በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
” وَمَا تَشَاءُونَ إِلَّا أَنْ يَشَاءَ اللَّهُ رَبُّ الْعَالَمِينَ ” سورة التكوير 29
“የዓለማት ጌታ አላህ ካልሻም አትሹም” (ሱረቱ-ተክዊር 81፡29)፡፡
ባለፈው ክፍል አራት ላይ ‹‹አላህ የሻው እንጂ ምንም አይከሰትም›› የሚል ርእስ አንስተን ነበር፡፡ በውስጡም፡-
ሀ/ ሰው ነጻ ፈቃድ (መሻት) ያለው ፍጡር መሆኑና፡ ሆኖም ይህ ነጻ ፈቃዱ እውን የሚሆነው፡ የፈለገውን ነገር ሊያደርግበት የሚችለው አላህ ሲፈቅድለትና ይሁን ሲለው ብቻ ነው፡፡ ያለ አላህ ፈቃድ እራሳችንን ችለን የምናደርገው ምንም ነገር እንደሌለና፡ አላህም ፈቃዳችንን በፈቃዱ ስር በማድረግ የሚቆጣጠረን ጌታ መሆኑን አይተናል፡፡
ለ/ አላህ ብቻውን ፈጣሪ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ደግሞም በዓለሙ ላይ ብቻውን የነገሰ ንጉስ ነው፡፡ ሲፈጥረን በፈቃዱና በፍላጎቱ ብቻ እንደሆነው ሁሉ፡ ንጉስ በመሆንም ሲገዛን እሱ እንደፈለገው ነው እንጂ፡ እኛ እንደሻነው አይደለም፡፡ ስለዚህም ለባሮቹ የሰጣቸው ነጻ ፈቃድ የሱ ይሁንታ ካልታከለበት ወደ ተግባር በፍጹም ሊቀየር አይችልም ማለት ነው፡፡
ሐ/ ሰው ነጻ ፈቃድ አለው ማለት፡ ያለምንም ተቆጣጣሪ የፈለገውን ነገር ይተገብራል፡ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ የሰማይና የምድር ስርአት በተበላሸ ነበር፡፡ ነገር ግን ጥበበኛው አላህ ሰውን ከፈጠረው በኋላ፡ ነጻ ፈቃድ የሚባልን ነገር ሰጥቶ በልቅ አልተወውም፡፡ ይቆጣጠረዋል፡፡ እሱ አላህ የፈለገውን ነገር እንዲሳካለት ይፈቅዳል፡፡ ያልፈለገለትን ደግሞ እውን እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ጥበቡ የሱ ብቻ ነውና የሚል ነው፡፡ ዛሬ የምናየው የዚህን ሀሳብ ቀጣይ ክፍል ሆኖ፡ ቀደምት ነቢያትና (ዐለይሂሙ-ሰላም) አማኞችም በጉዳዩ ላይ ምን አይነት እምነት እንደነበራቸው የተወሰኑትን ለናሙና በመጥቀስ ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡ መልካም ንባብ!
1. ኑሕ (ዐለይሂ-ሰላም)፡-
” قَالُوا يَا نُوحُ قَدْ جَادَلْتَنَا فَأَكْثَرْتَ جِدَالَنَا فَأْتِنَا بِمَا تَعِدُنَا إِنْ كُنْتَ مِنَ الصَّادِقِينَ * قَالَ إِنَّمَا يَأْتِيكُمْ بِهِ اللَّهُ إِنْ شَاءَ وَمَا أَنْتُمْ بِمُعْجِزِينَ * وَلَا يَنْفَعُكُمْ نُصْحِي إِنْ أَرَدْتُ أَنْ أَنْصَحَ لَكُمْ إِنْ كَانَ اللَّهُ يُرِيدُ أَنْ يُغْوِيَكُمْ هُوَ رَبُّكُمْ وَإِلَيْهِ تُرْجَعُونَ ” سورة هود 34-32
“ኑሕ ሆይ በእርግጥ ተከራከርከን፤ እኛን መከራከርህንም አበዛኸው፣ ከእውነተኞቹም እንደሆንክ የምታስፈራራብንን ቅጣት አምጣው አሉ። ፦ እርሱን የሚያመጣባችሁ የሻ እንደሆነ አላህ ብቻ ነው፤ እናንተም የምታቅቱ አይደላችሁም አላቸው። ለናንተም ልመክራችሁ ብሻ አላህ ሊያጠማችሁ ሽቶ እንደ ሆነ ምክሬ አይጠቅማችሁም፤ እርሱ ጌታችሁ ነው፤ ወደ እርሱም ትመለሳላችሁ፤ (አላቸው)።” (ሱረቱ ሁድ 11፡32-34)፡፡
ነቢዩላህ ኑሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ህዝቦቹን ወደ አላህ መንገድ በመጣራት፡ አላህን ብቻ እንዲገዙና ከጣኦት አምልኮ እራሳቸውን እንዲያገልሉ አስተማረ፡፡ ከህዝቦቹም በኩል፡- ኑሕ ሆይ! በዚህ ነገር በጣም ተከራከርከን፡፡ እኛ እንደሆነ አናምንልህምና፡ ካላመናችሁ ይመጣባችኋል እያልክ የምታስፈራራንን ቅጣት አምጣብን አሉት፡፡ እሱም፡- ነገሩ ሁሉ ያለው በአላህ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ቅጣቱንም ከፈለገ የሚያመጣባችሁ እሱ ነው፡፡ እኔ የቱንም ያህል እናንተን መምከር ብፈልግም፡ *አላህ ሊያጠማችሁ እስከፈለገ* ድረስ ምክሬ አይጠቅማችሁም አላቸው፡፡ የአላህ ፈቃድ የበላይ ነው፡፡ ፍላጎቱም ተፈጻሚ ነው፡፡ (ተፍሲር ኢብኑ ከሢር፣ ተፍሲር አስ-ሰዕዲይ ተይሲር ከሪሙ-ራሕማን)፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ ሁለት መልክቶች አልሉ፡-
ሀ/ ‹‹እርሱን የሚያመጣባችሁ የሻ እንደሆነ አላህ ብቻ ነው›› በማለት፡ ፈቃድን ወደ አላህ ማስጠጋቱ፡ ነገራት በጠቅላላ የሚፈጸሙት በአላህ ይሁንታ መሆኑን ማመኑን ያሳየናል፡፡ ኑሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ስለጠየቀ ሳይሆን አላህ ከፈለገ ብቻ ነው ቅጣቱም የሚመጣባቸው ማለት ነው፡፡
ለ/ ‹‹ለናንተም ልመክራችሁ ብሻ አላህ ሊያጠማችሁ ሽቶ እንደ ሆነ ምክሬ አይጠቅማችሁም›› ማለቱም ተመሳሳይ ሀሳብን ይሰጠናል፡፡ ጌታ አላህ የሰዎችን ልብና መሻት ያውቃል፡፡ እንደ ሰው ከላይ ያለን ገጽታን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፡ የልብንም ድብቅ ሀሳብ የሚያይና የሚያውቅ አምላክ ነው (አል-ሙልክ 67፡13-14)፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የነቢያቸውን ኑሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ሃይማኖታዊ ጥሪ አሻፈረኝ በማለት እንደማይቀበሉ አስቀድሞውኑ የሚያውቅ አምላክ በመሆኑ፡ አላህ ጥንቱኑ እነሱን ሊያጠማቸው ከፈለገ፡ የኑሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ምክር ሊጠቅማቸው አይችልም ማለት ነው፡፡
እኛም መረዳት ያለብን፡ ህዝቦቹ የኑሕን ዳዕዋ ለመቀበል ባለመፈለጋቸው ምክንያት አላህ አጠመማቸው የሚለውን ሀሳብ እንጂ፡ ነገሩን ገልብጠነው፡- አላህ ስላጠመማቸው የኑሕን ዳዕዋ መቀበል አልቻሉም አንልም፡፡ የጌታ አላህ እነሱን ማጥመም መሻቱ እምቢተኝነታቸውን ቀድሞውኑ በማወቁ እንጂ፡ በዘፈቀደ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ ደግሞም ባሮቹን ህግን በነቢያት በኩል ልኮላቸው፡ እነሱም አሻፈረኝ እስኪሉ ድረስ ማንንም ለጥመትና ለክህደት አይዳርግም፡፡ በሌላ ሱራ ላይ እንዲህ ይላል ጌታችን፡-
” وَمَا كَانَ اللَّهُ لِيُضِلَّ قَوْمًا بَعْدَ إِذْ هَدَاهُمْ حَتَّى يُبَيِّنَ لَهُمْ مَا يَتَّقُونَ إِنَّ اللَّهَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ ” سورة التوبة 115
“አላህም ሕዝቦችን ከአቀናቸው በኋላ፣ የሚጠነቀቁትን (ሥራ) ለርሱ እስከሚገልጽላቸዉ፣ (እስከሚተዉትም) ድረስ ጥፋተኛ የሚያደርግ አይደለም፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና።” (ሱረቱ-ተውባህ 9፡115)፡፡
የኑሕ (ዐለይሂ-ሰላም) ህዝቦችንም አላህ ማጥመምን መሻቱ፡ ይህን የእንቢተኝነት ባህሪቸውን ቀድሞ በማወቁ የቀጣቸው ቅጣቱ እንጂ፡ ለነሱ መካድ እንደ ሰበብ የሚታይ አይደለም፡፡ አላህ ባያጠመን ኖሮ እምቢተኛ አንሆንም ነበር! ማለት አይችሉም፡፡ በተቃራኒው የሚባሉት፡- እምቢተኛ ባትሆኑ ኖሮ አላህ አያጠማችሁም ነበር! ቀድሞውኑ ይህን እምቢተኝነታችሁን ስላወቀ ነው ለጥመት የዳረጋችሁ እንጂ! ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡
2/ ኢስማዒል (ዐለይሂ-ሰላም)፡-
” فَلَمَّا بَلَغَ مَعَهُ السَّعْيَ قَالَ يَا بُنَيَّ إِنِّي أَرَى فِي الْمَنَامِ أَنِّي أَذْبَحُكَ فَانْظُرْ مَاذَا تَرَى قَالَ يَا أَبَتِ افْعَلْ مَا تُؤْمَرُ سَتَجِدُنِي إِنْ شَاءَ اللَّهُ مِنَ الصَّابِرِينَ ” سورة الصافات 102
“ከርሱም ጋር ለስራ በደረሰ ጊዜ ‹‹ልጄ ሆይ! እኔ በሕልሜ እኔ የማርድህ ሆኜ አያለሁ፡፡ ተመልከትም፣ ምን ታያለህ›› አለው፡፡ ‹‹አባቴ ሆይ! የታዘዝከውን ስራ፡፡ አላህ ቢሻ ከታጋሾቹ ኸኜ ተገኘኛለህ›› አለው፡፡” (ሱረቱ-ሷፍፋት 37፡102)፡፡
ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) አባቱን ለማገዝ፡ ለስራ የደረሰውን ታዳጊ ወጣት የመጀመሪያ ልጁን ኢስማዒልን (ዐለይሂ-ሰላም) ለአላህ ብሎ እንዲያርደው በህልሙ መልእክት ይመጣለታል፡፡ የነቢያት ህልም ደግሞ ወሕይ ‹መለኮታዊ ራእይ› እንጂ፡ እንደኛ ቀኑን ሙሉ ስናስበው የዋልነውን፡ በሌሊት የምናየው ግልባጭ አይደለም፡፡ ኢብራሂምም የአላህን ትእዛዝ በመቀበል፡ ልጁንም ለአላህ ትእዛዝ ፈቃደኛ እንዲሆን ለማዘጋጀት፡ በህልሙ ያየውን በቀጥታ ይነግረዋል፡፡
ኢስማዒልም (ዐለይሂ-ሰላም)፡- አባቴ ሆይ! ትእዛዙ ከአላህ ዘንድ ከመጣማ የታዘዝከውን ስራ! እኔም *አላህ ቢሻ* ለትእዛዙ ከሚታገሱት እሆናለሁ በማለት መለሰ፡፡ ይህ የሚያሳየን፡- ኢስማዒል (ዐለይሂ-ሰላም) የራሱን ታዛዥነትና ታጋሽነት በአላህ ፈቃድ ስር በማድረግ፡ ያለ አላህ ፈቃድ ሊከናወን የሚችል ነገር እንደሌለ ማመኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ምንም አማኝ የሆነ ሰው ለአላህ ፈቃድ ታዛዥ ቢሆንም፡ ነገሩ እንዲገራለት የአላህ ፈቃድ የግድ ያስፈልገዋልና፡፡ ብቻውን ሆኖ ያለ ረዳት የሚያከናውነው አንድም ነገር የለም ማለት ነው፡፡
3/ ዩሱፍ (ዐለይሂ-ሰላም)፡-
” وَرَفَعَ أَبَوَيْهِ عَلَى الْعَرْشِ وَخَرُّوا لَهُ سُجَّدًا وَقَالَ يَا أَبَتِ هَذَا تَأْوِيلُ رُؤْيَايَ مِنْ قَبْلُ قَدْ جَعَلَهَا رَبِّي حَقًّا وَقَدْ أَحْسَنَ بِي إِذْ أَخْرَجَنِي مِنَ السِّجْنِ وَجَاءَ بِكُمْ مِنَ الْبَدْوِ مِنْ بَعْدِ أَنْ نَزَغَ الشَّيْطَانُ بَيْنِي وَبَيْنَ إِخْوَتِي إِنَّ رَبِّي لَطِيفٌ لِمَا يَشَاءُ إِنَّهُ هُوَ الْعَلِيمُ الْحَكِيمُ ” سورة يوسف 100
“ወላጆቹንም በዙፋኑ ላይ አወጣቸው፤ ለርሱም ሰጋጆች ሆነው ወረዱለት፤ አባቴም ሆይ ይህ ፊት ያየኋት ሕልሜ ፍች ነው፤ ጌታዬ በእርግጥ እውነት አደረጋት፤ ከወህኒ ቤትም ባወጣኝና ሰይጣንም በኔና በወንድሞቼ መካከል ከአበላሸ በኋላ እናንተን ከገጠር ባመጣችሁ ጊዜ፣ በእርግጥ ለኔ መልካም ዋለልኝ፤ ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው፤ እነሆ እርሱ ዐዋቂው ጥበበኛው ነው፤ አለ።” (ሱረቱ ዩሱፍ 12፡100)፡፡
ዩሱፍ (ዐለይሂ-ሰላም) አላህ የዋለለትን መልካም ጸጋ ያወሳል፡፡ በሸይጧን ሰበብ በሱና በወንድሞቹ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማጥፋቱ፣ ከእስር ቤት እንዲወጣ አድርጎ የህዝብ መሪና ነቢይ ማድረጉ፣ የተለያቸውንም ቤተሰቦቹን ከገጠር በማምጣት ከሱ ጋር ድጋሚ በህይወት ማገናኘቱ፣ እነሱም ለሱ የአክብሮትን ስግደት ማድረጋቸው የጌታው ጸጋ መሆኑን ገለጸና፡ ንግግሩን ሲዘጋው *ጌታዬ ለሚሻው ነገር እዝነቱ ረቂቅ ነው* አለ፡፡ አላህ እንዲሆን የሚፈልገውን ነገር በጠቅላላ ይሆን ዘንድ ሰበብ እንደሚያዘጋጅለትና፡ ነገሩም ይፈጸም ዘንድ መንገዶችን ሁሉ ገር እንደሚያደርገው ዩሱፍ አመነ፡ ተናገረ ማለት ነው፡፡ ‹‹አላህ የሻውና የፈለገው ነገር ሁሉ ይሆናል!›› የሚለው እምነት የነቢያትም እምነት ነበር ማለት ነው፡፡
4/ የሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) አሰሪ፡-
” قَالَ إِنِّي أُرِيدُ أَنْ أُنْكِحَكَ إِحْدَى ابْنَتَيَّ هَاتَيْنِ عَلَى أَنْ تَأْجُرَنِي ثَمَانِيَ حِجَجٍ فَإِنْ أَتْمَمْتَ عَشْرًا فَمِنْ عِنْدِكَ وَمَا أُرِيدُ أَنْ أَشُقَّ عَلَيْكَ سَتَجِدُنِي إِنْ شَاءَ اللَّهُ مِنَ الصَّالِحِينَ ” سورة القصص 27
“«ስምንትን ዓመታት ልታገለግለኝ እኔ ከእነዚህ ሁለት ሴቶቸ ልጆቼ አንዲቱን ላጋባህ እሻለሁ፡፡ ዐስርን ብትሞላም ከአንተ ነው፡፡ ባንተ ላይ ማስቸገርንም አልሻም፡፡ አላህ የሻ እንደ ኾነ ከመልካሞቹ ሰዎች ኾኜ ታገኘኛለህ» አለው፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡27)፡፡
ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) መንጎቻቸውን ውሀን ባጠጣላቸው ሁለት ሴቶች ሰበብ፡ ለሰራው መልካም ስራ አባታቸው ወሮታውን ይከፍለው ዘንድ ወደቤቱ ካስጠራው በኋላ፡ ሙሳም (ዐለይሂ-ሰላም) ታሪኩን አጫውቶት፡ ሰውየውም ከበደለኛ ሕዝቦች ድነሃል ይለውና፡ በመልካም ስብእናውና በታማኝነቱ ሰበብ እዛው ለአስር አመታት ከሱ ጋር አገልጋይ ይሆን ዘንድ ይጠይቀዋል፡፡ ደግሞም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ አንዲቷን እንደሚድርለት ይነግረዋል፡፡ አያይዞም *አላህ ፈቃዱ ከሆነ* የገባሁትን ቃል በአግባቡ ለመፈጸም ከመልካሞቹ እሆናለሁ በማለት ይነግረዋል፡፡
ይህ ሰው ነቢዩላህ ሹዐይብ (ዐለይሂ-ሰላም) ነው ይላሉ ሙፈሲሮች፡፡ በአንቀጹ መሰረትም፡- ሹዐይብ (ዐለይሂ-ሰላም) ለሙሳ የገባውን ቃል ሊፈጽምለት ቃል መግባቱ ብቻ ሳይሆን የአላህም ፈቃድና እገዛ እንደሚያስፈልገው መናገሩ፡ ያለ አላህ መሻት ምንም ነገር ሊሆን እንደማይችል ማመኑን ያሳየናል ማለት ነው፡፡ (ፈትሑል-ቀዲር 4/169)፡፡
5/ መርየም (ዐለይሃ-ሰላም)፡-
” فَتَقَبَّلَهَا رَبُّهَا بِقَبُولٍ حَسَنٍ وَأَنْبَتَهَا نَبَاتًا حَسَنًا وَكَفَّلَهَا زَكَرِيَّا كُلَّمَا دَخَلَ عَلَيْهَا زَكَرِيَّا الْمِحْرَابَ وَجَدَ عِنْدَهَا رِزْقًا قَالَ يَا مَرْيَمُ أَنَّى لَكِ هَذَا قَالَتْ هُوَ مِنْ عِنْدِ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ يَرْزُقُ مَنْ يَشَاءُ بِغَيْرِ حِسَابٍ ” سورة آل عمران 37
“ጌታዋም በደህና አቀባበል ተቀበላት፤ በመልካም አስተዳደግም አፋፋት፤ ዘከሪያም አሳደጋት ዘከሪያ በርሷ ላይ በምኲራቧ በገባ ቊጥር እርስዋ ዘንድ ሲሳይን አገኘ፤፡- መርየም ሆይ ይህ ለአንቺ ከየት ነዉ? አላት፤፡- እርሱ ከአላህ ዘንድ ነዉ፤ አላህ ለሚሻዉ ሰዉ ሲሳዩን ያለድካም ይሰጣል አላችዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡37)፡፡
ጌታ አላህ የመርየምን እናት ሐናን (ዐለይሃ-ሰላም) ስለቷን ተቀበላት፡፡ የወለደቻትንም ልጇን መርየምን ለቤተ መቅደሱ አገልጋዮች አሳልፋ ሰጠች፡፡ በቤተ መቅደሱም ውስጥ እሷን ለማሳደግ በተነሳው የይገባኛል ጥያቄ፡ ዕጣ ተጣጥለው በዕጣው መሰረት ነቢዩላህ ዘከሪያ (ዐለይሂ-ሰላም) ይደርሰውና እሷን ኃላፊነቱን ወስዶ ይንከባከባታል፡፡ ነቢዩላህ ዘከሪያ (ዐለይሂ-ሰላም) ወደ መርየም ምኩራብ *የጸሎት ስፍራ* በገባ ቁጥር ሲሳይን እሷ ዘንድ ያገኝ ነበር፡፡ በመገረምም፡- መርየም ሆይ! ይህ ሪዝቅ ‹ሲሳይ› ላንቺ ከየት ነው የሚመጣልሽ? አላት፡፡ እሷም፡- ይህ ከአላህ ዘንድ ነው! አላህ *የፈለገውን* ሰው ያለ ድካም ይሰጠዋል በማለት በአላህ ላይ ያላትን ጽኑ እምነት ገለጠችለት፡፡ ከንግግሯም በመነሳት፡ ነገራት በጠቅላላ እውን የሚሆኑት፡ በአላህ ፍላጎትና ፈቃድ መሆኑን እንዳመነች መረዳት ይቻላል፡፡
6/ ሁለቱ ጓደኛሞች፡-
” وَدَخَلَ جَنَّتَهُ وَهُوَ ظَالِمٌ لِنَفْسِهِ قَالَ مَا أَظُنُّ أَنْ تَبِيدَ هَذِهِ أَبَدًا * وَمَا أَظُنُّ السَّاعَةَ قَائِمَةً وَلَئِنْ رُدِدْتُ إِلَى رَبِّي لَأَجِدَنَّ خَيْرًا مِنْهَا مُنْقَلَبًا * قَالَ لَهُ صَاحِبُهُ وَهُوَ يُحَاوِرُهُ أَكَفَرْتَ بِالَّذِي خَلَقَكَ مِنْ تُرَابٍ ثُمَّ مِنْ نُطْفَةٍ ثُمَّ سَوَّاكَ رَجُلًا * لَكِنَّا هُوَ اللَّهُ رَبِّي وَلَا أُشْرِكُ بِرَبِّي أَحَدًا * وَلَوْلَا إِذْ دَخَلْتَ جَنَّتَكَ قُلْتَ مَا شَاءَ اللَّهُ لَا قُوَّةَ إِلَّا بِاللَّهِ إِنْ تَرَنِ أَنَا أَقَلَّ مِنْكَ مَالًا وَوَلَدًا * فَعَسَى رَبِّي أَنْ يُؤْتِيَنِ خَيْرًا مِنْ جَنَّتِكَ وَيُرْسِلَ عَلَيْهَا حُسْبَانًا مِنَ السَّمَاءِ فَتُصْبِحَ صَعِيدًا زَلَقًا” سورة الكهف 40-35
“እርሱም ነፍሱን በዳይ ሆኖ ወደ አትክልቱ ገባ፤ ይህች ዘለዓለም ትጠፋለች ብዬ አልጠረጥርም፣ አለ። ሰዓቲቱንም ቋሚ (ኋኝ) ናት ብዬ አልጠረጥርም፤ (እንደምትለው) ወደ ጌታዬም ብመለስ ከርሷ የበለጠን መመለሻ በእርግጥ አገኛለሁ፥ (አለው)።ጓደኛው፥ (አማኙ)፣ እርሱ ለርሱ የሚመላለሰው ሲሆን ፦ በዚያ ከዐፈር ከዚያም ከፍቶት ጠብታ በፈጠረህ፣ ከዚያም ሰው ባደረገህ፥ (አምላክ) ካድህን? አለው። እኔ ግን እርሱ አላህ ጌታዬ ነው፤ (እላለሁ)፤ በጌታዬም አንድንም አላጋራም። አትክልትህንም በገባህ ጊዜ፣ አላህ የሻው ይሆናል፤ በአላህ ቢሆን እንጂ ኀይል የለም፤ አትልም ኖሯልን? እኔን በገንዘብም በልጅም ካንተ በጣም ያነስኩ ሆኜ ብታየኝ፥ ጌታዬ ከአትክልትህ የበለጠን ሊሰጠኝ በርሷም (በአትክልትህ) ላይ ከሰማይ መብረቆችን ሊልክባትና የምታንዳላጥ ምልጥ ምድር ልትሆን ይቻላል።” (ሱረቱል ከህፍ 18፡35-40)፡፡
ከሀዲው ጓደኛ ባለው ሰፊ የአትክልታማ ስፍራና በልጆች ብዛት በመኩራራት፡ ወደ አትክልታማ ስፍራው ይገባና ‹‹ይህቺ ዘለዓለም ትጠፋለች ብዬ አላስብም፡፡ እንዲሁም ቂያማ ይመጣል የሚልም እምነት የለኝም! ብሎ ሲናገር፡ አማኙ ጓደኛው ደግሞ በአንጻሩ፡- ከአፈር እንዲሁም ከፍትወት ጠብታ ፈጥሮ ሰው ባደረገህ ጌታ ትክዳለህን? እኔ ግን ጌታዬ አላህ ነው! በጌታዬም አላጋራም ይለዋል፡፡ በመቀጥልም፡- ወደ አትክልት ስፍራህ በገባህ ጊዜ *ነገሮች ሁሉ የሚሆኑት አላህ የሻ እንደሆነ ነው* አትልም እንዴ? *ኃይልም ቢሆን በአላህ እንጂ የለም ብለህ አትናገርምን?* በማለት ይወቅሰዋል፡፡ ምክንያቱም አትክልታማው ስፍራ ከፈለገ የሚያቆያት፡ ካልሆነም የሚያጠፋት አላህ ብቻ ነውና፡፡ ይህ የአንተ ስራና ጥበብ አይደለም በማለት ገለጠለት፡፡ ‹‹አላህ የሻው ይሆናል፣ እሱ ያልሻው አይሆንም›› የሚለው እምነት፡ የቀደምት ነቢያትም የአማኞችም ትክክለኛ እሳቤ ነው ማለት ነው፡፡
እነዚህ ለናሙና የቀረቡ ስድስት ምሣሌዎች ናቸው፡፡ አጠቃላይ መልእክታቸው፡- ጌታ አላህ የራሱ የሆነ ፈቃድና ፍላጎት ያለው አምላክ መሆኑን፣ እሱ የፈለገውና የሻው ነገር በጠቅላላ ከመሆን ሊያስቀረው የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ፣ ሰውም የተሰጠውን ነጻ ፈቃድና ውስን ኃይል ተጠቅሞ አንድን ነገር ለማድረግ ቢፈልግ፡ አላህ ካልሻለትና ካልፈቀደለት በስተቀር በራሱ ፍላጎት ብቻ የፈለገውን ሁሉ ማድረግ እንደማይችል፣ የአላህ ፈቃድና ፍላጎት የሁሉንም ፈቃድና ፍላጎት ያሸነፈና የገዛ መሆኑን በአንድ ድምጽ ያሰማሉ፡፡
ይቀጥላል ኢንሻአላህ፡፡
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


