የሕያ ኢብኑ ኑህ
“ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቷል” የሚለውን ቃል እየደጋገመ እንደሚፎክር ሰባኪ የሚያሳዝነኝ ሰው የለም። ግለሰቡ የዚህ እምነቱ “ድንቅነት” ያስገረመበት ምክንያት ኢየሱስን አስመልክቶ ያለው ምልከታ በጥርጣሬ ወጀብ የተመታ ስለሆነ ነው። ከመነሻው ፈጣሪ ሞት የሚባለውንና እራሱ የፈጠረውን ነገር ማሸነፉ ምኑ ነው እንደ ትልቅ ጀብድ የእድሜ ልክ የሰበካ ርዕስ የሚሆነው? ምናልባት በሰባኪው ልቦና ውስጥ የኢየሱስ ቦታ የተደናገረ ደረጃ ካለው (ፍጡር ወይንስ ፈጣሪ የሚለው) ክስተቱን ቢያገዝፈው አይደንቅም። አንድ ፍጡር ሞትን ድል አድርጎ ቢነሳ የምርም ይገርማል፤ በዚህ መሀል በጥርጣሬ ለሚዋልል ሰው የኢየሱስን ከሞት መነሳትን ማመን እንደ ትልቅ ነገር ቢመለከተው አይገርምም። በዚህ ሰው እምነት ውስጥ ግን ኢየሱስ በትክክልም ከቃል በዘለለ ልቦናው ላይ አምላክነቱ ታምኖ እንዳልተቀመጠለት በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።
…..
አንድ ተጨማሪ ነገር
…
የኢየሱስ ሞትን ድል ማድረጉ ትልቅ የክርስትና ስኬት ተደርጎ በጳውሎስ መጠቀሱም አስገራሚው ክፍል ነው። ጳውሎስ ኢየሱስ ባይነሳ ኑሮ ክርስትና ከንቱ እንደነበር እንዲህ ይነግረናል፦
.
“ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው።”
— 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥14 (አዲሱ መ.ት)
.
አስቡት አንድ አምላክ እንደሞተ ቢቀር ቅድሚያ ሊያስጨንቅ የሚገባው የዚህ አጽናፈ አለም ህልውና ነው ወይንስ ከህልውናው ቀጥሎ የሚመጣው ሰበካ ነው? ክርስትና በምናብ አለም ባዶ ነገር ላይ አይሰበክም፤ ክርስትና ለሰው ልጅ ይሰበክ ዘንድ የሚሰበክበት ምድርና የሚሰበክለት የሰው ልጅ ሊኖር ይገባል። የሚያስተናብረው አምላክ ከሌለ ደግሞ የሰውን ልጅ ጨምሮ አጽናፈ አለሙ አይኖርም። ታዲያ ጳውሎስ ስለየትኛው ስብከቱ ከንቱነት ነው የሚያወራው? ነው ወይንስ እንደ ጳውሎስ እሳቤ መሠረት ኢየሱስ ሀያሉ አምላክ ነው የሚለውን የስላሴ አማኞች አስተምህሮ አይቀበልም?
.
ጳውሎስ የዘነጋው ነገር ቢኖር ግን የኢየሱስ ትንሳኤው ሳይሆን ስቅለቱ ነበር ዋጋ ቢሱ..! ኢየሱስ ሊሞትለት የሚገባ ጉዳይ ፈጽሞ አልነበረውም። ምናልባት አይሁዶች እንደሚገድሉት በማወቁ ተጨንቆ እያለቀሰ አምላኩን እንዲያድነው ለምኗል፤ ከዚያ በተረፈ የሚሞትለት ሌላ አላማ አልነበረውም። በሶስተኛው ቀን እንደሚነሳ እያወቀ በተከታዮቹ ላይ ተራ ድራማ መስራትም አይጠበቅበትም። ስቅለቱ ከመነሻው አላስፈላጊና ዋጋ ቢስ ነበር፤ አልሐምዱሊላህ አሏህ ﷻ ከግድያቸው አድኖታል፤ ባይሆንና ቢገደል ኑሮ እንኳን ከሱ በፊት የነበሩ ነብያትን እንደገደሉት ሁሉ የሱም ሞት ሌላ ትርጉም የሌለው የአይሁዳውያን ግድያ ይሆን ነበር። በርግጥም ግን ያዳነው አሏህ አሸናፊና ጥበበኛ ነው።


