በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
አንዳንድ አላዋቂዎች ከእምነታቸው ጉድለት: ከግንዛቤያቸውም እጥረት “ሰው የተፈጠረው ለፈተና ነው!” የሚለውን የሙስሊሞችን እምነት ይቃወማሉ። እንዲህ ሲሉም ተቃውሞ ያቀርባሉ፡- አላህ ሰውን የፈጠረው ለፈተና ከሆነ፡ እሱ መልካም አምላክ ሳይሆን ክፉ ነው ማለት ነው! ደግሞስ መፈተኑ ቀድሞ አያውቅም ነበር ማለት ነውን? የሚል ነው፡፡
የኛም ምላሽ በአላህ ፈቃድ እንደሚከተለው ይሆናል፡-
1ኛ. ለዚህ ለተሳሳተ ግንዛቤ መነሻ ችግር የሆነው ለምን እንደተፈጠርን አለማወቁ ነው፡፡ ፈጣሪ አምላክ አላህ ሰውን በዚህ ምድር ላይ የመፍጠሩን ዓላማ የተረዳ ሰው ‹‹ለፈተናም የተዘጋጀ›› መሆኑን በቀላሉ ይረዳል፡፡
የአምላክ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርኣን ለምን እንደተፈጠርን ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
‹‹ጋኔንንና ሰውን ሊገዙኝ እንጅ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም።›› (ሱረቱ-ዛሪያት 56)፡፡
ከዚህ አንቀጽ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው እኛ ሰዎች ብቻ ሳንሆን አጋንንት (ጂንኒ) እንኳን የተፈጠሩበት ዓላማ አላህን በብቸኝነት ለማምለክና ለመገዛት ነው፡፡ ሰው ከእንሰሳ የሚለይበት ትልቁ ነጥብም እዚህ ጋር ነው፡፡ እንሰሳዎች ህግ የላቸውም፡፡ በደመ-ነፍስ ነው የሚጓዙት፡፡ የተፈጠሩትም ለአምልኮ ሳይሆን ለሰው ልጅ ግልጋሎት ነው (አል-በቀራህ 29)፡፡ ሰው ደግሞ ፈጣሪ አምላኩን አላህን ለማገልገልና በትእዛዙ ስር ለመኖር ነው የተፈጠረው፡፡ ለምን እንደተፈጠረ ያላወቀ ሰው፡ በማን ትእዛዝ ስር መኖር እንዳለበት ያልተረዳ ሰው ከእንሰሳ በምን ይለያል? ሁለቱም ይበላሉ፡ ይጠጣሉ፡ ቆሻሻቸውን ያራግፋሉ፡ ይተኛሉ፡ መጨረሻም ይሞታሉ!!!
2ኛ. የተፈጠርንበትን ዓላማ ካወቅንና ከተረዳን ደግሞ ቀጣዩን ነጥብ እናንሳው፡፡ እሱም፡- የተፈጠርነው ለአምልኮ ከሆነ፡ ለምን እንደ መላእክት ከኃጢአት ፈቃድ እና ስሜት ነጻ ተደርገን፡ ለአምልኮ ብቻ የተዘጋጀን ሆነን ለምን አልተፈጠርንም? ለምን አምላካችን አላህ ‹‹ስሜት›› የሚባለው ውስጣዊ ጠላታችን እንዲኖር ፈቀደ? ለምንስ ሰይጣናት እኛን ከሐቅ መንገድ ለማውጣት እንዲሞክሩ ፈቃዱ ሆነ? ይህ ሁሉ ለፈተና መሆኑን አያሳይም? ደግነቱ አላህ እነዚህን ፈተናዎችንም ተቋቁመን ለማለፍ ከፈቀድን የሚያግዘንንም አቅም ለግሶናል፡፡ የራሱም እርዳታ እንደማይለየን ነግሮናል (አል-ፋቲሓ 5)፡፡
ሰው ያለ ፈተና ለአምልኮ ብቻ የተዘጋጀ እንዲሆን የተፈጠረ ቢሆን ኖሮ፡ አላህ ሰይጣናትን ዝም ይላቸው ነበርን? የሰይጣናትን ዓላማ የሚያሳኩ የሰው ሰይጣናትንስ እንዲኖሩ ይፈቅድ ነበርን? በምድራዊው ትምህርት ቤት እንኳ ያለ-ፈተና ውጤት የለም! አይደል የሚባለው?፡፡
3ኛ. ሰው ነጻ ፈቃድ (free will) ያለው ፍጡር ነው፡፡ እንደ ሮቦት በተሞላው ብቻ የሚንቀሳቀስ ፍጥረት አይደለም፡፡ ከአምላኩ አላህ ዘንድ ‹‹አድርግ!›› የተባለውን ትእዛዝ ለመፈጸምም ሆነ ለመተው፡ ‹‹አታድርግ›› ተብሎ የታቀበውንም ነገር ለመራቅም ሆነ ለመዳፈር የሚያስችለው ምርጫና ውስን አቅም ተሰጥቶታል፡፡ ይህ በራሱ ፈተና አይደለምን? አንተ ራስህ በአንድ ነገር ላይ ለማድረግም ሆነ ለመተው ነጻ ፈቃዱ ተሰጥቶሀል ብትባል፡ እስኪ ምን ታደርግበታለህ በሚል ቋንቋ እየተፈተንክ መሆኑ አይገባህምን?
አላህ ትዳርን ፈቅዶ ዝሙትን መከልከሉ፣ ንግድን ፈቅዶ ወለድን መከልከሉ፣ ውሀና መሰል መጠጦችን ፈቅዶ መጠጥና አስካሪ ነገሮችን በመላ መከልከሉ፣ በስሙ የታረደን ምግብ ፈቅዶ ለጣኦት የተሰዋን ምግብ እርም ማድረጉ፣ እሱን ብቻ እንድናመልክ አዝዞ ጣኦት አምልኮን መከልከሉ ፈተና አይደለምን? ፈተና አይደለም ካላችሁ ምን እንበለው ታዲያ? ፈተናስ ካልሆነ ለምን የተከለከልናቸውን ነገራት ከፈለግን እንድንጠቀም ነጻ ፈቃዱን ሰጠን?
4ኛ. አላህ ሰዎችን ሊፈትናቸው ፈጠራቸው ማለት እርሱ መልካም አምላክ አይደለም ለማለት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ ምክንያቱም፡- የታዘዝነውን ለመፈጸምም ሆነ የተከለከልነውን ለመራቅ የሚያስችል አቅምን ለግሶናልና፡፡ በዛም ሳያበቃ ‹‹የኔንም እገዛ ከሻችሁ አግዛችኋለሁ›› በማለት ቃል ገብቶልናልና፡፡ ከዛ በበለጠ የሚደንቀው ደግሞ፡- ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ሲመጣ እንኳ የታዘዝነው ግዳጅ እንደሚነሳልን መናገሩ ነው (አል-በቀራህ 286)፡፡ እንግዲያውስ መጥፎነቱ ምኑ ላይ ነው?
“በናንተ ላይ እርም ያደረገው፣ በክትንና ደምን፣ የአሳማንም ሥጋ፣ ያንንም (በመታረድ ጊዜ) በርሱ ከአላህ ስም ሌላ የተነሳበትን ብቻ ነው፤ አመጠኛም ወሰን አላፊም ሳይሆን (ለመብላት) የተገደደ ሰው (ይፈቀድለታል)፤ አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና።” (ሱረቱ-ነሕል 115)፡፡
5ኛ. ከግንዛቤ ጉድለት የመነጨው ሌላው ጥያቄ እዚህ ጋር ነው፡፡ አላህ ሰዎችን የፈጠራቸው ሊፈትናቸው ነው ከተባለ፡ ምነው ቀድሞ አላወቀም ነበር ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል ይላሉ፡፡ መልሱም እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ሀ. አላህ ሁሉን ዐዋቂ የሆነ አምላክ ነው፡፡ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማረጋገጫ ቀጣዩ አንቀጽ ነው፡፡
‹‹የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም፡፡ በየብስና በባሕር ያለውንም ሁሉ ያውቃል፡፡ ከቅጠልም አንዲትም አትረግፍም የሚያውቃት ቢኾን እንጅ፡፡ ከቅንጣትም በመሬት ጨለማዎች ውስጥ የለም ከእርጥብም ከደረቅም አንድም የለም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውሰጥ (የተመዘገበ) ቢኾን እንጅ፡›› (ሱረቱል አንዓም 59)፡፡
ለ. ታዲያ እኛን ለምን ፈተነን? ከተባለም መልስ የሚሆነው፡- የነገው ቤታችንን በገዛ ፈቃዳችን ከወዲሁ መርጠን እንድንጓዝ የሚል ነው፡፡ ‹ጀነት› እና ‹ጀሀነም› የሚባሉ የተድላና የስቃይ ዓለም ከፊት-ለፊታችን ይጠብቁናል፡፡ ሁለቱም ለነዋሪዎቻቸው ዘላለማዊ ቤት ናቸው፡፡ ዛሬ በዚህ ምድር ፈጣሪ አምላኩን አላህን እየተገዛ፡ በሱ አምልኮ ላይ ማንንም ሳያጋራ የሞተ ባሪያ ወደ ጀነት ሲገባ፡ ከዚህ ውጭ ያለው ሁሉ ለእሳት ይዳረጋል፡፡ ከሁለት አንዱን መርጠን እንድንጓዝ ግን ፈተናውና ነጻ ፈቃዱ በዚህ ምድር ላይ ሆነ፡፡
ሐ. አላህ በዚህ ምድር ላይ ፈተናን ሳያዘጋጅ በሁሉን ዐዋቂነቱ ብቻ ፍርድን ላዘጋጅ ቢል ይችላል፡፡ ፍርዱም ፍትሀዊ ነው፡፡ ሰው ግን ይህን ለመቀበል እምቢተኛ ነው፡፡ የተበዳይነት ስሜት ይሰማዋል፡፡ መች ተሞከርኩኝና! ይላል፡፡ ቁርኣን ይህን እውነት እንዲህ ያብራራዋል፡-
‹‹እኛም ከርሱ (ከሙሐመድ መላክ) በፊት በቅጣት ባጠፋናቸው ኖሮ፦ ጌታችን ሆይ! ከመዋረዳችንና ከማፈራችን በፊት አንቀጾችህን እንከተል ዘንድ ወደኛ መልክተኛን አትልክም ነበርን? ባሉ ነበር።›› (ሱረቱ ጣሀ 134)፡፡
አዎ! ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መልክተኛ አድርጎ ከመላኩ በፊት ጣኦታውያንን በጣኦት አምልኮአቸው ሰበብ በቅጣት ቢያጠፋቸው ኖሮ የሚያቀርቡት ከንቱ ምክንያት፡- ይህ የጣኦት አምልኮ አንተ ዘንድ የተጠላ መሆኑን ባለማወቃችን ነው! የሚያብራራልንም መልክተኛ ስላላክልን ነው እንጂ የአንተን ፈቃድ ለመጣስ ፈልገን አይደለም ይላሉ፡፡
አላህም ሰዎች ለክህደታቸውና ለአመጻቸው ነጌ በጌታቸው ፊት ቀርበው ሲጠየቁ ምንም ምክንያት እንዳይኖራቸው ገና ከወዲሁ በምድር ላይ በተለያየ ዘመንና በተለያየ ስፍራዎች ነቢያትን ከመሀከላቸው መርጦ ላከ፣ መለኮታዊ መጽሐፍትንም አወረደ፣ ማስረጃዎቹንም በባሪያዎቹ ላይ አቆመ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰው ማስረጃው ደርሶት ለጥፋቱ ምክንያት አይኖረውም ማለት ነው፡፡
‹‹ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች የሆኑን መልክተኞች፣ (ላክን)፤ አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።›› (ሱረቱ-ኒሳእ 165)፡፡
መ. ባርነትን በተግባር ለማሳየት፡- ሌላው የመፈተናችን ሚስጥር ነው፡፡ አላህ ሰዎችን በዚህ ምድር ላይ ኃላፊነትን አሸክሟቸው ነው ያኖራቸው፡፡ ትክክለኛ የእርሱ ባሪያ መሆናቸውን በፈቃዳቸው እንዲያረጋግጡ ይፈልጋል፡፡ እውነተኛ የአላህ ባርነት ደግሞ የሚረጋገጠው በፈተና በኩል ሲያልፍ ነው፡፡ ማንኛውንም አምላካዊ ትእዛዛት ለመፈጸም የተወሰነ መስዋእትነት ካልተከፈለ በስተቀር አለመቻሉ ለዚህ ትልቅ አስረጂ ነው፡፡
ምድራዊ ህይወት ከፈተና የጸዳች ከሆነ፡ መከራና ችግር፡ ስቃይና እንግልት ከሌለባት፡ የአምልኮ ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው?
ጌታ አላህ ባሪያውን፡ ካለው ንብረቱ ለተቸገሩ ሰዎች እንዲለግስ እና እንዲሰጥ አዝዞታል፡፡ በዛው ተቃራኒ ራስ-ወዳድነትንና ስስታምነትን ስሜቱ ላይ አስቀምጦበታል፡፡
እንዲሁም በአላህ መንገድ የሐቅና የኢስላም ጠላቶችን እንዲፋለማቸው አዘዘው፡፡ ህይወትን ግን ወዳድ ሆኖ ተፈጠረ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው ሰው ሳይፈተን እና ሳይሞከር በፍጹም እንደማያልፍ ነው፡-
“ሰዎቹ አምነናል በማለታቸው ብቻ እነሱ ሳይፈተኑ የሚትተዉ መሆናቸውን ጠረጠሩን? እነዚያንም ከነሱ በፊት የነበሩትን በእርግጥ ፈትነናል፤ እነዚያንም እውነት የተናገሩትን አላህ በእርግጥ ያውቃል፤ ውሸታሞችንም ያውቃል።” (ሱረቱል ዐንከቡት 2-3)፡፡
ሠ. ለተውበት ለማዘጋጀት፡- እንዲሁም ሌላኛው የፈተና ዓላማ፡ ለከሀዲያንና ለአመጸኞች የተውበት በርን ለመክፈት ያመች ዘንድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ መከራና ስቃይ የመጣብን በኃጢአታችን ሰበብ ነው! በማለት በፍጥነት ወደ ጌታቸው ምህረት ይቻኮሉ ዘንድም ለመርዳት ነው፡፡
ረ. የአማኞችን ደረጃ ከፍ ለማድረግ፡- በአላህ ያመኑ ሙስሊሞችን ከኃጢአት ለማንጻት፡ ደረጃቸውንም ከፍ ለማድረግ ያግዛቸዋል፡፡
በሐዲሥ ላይ እንደተገለጸው፡- “ሙስሊምን ድካም፣ በሽታ፣ ሀሳብ፣ ጭንቀት፣ መከራ፣ የእሾህ ውጋት እንኳ አይነካውም፡፡ አላህ በነሱ ሰበብ ኃጢአቱን የደመሰሰለት ቢሆን እንጂ” (ቡኻሪይ 5641፣ ሙስሊም 2573)፡፡
6ኛ. አሁንም ፈተና የፈታኝን ቀድሞ አለማወቅ ይገልጻል በሚለው አቋማችሁ ግትር ካላችሁ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዴት ልትፈቱት ነው፡-
‹‹ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ። የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።›› (ኦሪት ዘፍጥረት ምእ 22፡ ቁ 1-2)፡፡
እግዚአብሄር አብርሀምን ልጅህን ለእኔ ብለህ እረድ! ብሎ ሲፈትነው አብርሀም ታዛዥ ይሁን አይሁን አላወቀም ነበር ማለት ነው? ያውቃል ካላችሁ ለምን ፈተነው ታዲያ? ነገሩ በጣም የሚገርመው እግዚአብሄር አብርሀም ታዛዥ መሆኑን ያወቀው ልጁን ሊያርድ ቢላዋ ሲያነሳ እንደሆነ መጽሐፉ መናገሩ ነው፡-
‹‹አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤ እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ #አሁን አውቄአለሁ አለ።›› (ኦሪት ዘፍጥረት 22፡ 10-12)፡፡
የያእቆብን መልክት በመጥቀስ ‹እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም› የምትሉን ወገኖች! ኢየሱስ በሰይጣን የተፈተነው እሱ እግዚአብሄር ስላልነበረ ነው ማለት ነው?
አላህ ወደሱ ከሚመሩት መልካም ባሮቹ ያድርገን።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


