በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
በብዛት የሚደጋገም ጥያቄ ነው፡፡ የመርየምን ልጅ ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) ከሌሎች ቀደምት ነቢያቶች ለመለየትና እሱን ከፍ ለማድረግ ከሚጠቀሙበት አስረጂዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ እሱም፡- እንደ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ከድንግል ብቻ የተወለደ ሌላ ነቢይ ማነው? ይህ ብቻ ከሁሉ ነቢያት የተለየ አያደርገውምን? የሚል ጥያቄ!፡፡ የኛ ምላሽም በአላህ ፈቃድ እንደሚከተለው ይቀርባል ኢንሻአላህ፡፡
1ኛ. ኢስላም ያስተማረን አላህ የላካቸውን ነቢያት በጠቅላላ ነቢይነታቸውን አምነን እንድንቀበል ነው፡፡ ነቢይ መሆናቸውን አምነን ስንቀበል ደግሞ በመሐከላቸው ምንም አይነት የእምነት ልዩነት ሳናደርግ መሆን አለበት፡፡ ያ ማለት፡- በከፊሎቹ ነቢይነት አምነን ከፊሉን ደግሞ መካድ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የነቢይነትን ማዕረግ ተቀብለው የተላኩት ከአንዱና ከእውነተኛው አምላክ ከአላህ ዘንድ ነውና፡፡ ይህን አስተምህሮ ቀጥሎ ከሚቀርቡት የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች እናገኘዋለን፡-
“«በአላህና ወደኛ በተወረደው (ቁርኣን) ወደ ኢብራሂምም ወደ ኢስማዒልና ወደ ኢስሐቅም ወደ ያዕቁብና ወደ ነገዶቹም በተወረደው በዚያም ሙሳና ዒሳ በተሰጡት በዚያም ነቢያት ሁሉ ከጌታቸው በተሰጡት ከነርሱ በአንድም መካከል የማንለይ ስንኾን አመንን፤ እኛም ለርሱ (ለአላህ) ታዛዦች ነን» በሉ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2:136)፡፡
“መልክተኛው ከጌታው ወደ እርሱ በተወረደው አመነ፡፡ ምእምኖቹም (እንደዚሁ)፡፡ ሁሉም በአላህ፣ በመላዕክቱም፣ በመጻሕፍቱም፣ በመልክተኞቹም ከመልክተኞቹ «በአንድም መካከል አንለይም» (የሚሉ ሲኾኑ) አመኑ፡፡ «ሰማን፤ ታዘዝንም፡፡ ጌታችን ሆይ! ምሕረትህን (እንሻለን)፡፡ መመለሻም ወዳንተ ብቻ ነው» አሉም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2:285)፡፡
“በአላህ አመንን፤ በኛ ላይ በተወረደዉም፥ (በቁርአን) በኢብራሂምና በኢስማዒልም፣ በኢስሐቅም በያዕቁብም፣ በነገዶችም ላይ በተወረደዉ፤ ለሙሳና ለዒሳም፣ ለነቢያትም ሁሉ ከጌታቸዉ በተሰጠው (አመንን)፤ ከነርሱ መካከል አንዱንም አንለይም፤ እኛ ለርሱ ታዛዦች ነን፣ በል።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3:84)፡፡
2ኛ. አላህ የላካቸውን ነቢያት በጠቅላላ ምንም አይነት ልዩነት ሳያደርግ ያመነና በዛው እምነቱ የሞተ ሙስሊም ደግሞ፡ በአላህ ራሕመት ከጀነት ሰዎች ይሆናል፡፡ በከፊሉ አምኖ በከፊሉ እክዳለሁ የሚል ሰው ደግሞ ከክስረት ሌላ የሚያተርፈው ምንም ነገር የለውም፡፡ ደግሞም አማኝ ሳይሆን በሁሉም የካደ ካፊር ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ የሙሳን ነቢይነት ያመነ አይሁዳዊ በዒሳ አላምንም ቢል፡ ቀድሞውኑ በሙሳም ያላመነ ከሀዲ እንጂ አማኝ አይደለምና፡፡፡ ምክንያቱም ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በዒሳ አትመኑ ብሎ አላስተማረምና፡፡ በዒሳ ያመነ ክርስቲያን በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት ባያምን፡ በዒሳም ጭምር ያላመነ ካፊር ይባላል፡፡ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አትከተሉ ብሎ አላስተማረምና፡፡ በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይነት ያመነ ሙስሊም ደግሞ ከዛ በፊት በነበሩት ነቢያት ሁሉ ያመነ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ እሳቸው የተላኩት የቀደሙትን ለማረጋገጥና የጠፋውንም ትምህርት ለማደስ፡ አዲስ ስርአትና ቀለል ያለ የጀነትንም መንገድ ለማስተማር ነውና፡-
“እነዚያም በአላህና በመልክተኞቹ ያመኑት፣ እነዚያ እነሱ በጣም እውነተኞቹ በጌታቸውም ዘንድ መስካሪዎቹ ናቸው፤ ለነርሱ ምንዳቸው ብርሃናቸውም አልላቸው፤ እነዚያም የካዱት በአንቀጾቻችንም ያስተባበሉት፣ እነዚያ የእሳት ጓዶች ናቸው።” (ሱረቱል ሐዲድ 57:19)፡፡
“ከጌታችሁ ወደ ሆነች ምሕረት ወርዷ እንደሰማይና ምድር ወርድ ወደ ሆነችም ገነት ተሽቀዳደሙ፤ ለነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ ላመኑት ተዘጋጅታለች። ይህ የአላህ ችሮታ ነው፤ ለሚሻው ሰው ይሰጠዋል፤ አላህም የታላቅ ችሮታ ባለቤት ነው።” (ሱረቱል ሐዲድ 57:21)፡፡
“እነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ የሚክዱ፣ በአላህና በመልክተኞቹም መካከል መለየትን የሚፈልጉ፣ በከፊሉም እናምናለን፣ በከፊልም እንክዳለን የሚሉ በዚህም መካከል መንገድን ሊይዙ የሚፈልጉ፤ እነዚያ በውነት ከሐዲዎቹ እነርሱ ናቸው። ለከሐዲዎችም አዋራጅን ቅጣት አዘጋጅተናል። እነዚያ በአላህና በመልክተኞቹ ያመኑ፣ ከነሱም በአንድም መካከል ያልለዩ እነዚያ ምንዳዎቻቸውን በእርግጥ ይሰጣቸዋል። አላህም መሐሪ አዛኝ ነው።” (ሱረቱ-ኒሳእ 4:150-152)፡፡
3ኛ. ነቢያት በጠቅላላ በጌታቸው አላህ ዘንድ የተከበሩ ከመሆናቸው ጋር በመሐከላቸው የደረጃ መበላለጥ መኖሩንም አምነን እንቀበላለን፡፡ ይህን መበላለጥ የምንገልጸው ግን፡ ጌታ አላህ ራሱ በነገረን መሰረት እንጂ ከስሜታችን ተነስተን፡ በኛ የሂሳብ ስሌት መሠረት መሆን የለበትም፡፡ አላህ የሰው ልጅን ከተቀሩት አብዛኞቹ ፍጥረታት መካከል መረጠው (ሱረቱል ኢስራእ 17:70)፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል ደግሞ በአላህ ያመኑ መልካም የአላህ ባሮች የተመረጡ ናቸው (ሱረቱ-ሰጅዳህ 32:18፣ ሱረቱ ጋፊር (ሙእሚን) 40:58)፡፡ ከአማኞች መካከል ደግሞ ነቢያትና መልክተኞች የተመረጡ ናቸው (ሱረቱል ሐጅ 25:75)፡፡ ከመልክተኞች መካከል ደግሞ አምስቱ ‹‹ኡሉል-ዐዝም›› (የቆራጥነት ባልተቤቶች) የተመረጡ ናቸው (ሱረቱል አሕቃፍ 46:35)፡፡ እነዚህ አምስቱ:– (ኑሕ፣ ኢብራሂም፣ ሙሳ፣ ዒሳ፣ ሙሐመድ) ዐለይሂሙ-ሰላም ናቸው፡፡ ከአምስቱ ደግሞ አሽረፉል ኸልቅ (የፍጥረት ሁሉ የበላይ) ሆነው የተመረጡት ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ናቸው፡፡
“እነዚህን መልክተኞች ከፊላቸውን በከፊሉ ላይ አበለጥን፡፡ ከእነርሱ ውስጥ አላህ ያነጋገረው አልለ፡፡ ከፊሎቻቸውንም በደረጃዎች ከፍ አደረገ…” (ሱረቱል በቀራህ 2:253)፡፡
“ጌታህም በሰማያትና በምድር ያለውን ሁሉ ዐዋቂ ነው፤ ከፊሉንም ነቢያት በከፊሉ ላይ በእርግጥ አብልጠናል፤ ዳውድንም ዘቡርን ሰጥተነዋል።” (ሱረቱል ኢስራእ 17:55)፡፡
4ኛ. ሶስቱን ነጥቦች ለመግቢያ ያህል ካየናቸው፡ ከላይ ወዳነሳነው ጥያቄ ስንመለስ፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ያለ ወንድ ሰጋ–ፈቃድ ከድንግል (ከመርየም) መወለዱ ከሌሎች ነቢያት አያስበልጠውም ወይ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ፡ መልሳችንም፡- በጭራሽ! የሚል ነው፡፡ እንዴት? የሚል ጥያቄ ከተከተለም፡-
ሀ. ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ከድንግል መወለዱና መፈጠሩ የጌታው የአላህ ፈቃድ እንጂ የዒሳ የግል ፍላጎትና ምርጫ አይደለም፡፡ ማንም ሰው እኔ በዚህ መልኩ ልወለድ (ልፈጠር) አላለም፡፡ ምክንያቱም፡- መፍጠር የአላህ ፈቃድና ስራ እንጂ የሰው ምርጫ አይደለምና፡፡ ታዲያ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም)፡- እኔ እንደቀደሙት ነቢያት ከስጋ ፈቃድ መወለድ የለብኝም፡ ከድንግል ብቻ ነው የሚገባኝ ብሎ መርጦ ነው እንዴ የተወለደው? አይደለም፡፡ ምርጫው የፈጣሪ አምላኩ የአላህ እንጂ፡ የተፈጣሪው የዒሳ አልነበረም፡-
“ጌታዬ ሆይ! ሰዉ ያልነካኝ ስሆን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፤ ነገሩ እንደዚህሽ ነዉ፤ አላህ የሚሻዉን የፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ሁን ይለዋል ወድያዉኑም ይሆናል፥ አላት።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3:47)፡፡
“ጌታህም የሚሻውን ይፈጥራል፤ ይመርጣልም፡፡ ለእነርሱ (ለሰዎቹ) ምርጫ የላቸውም፡፡ አላህ ከማይግገባው ሁሉ ጠራ፡፡ ከሚያጋሯቸውም ላቀ፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28:68)።
“እርሱ ያ በማሕፀኖች ዉሰጥ እንደሚሻ አድርጎ የሚቀርጻችሁ ነዉ። ከርሱ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፤ አሸናፊዉ ጥበበኛዉ ነዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3:6)፡፡
ለ. ምንግዜም ቢሆን አንድ ‹ሥራ› ጥሩም ሆነ መጥፎ የሚገልጸው የሰሪውን ጥበብና ችሎታ ነው፡፡ ባማረ ዲዛይንና ቅርጽ የተሠራ ህንፃ ብንመለከት፡ አድናቆትን የምንቸረው ለመሀንዲሱና አርክቴክቸሩ እንጂ ለህንጻው አይደለም፡፡ እኛ ደግሞ የአላህ ህንፃዎች ነን፡፡ አፈጣጠራችን የሱን ጥበብና ችሎታ ነው የሚናገረው፡፡ ታዲያ እንዴት ሆኖ ነው ያኛው ከድንግል ስለተወለደ፡ ይሄኛው ደግሞ ከስጋ ፈቃድ ስለተወለደ ከዚያኛው ያንሳል የምንለው? ከድንግል የተወለደው፡ ከድንግል ለመወለድ ያደረገው አስተዋጽኦ ነበርን? እናስተውል ጎበዝ!፡፡
ሐ. የዒሳ አፈጣጠር ብቻ ሳይኾን አራቱም አይነት የሰው አፈጣጠር እጅግ የሚደንቁና የሚያስደምሙ ናቸው፡፡ ጌታ አላህ ፍጥረቱን በተሟላ መንገድ ለማድረግ፡ ችሎታውንም በተግባር ለማሳየት ሰውን በአራት አይነት መንገድ ፈጥሮታል፡፡ ልክ ቤተሰብ ሲመሰርት በአራት አይነት መንገድ እንደሚመሰርተው ማለት ነው፡፡ እንዴት? ካላችሁም፡-
አንደኛ፡- በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የሚወለዱ ልጆችን በጠቅላላ ወንዶች በማድረግ፡ ሴትን ይከለክልና ያን ቤተሰብ ወንድማሞች ብቻ ያደርጋቸዋል፡፡
ሁለተኛ፡- በሌላ ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ በተቃራኒው የሚወለዱ ልጆችን ሴቶች ብቻ እንዲሆኑ በማድረግ ወንድን ይከለክልና እህትማሞች ብቻ ያደርጋቸዋል፡፡
ሶስተኛ፡- እዚህኛው ቤት ውስጥ ደግሞ ወንድንና ሴትን ቀላቅሎ በመስጠት የተወለዱትን ልጆች ወንድምና እህት በማድረግ ያጠናዳቸዋል፡፡
አራተኛ፡- በዚህ ቤት ውስጥ ደግሞ በባልና ሚስት መሀል ፍቅርን ብቻ ያሰፍንና፡ ግን ልጅን ይከለክላቸዋል (መሀን ያደርጋቸዋል)፡፡ ሚስጥሩና ጥበቡ እሱ ዘንድ ብቻ ነውና ያለው፡፡
“የሰማያትና የምድር ንግሥና የአላህ ነው፤ የሚሻውን ይፈጥራል፤ ለሚሻው ሰው ሴቶችን (ልጆች) ይሰጣል፤ ለሚሻውም ሰው ወንዶችን ይሰጣል። ወይም ወንዶችና ሴቶች አድርጎ ያጠናዳቸዋል። የሚሻውንም ሰው መካን ያደርገዋል፤ እርሱ ዐዋቂ ቻይ ነውና።” (ሱረቱ-ሹራ 42:49-50)፡፡
ታዲያ ወንድና ሴት የወለደውን ቤተሰብ ከሁለት አንዱን ብቻ ከወለደው፡ ወይም ምንም ካልወለዱት ጋር በማነጻጸር እናንተ ትበልጣላችሁ! ማለት እንችላለንን? በፍጹም አንችልም፡፡ ሥራው የአላህ እንጂ የቤተሰቡ አልነበረምና!!
በዛው መልኩም ጌታ አላህ ሰውን ሲፈጥር በአራት መንገድ ፈጥሮታል፡-
አንደኛ፡- ያለ ወንድ ያለ ሴት (እናትና አባት ሳይኖር) አባታችንን አደምን (ዐለይሂ-ሰላም) ከምድር አፈር ፈጠረው (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3:59)፡፡
ሁለተኛ፡- ከወንድ ብቻ ያለ ሴት (እናት ሳትኖር) እናታችንን ሐዋእን (ዐለይሃ-ሰላም) ከአደም የጎን አጥንት ፈጠራት (ሱረቱ-ኒሳእ 4:1)፡፡
ሶስተኛ፡- ከወንድና ከሴት (ከእናትም ከአባትም) የዘር ፈሳሽ የአደምንና የሐዋእን ዘሮች በጠቅላላ እስካሁን ድረስ ያሉትንም ወደፊት የሚመጡትንም ፈጠራቸው (ሱረቱል ሑጁራት 49:13)፡፡
አራተኛ፡- ከሴት ብቻ ያለ ወንድ (አባት ሳይኖር) ከመርየም (ዐለይሃ-ሰላም) ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) “ኹን” በሚለው መለኮታዊ ቃሉ ፈጠረው (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3:45-47)፡፡
አራቱንም አፈጣጠሮች ከልቡ ላስተዋለ ሰው እጅጉኑ የሚደንቁ ናቸው፡፡
፡- አፈር ሰው ሆኖ ቆሞ መሄድና መራመድ መቻሉ እንዴት አያስደንቅም?
፡- አጥንትስ ሴት ሁና ተፈጥራ ሰው ሆና ለባለቤቷ ሚስት ተደርጋ ከዛም ስትራመድ ማየት እንዴት አያስገርምም?
፡- ደካማና ዝልግልግ የሆነው የዘር ፈሳሽስ ከሴቷ እንቁላል ጋር ተገናኝቶ በዘጠኝ ወር ውስጥ 3ኪሎ ግራም የሚመዝን ያማረና የተስተካከለ አቋም ያለው ሰው ሆኖ ከናቱ ማኅጸን ሲወጣና ሲፈጠር እንዴት አያስደምምም?
፡- ምንም አይነት የወንድ ሰጋ-ፈቃድ (ግብረ-ስጋ ግኑኝነት) ጣልቃ ገብነት ሳይኖረው፡ ‹‹ኹን!›› በሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ ብቻ መርየም በማኅጸኗ የተነፋባትን (እፍ የተባለባትን) አርግዛ፡ በመውለጃዋ ጊዜ ሙሉ ሰውን መውለዷስ ለምን አያስደንቅም?
ሁሉም የአላህ ጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከኛ የሚጠበቀው ‹ሱብሐነከ ያረብ› (ጌታችን ሆይ! ከጉድለት ባሕሪያት ጥራት ይገባህ) በማለት ማመስገን ነው፡፡ በግድ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ያለ አባት ከድንግል ተወልዷልና እሱን ከሌሎች ነቢያት ማስበለጥ አለብን ከተባለ፡ ያለ አባትም ያለ እናትም ከምድር አፈር የተፈጠረውን አደምን ልንረሳ አይገባንም፡-
“አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ፥ እንደ አደም ብጤ ነዉ፤ ከዐፈር ፈጠረዉ፤ ከዚያም ለርሱ (ሰዉ) ሁን አለዉ፥ ሆነም።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3:59)፡፡
ማጠቃለያ:–
የመርየም ልጅ የዒሳ (ዐለይሂ–ሰላም) ከድንግል ብቻ መወለድ የሚደንቅ ተአምር ቢሆንም: አድናቆቱ ግን ዒሳን በዚህ መልክ ለፈጠረው አምላክ ለአላህ ነው መኾን ያለበት። አላህም እሱን በዚህ መልክ የፈጠረው ችሎታውንና ተአምሩን ለዓለማት በተግባር በማሳየት ምልክት ሊያደርገው ነው። የአላህ ቃል እንዲህ ይላል:–
“«(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ሆኜ አመንዝራም ሳልሆን ለእኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!» አለች፡፡ አላት «(ነገሩ) እንደዚህሽ ነው፡፡» ጌታሽ «እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው፡፡ ለሰዎችም ታምር ከእኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው» አለ፤ (ነፋባትም)፡፡” (ሱረቱ መርየም 19:20–21)።
ጨርሻለሁ!
“አንተ ነቢዩ ሆይ! እኛ መስካሪ አብሳሪና አስፈራሪም አድርገን ላክንህ። ወደ አላህም በፈቃዱ ጠሪ፣ አብሪ ብርሃንም፣ (አድርገን ላክንህ)፤ አማኞችንም ከአላህ ዘንድ ለነርሱ ታላቅ ችሮታ ያላቸው መሆኑን አብስራቸው። ከሐዲዎችንና መናፍቃንንም አትታዘዛቸው፤ ማሰቃየታቸውንም (ለአላህ) ተው፤ በአላህም ላይ ተጠጋ፤ መጠጊያም በአላህ በቃ።” (ሱረቱል አሕዛብ 45-47)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


