በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)፡ ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)፡ የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
አንዳንድ ሰዎች ለጥፋታቸው ተውበት ከማድረግ ይልቅ በቀደር ያሳብባሉ፡፡ እንዲህ ሲሉም ይደመጣሉ፡- ይህ ተግባር ቀድሞውኑ በኛ ላይ ተጽፎብን ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ከተጻፈው መውጣት ስለማንችል ለዛ ነው የፈጸምነው!፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ምክንያት ምላሹም በአላህ ፈቃድ የሚከተለው ይሆናል ኢንሻአላህ፡፡
1ኛ/ አላህ ምድራዊ ሲሳያችንን ቀድሞ ወስኖታል፡፡ እሱ ባወቀውና በወሰነው ልክ ተቀምጧል፡፡ ከዕውቀቱ ሊወጣ የሚችል አዲስ የሆነ ‹ጉርሻ› እንኳ የለንም፡፡ ከመሆኑም ጋር ስራን እንድንሰራና ሪዝቃችንን እንድንፈልግ አዞናል፡፡
ምድራዊ ቆይታችንን (ዕድሜ) መልአኩ በእናታችን ማኅፀን ጽንስ እያለን እንዲጽፍና እንዲወስን ከአላህ ዘንድ ታዟል፡፡ አላህ ዘንድ ከታወቀውና ከተጻፈልን ዕድሜ ውጭ የምንኖረው ትርፍ ጊዜ የለንም፡፡ ከመሆኑም ጋር እራሳችንን ከአደጋ እንድንከላከል፣ ለጉዳት ከሚዳርጉ ነገራት እንድንርቅ፣ ስንታመምም መድኃኒትን እንድንጠቀም ታዘናል፡፡
እንደዚሁም ፍጻሜአችን ምን እንደሆነ አላህ ዘንድ የታወቀና ተወስኖ የተቀመጠ ነገር ነው፡፡ ከዚህም ጋር የአላህን ትእዛዝ አክብረን በመልካም ስራ ላይ እንድንገኝ እና እራሳችንን ከኃጢአት እንድናርቅ፡ ኃጢአት ላይ በወደቅን ጊዜ ደግሞ በተውበት እንድንመለስ ታዘናል፡፡
እንግዲያውስ ለሚሰራቸው ክፉ ተግባራት በቀደር የሚያሳብበውን ሰው፡- ለምን በሪዝቅህና በጤናህስ ጉዳይ ቀደርን አታሳብብም? ድኃ መሆንህ ቀደር ከሆነ፡ ይህን ድኅነትህን በሐብት ለመቀየር መስራቱ ምን ያደርግልሀል? መታመምህ ቀደር ከሆነ፡ በጤና ለመቀየር በማሰብ በየፋርማሲውና ክሊኒኩ፡ ላይ ታች ማለቱ ምን ይጠቅምሀል? በማለት ልንጠይቀው ይገባል፡፡
ሲሳይን በመፈለግ በአላህ እገዛ ድኅነትን በሐብት መለወጥ ከተቻለ፣ መድኃኒትን በመጠቀም በሽታን በጤንነት መቀየር ከተቻለ፣ ታዲያ ኃጢአትንስ ተውበት በማድረግና አላህን ይቅርታ በመጠየቅ ወደ ሐሰናት መቀየር አይቻልምን? አንዱን በሌላው ለመተካት መልፋት በሪዝቅና በጤና ጉዳይ ብቻ ነው ያለው ማው? ኃጢአት መስራቴ ቀደር ነው ብለህ የምታመካኝ ከሆነና ተውበት ለማድረግ የማትጥር ከሆነ፡ ቀዷ ወል-ቀደር ኃጢአት ላይ ብቻ አይደለምና፡ ድኅነቴም መታመሜም ቀደር ነውና በሐብትና በመድኃኒት ልለውጠው አልችልም ብለህ እጅ ስጥና አርፈህ ተቀመጥ! መባል አለበት፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላውን ጥሎ አይሰራምና፡፡ ደግሞስ ኃጢአት መስራትህ ቀደር መሆኑን ማን አሳወቀህ? ሳትሰራው በፊት ተነግሮህ ነበርን? ስለዚህ በማናውቀው የገይብ ጉዳይ ጣልቃ ገብተን ለጥፋታችን በቀደር ማሳበቡ አይበቃልንም፡፡ በሌላ ጥፋት ድጋሚ ሊያስጠይቀን ይችላልና፡፡
2ኛ/ ለሚሰራው ኃጢአት በቀደር የሚያሳብብ ሰው ከራሱ ሀሳብ ጋር የተምታታ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው አንድ ሌላ ሰው በራሱ ላይ ወሰን ቢያልፍበት፣ ንብረቱን ቢቀማው፣ ደሙን ቢፈሰው ወይም በክብሩ ቢሳለቅበትና ከዛም ይህ ወሰን አላፊው ሰው ለዚህ ግለሰብ፡- ይቅርታ! ይህን ሁሉ ያደረግሁብህ ፈልጌ ሳይሆን አላህ የወሰነብህ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ እኔን እንዳትቆጣኝ ቢለው፡ ምክንያቱን ይቀበለዋልን? ወይስ የበለጠ ያስቆጣዋል? የወሰን አላፊውን ሰውዬ በቀደር ማሳበብ እንደ ዑዝር ካልተቀበለው፡ እንዴት ለራሱ ጊዜ በአላህ ህግ ላይ ወሰንን ሲያልፍ ቀደርን እንደ ዑዝር ማቅረብ ይፈልጋል? ይህ ከራስ ሀሳብ ጋር መጋጨት አይደለምን?
وقد ذكر أن أمير المؤمنين عمر بن الخطاب رضي الله عنه أتي بسارق فأمر بقطع يده، فقال السارق: مهلا يا أمير المؤمنين، والله ما سرقت إلا بقضاء الله وقدره، فقال عمر : ونحن نقطع يدك بقضاء الله وقدره. فاحتج عليه عمر بما احتج به هو على عمله السيئ. مجموع فتاوى ورسائل ابن عثيمين: الجزء الخامس 234.
አሚረል ሙእሚኒን ዑመር ኢብኑል-ኸጥጣብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዘንድ አንድ ሌባ ተይዞ ቀረበ፡፡ እሳቸውም፡- “እጁን ቁረጡት! በማለት ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ሰሪቂውም መላ ያገኘ መስሎት፡- ‹‹ያ አሚረል ሙእሚኒን እባክዎ ይረጋጉ! በጌታዬ በአላህ ይሁንብኝ እኔ የተቀደረብኝ (የተወሰነብኝ) ሆኖ እንጂ አልሰረቅሁም›› አለ፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹እኛም እጅህን በተቀደረው (በተወሰነው) መሰረት እንቆርጠዋለን አሉት››” (መጅሙዕ ፈታዋ ወረሳኢል ሸይኽ ኢብኑ ዑሠይሚን ቅጽ 5 ገጽ 234)፡፡
3ኛ/ ሰዎች በፈቃዳቸው ለሚተገብሩት የኃጢአት ተግባር በቀደር ማሳበብ እውነት እና አግባብነት ያለው ነገር ነው ማለት፡ የአላህ ወዳጆችንና ጠላቶችን በእኩል ወደ ማየት ያመጣናል፡፡ አማኞችን ከከሀዲዎች ጋር ማመሳሰልን ያስይዘናል፡፡ የጀነት ሰዎችንና የጀሀነም ሰዎችን መለየት ያቅተናል፡፡ ምክንያቱም የአማኞች እምነትም ሆነ የከሀዲዎች ክህደት ሁለቱም ቀደር ነውና ስለሚባል፡፡ አላህ ግን በቃሉ እንዲህ ይላል፡-
” أفنجعل المسلمين كالمجرمين * ما لكم كيف تحكمون ” سورة القلم 36-35
“ሙስሊሞቹን እንደ ከሐዲዎች እናደርጋለን? ለናንተ ምን (አስረጅ) አላችሁ? እንዴት ትፈርዳላችሁ።” (ሱረቱል ቀለም 68፡35-36)፡፡
“لا يستوي أصحاب النار وأصحاب الجنة أصحاب الجنة هم الفائزون” سورة الحشر 20
“የእሳት ጓዶችና የጀነት ጓዶች አይስተካከሉም፤ የጀነት ጓዶች እነሱ ምኞታቸውን አግኚዎች ናቸው።” (ሱረቱል ሐሽር 59፡20)፡፡
እውነታው ግን፡ ሰዎች አማኝና ከሀዲ ተብለው ለሁለት የተከፈሉት በተሰጣቸው ነጻ ፈቃድ፡ በቀረበላቸው ፈተናና እነሱም ባስመዘገቡት ውጤት ልክ መሆኑ ነው፡፡ አላህ ይህን ሁሉ ተግባር አስቀድሞ ማወቁና በለውሐል መሕፉዝ ወስኖ ማኖሩ፡ ማንም ሊያሳብብበት አይችልም፡፡ ቀድሞ የተጻፈው ምን እንደሆነ ማወቅ ስለማይችል፡፡ ደግሞም ቀድሞ የተጻፈው የሱን ነጻ ፈቃድ የማይጋፋ በመሆኑና፡ የቂያም ቀንም ፍርድ የሚሰጠው ሰውየው በሰራው እንጂ ቀድሞ በተጻፈው ባለመሆኑ ማለት ነው፡፡
4ኛ/ ቀደር ከሰዎች ጥፋት በፊት የቀደመና የተጻፈ መሆኑ፡ ለኃጢአተኞች ማሳበቢያ ምክንያት መሆን ቢችል ኖሮ፡ አላህ ከዚህ በፊት በኃጢአታቸው ሰበብ ያጠፋቸው የነቢያት ህዝቦችም ዑዝር ሊሆናቸው በቻለ ነበር፡፡ እነሱም በቅጣቱ በመጥፋታቸው ተበድለዋል ማለት ይቻል ነበር፡፡ እውነታው ግን እንደዛ ባለመሆኑ ጌታቸው አላህም አልበደላቸውም፡ ቀደርም ለነሱ መከላከያ ምክንያት ሊሆናቸው አይችልም፡፡ አላህ እንዲህ ይላል፡-
” وما ظلمناهم ولكن ظلموا أنفسهم…” سورة هود 101
“እኛም አልበደልናቸውም፤ ግን ነፍሶቻቸውን በደሉ…” (ሱረቱ ሁድ 11፡101)፡፡
” فكلا أخذنا بذنبه..” العنكبوت: 40
“ሁሉንም በሐጢአቱ ያዝነው…” (ሱረቱል ዐንከቡት 29፡40)፡፡
ምንጭ፡- አል-በያን ፊ አርካኒል ኢማን ፡ሸይኽ አሕመድ ቢን መጅድ መኪይ ገፅ 469-471.
5ኛ/ ለማንኛውም አይነት የኃጢአት ተግባር ‹‹አላህ የቀደረብኝ ነው!›› ብሎ ማሳበብ ትክክለኛ ምክንያት ቢሆን ኖሮ፡ አላህም በተቀበለው ነበር፡፡ እንደ አላህ ምክንያትን መቀበል የሚወድ ማንም የለምና፡፡ ለዚህም ሲባል ነው፡ ሰዎች በኃጢአት ባሕር እንዳይዋኙና ሰምጠው እንዳይቀሩ፡ በየጊዜውና በየቦታው ነቢያትን ከህዝቦቻቸው መርጦ የላከው፡፡ መለኮታዊ መጻሕፍትንም ያወረደው፡፡ ከአቅም በላይም የሆነ ነገር በሚገጥም ጊዜ ግዳጅ የተደረጉ ነገሮችም ከላያችን ላይ የሚነሳው፡፡ ከዚህ የበለጠ ፍፁም ምክንያታዊነት ይኖር ይሆን? የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” رُسُلًا مُبَشِّرِينَ وَمُنْذِرِينَ لِئَلَّا يَكُونَ لِلنَّاسِ عَلَى اللَّهِ حُجَّةٌ بَعْدَ الرُّسُلِ وَكَانَ اللَّهُ عَزِيزًا حَكِيمًا ” سورة النساء 165
“ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች የሆኑን መልክተኞች፣ (ላክን)፤ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡165)፡፡
عَنْ عَبْدِ اللهِ بْنِ مَسْعُودٍ، قَالَ: قَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: «…لَيْسَ أَحَدٌ أَحَبَّ إِلَيْهِ الْعُذْرُ مِنَ اللهِ، مِنْ أَجْلِ ذَلِكَ أَنْزَلَ الْكِتَابَ وَأَرْسَلَ الرُّسُلَ» رواه مسلم 2760.
ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ምክንያትን ማቅረብ እንደ አላህ እሱ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ አንድም የለም፡፡ በመሆኑም ምክንያት መጽሐፍትን አወረደ፡፡ መልክተኞችንም ላከ” (ሙስሊም 2760)፡፡
ከቁርኣኑም ከሐዲሡ ተመሳሳይ ሀሳብን እናገኛለን፡፡ እሱም፡- አላህ ባሮቹን አስቀድሞ ባወቀውና በወሰነው ነገር ብቻ መቅጣትን ስላልፈለገና፡ በነሱ ላይ ምክንያታዊ ሆነ ማስረጃን ማቅረብ ስለወደደ አስቀድሞ ነቢያትን ላከላቸው፡፡ ቃሉንም በነዚህ ነቢያት በኩል አወረደላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ የጥመትና የሐቅ መንገድ በነቢያት በኩል ተብራርቶል ሲያበቃ በገዛ ፈቃዱ ኃጢአት ላይ የሚዘፈቅ የአላህ ባሪያ ነጌ በጌታው ፊት የሚያቀርበው የመከላከያ ምክንያት አይኖረውም ማለት ነው፡፡ የነቢያት መልእክት፡ የአላህ ቃል ያልደረሰው ሰው ግን፡ ባልደረሰው ነገር እንደማይቀጣ ጌታ አላህ እንዲህ ተናገረ፡-
” مَنِ اهْتَدَى فَإِنَّمَا يَهْتَدِي لِنَفْسِهِ وَمَنْ ضَلَّ فَإِنَّمَا يَضِلُّ عَلَيْهَا وَلَا تَزِرُ وَازِرَةٌ وِزْرَ أُخْرَى وَمَا كُنَّا مُعَذِّبِينَ حَتَّى نَبْعَثَ رَسُولًا ” سورة الإسراء 15
“የተመራ ሰው የሚመራው ለራሱ ብቻ ነው፤ የተሳሳተም ሰው፣ የሚሳሳተው (ጉዳቱ) በርሷ ላይ ነው፤ ተሸካሚም (ነፍስ፣) የሌላይቱን ኃጢአት አትሸከምም፤ መልክተኛንም እስከምንልክ ድረስ የምንቀጣ አይደለንም።” (ሱረቱል ኢስራእ 17፡15)፡፡
ታዲ የአላህ መልክት በነቢያቱና በዑለማኦች አማካኝነት ያልደረሰው ሰው እንደ ዑዝር ተቆጥሮለት አላህ ዘንድ የማይቀጣ ከሆነ፡ ቀዷ ወል-ቀደርን ለጥፋቱ የሚያሳብብ ሰው ዑዝር ቢሆነው ኖሮ ይቀጣ ነበርን? በፍፁም አይቀጣም ነበር! ግን በቀደር ማሳበብ ለማንም ምክንያት መሆን አይችልምና ከተጠያቂነት አይድንም ማለት ነው፡፡
6ኛ/ ሰዎች ለፈፀሙት ኃጢአት በቀደር ማሳበባቸው አላህ ዘንድ እንደ ዑዝር ሆኖ መቅረብ ቢችል ኖሮ፡ በጥፋታቸውና በክህደታቸው ምክንያት ጀሀነም የተፈረደባቸው ሰዎች እጅጉኑ ባስፈለጋቸው ነበር፡፡ እሳቲቷን ባዩ ጊዜና ገቢዎች መሆናቸውን ባወቁ ሰአት ቀደርን ማሳባብ ትዝ ባላቸው ነበር፡፡ ይልቁኑ እነሱ የሚሉት (አላህ ይጠብቀን) ከዚህ በተቃራኒ በራሳቸው ላይ በመፍረድ እንዲህ በማለት ነው፡-
” وَأَنْذِرِ النَّاسَ يَوْمَ يَأْتِيهِمُ الْعَذَابُ فَيَقُولُ الَّذِينَ ظَلَمُوا رَبَّنَا أَخِّرْنَا إِلَى أَجَلٍ قَرِيبٍ نُجِبْ دَعْوَتَكَ وَنَتَّبِعِ الرُّسُلَ أَوَلَمْ تَكُونُوا أَقْسَمْتُمْ مِنْ قَبْلُ مَا لَكُمْ مِنْ زَوَالٍ ” سورة أبراهيم 44
“ሰዎችንም ቅጣቱ የሚመጣባቸውን ቀን አስፈራራቸው፤ እነዚያም የበደሉት፦ ጌታችን ሆይ ወደ ቅርብ ጊዜ ድረስ አቆየን፤ ጥሪህን እንቀበላለንና መልክተኞቹንም እንከተላለንና ይላሉ፤ ከአሁን በፊት (በምድረ ዓለም)፤ ለናንተ ምንም መወገድ የላችሁም በማለት የማላችሁ አልነበራችሁምን? (ይባላሉ)።” (ሱረቱ ኢብራሂም 14፡44)፡፡
” أَلَمْ تَكُنْ آيَاتِي تُتْلَى عَلَيْكُمْ فَكُنْتُمْ بِهَا تُكَذِّبُونَ * قَالُوا رَبَّنَا غَلَبَتْ عَلَيْنَا شِقْوَتُنَا وَكُنَّا قَوْمًا ضَالِّينَ * رَبَّنَا أَخْرِجْنَا مِنْهَا فَإِنْ عُدْنَا فَإِنَّا ظَالِمُونَ ” سورة المؤمنون 107-105
“«አንቀጾቼ በእናንተ ላይ የሚነበቡላችሁና በእነርሱ የምታስተባብሉ አልነበራችሁምን» (ይባላሉ)፡፡ይላሉ «ጌታችን ሆይ! በእኛ ላይ መናጢነታችን አሸነፈችን፡፡ ጠማማዎችም ሕዝቦች ነበርን፡፡ «ጌታችን ሆይ! ከእርሷ አውጣን፡፡ (ወደ ክህደት) ብንመለስም እኛ በደዮች ነን፡፡»” (ሱረቱል ሙእሚኑን 23፡105-107)፡፡
” تَكَادُ تَمَيَّزُ مِنَ الْغَيْظِ كُلَّمَا أُلْقِيَ فِيهَا فَوْجٌ سَأَلَهُمْ خَزَنَتُهَا أَلَمْ يَأْتِكُمْ نَذِيرٌ * قَالُوا بَلَى قَدْ جَاءَنَا نَذِيرٌ فَكَذَّبْنَا وَقُلْنَا مَا نَزَّلَ اللَّهُ مِنْ شَيْءٍ إِنْ أَنْتُمْ إِلَّا فِي ضَلَالٍ كَبِيرٍ * وَقَالُوا لَوْ كُنَّا نَسْمَعُ أَوْ نَعْقِلُ مَا كُنَّا فِي أَصْحَابِ السَّعِيرِ * فَاعْتَرَفُوا بِذَنْبِهِمْ فَسُحْقًا لِأَصْحَابِ السَّعِيرِ ” سورة الملك 11-8
“ከቁጭትዋ የተነሳ ልትቆራረጥ ትቀርባለች፤ በውስጧ ጭፍሮች በተጣሉ ቁጥር ዘበኞችዋ አስፈራሪ (ነቢይ) አልመጣችሁምን? በማለት ይጠይቋቸዋል። አይደለም በእርግጥ አስፈራሪ መጥቶናል፤ አስተባበልንም፤ አላህም ምንም አላወረደ እናንተ (አውርዷል ስትሉ) በትልቅ ስሕተት ውስጥ እንጅ አይደላችሁም አልን፣ ይላሉ። የምንሰማ ወይንም የምናስብ በነበርን ኖሮ በነዳጅ እሳት ጓዶች ውስጥ ባልሆን ነበር ይላሉ። በኅጢአታቸውም ያምናሉ ለእሳት ጓዶችም (ከእዝነት) መራቅ ተገባቸው።” (ሱረቱል ሙልክ 67፡8-11)፡፡
እነዚህ ስድስቱ ለአብነት የቀረቡ ምሣሌዎች ናቸው፡፡ በጥቅሉ አንድ ሙስሊም መልካም ስራን ቢሰራ፡ የአላህ እገዛና ራሕመት መሆኑን አውቆ ጌታውን ያመስግን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኃጢአት ላይ ከወደቀ የነፍሲያው ድክመትና የሸይጧን ጉትጎታ መሆኑን በማመን ቶሎ ወደ ተውበት ይመለስ፡፡ ከተውበት በኋላ ይሁ ነገር ‹ቀደር› ነው ብሎ ቢናገር፡ ንግግሩም ትክክል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከቀደር የወጣ ነገር የለምና፡፡ ከተውበት በፊት ግን እኔ ላይ የተጻፈ ነው ብሎ ማሳበብ፡ ለተውበት ግርዶሽ የሚሆንና የራስን ድክመት ዞር ብሎ ለማየት እንቅፋት የሚሆን ነገር ነው፡፡ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ እራሱን ያልወቀሰ ነፍስ እንዴት ተውበት ያደረጋል? ከተውበት መስፈርቶችስ አንዱ ‹ነዳማህ› (ጸጸት) አይደለምን? አላህ ትክክለኛ ግንዛቤን ይወፍቀን፡፡
ይቀጥላል
ወአኺሩ ዳዕዋና ዐኒል-ሐምዱ ሊላሂ ረቢል ዓለሚን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


