በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ከተወሰኑ አመታት በፊት እዛው በሀገሬ ሳለሁ አንድ የክርስትና (ፕሮቴስታንት) እምነት ተከታይ ከሆነ ሰው ጋር ስወያይ፡ እኔንም የጠየቀኝ ጥያቄ ነበር፡፡ የጥያቄው ይዘትም፡- አንተ ጀነት ትገባለህ ወይስ አትገባም? የሚል ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ አጠር አድርጌ፡- እኔንጃ! አልኩት፡፡ እሱም ቀጠለና፡- ታዲያ ጀነት ግባ አትግባ እርግጠኛ ያልሆንክበትን እምነት እንዴት ትከተላለህ? አለኝ፡፡ እኔም የምፈልገው ይህ ጥያቄ እንዲነሳ ስለነበር፡ ከዚያ በኋላ አብራራሁለት፡፡ ምን ብለህ? ትሉኛላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ኢንሻአላህ በአላህ ፈቃድ ያብራራሁለትን እነግራችኋለሁ፡፡ ዛሬም በፌስቡክ ላይ ጥያቄው ተደጋግሞ ሲነሳ ስላየሁ፡ ለሁላችን ይሆን ዘንድ ሰፋ ባለ ማብራሪያ ለናንተ ላቀርበው ወደድኩ፡፡ አላህ እውነቱን ተረድተን በሐቅ ላይ የምንጸና ያድርገን፡፡ ምላሹም ይህን ይመስላል፡-
1ኛ. አንድ ሙስሊም እኔ የጀነት ነኝ ወይም አይደለሁም ለማለት አልችልም ብሎ መናገሩ፡ መጠራጠሩን ያመላክታል ከተባለ እንኳ፡ ጥርጣሬው የራሱ ማንነት ላይ እንጂ፡ የሚከተለው እምነትና ሃይማኖት ላይ አለመሆኑ ቅድሚያ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የሚለው፡- አንተ ጀነት ትገባለህ ወይስ አትገባም? የሚል እንጂ፡ የምትከተለው እምነትና ሃይማኖት ወደ ጀነት ያደርሳል ወይስ አያደርስም? የሚል ባለመሆኑ፡፡
የተነሳው ጥያቄ ስለ ሃይማኖታችን ቀጥተኝነት ቢሆን ኖሮ፡ ያለ-ምንም ማመንታት ሰዎችን ሁሉ ካመኑበትና ከተከተሉት ወደ ጀነት ሊያደርሳቸው የሚችል ብቸኛው የመዳኛ መንገድ መሆኑን በመሰከርን ነበር፡፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መንገድ ውጪ ያሉት መንገዶች ሁሉ ወደ ጀሀነም ገደል የሚወስዱና ወደ አዘቅቱም የሚጥሉ እንጂ፡ ሰውን ለጀነት ብቁ የሚያደርጉ አይደሉም፡፡ ጌታ አላህ በቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላልና፡-
” وَأَنَّ هَذَا صِرَاطِي مُسْتَقِيمًا فَاتَّبِعُوهُ وَلَا تَتَّبِعُوا السُّبُلَ فَتَفَرَّقَ بِكُمْ عَنْ سَبِيلِهِ ذَلِكُمْ وَصَّاكُمْ بِهِ لَعَلَّكُمْ تَتَّقُونَ ” سورة الأنعام 153
“«ይህም ቀጥተኛ ሲኾን መንገዴ ነው፤ ተከተሉትም፡፡ (የጥመት) መንገዶችንም አትከተሉ፡፡ ከ(ቀጥተኛው) መንገዱ እናንተን ይለያዩዋችኋልና፡፡እነሆ ትጠነቀቁ ዘንድ በርሱ አዘዛችሁ፡፡»” (ሱረቱል አንዓም 153)፡፡
” وَمَنْ يَبْتَغِ غَيْرَ الْإِسْلَامِ دِينًا فَلَنْ يُقْبَلَ مِنْهُ وَهُوَ فِي الْآخِرَةِ مِنَ الْخَاسِرِينَ ” سورة آل عمران 85
“ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰዉ፣ ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለዉም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎች ነዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 85)፡፡
አንባቢን ላለማድከም እንጂ በዚህ ዙሪያ ያሉ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሐቅን ለፈለገ ግን እነዚህ ሁለት አንቀጾች ብቻ በቂ ናቸው፡፡ በኢስላም ላይ የጀነት ብቸኛው መንገድ ለመሆኑ የትንኝ ክንፍ ያህል ጥርጥር የለንም፡፡
ጉዳዩ እንደዛ ከሆነ አሁን የሚነሳው ጥያቄ፡- ታዲያ አንተ ኢስላምን እየተከተልህ አይደለም ወይ? ኢስላም ደግሞ ብቸኛው የጀነት መንገድ ነው ከተባለ፡ ለምን እኔ የጀነት ነኝ ለማለት ፈራህ? የሚለው ነው፡፡
2ኛ. በኢስላም አስተምህሮ መሰረት እምነትና ስራ ዋጋ የሚኖረው ፍጻሜው ሲያምር ነው፡፡ ‹‹አል-አዕማሉ ቢል-ኸዋቲም›› (ስራዎች በፍጻሜያቸው ነው የሚታዩት)፡፡ እኔ ዛሬ ያለሁበት ተጨባጭና ማንነት፡ ለነጌው ማንነቴ ገላጭና አስረጂ አይሆንም፡፡ ኢማን (እምነት) የሚባለው ነገር በአማኞች ልቦና ውስጥ ከገባ በኋላ፡ ተደላድሎና ተመቻችቶ በገባበት መልኩ የሚቀጥል አይደለም፡፡ ተለዋዋጭ ነው፡፡ እያደገና እየጠነከረ እንዲሁም እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በተቃራኒው እየቀነሰና እየሳሳ እንዲሁም እየተዳከመ ይወርዳል፡፡ ለዚህ ደግሞ አይነተኛ ምክንያቱ ውጫዊ ማንነታችን (ታዛዥነት) ነው፡፡ በመልካም ስራ ላይ በመጠናከርና ከኃጢአት እራስን በማራቅ እምነትን ማሳደግ እንደሚቻለው፡ በአገልባጩም ከመልካም ተግባራት በመራቅና በኃጢአት ባህር ላይ በመዋኘት እምነትን ማዳከምና መግደልም ይቻላል፡፡
እኔ ዛሬ ያለሁበት ማንነቴ ለነጌውና ለመጨረሻው ማንነቴ ገላጭ መሆን እንደማይችል መረዳት ከፈለግሁ ትላንት ማን ነበርኩ? የሚለውን ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት የኢማን ደረጃችን ምን ላይ ነበር? ብለን እራሳችንን እንጠይቅ፡፡ የምናገኘው መልስ፡- በአላህ ፈቃድና እዝነት ኢማናችን ጠንክሮ መልካም ስራችን በዝቶ ጎብዘን ነበር፡፡ ዛሬ ግን በምድራዊ ብልጭልጭ ነገሮች ተስበን፣ መጥፎ ጓደኞችንም ተጎዳኝነትን፣ ከአላህ ትእዛዝ በፊት ስሜታችንን አስቀድመን፡ ኢማናችን ደክሞ ቀዝቅዞ እንገኛለን፡፡ ወይም ደግሞ፡- በሸይጧን አሳሳችነትና በኛም ስንፍና ኢማናችን ደክሞ መልካም ስራችን ቀንሶ ሰንፈን ነበር፡፡ ዛሬ ግን በአላህ ቸርነት፣ በዑለሞቻችን አስታዋሽነት፣ በጓደኞቻችን መካሪነትና አርአያነት ኢማናችን ጠንክሮ፡ መልካም ስራችን በዝቷል የሚል ነው፡፡ ጉዳዩ እንደዛ ከሆነ፡ ነጌስ መጨረሻዬ ምን ይሆን? የሚለውን ዛሬ ላይ ሆኜ መግለጽ አልችልም፡፡ ባይሆን እኔ ምለው፡- በጌታዬ በአላህ ላይ ተስፋ አለኝ፡፡ እሱ በራሕመቱ (በቸርነቱ) ሙስሊም አድርጎ እንደፈጠረኝ፡ ሙስሊም አድርጎ በማቆየት፡ ሙስሊም አድርጎ ይገድለኛል ብዬ እተማመናለሁ፡፡ ስራዬ ግን ምንም ዋስትና የለውም ነው፡፡ ለዚህ ነው በሶላቴ ላይ ሆኜ በቀን በትንሹ 17 ጊዜ፡- ‹‹ቀጥተኛውን መንገድ ምራን›› (አል-ፋቲሓ 6)፡፡ የምለው፡፡ የጌታዬ ምሪት እስከ ዕለተ-ሞቴ ድረስ ያስፈልገኛል፡፡ አንዴ መርተኸኛልና ለቀረው አታስፈልገኝም፡፡ እኔ ብቻዬን እወጣዋለሁ የሚል ማንነት የለኝም፡፡ ስለዚህ ሁሌም የአንተ መሪነት አይለየኝ ነው መልእክቱ፡፡
በተግባርስ ስንቶችን አየናቸው!! ትላንት ከላይ ሲታዩ ሙስሊም የነበሩ፡ እንደኛው መስጂድ ገብተው ይሰግዱ የነበሩ፡ ዛሬ ግን ኩፍር ውስጥ የገቡ የሉምን? በተቃራኒውስ ትላንት በኩፍር ጨለማ ውስጥ ሲዳክሩ የነበሩ፡ የአላህ ፈቃዱና እዝነቱ ሆኖ የኢስላም ብርሐን ደርሷቸው፡ ሙስሊም ወንድሞቻችንና እህቶቻችንስ የሆኑ ስንትና ስንት ናቸው? ታዲያ በምን መልኩ ነው ዛሬ ላይ ሆኜ ፍጻሜዬን ከወዲሁ ማየትና ማወቅ ያልቻልኩ ሰው፡ ‹እኔ የጀነት ሰው ነኝ›› ብዬ በድፍረት እንድናገር የምጠየቀው?
አዎ! እኔ የጀነት ሰው ነኝ ብዬ ላንተ ለመናገር የምፈራው እራሴ ላይ ስለማልተማመን ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልብ ተገለባባጭ ነውና፡፡ ይህን የመለዋወጥ ባሕሪውን ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በተሻለ መልኩ የገለጸው ሰው ስለሌለና ስለማይኖርም፡ እሳቸው እንዴት አድርገው ገልጸው እንዳስተማሩ እንመልከት፡-
قَالَ الْمِقْدَادُ بْنُ الْأَسْوَدِ : لَا أَقُولُ فِي رَجُلٍ خَيْرًا وَلَا شَرًّا حَتَّى أَنْظُرَ مَا يُخْتَمُ لَهُ يَعْنِي بَعَدَ شَيْءٍ سَمِعْتُهُ مِنَ النَّبِيِّ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ ، قِيلَ : وَمَا سَمِعْتَ ؟ قَالَ : سَمِعْتُ رَسُولَ اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ يَقُولُ : ” لَقَلْبُ ابْنِ آدَمَ أَشَدُّ انْقِلَابًا مِنَ الْقِدْرِ إِذَا اجْتَمَعَتْ غَلْيًا ” السلسلة الصحيحة 1772.
ሚቅዳድ ኢብኑል-አስወድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- “ከአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የሆነ ነገርን ከሰማሁ በኋላ፡ በማንም ሰው ላይ መጨረሻው ምን እንደሆነ እስከማውቅ ድረስ የጥሩም ሆነ የመጥፎነት ምስክርነትን አልሰጥም፡፡ ‹‹ምን ሰምተህ ነው››? ተብሎ ሲጠየቅ እንዲህ አለ፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡- ‹‹የአደም ልጆች ልብ፡ ድስት በእሳት ላይ ሲጣድ ውሃው ከሚገነፍለው በላይ የሚገለባበጥ ነው›› (ሲልሲለቱ-ሶሒሓህ 1772)፡፡
ታዲያ እንዲህ አይነት ልቦና ያለው ሰው ነው፡ ዛሬ ላይ ሆኖ የጀነት ነኝ ብሎ ፍርድ የሚሰጠው? ባይሆን ከኛ የሚጠበቀው ጌታችንን በመተናነስና በመዋረድ በኃጢአታችን ምክንያት የእውነትን መንገድ ከልባችን እንዳዘጋብን መማጸን ነው፡፡ ቀደምት የእምነት መሪዎቻችንም እንዳሉት፡ ጌታችንም ለአብነት በቃሉ እንደጠቀሰልን እንዲህ እንበል፡-
“(እነሱም ይላሉ) ፦ጌታችን ሆይ! ቅኑን መንገድ ከመራኸን በኋላ ልቦቻችንን አታዘምብልብን፤ ከአንተ ዘንድ የሆነን ችሮታም ለኛ ስጠን፤ አንተ በጣም ለጋስ ነህና።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 8)፡፡
3ኛ. እነዚህ ወገኖች ሌላው ያልገባቸው ነገር የጀነትን ውድነት ነው፡፡ ጀነት የአላህ ንብረት ነች፡፡ ይህቺን የጸጋ ዓለም ለማግኘት ማን ተገቢዋ እንደሆነ አላህ ዐዋቂ ነው፡፡ በፍጹማዊ ዐዋቂነቱ ከተስማማን፡ ፍርድም የሱ መሆኑን ልንስማማ ይገባል፡፡ ከሱ በላይ ወይም እንደሱ ፍትሐዊ የሆነ ማንም የለምና፡፡ ስለዚህ እምነቴና መልካም ስራዬ (ታዛዥነቴ) እሱን ምን ያህል እንዳስደሰተው ያላወቅሁ እኔ ደካማ ባሪያው፡ ልክ የጀነት ቁልፍ በእጁ እንዳለ ሰው፡ እንዴት እኔ የጀነት ነኝ ብዬ ገና ምድራዊ ፈተናዬን ሳላጠናቅቅና መጨረሻዬንም ሳላይ መናገር እችላለሁ?
አሁንም ከኔ የሚጠበቀው ጌታዬን፡- አምላኬ አላህ ሆይ! በትንሹ መልካም ስራዬ ሳይሆን በአንተ ትልቁ ቸርነት አይተኸኝ፣ እንደ ኃጢአቴ መብዛት ሳይሆን፡ እንደ ራሕመትህ ስፋት ተመልክተኸኝ ጀነትን በተውፊቅህ ለግሰኝ ማለት ነው እንጂ፡ እኔ ድኛለሁ ብሎ ከወዲሁ መፎከርና መሸለል የትም አያደርስም፡፡ ለመዳን ብቸኛው መንገድ በትክክለኛው የኢስላም መንገድ ላይ መጽናት ነው፡፡ የአላህን ጌትነት አምኖ፡ ጌታውን እያመለከ በዚሁ እምነቱ ጸንቶ የሞተ ሰው ያለ ጥርጥር የጀነት ነው፡፡ ቀጣዮቹ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችም ይህንን ያስረዳሉ፡-
” إِنَّ الَّذِينَ قَالُوا رَبُّنَا اللَّهُ ثُمَّ اسْتَقَامُوا تَتَنَزَّلُ عَلَيْهِمُ الْمَلَائِكَةُ أَلَّا تَخَافُوا وَلَا تَحْزَنُوا وَأَبْشِرُوا بِالْجَنَّةِ الَّتِي كُنْتُمْ تُوعَدُونَ ” سورة فصلت 30
“እነዚያ ጌታችን አላህ ነው ያሉ፣ ከዚያም ቀጥ ያሉ ፦ አትፍሩ፤ አትዘኑም፤ በዚያችም ተስፋ ቃል ትደረግላችሁ በነበራችሁት ገነት ተበሰሩ፤ በማለት በነሱ ላይ መላእክት ይወርዳሉ።” (ሱረቱ ፉሲለት 30)፡፡
“እነዚያ ጌታችን አላህ ነው ያሉ ከዚያም ቀጥ ያሉ በነርሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም እነርሱም አያዝኑም፡፡ እነዚያ የገነት ጓዶች ናቸው በርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ስሆኑ በዚያ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ታላቅን ምንዳ (ይመነዳሉ)” (ሱረቱል አሕቃፍ 13-14)፡፡
4ኛ. በመጨረሻም ለነዚህ ወገኖች ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት፡- ማንም ሰው የነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይ ሆኖ መላክ ሰምቶ በሳቸው ነቢይነት ሳያምን ቢሞት እጣ ፈንታው ጀሀነም እሳት እንጂ ሌላ አይደለም የሚለውን ነው፡፡ በሳቸው ነቢይነት ሳያምኑ ጀነትን መመኘት እራስን ማሞኘት ነው፡፡
عن أبي هريرة -رضي الله عنه- أن النبي صلى الله عليه وسلم قال: وَالَّذِي نَفْسُ مُحَمَّدٍ بِيَدِهِ، لاَ يَسْمَعُ بِي أحد من هذه الأمة لا يَهُودِيٌّ، وَلاَ نَصْرَانِيٌّ، ثُمَّ يَمُوتُ وَلَمْ يُؤْمِنْ بِالَّذِي أُرْسِلْتُ بِهِ إِلاَّ كانَ مِنْ أَصْحَابِ النار. رواه مسلم.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን፡ የአላህ ነቢይ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የሙሐመድ ነፍስ በእጁ በሆነው ጌታ (በአላህ) እምላለሁ፡፡ ከዚህ ኡምማህ (ህዝብ) አይሁዳዊም ይሁን ክርስቲያን የኔን ነቢይ ሆኖ መላክ ሰምቶ፡ ከዚያም በነቢይነቴ ሳያምን ቢሞት እሳት ቢገባ እንጂ አይተርፍም” (ሙስሊም የዘገበው)፡፡
ያረብ! ፍጻሜአችንን አሳምረው፡፡ ሙስሊም አድርገህም ግደለን
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


