢዳህ 116)፡፡
ለዚህ አግባብነት ለጎደለው ክስ ምላሻችን እንደሚከተለው ይሆናል፡-
1ኛ. በመጀመሪያ ሊታወቅ የሚገባው ነገር የቅዱስ ቁርኣኑ ጥቅስ እየተናገረ ያለው ሰዎች ከአላህ ውጪ ዒሳንና እናቱን መርየምን (የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን) አምላክ አድርገው መያዛቸውን እንጂ፡ ሥላሴዎች ናቸው ብለዋል ብሎ እያስተማረ አለመሆኑን ነው፡፡ አንድን አካል አምላክ አድርጎ መያዝ ማለት ያንን አካል ሥላሴ ነው ብሎ መያዝ እንዳልሆነ እነሱም ያውቃሉ፡፡
2ኛ. እሺ አምላክ አድርገውስ እንዴት ያዙ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) አምላክ አድርገው መያዛቸው ምንም የሚያከራክር ነገር አይደለም፡፡ ምናልባት መርየምን (ዐለይሃ-ሰላም) መች አምላክ አድርገን ያዝናት? ማንስ አምላክ ነች ብሎ ሰየማት? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ ለማግኘት ‹አምላክ አድርጎ መያዝ› ማለት ፍቺው ምንድነው? የሚለውን ማወቁ የግድ ነው፡፡
አንድን አካል አምላክ አድርጎ ለመያዝ ያንን ግለሰብ አምላኬ፣ ጌታዬ፣ ፈጣሪዬና በመሳሰሉት ቋንቋ መጥራት ብቸኛ መገለጫ አይደለም፡፡ ያንን ግለሰብ በነዚህ ስያሜዎች ሳንጠራው፡ ነገር ግን ለእውነተኛው አምላክ ለአላህ የምንሰጠውን የአምልኮ አይነት ለዚህም ሰው ከሰጠነው፡ ሰውየውን አምላክ አድርገን ያዝነው ማለት ነው፡፡ ሙስሊሞች ፈጣሪ አምላካቸውን አላህ፡- አንተ ፈጣሪያችን፣ አምላካችንና ጌታችን ነህ ቢሉት፡ ነገር ግን ለሱ ምንም አይነት አምልኮ ባያቀርቡለት በምላስ ስላወደሱት ብቻ አመለኩት ይሰኛልና? በዛው ተቃራኒም አንድን ፍጡር ለአምላክ የሚቀርበውን የአምልኮ አይነት ለሱ እየሰጠን ነገር ግን አምላካችን፣ ጌታችንና ፈጣሪያችን ብለን ስላልጠራነው አላመለክነውም ሊባል ነውን? አይባልም፡፡ በደንብ አምልከነዋል፡፡ ይህንን ሀሳብ የሚደግፍ አንድ የቁርኣን ጥቅስ እንመልከት፡-
” أَفَرَأَيْتَ مَنِ اتَّخَذَ إِلَهَهُ هَوَاهُ وَأَضَلَّهُ اللَّهُ عَلَى عِلْمٍ وَخَتَمَ عَلَى سَمْعِهِ وَقَلْبِهِ وَجَعَلَ عَلَى بَصَرِهِ غِشَاوَةً فَمَنْ يَهْدِيهِ مِنْ بَعْدِ اللَّهِ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ ” سورة الجاثية 23
“ዝንባሌውን አምላኩ አድርጎ የያዘውን፣ አላህም ከዕውቀት ጋር ያጠመመውን፣ በጆሮውና በልቡ ላይም ያተመበትን፣ በዓይኑም ላይ ሺፋን ያደረገበትን፣ ሰው አየህን! ታዲያ ከአላህ ኋላ የሚያቀናው ማነው? አትገሠጹምን?” (ሱረቱል ጃሢየህ 23)፡፡
በዚህ ቅዱስ አንቀጽ መሰረት፡- ‹ዝንባሌውን፡ ስሜቱን› አምላኩ አድርጎ የሚይዝ ሰው መኖሩን መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ የራሱን ፍላጎትና ስሜት እንዲሁም ዝንባሌ ‹አምላኬና ጌታዬ› ብሎ የሚጠራ ሰው ገጥሟችሁ ያውቃል? ከሰውስ ሰምታችኋል? የለም፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ዝንባሌውን አምላኩ አድርጎ የሚይዘው? ከተባለ፡ ምላሹም፡- ከጌታው ፈቃድ በፊት የነፍሲያውን ፍላጎት የሚያስቀድም፣ ጌታው የከለከለውን ነፍስያው ከፈለገች የሚያሟላላት፣ ጌታው ያዘዘውን ነፍሲያው ከከበዳት የሚተውላት ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፡- የአላህን ፈቃድ መፈጸም አላህን ማምለክ እንደሆነ ሁሉ፡ የነፍሲያን ፍላጎቶች ሁሉ ከአላህ ህግ ጋር ቢጋጭም ሟሟላት ደግሞ ነፍሲያን ማምለክ ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንድን አካል አምላክ አድርጎ ለመያዝ ‹አምላኬ!› ብሎ መጥራት የግድ እንዳልሆነ አሁን ግጽ ይመስለኛል፡፡ የአምልኮን ጽንሰ ሀሳብ በዚህ መልኩ ከተረዳን፡ ወደ መነሻ ነጥባችን እንመለስና፡- ታዲያ ማነው ማርያምን አምላክ አድርጎ የያዛት? ለሚለው ጥያቄ ማብራሪያውን እንስጥ፡፡
ማሪያምን አምላክ አድርጎ የያዛት፡- አንቺ አለኝታዬና መከታዬ ነሽ፡ ባንቺ ታመንኩ! የሚለው ሰው ነው፡፡
ማሪያምን አምላክ አድርጎ የያዛት፡- አንቺ ጠባቂዬ ነሽ! ስለዚህ ከፊቴም ከኋላዬም ጠብቂኝ፣ ተከተዪኝ የሚለው ሰው ነው፡፡
ማሪያምን አምላክ አድርጎ የያዛት፡- ኢትዬጵያ ለአንቺ አስራት ተደርጋ ተሰጥታለችና ኢትዮጵያና ህዝቦቿን አንቺ ጠብቂያቸው ብሎ የሚማጸነው ሰው ነው፡፡
ማሪያምን አምላክ አድርጎ የያዛት፡- ሴት ልጅ በወሊድ ሰዓት፡ በዛ በጭንቁ ጊዜ ከሞት የማይተናነስ የምጥ ስቃይን ተመልክታ፡ ከዛ ጠባብ ማኅጸን ሶስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ህያው ፍጥረትን በአላህ እገዛና ጥበቃ በሰላም ተገላግላ ስታበቃ ‹እንኳን ማሪያም ማረችሽ!› ብሎ የአምላክን ስራ ወደሷ የሚያስጠጋ ሰው ነው፡፡
ማሪያምን አምላክ አድርጎ የያዛት፡- ሴትን ልጅ በወሊድ ቀናቶቿ ጊዜ ከ 20-40 ቀናትን እሷንም እንዲሁም አዲሱን እንግዳ በመለኮታዊ እንክብካቤው አላህ በሰላም አቆይቶ፡ በሰላም ያውጣሽ ማለት ሲገባ ‹ማሪያም በሽልም ታውጣሽ› የሚለው ሰው ነው፡፡
እንዲህ አይነት እምነት ያላቸው ሰዎች በጠቅላላ መርየምን (ዐለይሃ-ሰላም) አምላክ አድርገው ይዘዋታል፡፡ አምላክ ብለው ባይጠሯትም፡፡
እኔ የምለው፡- መጠበቅ፣ ከጭንቅ ማዳን፣ ምኞትን ማሳካት የአንዱ አምላክ የአላህ ስራ ብቻ አይደለም እንዴ? መች ነው እሱ ይህንን መለኮታዊ ክብሩን ለሌላ ማጋራት የጀመረው? ወይንስ ስልጣኑን ለሌላ አሳልፎ ሰጠ ሊባል? (ተዓለሏሁ ዐምማ-የቁሉ ዟሊሙነ ዑሉወን-ከቢራ)፡፡ ደግሞስ ልንመካና ልንታመንበት የሚገባው እሱ ብቻ ሆኖ ሳለ ለምን በፍጡር ላይ መመካት አስፈለገ? እሱ አቅም አላነሰው ወይ ረዳት ኃይል አላስፈለገው? እኮ ለምን? የጻድቃን (የአላህ መልካም ባሮች ሷሊሖች) ክብር ሊገለጽ የሚገባው ከመጠን ባለፈ ፍቅርና ውዴታ ሳይሆን፡ አላህ የሰጣቸውን ክብርና ማእረግ ሳንጨምርና ሳንቀንስ ያንኑ ክብር በመስጠት ነው፡፡ ፍቅርና ውዴታ ድንበር ሲጥስ ወደ አምልኮ ይቀየራልና፡፡
3. ይህ ስለ አምልኮና አምላክ አድርጎ መያዝ የቀረበው ትንታኔ የማይዋጥላቸው ወገኖች ካሉም፡ ጉዳዩን ለማብራራት እነሱ ከሚያምኑበት መጽሐፍ አንድ ጥቅስ እንመልከት፡-
“ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው።” (ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ምዕ 3 ቁ 18-19)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥› የሚል ኃይለ-ቃል አለ፡፡ ማነው ደግሞ ሆዱን አምላክ አድርጎ የያዘ? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ምላሹ ከላይ ከተብራራው ውጪ ምን ሊሆን ይችላል? ‹‹ሆዳችን አምላካችን!›› የሚል የሃይማኖት ቡድን አልተቋቋመም፡፡ ማለት የተፈለገው ግን፡- ለሆዳቸው ያደሩ፣ ለጥቅም የተገዙ….ከሆነ፡ ታዲያ የእውነተኛውን አምላክ የአላህን መለኮታዊ ክብር ለፍጡር አሳልፎስ መስጠት፡ ያንን አካል አምላክ አድርጎ መያዝ አይደለምን?
4ኛ. ይህ ጥያቄ ለዒሳ (ዐለይሂ ሰላም) የሚቀርብለት ነገ የውሙል-ቂያም (ዕለተ-ትንሳኤ) ነው፡፡ በጥቅሱም ውስጥ ‹‹አላህም፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ ፦ እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሃልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ)›› የሚል ቃል አለ፡፡ ‹በሚለው ጊዜ› የሚለው ቃል የሚያመላክተው ወደፊት የሚከሰት ገና ያልመጣ መሆኑን ነው፡፡ እንደውም ከዚህ በፊት አንድ ክርስቲያን እንዲህ ብሎ ጠይቆኝ ነበር፡- አላህ ለዒሳ (ዐለይሂ ሰላም) ፡ አንተ ለሰዎቹ እኔና እናቴን ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለህ ነበርን? በማለት የፍርዱ ቀን የሚጠይቀው፡ ይህ ትምህርት (ዒሳንና እናቱን አምላክ አድርጎ መያዝ) ከራሱ ከዒሳ የመነጨ ይሁን ወይንስ ሰዎች ከራሳቸው የፈጠሩት አዲስ ስርዓት ይሁን፡ አላህ አላወቀም ነበር ማለት ነው? ካወቀስ ዒሳን መጠየቁ ለምን አስፈለገ?
እኔም በወቅቱ የሰጠሁት ምላሽ፡- ባይገርምህ አላህ ሁሉን ዐዋቂ ጌታ መሆኑን ከሚያመላክቱ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾች መካከል አንዱ ይኸው ጥቅስ ነው፡፡ እንዴት? ካልከኝም፡- በጥቅሱ ላይ የተጻፈው ጌታችን አላህ ወደፊት የቂያም ዕለት ዒሳን እንደሚጠይቀው ብቻ አይደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ አንተ ያነሳኸው ጥያቄ ትንሽ ቆም ያደርገኝ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ጌታችን አላህ በዚያን ቀን ጥያቄ ዒሳ የሚመልሰውንም አብሮ ነግሮናል፡፡ እንዲህ ይላልም አለን፡- “ጥራት ይገባህ፤ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም፤ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል፤ በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፤ ግን ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና ይላል” ፡፡ ታዲያ የቂያም ቀኑን የጌታችን ጥያቄና የተጠያቂውንም የዒሳን ምላሽ ገና ጊዜው ከመድረሱ ከዛሬ 1,400 ዓመታት በፊት አላህ አስቀድሞ በቁርኣኑ ለኛ መንገሩ እሱ ሁሉን ዐዋቂ አምላክ መሆኑን እንጂ ሌላ ምን ሊያሳይ ይችላል? የሚል ነበር፡፡
እንግዲያውስ የዒሳንም ምላሽ ቀድሞ ካወቀ አሁን መግለጹና ዒሳንም የዛኔ መጠየቁ ለምን አስፈለገ? ለሚለው ደግሞ ምላሽ የሚሆነው፡- ከአላህ ውጭ ለማንኛውም አካል የሚቀርብ አምልኮ (ለዒሳም ቢሆን) ከንቱ እንደሆነና አላህ ዘንድም ተቀባይነት እንደሌለው ሰዎች እንዲውቁ፣ ዒሳም ቢሆን ይህን አምልኮ እሱ እንዳላስተማረና ከቶውኑም እንደማይቀበለው፡ በሚያመልኩትም ሰዎች እንደሚክድባቸው ከወዲሁ ተገንዝበው ወደ እውነተኛው አምላክ አላህ መንገድ በተውበት (ንሰሀ) በመመለስ አላህን ብቻ በብቸኝነት እንዲያመልኩ ለማስተማርና ለሌሎቹም አማኞች በሀሰት ትምህርት እንዳይታለሉ የማንቂያ ደወል እንዲሆን ነው፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ቁርኣኑ መልእክት፡- ዒሳንም ሆነ እናቱን፡ እንዲሁም ማንኛውንም ከጌታ አላህ ውጪ የሆነን አካል ማምለክ ተቀባይነት የሌለው ከንቱ ስራ መሆኑን መግለጽና ሰዎችን ወደ እውነተኛው ጌታ ወደ አላህ መንገድ መጣራት ነው፡-
“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በኛና በናንተ መካከል ትክክል ወደሆነች ቃል ኑ፤ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጐ ላይይዝ ነዉ፤ በላቸዉ። እምቢ ቢሉም ፡- እኛ ሙስሊሞች መሆናችንን መስክሩ በሏቸው” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 64)፡፡
“እርሱ እውነተኛ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእውነትም በኋላ ጥመት እንጂ ሌላ ምን አለ (ከውነት) እንዴት ትዞራላችሁ” (ሱረቱ ዩኑስ 32)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


