በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡
ሀሰት ሲደጋገም እውነት ይመስላል እንዲሉ ሆነና፡ ከሰብአዊ ፍጡርነትና ከነቢይነት ውጪ ምንም ድርሻ የሌለውን የመርየምን ልጅ ዒሳን (የአላህ ሰላም በሁለቱም ላይ ይሁን) አምላክና ፈጣሪ ለማድረግ የቅጥፈት ዘመቻዎች በየአቅጣጫው እየተደጋገሙ ነው፡፡ ከነዛም ውስጥ አንዱ፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ወፍን ፈጥሯል የሚለው ተረት ተረት ነው፡፡ እንኳን ወፍን ሊፈጥር ይቅርና ፍጥረተ ዓለሙ እራሱ ቢተባበረውና ቢያግዘው: ዝንብን እንኳ መፍጠር አይችልም!!፡፡ ይህ የጌታችን ቃል ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
” يَا أَيُّهَا النَّاسُ ضُرِبَ مَثَلٌ فَاسْتَمِعُوا لَهُ إِنَّ الَّذِينَ تَدْعُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ لَنْ يَخْلُقُوا ذُبَابًا وَلَوِ اجْتَمَعُوا لَهُ وَإِنْ يَسْلُبْهُمُ الذُّبَابُ شَيْئًا لَا يَسْتَنْقِذُوهُ مِنْهُ ضَعُفَ الطَّالِبُ وَالْمَطْلُوبُ * مَا قَدَرُوا اللَّهَ حَقَّ قَدْرِهِ إِنَّ اللَّهَ لَقَوِيٌّ عَزِيزٌ ” سورة الحج 74-73
“እላንተ ሰዎች ሆይ! አስደናቂ ምስሌ ተገለጸላችሁ ለእርሱም አድምጡት፤ እነዚያ ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸው (ጣዖታት) ዝምብን ፈጽሞ አይፈጥሩም፤ ለርሱ (ለመፍጠር) ቢሰበስቡም እንኳ (አይችሉም)፡፡ አንዳችንም ነገር ዝንቡ ቢነጥቃቸው ከርሱ አያስጥሉትም ፈላጊውም ተፈላጊውም ደከሙ (ደካሞች ናቸው)። አላህን ተገቢ ክብሩን አላከበሩትም፡፡ አላህ በጣም ኃያል አሸናፊ ነው፡፡” (ሱረቱል ሐጅ 22፡73-74)፡፡
እንዲያውስ ከምን ተነስተው ነው ዒሳን ወፍ እንደፈጠረ ለማሳመን የሚጥሩት? ከተባለም፡ ቀጣዩን ማስረጃ ይሆነናል ያሉትን ጥቅስ እናቅርበውና ምላሹን አብረን እንከታተል፡-
“وَرَسُولًا إِلَى بَنِي إِسْرَائِيلَ أَنِّي قَدْ جِئْتُكُمْ بِآيَةٍ مِنْ رَبِّكُمْ أَنِّي أَخْلُقُ لَكُمْ مِنَ الطِّينِ كَهَيْئَةِ الطَّيْرِ فَأَنْفُخُ فِيهِ فَيَكُونُ طَيْرًا بِإِذْنِ اللَّهِ وَأُبْرِئُ الْأَكْمَهَ وَالْأَبْرَصَ وَأُحْيِ الْمَوْتَى بِإِذْنِ اللَّهِ وَأُنَبِّئُكُمْ بِمَا تَأْكُلُونَ وَمَا تَدَّخِرُونَ فِي بُيُوتِكُمْ إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآيَةً لَكُمْ إِنْ كُنْتُمْ مُؤْمِنِينَ ” سورة آل عمران 49
“ወደ እሥራኤልም ልጆች መልክተኛ ያደርገዋል፤ (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፥ ለምጸኛንም፥ አድናለሁ፤ ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡49)፡፡
በዚህ የቁርኣን ክፍል ላይ ‹‹እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል።›› የሚለውን ኃይለ-ቃል በመምዘዝ ነው እንግዲህ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሕይወትን ፈጥሯል የሚሉን!፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ የኛም ምላሽ በመጠኑ እንዲህ ይቀርባል፡-
1ኛ/ የአላህ ቃል የኾነው ቅዱስ ቁርኣን እንደሚያስተምረው፡ የተፈጥሮ ስርዓትም እንደሚመሰክረው፡ አላህ ብቻውን የዓለማት ፈጣሪና አስገኚ ነው፡፡ ‹ነገር› የተባለን በጠቅላላ የፈጠረው እሱ ነው፡፡ ከአላህ ሌላ ፈጣሪና አስገኚ ማንም አልነበረም፣ የለም፣ አይኖርምም!፡፡ ስለዚህም እሱ አላህ የነገራት ኹሉ ፈጣሪ ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” ذَلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ فَاعْبُدُوهُ وَهُوَ عَلَى كُلِّ شَيْءٍ وَكِيلٌ ” سورة الأنعام 102
“ይህ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ #ነገርን ሁሉ ፈጣሪ ነው፡፡ ስለዚህ ተገዙት፡፡ እርሱም በነገሩ ሁሉ ላይ ተጠባባቂ ነው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡102)፡፡
” قُلْ مَنْ رَبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ قُلِ اللَّهُ قُلْ أَفَاتَّخَذْتُمْ مِنْ دُونِهِ أَوْلِيَاءَ لَا يَمْلِكُونَ لِأَنْفُسِهِمْ نَفْعًا وَلَا ضَرًّا قُلْ هَلْ يَسْتَوِي الْأَعْمَى وَالْبَصِيرُ أَمْ هَلْ تَسْتَوِي الظُّلُمَاتُ وَالنُّورُ أَمْ جَعَلُوا لِلَّهِ شُرَكَاءَ خَلَقُوا كَخَلْقِهِ فَتَشَابَهَ الْخَلْقُ عَلَيْهِمْ قُلِ اللَّهُ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ وَهُوَ الْوَاحِدُ الْقَهَّارُ ” سورة الرعد 16
“«የሰማያትና የምድር ጌታ ማን ነው» በላቸው፡፡ «አላህ ነው» በል፡፡ «ለነፍሶቻቸው ጥቅምንም ጉዳትንም የማይችሉን ረዳቶች ከርሱ ሌላ ያዛችሁን» በላቸው፡፡ «ዕውርና የሚያይ ይስተካከላሉን ወይስ ጨለማዎችና ብርሃን ይስተካከላሉን ወይስ ለአላህ እንደርሱ አፈጣጠር የፈጠሩን ተጋሪዎች አደረጉለትና ፍጥረቱ በእነሱ ላይ ተመሳሰለባቸውን» በል፤ «አላህ #ሁለመናውን ፈጣሪ ነው፡፡ እርሱም አንዱ አሸናፊው ነው» በል፡፡” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡16)፡፡
” ذَلِكُمُ اللَّهُ رَبُّكُمْ خَالِقُ كُلِّ شَيْءٍ لَا إِلَهَ إِلَّا هُوَ فَأَنَّى تُؤْفَكُونَ ” سورة غافر 62 الزمر 62
“ይሃችሁ ጌታችሁ አላህ ነው፤ #የነገሩ ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ ከርሱ ሌላ አምላክ የለም፤ ታዲያ (ከእምነት) ወዴት ትመለሳላችሁ፡፡” (ሱረቱ ጋፊር 40፡62፣ ሱረቱ-ዙመር 39፡62)፡፡
‹‹ነገራት ሁሉ›› በሚለው ቃል ውስጥ የመርየም ልጅ ዒሳም (ዐለይሂ-ሰላም) ይካተታል፡፡ እሱም አላህ ከፈጠራቸው ነገራት ውስጥ አንዱ ነውና፡፡ ታዲያ በአላህ የተፈጠረው ዒሳ: ተመልሶ ፈጣሪ ይሆናል ብሎ ማሰብ ይቻላልን?
2ኛ/ ፈጣሪ አምላካችን አላህ ከሱ ሌላ ፈጣሪ አምላክ አለመኖሩን የሚገልጽበት ሌላው መንገድ፡ የሱን የፍጥረት ሥራዎች ይዘረዝርና፡ እናንተ ከአላህ ሌላ የምታመልኳቸው አካላት እስኪ ምን የፈጠሩት ነገር አልላቸው? በማለት ነው፡፡ እስኪ ማነው ከአላህ ሌላ እኔ ሰማይንና ምድርን፣ ወይንም ሰውንና እንሰሳትን ወይም በራሪዎችንና ነፍሳትን፣ ወይም መላእክትንና አጋንንትን ፈጠርኩ ያለ? አንድም የለም! አይኖርምም!፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” خَلَقَ السَّمَاوَاتِ بِغَيْرِ عَمَدٍ تَرَوْنَهَا وَأَلْقَى فِي الْأَرْضِ رَوَاسِيَ أَنْ تَمِيدَ بِكُمْ وَبَثَّ فِيهَا مِنْ كُلِّ دَابَّةٍ وَأَنْزَلْنَا مِنَ السَّمَاءِ مَاءً فَأَنْبَتْنَا فِيهَا مِنْ كُلِّ زَوْجٍ كَرِيمٍ * هَذَا خَلْقُ اللَّهِ فَأَرُونِي مَاذَا خَلَقَ الَّذِينَ مِنْ دُونِهِ بَلِ الظَّالِمُونَ فِي ضَلَالٍ مُبِينٍ ” سورة لقمان 11-10
“ሰማያትን ያለምታዩዋት አዕማድ (ምሰሶዎች) ፈጠረ፡፡ በምድርም ውስጥ በእናንተ እንዳታረገርግ ተራራዎችን ጣለ፡፡ በእርሷም ላይ ከተንቀሳቃሽ ሁሉ በተነ፡፡ ከሰማይም ውሃን አወረድን፡፡ በእርሷም ውስጥ ከመልካም ዓይነት ሁሉ አበቀልን፡፡ (10) ይህ የአላህ ፍጡር ነው፡፡ እነዚያ ከእርሱ ሌላ ያሉት ምንን እንደፈጠሩ እስኪ አሳዩኝ፡፡ በእውነቱ በዳዮቹ በግልጽ ጥመት ውስጥ ናቸው፡፡” (ሱረቱ ሉቅማን 31፡11)፡፡
” قُلْ أَرَأَيْتُمْ شُرَكَاءَكُمُ الَّذِينَ تَدْعُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ أَرُونِي مَاذَا خَلَقُوا مِنَ الْأَرْضِ أَمْ لَهُمْ شِرْكٌ فِي السَّمَاوَاتِ أَمْ آتَيْنَاهُمْ كِتَابًا فَهُمْ عَلَى بَيِّنَتٍ مِنْهُ بَلْ إِنْ يَعِدُ الظَّالِمُونَ بَعْضُهُمْ بَعْضًا إِلَّا غُرُورً ” سورة فاطر 40
“በላቸው «እነዚያን ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን ተጋሪዎቻችሁን አያችሁን? ከምድር ምንን እንደ ፈጠሩ አሳዩኝ፡፡ ወይስ ለእነርሱ በሰማያት ውስጥ ሽርክና አላቸውን? ወይስ መጽሐፍን ሰጠናቸውና እነርሱ ከርሱ በግልጽ አስረጅ ላይ ናቸውን? አይደለም በደለኞች ከፊላቸው ከፊሉን ማታለልን እንጂ አይቀጥሩም፡፡»” (ሱረቱ ፋጢር 35፡40)፡፡
” قُلْ أَرَأَيْتُمْ مَا تَدْعُونَ مِنْ دُونِ اللَّهِ أَرُونِي مَاذَا خَلَقُوا مِنَ الْأَرْضِ أَمْ لَهُمْ شِرْكٌ فِي السَّمَاوَاتِ ائْتُونِي بِكِتَابٍ مِنْ قَبْلِ هَذَا أَوْ أَثَارَةٍ مِنْ عِلْمٍ إِنْ كُنْتُمْ صَادِقِينَ ” سورة الأحقاف 4
“«ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን አያችሁን? ከምድር ምንን እንደ ፈጠሩ አሳዩኝ፡፡ ወይም በሰማያት ለእነርሱ (ከአላህ ጋር) መጋራት አላቸውን? (ያማልዱናል በማለታችሁ) እውነተኞች እንደ ኾናችሁ ከዚህ (ቁርኣን) በፊት የኾነን መጽሐፍ ወይም ከዕውቀት የኾነ ቅርስን አምጡልኝ» በላቸው፡፡” (ሱረቱል አሕቃፍ 46፡4)፡፡
3ኛ/ ጉዳዩ ከላይ እንዳነበብነው፡ አላህ ብቻውን ፈጣሪ ከሆነና፡ በዚህ የመፍጠር ሥራውም ምንም አይነት ተጋሪ የሌለው ከኾነ፡ እንግዲያውስ በሱራ 3፡49 ላይ ለተፈጠረው የወገኖቻችን የተሳሳተ ግንዛቤ እንዴት ምላሽ መስጠት ይቻላል? ወደሚለው እንግባ፡፡ አንቀጹን በመጠኑም ቢኾን ማብራሪያ እንስጥበት፡፡
ሀ. ‹‹ወደ እሥራኤልም ልጆች መልክተኛ ያደርገዋል››
ይህ የሚያስረዳን ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) መልክተኛ መሆኑንና የተላከውም ወደ ቤተ እስራኤል ብቻ እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ መልክተኝነት ውጪ ሌላ ሚና የለውም፡፡ በሌላም አንቀጽ ላይ እንደተነገረው የሱ መልክተኝነት እንዳለፉት መልክተኞች የሆነ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
“የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፤ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፤ (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ፤ አንቀጾችን ለነርሱ (ለከሐዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት፤ ከዚያም (ከውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት።” (ሱረቱል ማኢዳህ 75)፡፡
ለ. ‹‹እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ››
በማለት አላህ የዒሳ ጌታውና አምላኩ እንደሆነ መስክሯል፡፡ ተአምርንም ያመጣው ከሱ ዘንድ እንጂ ከራሱ እንዳልሆነም አብሮ ገልጾአል፡፡ በአምስት የቁርኣን አንቀጾች ላይ አላህ የሱም የሕዝቦቹም ጌታ እንደሆነና እሱ ብቻ መመለክ እንዳለበትም አስተምሯል፡-
“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።” (ሱረቱል ማኢዳህ 72)፡፡
ሐ. ‹‹እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ››
ቁም ነገሩ እዚህ ጋር ነው ያለው፡፡ አማርኛ ማንበብን ለቻለ ሰው አንቀጹ የሚናገረው ስለ ወፍ ቅርጽ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግተውም፡፡ ዒሳ ከጭቃ ‹‹እንደ ወፍ ቅርጽ›› እፈጥራለሁ አለ እንጂ፡ መች ወፍ እፈጥራለሁ አለ? ጭቃ አምጥቶ የወፍ ቅርጽ መፍጠር ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችል ቀላል ተግባር ነው፡፡ ቁም ነገሩ በወፍ ቅርጽ በተሰራው ጭቃ ላይ ሕይወትን ዘርቶ የእውነት ወፍ እንዲሆን በማድረግ እንዲበር ማስቻሉ ነው፡፡ ታዲያ ዒሳ ይህን አላደረገም ወይ? ከተባለም፡ አንቀጹ ይቀጥልና፡-
መ. ‹‹በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል››
በማለት ወፍ አድራጊው የጌታ አላህ ፈቃድና ኃይል እንጂ የዒሳ ችሎታ እንዳልነበር ያሳያል፡፡ የታለ ታዲያ ዒሳ ወፍ ፈጠረ የሚለው? የአላህ ፈቃድ ባይኖር ኖሮ ጭቃው ጭቃ እንደሆነ ይቀር ነበር እንጂ መች ወፍ ሆኖ ይበር ነበር?፡፡ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ጭቃውን አምጥቶ የወፍ ቅርጽ የሰራው እንኳ በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በጌታው አላህ ፈቃድ እንደሆነ ቅዱስ ቁርኣን በሱረቱል ማኢዳህ ቁጥር110 ላይ ይናገራል፡፡
ሠ. ‹‹በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፥ ለምጸኛንም፥ አድናለሁ ሙታንንም አስነሳለሁ።››
እነዚህም ተአምራት የተከናወኑት አሁንም በአላህ ፈቃድ እንጂ በዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ችሎታ አይደለም፡፡
ረ. ‹‹የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ››
አንዳንድ ወገኖች ይህን ሀሳብ ይዘው ‹ዒሳ ሁሉን እንደሚያውቅ ቁርኣን መሰከረ› ይሉናል፡፡ ሰዎቹ የሚበሉትንና በቤታቸው ያከማቹትን መናገር ሁሉን ማወቅ ሆነ በቃ? ይህ ዕውቀት በጊዜም፣ በቦታም፣ በአይነትም የተገደበ ዕውቀት እንጂ ሁሉን የማወቅ ስልጣን አይደለም፡፡ እንዴት የሚሉ ከሆነም፡-
ከጊዜ አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እየተናገረ ያለው በሱ ዘመን ስለነበሩት ህዝቦቹ እንጂ ከሱ በፊት ስላለፉት ወይም ወደፊት ስለሚመጡት ትውልዶች አይደለም፡፡ በወቅቱ የነበረውን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡
ከቦታ አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እየተናገረ ያለው ነቢይ ሆኖ በተላከበት አካባቢ ለነበሩት እስራኤላውያን እንጂ በሌላ አካባቢ ስላሉት ህዝቦች አይደለም፡፡ አሁንም ዕውቀቱ ከቦታ አንጻር ግድብ ነው፡፡
ከአይነት አንጻር፡- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እነግራችኋለሁ በማለት እየተናገረ ያለው ስለ መብላቸው ብቻ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ስለሌላ ነገር አልተናገረም፡፡ ታዲያ በምን መልኩ ነው ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሁሉን ያውቃል ብለን ድምዳሜ የምንሰጠው?
ሰ. ‹‹የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት››
በማለት አንቀጹ ይጠናቀቃል፡፡ እኛም ምላሻችን፡- አዎ አምነናል! የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ከአላህ ዘንድ በተአምራት የተላክህ የሱ መልክተኛ እንደሆንክ አምነን ተቀብለናል፡፡ ደግሞም መስክረናል፡፡ አምላክ ግን አልነበርክም፣ አይደለህምም፣ ወደፊትም አትሆንም፡፡
4ኛ/ ወገኖች ሆይ! ኢየሱስ ተአምራትን በራሱ ኃይል ማድረግ እንደማይችል የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የት አድርጋችሁት ነው በኛ ቅዱስ ቁርኣን ላይ የምትከራከሩን?
‹‹ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።›› (ማቴዎስ ወንጌል 28፡18)፡፡
ኢየሱስ ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነ፡ በሰማይና በምድር ያሉ ስልጣኖችን ከማን ነው የተቀበለው? አምላክ ይሰጣል ወይንስ ይቀበላል?
‹‹እኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አይቻለኝም፤ እንደ ሰማሁ እፈርዳለሁ ፍርዴም ቅን ነው፥ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና።›› (ዮሀንስ ወንጌል 5፡30)፡፡
አንዳችንም ነገር ከራሱ ማድረግ የማይችል አካል፡ እንዴት ብዬ ነው አምላክ አድርጌ የምይዘው? ደግሞስ የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም እያለ፡ እንዴት ብዬ ነው መልክተኛ ነህ የማልለው? አዎ! እሱ መልክተኛ ብቻ ነው፡፡
ወገኖች ሆይ! ለነገው ዓለም የሚያዋጣችሁ አንዱንና እውነተኛውን አምላክ አላህን በማምለክ፡ ለናንተም ጭምር ነቢይና መልክተኛ አድርጎ በላካቸው ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ስታምኑ ብቻ ነው፡፡ መልካም ይሆንላችሁ ዘንድ ካሰባችሁ፡፡ እሱም እንዲህ ይላል፡-
“…የመጽሐፉም ሰዎች ባመኑ ኖሮ ለነርሱ የተሻለ በሆነ ነበር፤ ከነርሱ አማኞች አሉ፤ አብዛኞቻቸዉ ግን አመጸኞች ናቸው።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡110)፡፡
በአላህ አምላክነት፡ በቅዱስ ቁርኣን የአምላክ ቃልነት፡ በነቢዩ ሙሐመድ ነቢይነት የካደና በዛው ክህደቱ የሞተ ሰው ጀነት ለሱ እርም ናት፡-
“እነዚያ አንቀጾቻችንን ያስተባበሉ ከርሷም የኮሩ ለነርሱ የሰማይ ደጃፎች አይከፈትላቸውም፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ እስከሚገባ ድረስ ነትን አይገቡም፤ እንደዚሁም አጋሪዎችን እንቀጣለን።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡40)፡፡
ኢስላም ብቸኛው የጀነት መንገድ ነው!
አላህ ሆይ መልክቴን አድርሻለሁ አንተው ምስክር ሁነኝ፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


