በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ዛሬ የምናስተናግደው ጥያቄ ደግሞ ይህ ነው፡፡ እሱም፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሳይሞትና ሳይገደል አላህ ወደራሱ ካነሳው (ከወሰደው)፣ እስካሁንም በሕይወት ካለ፡ በርግጥም እሱ ምድራዊ ቆይታቸውን ፈጽመው፡ ወደ መቃብር ዓለም ገብተው ስጋቸውና አጥንታቸው በስብሶ ከቀረው ነቢያት ይበልጣል ማለት ነው! የሚለውን ነው፡፡ ይህ አመለካከት ግን ፍጹም ስህተት መኾኑን ቀጥሎ ባሉት ምክንያቶች ይብራራል፡-
1ኛ/ ነቢያት ምድራዊ ቆይታቸውን ሲጨርሱ ይሞታሉ፡፡ አላህ ከወሰነው ሞት ሊያመልጥ የሚችል አንድም የለም!፡፡ ሞት የኃጢአት ውጤት ሳይሆን፡ ወደ አኼራ (ወደ ዘላቂው ሕይወት) መሸጋገሪያ ድልድይ ነው፡፡ ኾኖም ነቢያት ቢሞቱና ቢቀበሩም፡ ምድር የነሱን ክቡር ገላ በፍጹም አትበላውም፡፡ አላህ እርም አድርጎባታልና!፡፡ ቀጣዩ ሐዲሥ ይህን ያሳያል፡-
عن أوس بن أوس قال: قال رسول الله صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: ” إن مِنْ أفضل أيامكم يومَ الجمعة؛ فيه خُلِقَ آدم، وفيه قُبِض، وفيه النَّفخة، وفيه الصعقة، فأكثروا علي من الصلاة فيه؛ فإن صلاتكم معروضة علي “.قال: قالوا: يا رسول الله! وكيف تعْرَضُ صلاتنا عليك وقد أرَمْتَ؟! قال: يقولون: بَلِيت! فقال: ” إن الله عز وجل حَرَّمَ على الأرض أجسادَ الأنبياءِ “صحيح أبي داود 962.
አውስ ኢብኑ አውስ (ረዲየላሁ አንሁ) እንዳስተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል አለ፡- “ከቀናቶቻችሁ ሁሉ በላጩ የጁሙዓ ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን (አባታችን) አደም ተፈጠረ፣ ህይወቱም ያለፈው በዚህ ቀን ነው፣ በጥሩንባ የሚነፋውና ትንሳኤም የሚቆመው በዚህ ቀን ነው፣ በዚህ ቀን በኔ ላይም ሶላዋት አብዙ፡ የናንተ ሶላዋት (በአላህ ፈቅድ) ይደርሰኛልና” ሶሓቦችም፡- ‹‹አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! የኛ ሰላምታ እንዴት ይደርሶታል? ከሞቱ በኋላ አፈር ይበላዎት አይደለም ወይ?›› አሉ፡፡ መልክተኛውም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- “ አላህ ምድርን የነቢያትን አካል ከመብላት እርም አድርጎባትል” በማለት መለሱ፡፡ (አቡ ዳውድ (1047.1631) አሕመድ ሙስነድ (4/8) ኢብኑ ማጀህ (1085-1636) ነሳኢይ (3/62-91) ሌሎችም የዘገቡት፡፡
ከዚህ ነቢያዊ አስተምህሮ በመነሳት፡ ነቢያት በመቃብሩ ዓለም ስጋቸውና አጥንታቸው የበሰበሰና አፈር የኾነ ነው! የሚለው አስተምህሮ ስህተት መኾኑን መረዳት እንችላለን፡፡
2ኛ/ አላሁ (ሱብሐነሁ ወተዓላ) ሞትና ሕይወትን የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ ሕይወት የመልካም ሥራ ውጤት እንዳልሆነው ሁላ፡ ሞትም የኃጢአት ውጤት አይደለም፡፡ ሰው ቀድሞውኑ በዚህ ምድር ላይ ሲፈጠር በአምላካዊ ህግጋቶች (ይህን ፈጽም፡ ያን ደግሞ አትቅረብ በሚሉት) ሊፈተን እንጂ፡ ለዘለዓለም እንዲኖር አይደለም፡፡ ዘላለማዊነትን (በጀነት ወይም በጀሀነም) የሚረከብበት ዓለም የውሙል ቂያም (የትንሳኤው ዕለት) ነው፡፡ በዚህም ሰበብ በምድራዊ ቆይታው ከአምላኩ ከአላህ ዘንድ ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ሞትንም ጭምር ተቀብሎ ነው የመጣው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“الَّذِي خَلَقَ الْمَوْتَ وَالْحَيَاةَ لِيَبْلُوَكُمْ أَيُّكُمْ أَحْسَنُ عَمَلًا وَهُوَ الْعَزِيزُ الْغَفُورُ ” سورة الملك 2
“ያ የትኛችሁ ሥራው ይበልጥ ያማረ መሆኑን ሊሞክራችሁ፣ ሞትንና ሕይወትን የፈጠረ ነው፤ እርሱም አሸናፊው መሐሪው ነው።” (ሱረቱል ሙልክ 67፡2)፡፡
ስለዚህ በሕይወት መኖርም ሆነ መሞት የአላህ መለኮታዊ ውሳኔ ከኾነ፡ ነቢያትን በሱ ማወዳደር አንችልም ማለት ነው!
3ኛ/ ማንም ሰው ምድራዊ ተልእኮውን ከፈጸመ በኋላ ከአላህ ዘንድ የተወሰነለት ምድራዊ ቆይታ ሲጠናቀቅ (አጀሉ ሲደርስ) መሞቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከሞት ሊያመልጥ የሚችል አንድም ነፍስ የለም፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሁሉም ከሞት በታች ነውና፡፡ የአላህ ቃል ይህንን እውነት እንዲህ ያጎላዋል፡-
“كُلُّ نَفْسٍ ذَائِقَةُ الْمَوْتِ وَإِنَّمَا تُوَفَّوْنَ أُجُورَكُمْ يَوْمَ الْقِيَامَةِ فَمَنْ زُحْزِحَ عَنِ النَّارِ وَأُدْخِلَ الْجَنَّةَ فَقَدْ فَازَ وَمَا الْحَيَاةُ الدُّنْيَا إِلَّا مَتَاعُ الْغُرُورِ ” سورة آل عمران 185
“ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፤ ምንዳዎቻችሁንም የምትሞሉት (የምትሰጥጡት) በትንሣኤ ቀን ብቻ ነዉ። ከእሳትም የተራቀና ገነትን የተገባ (እንዲገባ የተደረገ) ሰዉ፣ በእርግጥ ምኞቱን አገኘ ቅርቢቱም ሕይወት የመታለያ መሣሪያ እንጅ ሌላ አይደለችም።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡185)፡፡
“كُلُّ نَفْسٍ ذَائِقَةُ الْمَوْتِ وَنَبْلُوكُمْ بِالشَّرِّ وَالْخَيْرِ فِتْنَةً وَإِلَيْنَا تُرْجَعُونَ ” سورة الأنبياء 35
“ነፍስ ሁሉ ሞትን ቀማሽ ናት፤ ለመፈተንም በክፉም በበጎም እንሞክራችኋለን፤ ወደኛም ትመለሳላችሁ።” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡35)፡፡
“وَلَوْ يُؤَاخِذُ اللَّهُ النَّاسَ بِظُلْمِهِمْ مَا تَرَكَ عَلَيْهَا مِنْ دَابَّةٍ وَلَكِنْ يُؤَخِّرُهُمْ إِلَى أَجَلٍ مُسَمًّى فَإِذَا جَاءَ أَجَلُهُمْ لَا يَسْتَأْخِرُونَ سَاعَةً وَلَا يَسْتَقْدِمُونَ ” سورة النحل 61
“አላህም ሰዎችን በበደላቸው በያዛቸው ኖሮ፣ በርሷ (በምድር) ላይ ከተንቀሳቃሽ ምንንም ባልተወ ነበር፤ ግን እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ያቆያቸዋል፤ ጊዜያቸውም በመጣ ወቅት አንዲትን ሰዓት አይቆዩም፤ አይቀደሙምም።” (ሱረቱ-ነሕል 16፡61)፡፡
ከነዚህ አንቀጾች በግልጽ የምንረዳው፡- ሕይወታችንና ሞታችን ያለው በአላህ ዘንድ ብቻ ነው፡፡ እሱ የሻውን ነፍስ የፈለገው ያህል ጊዜ ያቆየዋል፡፡ ሲፈልግ ሩሑን (መንፈሱን) ከውስጡ እንዲወጣ በማዘዝ ይገድለዋል፡፡ ያለ አላህ ፈቃድና ኃይል የተፈጠረና ሕያው የሆነ ነፍስ እንደሌለ ሁሉ፡ ያለሱ ፈቃድም የምትሞት አንዲትም ነፍስ የለችም፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” وَمَا كَانَ لِنَفْسٍ أَنْ تَمُوتَ إِلَّا بِإِذْنِ اللَّهِ كِتَابًا مُؤَجَّلًا…” سورة آل عمران 145
“ለማንኛይቱም ነፍስ በአላህ ፍርድ ቢሆን እንጅ ልትሞት አይገባትም፤ (ጊዜዉም) ተወስኖ ተጽፏል…” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡145)፡፡
4ኛ/ የመርየም ልጅ ዒሳም (ዐለይሂ-ሰላም) ቢሆን ሟች ነው፡፡ ከሞት ሊያመልጥና ሊተርፍ አይችልም፡፡ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) አልሞተም ማለት አይሞትም ማለት አይደለም፡፡ ወደፊት ቂያማ ከመቆሙ በፊት በመቃረቢያው ላይ ወደዚህ ምድር ይወርዳል፡፡ ተልእኮውንም ከፈጸመ በኋላ ሰብአዊ ፍጡር ነውና ይሞታል፡፡ ይህንን እውነታ በራሱም አንደበት እንደተናገረ ጌታችን በቃሉ እንዲህ ይነግረናል፡-
“وَالسَّلَامُ عَلَيَّ يَوْمَ وُلِدْتُ وَيَوْمَ أَمُوتُ وَيَوْمَ أُبْعَثُ حَيًّا ” سورة مريم 33
“ሰላምም በኔ ላይ ነው፣ በተወለድሁ ቀን፣ በምሞተበትም ቀን፣ ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን” (ሱረቱ መርየም 19፡33)፡፡
በደንብ አስተውሉ! ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) መወለዱን ለመግለጽ ‹በተወለድሁ ቀን› አለ እንጂ፡ ‹በምወለድበት ቀን› አላለም፡፡ ተወልዷልና፡፡ ሟች መሆኑን ለመግለጽ ግን ‹በምሞትበት ቀን› አለ፡፡ አልሞተምና ‹በሞትሁበት ቀን› ብሎ እንደ ውልደቱ ድርጊቱን ኃላፊ ጊዜ አድርጎ አልተጠቀመም፡፡ ስለዚህ ወደፊት ይመጣል ይሞታል ይቀሰቀሳልም!!
5ኛ/ ወደ ገደለው እንግባና፡- እንግዲያውስ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እስካሁን ድረስ አልሞተምና፡ ሌሎች ነቢያት ግን (ዐለይሂሙ-ወሰለም) በመሞታቸው ከነሱ ይበልጣል! ማለት ነው ስንል፡ ቀጣዩን ጥያቄ በአግባቡ መልስ ልንሰጥበት ይገባል፡-
የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እስካሁን በሕይወት የቆየው በራሱ ፈቃድ ነውን? ደግሞስ በሕይወት እንዲቆይ ያደረገው የተለየ መልካም ሥራ ኖሮት ነውን? በዛው ተቃራኒ ሌሎች ነቢያትም (ዐለይሂሙ-ሰላም) የሞቱትና እስካሁን በሕይወት ያልቆዩት ኃጢአታቸው በመብዛቱ ሰበብ ነውን?
ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ፡- በፍጹም! የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም በመግቢያችን ላይ እንዳየነው ሞትና ሕይወት ከአላህ ዘንድ ለባሮቹ የሚለገስ መለኮታዊ ውሳኔ እንጂ፡ የጽድቅና የኃጢአት ውጤት አይደለም፡፡ የዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እስካሁን በሕይወት መቆየት የጌታው ፈቃድና ዓላማ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የነቢያትም መሞት መለኮታዊ ፍርድ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ በመሆኑም የመለኪያው መስፈርት እጅግ የተሳሳተ ነው!!
6ኛ/ እኛ ሙስሊሞች ከጌታ አላህ ዘንድ የታዘዝነው በነቢያት መካከል ምንም አይነት የእምነት ልዩነት ሳናደርግ (በአንዱ አምኖ በሌላው መካድ ሳይኖር) በሁሉም ነቢይነት እንድናምን እንጂ፡ ሰዋዊ መለኪያዎችን እያስቀመጥን አንዱን ከሌላው እንድናወዳድር አይደለም፡፡ ይህ አካሄድ ኋላ ላይ አንዱን ነቢይ ከፍ ለማድረግ ሲባል የሌላውን ነቢይ ክብር በመንካት ከአላህ ጋር ወደ መጣላት ያደርሰናል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“قُولُوا آمَنَّا بِاللَّهِ وَمَا أُنْزِلَ إِلَيْنَا وَمَا أُنْزِلَ إِلَى إِبْرَاهِيمَ وَإِسْمَاعِيلَ وَإِسْحَاقَ وَيَعْقُوبَ وَالْأَسْبَاطِ وَمَا أُوتِيَ مُوسَى وَعِيسَى وَمَا أُوتِيَ النَّبِيُّونَ مِنْ رَبِّهِمْ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِنْهُمْ وَنَحْنُ لَهُ مُسْلِمُونَ ” سورة البقرة 136
“«በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል #የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን» በሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡136)፡፡
“آمَنَ الرَّسُولُ بِمَا أُنْزِلَ إِلَيْهِ مِنْ رَبِّهِ وَالْمُؤْمِنُونَ كُلٌّ آمَنَ بِاللَّهِ وَمَلَائِكَتِهِ وَكُتُبِهِ وَرُسُلِهِ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِنْ رُسُلِهِ وَقَالُوا سَمِعْنَا وَأَطَعْنَا غُفْرَانَكَ رَبَّنَا وَإِلَيْكَ الْمَصِيرُ ” سورة البقرة 285
“መልክተኛው ከጌታው ወደ ርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል #አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡:” (ሱረቱል በቀራህ 2፡285)፡፡
“قُلْ آمَنَّا بِاللَّهِ وَمَا أُنْزِلَ عَلَيْنَا وَمَا أُنْزِلَ عَلَى إِبْرَاهِيمَ وَإِسْمَاعِيلَ وَإِسْحَاقَ وَيَعْقُوبَ وَالْأَسْبَاطِ وَمَا أُوتِيَ مُوسَى وَعِيسَى وَالنَّبِيُّونَ مِنْ رَبِّهِمْ لَا نُفَرِّقُ بَيْنَ أَحَدٍ مِنْهُمْ وَنَحْنُ لَهُ مُسْلِمُونَ ” سورة آل عمران 84
“በአላህ አመንን፤ በኛ ላይ በተወረደዉም፥ (በቁርአን) በኢብራሂምና በኢስማዒልም፣ በኢስሐቅም በያዕቆብም፣ በነገዶችም ላይ በተወረደዉ፤ ለሙሳና ለዒሳም፣ ለነቢያትም ሁሉ ከጌታቸዉ በተሰጠዉ (አመንን)፤ ከነርሱ መካከል አንዱንም #አንለይም፤ እኛ ለርሱ ታዛዦች ነን፣ በል።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡84)፡፡
7ኛ/ በመጨረሻም ለወገኖቻችን የምናቀርበው ጥያቄ፡- አንድ ነቢይ ለረጅም ዘመናት በሕይወት መቆየቱ፡ ረጅም ዘመን ሳይኖር ከሞተው ሌላ ነቢይ በደረጃ የሚያስበልጠው ከሆነ፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱሳችሁ አስተምህሮ መሰረት ሄኖክና ኤልያስ ከነቢያት ሁሉ ይበልጣሉ ማለት ነውን?
በእናንተ ዘንድ እንደሚታወቀው ሙሴ/ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሊቀ-ነቢያት ነው፡፡ ሌሎችም አበይት/ዋና ነቢያት የሚባሉ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ምድራዊ ተልእኮአቸውን ሲፈጽሙ ሞተዋል፡፡ በክብር ተቀብረዋል፡፡ ሄኖክ/ኢድሪስ (ዐለይሂ-ሰላም) ግን መጽሓፋችሁ እንደሚናገረው በእምነት አምላኩን በማስደሰቱ ሞትን እንዳያይ ተወስዷል፡-
‹‹ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና፤›› (ዕብራዊያን፡ 11፡3)፡፡
ነቢዩ ኤልያስም/ኢልያስ (ዐለይሂ-ሰላም) ቢሆን በአውሎ ነፋስ አማካኝነት ወደ ሰማይ እንደተወሰደ መጽሐፉ ይናገራል፡፡ ተመልሶ መምጣቱንና መሞቱን አይገልጽም፡-
‹‹ሲሄዱም፦ እያዘገሙም ሲጫወቱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በመካከላቸው ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ወጣ።›› (2ኛ ነገስት 2፡11)፡፡
በዚህ ምክንያት እነዚህ ሞትን ያላዩ ነቢያት፡ ከሞቱት (አብረሃም፣ ሙሴ፣ ኢሳይያስ፣ ኤርሚያስ፣ ዳንኤል፣ ህዝቅኤል…) በክብርና በደረጃ ይበልጣሉ ማለት ነውን? ወይስ መመዘኛው የሚያገለግለው ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሲሆን ብቻ ነው? አላህ ወደ ሐቁ ጎዳና ይምራችሁ፡፡ እኛንም በእምነታችን ጽናት ይስጠን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


