በኡስታዝ አቡ ሀይደር
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
በክፍል አንድ ትምሕርታችን ላይ ጨረቃ በኢስላም ያለውን ምልከታ በመጠኑ ቃኝተናል፡፡ በውስጡም ጨረቃ የአላህ ፍጥረት መሆኑን፣ በፈቃዱ ስር የተገራ እንደሆነና አምልኮም እንደማይገባው፡ እንዲሁም ለሰዎች የጊዜ ማወቂያ ምልክት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ በመስጂድም ላይ የሙስሊሞችን የአምልኮ ስፍራ ከጣኦታውያን የአምልኮ ስፍራ ለመለየት ምልክት መደረጉን እንጂ፡ ከአምልኮ ጋር ምንም ትስስር እንደሌለው ተመልክተናል፡፡ አልሐምዱ ሊላህ፡፡
ዛሬ የምንመለከተው ደግሞ ‹አላህ› የሚለውን መለኮታዊ ስምና የዓለማቱ ጌታን መጠሪያ ለዚሁ ለጨረቃ በመስጠት፡ ሙስሊሞች የሚያመልኩት የጨረቃን አምላክ ነው፡፡ ስሙም አላህ ተብሎ ይጠራ ነበር (ሱብሐነ ረቢ) የሚለውን ከመሃይምነትና ከጥላቻ የመነጨውን ግልብ ግንዛቤ እንዳስሰዋለን ኢንሻአላህ፡፡
‹‹አላህ›› የሚለው መለኮታዊ ስም!!
ይህ ስም የዓለሙ ፈጣሪና አስገኚ ለሆነው አምላክ የተጸውኦ ስም ነው፡፡ ስለሆነም በሱ አምላክነት ያመኑ ሙስሊሞች በጠቅላላ፡ ቋንቋቸውና ሀገራቸው ቢለያይም፡ አምላካቸው ግን አንድ አምላክ በመሆኑ፡ በዚሁ የተጸውኦ ስሙ ‹‹አላህ›› በማለት ይጠሩታል፡ ይማጸኑታል፡፡ ስሙ ያዘለውና ያቀፈው መልእክት ይብራራል ይገለጻል እንጂ፡ ማብራሪያውና ትርጉሙ ስምን ተክቶ እሱ እንዲጠራበት ግልጋሎት ላይ አይውልም፡፡ ምክንያቱም በቋንቋ ህግ የተጸውኦ ሥም (proper noun) አይተረጎምና!::
አንዳንድ የዋህ ወገኖች፡- ለምን እንደኛ የአምላካችሁን ስም በአማርኛ ተርጉማችሁ አትጠሩትም? ይላሉ፡፡ እኛም፡- የአላህ ስም ከቋንቋ በፊትም የነበረ፡ ሀልዎቱንም (ዛት) የሚጠቁም የግል ስሙ ስለሆነ በትርጉም ልንተካው አንችልም!፡፡ ታዲያ እናንተ በመጽሐፋቹ የተጠቀሰውን ታላቁን የአላህ ነቢይ ኢብራሂም (አብረሃም) ዐለይሂ-ሰላም በአማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ስሙን ‹የብዙኃን አባት› ብላችሁ ለምን አልቀየራችሁትም? የስሙ ትርጉም ያንን አይደል የሚገልጸው? እንላቸዋለን፡፡
አይ! አብረሀም የተጸውኦ ስሙ በመሆኑ ነው ካላችሁን፡ እንግዲያውስ የኢብራሂም ጌታና ፈጣሪ የሆነውን አምላክ፡ አላህ የሚለውን ስሙን ለምን በትርጉም እንዲተካ ፈለጋችሁ? እንላለን፡፡
ይህ ‹አላህ› የሚለው መለኮታዊ ስም ዓለማትና በውስጡ ያለው ነገር ከመፈጠሩና ከመገኘቱ በፊት የነበረ፡ ጥንታዊና መነሻ የሌለው፡ ዘላለማዊና ማብቂያ የሌለው የህላዌ ስሙ ነው፡፡ ጌታችን አላህ ቋንቋ ተፈልጎ አይደለም ስም የሚወጣለት፡፡ ይብላኝላቸው አምላካቸውን በሀገሩና በብሄሩ ስም ፈልገው ለሚሰይሙት!፡፡
ኢማም አቡ-ጃዕፈር አጥ-ጠሃዊይ (227-321 ሒጅ.) ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡-
ما زال بصفاته قديما قبل خلقه لم يزدد بكونهم شيئا لم يكن قبلهم من صفاته وكما كان بصفاته أزليا كذلك لا يزال عليها أبديا ليس بعد خلق الخلق استفاد اسم الخالق ولا بإحداث البرية استفاد اسم الباري. متن ااالعقيدة الطحاوية 10-9
“አላህ ከፍጡራኑ በፊት ከመለኮታዊ ባሕሪቶቹ አልተወገደም፡፡ ፍጥረታቱንም በማስገኘቱ፡ ከነሱ በፊት ያልነበረውና አሁን የጨመረው አዲስ የሆነ ባሕሪም የለውም፡፡ አላህ በባሕሪያቱ ጥንታዊ እንደሆነው ሁሉ፡ አሁንም በነዚሁ ባሕሪያት ዘላለማዊ ነው፡፡ ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ አይደለም ‹‹ፈጣሪ› የሚለውን ስም ያገኘው፡፡ ያልነበረውን ዓለም ካስገኘ በኋላ አይደለም ‹አስገኚ› የሚል ሥምን የተጎናጸፈው”(አል-ዐቂደቱ ጠሓዊየህ 9-10)፡፡
ከዚህ ታላቅ የኢሥላም ሊቅ የምንወስደው ትምሕርት፡ የአላህ ስሞችና ባሕሪት ከጊዜ በኋላ የሚመጡ፡ ከነገሮች መከሰት በኋላ የሚወጡ ሳይሆኑ፡ ጥንቱኑ ከሱ ጋር ያሉ የባሕሪ ስሞቹ መሆናቸውን ነው፡፡
አላህ የሚለው ስም፡ መሰረቱ ‹‹አል›› እና ‹‹ኢላህ›› ነበር ማለት፡ ከዛ የተገኘና የተፈጠረ ነው ማለት አይደለም፡፡ አል-ኢላህ ከሚለው ቃል ጋር በቃልም ሆነ በመልእክት ስምም ነው፡ አንድ ነው ለማለት እንጂ!፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ኢማም ኢብኑል-ቀዪም (691-751 ሒጅ.) ረሒመሁላህ እንዲህ ይላሉ፡-
ونحن لا نعني بالاشتقاق إلا أنها ملاقية لمصادرها في اللفظ والمعنى ، لا أنها متولدة منه تولد الفرع من أصله . كتاب: بدائع الفوائد 32.
“አላህ የሚለው መለኮታዊ ስም አል-ኢላህ ከሚለው ቃል የወጣ (የተራባ) ነው ማለታችን፡ ከቃሉ መሰረት (ስርወ-ግንድ) ጋር በመልክትም በቃልም ይስማማሉ፡ ይገናኛሉ ማለታችን እንጂ፡ አል-ኢላህ ከሚለው ዐረብኛ ቃል የተፈበረከና የተገኘ ነው ማለታችን አይደለም፡፡” (ኪታብ፡ በዳኢዑል-ፈዋኢድ 32)፡፡
ታዲያ ይህን መለኮታዊ ስም የጨረቃ ስም ማድረግን የቋመጡ የኩፍር አካላት ዐረቦች ለሚያመልኩት የጨረቃ አምላክ የሚሰጡት ስም ነበር ይሉናል፡፡ የኛም ምላሽ እንደሚከተለው ይሆናል፡-
1ኛ. ይህንኑ ጥያቄ በወቅቱ ለነበሩ ሙሽሪኩል-ዐረብ (ዐረብ ጣኦታውያን) እንዲህ ብለን እናቅርብላቸው፡፡ እውነት እናንተ ‹‹አላህ›› በሚል ስም የሚጠራ የጨረቃ አምላክ ታመልኩ ነበራችሁን? የነሱም ምላሽ እንዲህ የሚል ይሆናል፡-
“ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ፀሐይንና ጨረቃንም የገራ ማን እንደሆነ ብትጠይቃቸው በእርግጥ አላህ ነው ይሉሃል፤ ታዲያ እንዴት ይመለሳሉ!።” (ሱረቱል ዐንከቡት 61)፡፡
ጌታ አላህ በዚህ አንቀጽ ውስጥ በወቅቱ ስለነበሩት ሙሽሪኮች እየነገረን ነው፡፡ እነዚህ አጋሪዎች የሰማያትና የምድር እንዲሁም የፀሐይና የጨረቃ ፈጣሪ ማነው? ብለህ ብትጠይቃቸው፡ የነሱም ምላሽ፡- አላህ የሚል ይሆናል፡፡ አያችሁ ወንድሞችና እህቶች! ፈጣሪ የሆነውን አላህ ከተፈጠረው ጨረቃ እንዴት ለይተው እንዳስቀመጡ? እውነት ‹‹አላህ›› የሚለውን የፈጣሪ ስም ለጨረቃ አምላክ የሰጡ ቢሆን ኖሮ፡ ይህን መልስ ይመልሱ ነበርን? አላህን ፈጣሪ፡ ጨረቃንና ፀሐይን ተፈጣሪ ያደርጉ ነበርን? እናንተ ከየት አምጥታችሁ ነው እነዚህ ዐረቦች ‹‹አላህ›› የሚባል የጨረቃ አምላክን ያመልኩ ነበር የምትሉት?
“ለነሱም ለአባቶቻቸውም በርሱ ምንም ዕውቀት የላቸውም፤ ከአፎቻቸው የምትወጣውን ቃል ምን አከበዳት! ውሸትን እንጂ አይናገሩም።” (ሱረቱል ከህፍ 5)፡፡
2ኛ. ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከአላህ ዘንድ ነቢይና መልክተኛ ሆነው ተመርጠው ሲላኩ፡ ዋና ተልእኳቸው ምን ነበር? ይህንኑ የጣኦት አምልኮ መቃወም አልነበረም እንዴ? ቀድሞ ነገር አንድ መልክተኛ ከአላህ ዘንድ ወደ ህዝቦቹ ሲላክ፡ አላህን በብቸኝነት እንዲያመልኩ ማስተማርና፡ ከአላህ ውጪ ያለው አምልኮ በጠቅላላ ጣኦት ስለሆነ፡ ጣኦታትን ከማምለክ ተቆጠቡ ብሎ ሊያስተምር አይደለምን?
“በየሕዝቡም ሁሉ አውስጥ አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ፤ በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል…” (ሱረቱ-ነሕል 36)፡፡
የአላህ መልክተኛም ይህንኑ የነቢያትን ፈለግ ተከትለው፡ ማኃበረሰቡን ከጣኦት አምልኮ እንዲወጣና፡ አንዱንና እውነተኛውን አምላክ አላህን እንዲያመልክ ጥርሪ ሲያቀርቡለት፡ በስድብ የታጀበ ምላሽ ነበር የገጠማቸው፡-
“እነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ በነሩ። እኛ ለዕብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተዉ ነን? ይሉም ነበር።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 35-36)፡፡
እንግዲያውስ የአላህ ነቢይም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ስብከታቸው ወደ ጣኦት አምልኮ ከነበረ (ሓሻ ሊላሂ ወሊረሱሊሂ) ከጣኦት አምላኪው ማኃበረሰቡ ጋር ምን አጣላቸው ታዲያ? ከሚወዱት የትውልድ ሀገራቸው ተሰዶ መዲና እስከ መግባት ምን አደረሳቸው? ሰዎች ነቃ እንበል እንጂ!
3ኛ. የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት እያወቁ በህዝቦቻቸው ፍርሀትና ምድራዊ ጥቅም ታውረው ካልሰሙ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ውስጥ፡ በዚህ መለኮታዊ ስም እራሱን አስጠግቶ የሚጠራ ሰው መኖሩ በራሱ ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡ የሳቸውን ነቢይነት በሚገባ እያወቀ ካልሰለሙት መካከልም፡- ዐብዱላህ ኢብኑ ሱሪያ አንዱ ነው፡፡ ታዲያ ‹አላህ› የሚለው፡ ካፊሮች ዛሬ እንደሚያወሩት የአምላክ ስም ካልነበር፡ እንዴት እነዚህ አይሁዳውያኖች ስማቸውን ወደዚህ ስም አስጠግተው፡ እራሳቸውን የአላህ ባሪያ ‹ዐብዱላህ› ብለው መጥራት ፈለጉ? ወይንስ አይሁዶቹም ጣኦት አምላኪዎች ነበሩ?
4ኛ. መጽሐፍ ቅዱስ ከተተሮገመባቸው ቋንቋዎች መካከል አንዱ ዐረብኛ ቋንቋ ነው፡፡ በዐረብኛው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ ስም ‹‹አላህ›› ሁኖ ለ2246 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ታዲያ የዐረብኛው መጽሐፍ ቅዱስ እየሰበከ ያለው ጣኦትን ነው እያላችሁን ነውን? መቼም የክርስቲያን ዐረቦች ዐረብኛ፡ ከሙስሊም ዐረቦች ዐረብኛ የተለየ ነው! ብላችሁ እንደማታስቁን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
5ኛ. በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም! ነውና ነገሩ፡ የዓለም ሙስሊሞች አምላካችን ብለው የሚያመልኩትን አላህ የእውነተኛው አምላክ ስም አይደለም ካላችሁን፡ እስኪ ወደናንተ እንምጣና ደግሞ በተራችን እንጠይቃችሁ፡፡ እውን እግዚአብሄር የአምላክ ስም ነውን?
ከሁሉ በፊት ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር ‹እግዚአብሄር› በሚለው ስም ፈጣሪን የሰበከና ያስተዋወቀ አንድም ነቢይ የለም፡፡ በዚህ ስም የወረደ አንድም መለኮታዊ መጽሐፍ የለም፡፡
ይህ ስም ግዕዝ ወለድ የሆነ ስም ነው፡፡ ‹እግዚእ› እና ‹ብሄር› ከሚሉ ሁለት የግእዝ ቃላት እንደተገኘና እንደተዋቀረ በ1996 ለ6ተኛ ጊዜ የታተመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይገልጻል፡፡ ትርጉሙንም አያይዞ ሲፈታው፡- ‹እግዚእ› ማለት ‹ገዢ› ሲሆን፡ ‹ብሄር› ማለት ደግሞ ‹ህዝብ› ማለት ነው ይላል፡፡ አንድ ላይ ምን ሊሆን እንደሚችል ገምቱ፡፡
ለዚህም ነው ይህ ስም ‹እግዚአብሄር› አምላካዊ ስላልሆነ፡ ከኢትዮጵያ ውጪ በየትኛውም የአለማችን ክፍል በሚኖሩ ህዝቦች ዘንድ የማይታወቀው፡፡ ከአማርኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ውጪ ያሉት፡ በሌላ ሀገር ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች አያውቁትም፡፡
በዚህ ስም ኢትዮጵያዊው ክርስቲያን ከሌላ ሀገር መሰል ክርስቲያን ወገኑ ጋር መግባባትና ሰላምታ መለዋወጥ አይችልም፡፡ በዚህ ስም የጋራ ጸሎት ሊያደርጉበትም አይችሉም፡፡ እውነት ይህ ስም የእውነተኛው አምላክ አላህ ስም ቢሆን ኖሮ፡ ከነቢያት እንኳ አንድም የሚያውቀው ይጠፋ ነበር? ወይንስ ለኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ብቻ የተገለጸ ስም ነው?
አንዳንድ የዋሆች በመጽሐፋቸው ላይ በአማርኛ የተተረጎመውን ይዘው፡ ይኸው ለነቢያት እራሱን ‹‹እግዚአብሄር›› ነኝ ብሎ አስተዋውቋል ይሉናል፡፡ እውነት እናንተ እንደምትሉት ይህ ስም ከጥንትም ነቢያትን ያስተዋወቀበት ስሙ ከነበር፡ ለምንድነው በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ የማናየው? ደግሞስ መጽሐፋችሁ እንደሚያስተምረው ነቢያት በጠቅላላ ከእስራኤል አይደለም እንዴ የተነሱት? ታዲያ ግእዝ ወለድ የሆነው ስም እዛ ምን ከተተው?
ለምን አሳ ጎርጓሪ መሆንን ፈለጋችሁ? የሰውን ነውር ለመፈለግ ስትነሱ ቅድሚያ የራሳችሁን ማጥራታችሁን በደንብ አስተውሉ፡፡ ጨርሻለሁ
“እርሱ እውነተኛ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእውነትም በኋላ ጥመት እንጂ ሌላ ምን አለ (ከውነት) እንዴት ትዞራላችሁ” (ሱረቱ ዩኑስ 32)፡፡
“ይህ አላህ እርሱ እውነት በመሆኑ ከርሱም ሌላ የሚገዙት ነገር እርሱ ፍጹም ውሽት በመሆኑ አላህም እርሱ የሁሉ በላይ ታላቅ በመሆኑ ነው።” (ሱረቱል-ሐጅ 62)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


