የሕያ ኢብኑ ኑህ
አላህ (ሱ.ወ) አደምን አስቀምጦበት የነበረውንና ከእሷም እንዲወጣ ያደረገባቸውን ጀነት በተመለከተ ዑለሞች (ሙስሊም ምሁራን) የተለያየ አቋም አላቸው፡፡ በሰማያት ኣለም ነች ወይንስ በዚህች ምድር ላይ?
ተቀባይነት ያለው ሀሳብ ግን ይች በቁርዓን የተወሳችውና አደም ተቀምጠውባት የነበረችው ጀነት በምድር ላይ ነበረች የሚለው ነው፡፡
ምክንያም አላህ (ሱ.ወ) አደምን የፈጠረው መሬት ላይ ሲሆን ይህንኑ ‹‹እኔ ምድር ላይ ተተኪ ላደርግ ነው›› የሚለው ቃሉ ይደግፈዋል፡፡
ወደ ሰማይ ወሰድሁት ወይንም አነሳሁት የሚል ቃል አልተናገረም፡፡
እንዲሁም አላህ (ሱ.ወ) ለባሮቹ ያዘጋጃትን የሰማያት አለም ጀነት ‹‹ጀነተል ኹልድ›› የሚል ስያሜ ሰጥቷታል፡፡ ትርጉሙም ዘላለማዊ መኖሪያ ማለት ነው፡፡ አደም የነበሩባት ይህችኛዋ ጀነት ብትሆን ኖሮ ኢብሊስ ለአደም ‹‹ በመዘውተሪያ (የበላት ሁልጊዜ ህያው የሚሆንባት) ዛፍ በማይጠፋ ንግስናም ላመላክትህን›› አይላቸውም ነበር፡፡
ጀነተል ኹልድ የመቀማጠያ ዓለም(አገር) እንጅ የአላህ ባሮች የሚገደዱባት (የሚሰሩባት) አይደለችም፡፡ አላህ (ሱ.ወ) አደምና ሀዋ የዛችን ዛፍ ፍሬ እንዳይቀምሱ ግዴታ ጥሎባቸዋል፡፡
በተጨማሪም አላህ (ሱ.ወ) በሰማያት ዓለም የምትገኘውን ጀነት ጀነተል ኹልድና የሚገቡባትን ባሮቹን አውስቷል
‹‹እነሱ ከሷ ወጭዎች አይደሉም›› ፣ ‹‹እነዚያ የጸደቁትማ በጀነት ዘላለማዊ ሕይወት ውስጥ ናቸው››፡፡ በሌላ ቦታ አደምና ሀዋ ከነበሩበት ጀነት እንዲወጡ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ እነሱ የነበሩበት ጀነት አላህ (ሱ.ወ) የትንሳዔ ቀን መልካም የሱ ባሮች የእንዲገቡባት ያዘጋጀላቸው ጀነት አለመሆኗ ግልጽ ይሆናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኢብሊስ ለአደም አልሰግድም ባለ ጊዜ ተረግሞ ከጀነት ተባረረ፡፡ እሱ የነበረበት ጀነት ‹‹ኹሉድ›› ብትሆን ኖሮ ከወረደበት የአላህ ቁጣ ጋር ሆኖ ጀነተል-ኹልድ ለመግባትና አደምና ሀዋን ለማሳሳት ችሎት አይኖርም ነበር፡፡
ከላይ በተመከትነው መሰረት አደም ተቀምጠውበት የነበረው ጀነት አላህ (ሱ.ወ) ለመልካም ሰሪ ባሮቹ በሰማያት ዓለም ያዘጋጀላቸው ‹‹ኹልድ›› አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ አላህ (ሱ.ወ) አደምን አስቀምጦባት የነበረችው ጀነት ከምድር ገጽታ በላይ ሆና በዛፎች፣ በፍራፍሬ፣ በጥላዎችና በልዩ ልዩ መልካም ነገሮች ያሸበረቀች ልትሆን ትችላለች፡፡ አላህም (ሱ.ወ) ሲያወሳት፡-
إِنَّ لَكَ أَلَّا تَجُوعَ فِيهَا وَلَا تَعْرَىٰ [٢٠:١١٨]
‹‹ለአንተ በእርሷ ውስጥ አለመራብና አለመታረዝ አለህ፡፡›› 20፡118
የዚህም ትርጉም፡- በሷ ውስጥ ስትኖር አይርብህም፣ አይጠማህም፣ የልብስ እርዛት የለብህም፣ ውስጥህ በጥማት አይቃጠልም፣ ውጫዊ አካልህን የጸሀይ ሀሩር አይነካውም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አደምና ሀዋ የዛፊቱን ፍሬ በቀመሱ ጊዜ የጥመት፣ የልፋት የመከራና የፈተና ሥፍራ ወደ ሆነች ምድር ወረዱ (ተዛወሩ)፡፡
አደምና ሀዋ የነበሩት በጀነተል ኹልድ ነው ምክንያቱም አላህ (ሱ.ወ) ‹‹ሁላችሁም ውረዱ›› ብሏቸዋል የሚል ማስረጃ በማቅረብ የሚከራከር ሰው ቢኖር መልሱ መውረድ ማለት ከላይ ወደ ታች ወይንም ከከፍተኛ ወደ ዝቅተኛ ቦታ ቅልቅል መውረድ ማለት ብቻ አይደሉም፡፡ በዐረብኛ ቋንቋ አጠቃቀም ሥርአት መሰረት መውረድ ማለት ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው መንቀሳቀስ ማለትም ይሆናል የሚል ነው፡፡
ለምሳሌ፡- አላህ (ሱ.ወ) ፡‹‹ ምስር (ግብጽ) ውረዱና ለናንተ የጠየቃችሁት አለላችሁ›› ያለውን ቃል ብንወስድ ይህንን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን የሚያሳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ነብዩ ኑህን ከመርከቧ እንዲወጡ ትእዛዝ ሲሰጣቸው፡-
قِيلَ يَا نُوحُ اهْبِطْ بِسَلَامٍ مِّنَّا وَبَرَكَاتٍ عَلَيْكَ وَعَلَىٰ أُمَمٍ مِّمَّن مَّعَكَ ۚ وَأُمَمٌ سَنُمَتِّعُهُمْ ثُمَّ يَمَسُّهُم مِّنَّا عَذَابٌ أَلِيمٌ [١١:٤٨]
«ኑሕ ሆይ! ከእኛ በሆነ ሰላም ባንተ ላይና አንተም ጋር ባሉት ሕዝቦች (ትውልድ) ላይ በሆኑ በረከቶችም የተጎናጸፍክ ሆነህ ውረድ፡፡ (ከእነሱው ዘሮች የሆኑ) ሕዝቦችም በቅርቢቱ ዓለም በእርግጥ እናስመቻቸዋለን፡፡ ከዚያም ከኛ የሆነ አሳማሚ ቅጣት ይነካቸዋል» ተባለ፡፡ ›› 11፡48
ይህ እራሱ መውረድ ማለት ከላይ ወደታች ብቻ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል፡፡
አሏሁ አእለም!!!!!
(ከጥቂት የራሴ አገላለጽ በስተቀር ሙሉውን ጹሁፍ የወሰድኩት ‹‹መዐል አንቢያእ ፊል ቁርአኑል ከሪም›› ከሚለው የዶ/ር ዓፊፍ ዓብዱል ፈታህ መጽሀፍ ሲሆን በወንድም አወል ረታ ከተተረጎመው ገጽ 31 ነው)
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


