በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ፈጣሪ አምላካችን አላህ ሰውንና ጂንኒን እሱን በብቸኝነት እንዲያመልኩት ፈጥሯቸዋል (አዝ-ዛሪያት 56)፡፡ ትክክለኛ አምልኮ ምን እንደሆነ ያብራሩላቸው ዘንድ ከሰዎች መካከል የተወሰኑትን በፈቃዱ መርጦ፡ የመረጣቸውንም ነቢያትና መልክተኛ አድርጎ ወደ ህዝቦቻቸው ልኮአቸዋል፡፡ በነዚህ መልክተኞች በኩል ቃሉንም አውርዷል፡፡ ይህ ወደ ነቢያት የወረደው መለኮታዊ ቃል በጥቅሉ በዐረብኛው ‹ወሕይ› ይሰኛል፡፡
ወሕይ (መለኮታዊ ግልጸት) ወደ ነቢያት ሲመጣ በአንድ አይነት መንገድ አይደለም የመጣው፡፡ የተለያዩ መንገዶች አሉት፡፡ ቅዱስ ቁርኣን፡- ጌታ አላህ ከመረጣቸው ነቢያት ጋር በሶስት አይነት መንገድ ይገናኛቸው እንደነበር እንዲህ በሚለው ቃሉ ያስረዳናል፡-
” وَمَا كَانَ لِبَشَرٍ أَنْ يُكَلِّمَهُ اللَّهُ إِلَّا وَحْيًا أَوْ مِنْ وَرَاءِ حِجَابٍ أَوْ يُرْسِلَ رَسُولًا فَيُوحِيَ بِإِذْنِهِ مَا يَشَاءُ إِنَّهُ عَلِيٌّ حَكِيمٌ ” سورة الشورى 51
“ለሰው አላህ በራእይ፣ ወይም ከግርዶ ወዲያ፣ ወይም መልክተኛን (መልአክን) የሚልክና በፈቃዱ የሚሻውን ነገር የሚያወርድለት ቢሆን እንጅ፣ (በገሃድ) ሊያናግረው ተገቢው አይደለም። እርሱ የበላይ ጥበበኛ ነውና።” (ሱረቱ-ሹራ 51)፡፡
ዛሬ የምንነጋገረው ከነዚህ የአላህ ነቢያትና መልክተኞች፡ የመጨረሻውና መደምደሚያው (አል-አሕዛብ 40) ስለሆኑት ነቢይ፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይሆናል፡፡ አንዳንድ አላዋቂዎች ወደሳቸው ይመጣ የነበረውን የወሕይ መገለጥ በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ጥያቄ ስለፈጠረባቸው፡ መልስ ለመስጠትና እነሱንም ሐቁን እንዲረዱ ለማገዝ፡ በነሱ ምክንያትም ጥርጣሬ የሚገባው ሰው ወደ እርግጠኝነት ይመለስ ዘንድ ለመርዳት ነው፡፡ ነገራት ሁሉ በአላህ ፈቃድ ገር ይሆናሉ ኢንሻአላህ፡፡
ጥያቄ ሆኖ የተነሳው በቀጣዩ ሐዲሥ ላይ የሰፈረው ቃል ነው፡-
عَنْ عَائِشَةَ أُمِّ الْمُؤْمِنِينَ رَضِي اللَّهُ عَنْهَا: أَنَّ الْحَارِثَ بْنَ هِشَامٍ رَضِي اللَّهُ عَنْهُ سَأَلَ رَسُولَ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم فَقَالَ: يَا رَسُولَ اللَّهِ كَيْفَ يَأْتِيكَ الْوَحْي؟ فَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم: «يَأْتِينِي أَحْيَانًا فِي مِثْلِ صَلْصَلَةِ الْجَرَسِ ـ وَهُوَ أَشَدُّهُ عَلَيَّ ـ فَيُفْصَمُ عَنِّي وَقَدْ وَعَيْتُ مَا قَالَ ، وَأَحْيَانًا يَتَمَثَّلُ لِيَ الْمَلَكُ رَجُلاً فَيُعَلِّمُنِي فَأَعِي مَا يَقُولُ» . قَالَتْ عَائِشَةُ رَضِي اللَّهُ عَنْهَا: وَلَقَدْ رَأَيْتُهُ يَنْزِلُ عَلَيْهِ الْوَحْيُ فِي الْيَوْمِ الشَّدِيدِ الْبَرْدِ فَيُفْصَمُ وَإِنَّ جَبِينَهُ لَيَتَفَصَّدُ عَرَقًا. رواه البخاري ومسلم
የምእመናን እናት እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ሓሪሥ ኢብኑ-ሂሻም የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወሕይ (መለኮታዊ ግልጸት) እንዴት ነው የሚመጣሎት? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- ‹‹አንዳንድ ጊዜ እንደ ደወል ድምጽ አምሳያ ሆኖ ይመጣኛል፡፡ እሱ በኔ ላይ በጣም የሚበረታው ሁኔታ ነው፡፡ ላብም ይወርደኛል፡፡ (መልአኩ) የሚለውንም በልቦናዬ እይዘዋለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መልአኩ በሰው ይመሰልልኛል፡፡ ያስተምረኝና የሚለውንም በልቦናዬ እይዛለሁ››በማለት መለሱለት፡፡ ዓኢሻም (ረዲየላሁ ዐንሃ)፡- ‹‹እጅግ በጣም ብርዳማ በሆነ ወቅት ወሕይ ሲወርድላቸው አየሁኝ፡፡ ግንባራቸው ግን ላብን ሲያንጠባጥብ ነበር›› አለች፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት)፡፡
በዚህ ሐዲሥ ውስጥ ‹‹እንደ ደወል ድምጽ›› የሚለውን ቃል በመምዘዝ ብዥታ ለመፍጠር ሙከራ ተደረገ፡፡ እሱም፡- ‹‹ደወል የሸይጧን መዝሙር ነው›› (ሙስሊም የዘገበው) የሚለውን ሐዲሥ በመጥቀስ፡ ደወል የሸይጧን መዝሙሩ ከሆነ፡ እንዴት ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወሕይ (ራእይ) ሲመጣ በደወል ድምጽ ሊመጣ ቻለ? የሚል ነው፡፡ የኛም ምላሽ እንደሚከተለው ይሆናል፡-
1ኛ. ሐዲሡን በደንብ ላስተዋለ ሰው መልአኩ ጂብሪል ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከሚመጣባቸው መንገዶች አንዱ ‹‹በደወል ድምጽ አምሳያ›› ተብሎ ተገለጸ እንጂ፡ የደወል ድምጽ ወይም ደወል ተብሎ አልተነገረም፡፡ ታዲያ እንዴት የሸይጧን መዝሙር ተብሎ የተወገዘውን ደወል፡ መልአኩ ጂብሪል ከሚገለጽበት የደወል ድምጽ አምሳያ ጋር ማወዳደር ይቻላል?
2ኛ. በሐዲሡ ላይ ‹የሸይጧን መዝሙር› ተብሎ የተወገዘው ደወል እራሱ ሲሆን፡ እዚህ መልአኩ የሚመጣበት መንገድ ግን ‹የደወል ድምጽ አምሳያ› ተብሎ ነው የተጠቀሰው፡፡ ደወል አልተባለም፡፤ ወይም የደወል ድምጽ አልተባም፡፡ ባሌን ከቦሌ ማቀራረቡ ለምን አስፈለገ?
3ኛ. አንድ ወገኔ የጠየቀኝ ጥያቄ፡- ሐዲሡ ላይ ‹የደወል ድምጽ አምሳያ› ይላል እንጂ፡ መልአኩ የሚመጣበት አይልም፡፡ ስለዚህ ልምን የሌለ ትጨምራለህ? የሚል ነበር፡፡ ይህ በራሱ የሚያሳየው የወገኖቻችን ጥያቄ በቅብብሎሽ የመጣ እንጂ፡ ከማንበብ ብዛት የተፈጠረባቸው ጥያቄ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ሙሉውን ሐዲሥ ቢያነቡት ኖሮ መልሱን እዛው ላይ ያገኙት ነበር፡፡ ደግሞም በሌላ የቡኻሪይ ዘገባ ላይ እንዲህ ተብራርቶ ተገልጾአል፡-
عَنْ عَائِشَةَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهَا: أَنَّ الحَارِثَ بْنَ هِشَامٍ سَأَلَ النَّبِيَّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ كَيْفَ يَأْتِيكَ الوَحْيُ؟ قَالَ: «كُلُّ ذَاكَ يَأْتِينِي المَلَكُ أَحْيَانًا فِي مِثْلِ صَلْصَلَةِ الجَرَسِ، فَيَفْصِمُ عَنِّي، وَقَدْ وَعَيْتُ مَا قَالَ، وَهُوَ أَشَدُّهُ عَلَيَّ، وَيَتَمَثَّلُ لِي المَلَكُ أَحْيَانًا رَجُلًا فَيُكَلِّمُنِي، فَأَعِي مَا يَقُولُ» رواه البخاري 3215.
የምእመናን እናት እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ሓሪሥ ኢብኑ-ሂሻም የአላህ መልክተኛን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወሕይ (መለኮታዊ ግልጸት) እንዴት ነው የሚመጣሎት? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)፡- ‹‹አንዳንድ ጊዜ መልአኩ እንደ ደወል ድምጽ አምሳያ ሆኖ ይመጣኛል፡፡ ላብም ይወርደኛል፡፡ መልአኩ ያለውንም በልቦናዬ እይዘዋለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መልአኩ በሰው ይመሰልልኝና ያናግረኛል፡፡ የሚለውንም በልቦናዬ እይዛለሁ›› በማለት መለሱለት፡፡ (ቡኻሪይ 3215)፡፡
ወገኖቻችን እንግሊዘኛውን አንብበው ከተረዱት፡ እውነቱን እንዲያውቁ ለማገዝ እሱንም እንዲህ አስቀምጠንላቸዋል፡-
Narrated Aisha: Al Harith bin Hisham asked the Prophet, “How does the divine inspiration come to you?” He replied, “In all these ways: The Angel sometimes comes to me with a voice which resembles the sound of a ringing bell, and when this state abandons me, I remember what the Angel has said, and this type of Divine Inspiration is the hardest on me; and sometimes the Angel comes to me in the shape of a man and talks to me, and I understand and remember what he says.” sahih al-bukhari volume 4: book 54: number 438.
ወገኖቻችን ሆይ! The Angel sometimes comes to me with a voice which resembles the sound of a ringing bell በሚለው ሐዲሥ ውስጥ ‹በደውል ድምጽ አምሳያ› የተባለው ስለ መልአኩ እንደሆነ አሁንስ ተረዳችሁ? አላህ ልባችሁን ለእውነት ይክፈተው፡፡
4ኛ. ማጠቃለያ፡- ቅዱስ ቁርኣን ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይወርድ የነበረው በዚሁ መልአክ በጂብሪል (ዐለይሂ-ሰላም) አማካኝነት እንደነበር ጌታ አላህ በቃሉ በብዙ ስፍራዎች ነግሮናል፡፡ ይህም በራሱ ‹በደወል ድምጽ አምሳያ› ሆኖ ይመጣ የነበረው መልአኩ ጂብሪል እንደሆነ ዋና ማስረጃ ነው፡፡ ቀጣዮቹን አንቀጾች በጥሞና እናንብባቸው፡-
“ለጂብሪል ጠላት የኾነ ሰው (በቁጭት ይሙት) በላቸው፡፡ እርሱ (ቁርኣኑን) ከበፊቱ ለነበሩት (መጻሕፍት) አረጋጋጭ ለምእመናን መሪና ብስራት ሲኾን በአላህ ፈቃድ በልብህ ላይ አውርዶታልና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 97)፡፡
“እነዚያን ያመኑትን ለማረጋጋት ሙስሊሞቹንም ለመምራትና ለማብሰር (ቁርአንን)፣ ቅዱሱ መንፈስ (ጂብሪል) እውነተኛ ሲሆን ከጌታህ አወረደው በላቸው።” (ሱረቱ-ነሕል 102)፡፡
“እርሱም (ቁርኣን) በእርግጥ ከዓለማት ጌታ የተወረደ ነው፡፡ እርሱን ታማኙ መንፈስ (ጂብሪል) አወረደው” (ሱረቱ-ሹዐራእ 192-193)፡፡
አምላካችን አላህ ሆይ! በኢስላም ላይ ጽናትን፣ በሸሀደተይን ሞትን ለግሰን፡፤ ወገኖቻችንንም ካሉበት ጨለማ ወደ ኢስላም ብርሀን አምጣቸው፡፡ አላሁመ አሚን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


