በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡ (አል-ፋቲሓ 2) ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
1/ ከርሱ በሆነው ቃል፡-
” إِذْ قَالَتِ الْمَلآئِكَةُ يَا مَرْيَمُ إِنَّ اللّهَ يُبَشِّرُكِ بِكَلِمَةٍ مِّنْهُ اسْمُهُ الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ وَجِيهًا فِي الدُّنْيَا وَالآخِرَةِ وَمِنَ الْمُقَرَّبِينَ” سورة آل عمران 45
“መላእክት ያሉትን (አስታዉስ) ፡- መርየም ሆይ አላህ ከርሱ በሆነዉ ቃል፣ ስሙ አልመሲሕ ዒሳ የመርየም ልጅ፣ በዚህ ዓለምና በመጨረሻዉም ዓለም የተከበረ፣ ከባለማሎችም በሆነ (ልጅ) ያበስረሻል” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 45)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹‹ከርሱ በሆነ ቃል›› የሚለውን በመምዘዝ፡ ወገኖቻችን:- ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የአላህ ቃል ነውና አምላክ መሆን አለበት ይሉናል፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ የምንሰጠው ምላሽ የሚከተለው ይሆናል፡-
ሀ/ አምላካችን አላህ ማንኛውንምን ነገር መፍጠር ከፈለገ፡ ‹‹ሁን›› በሚለው መለኮታዊ ቃሉ አማካኝነት መፍጠርና ማስገኘት ይችላል፡፡ ይህ ፍጥረትና ግኝት ግን የ ”ይሁን” ቃሉ ውጤት እንጂ: እራሱ ቃል ተብሎ አይጠራም፡፡ ምክንያቱም የተገኘው ‹‹ሁን›› በሚለው መለኮታዊ ቃል አማካኝነት በመሆኑ!!
አላህ በመለኮታዊ ቃሉ አማካኝነት አንድን ነገር ይፈጥራል፣ ያስገኛል፣ ይሰራል እንጂ፡ ይህ መለኮታዊ ቃል እራሱ የተፈለገውን ነገር ሁኖ አይፈጠርም፣ አይሰራም፣ አይገኝምም፡፡ የአላህ ቃል፡ የራሱ የአላህ አንድ መለኮታዊ ባሕሪ እንጂ: ፍጥረትና ግኝት አይደለምና፡፡ ይህንን ሀሳብ የሚገልጹ የተወሰኑ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችን እንመልከት፡-
” إِنَّمَا قَوْلُنَا لِشَيْءٍ إِذَا أَرَدْنَاهُ أَن نَّقُولَ لَهُ كُن فَيَكُونُ ” سورة النحل 40
“ለማንኛውም ነገር (መሆኑን) በሻነው ጊዜ ቃላችን ለርሱ ሁን ማለት ብቻ ነው፤ ወዲያውም ይሆናል።” (ሱረቱ-ነሕል 40)፡፡
” بَدِيعُ السَّمَاوَاتِ وَالأَرْضِ وَإِذَا قَضَى أَمْراً فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ ” سورة البقرة 117
“ሰማያትንና ምድርን ያለብጤ ፈጣሪ ነው፤ ነገርንም (ማስገኘት) በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው፡- «ኹን ነው፤» ወዲያውም ይኾናል፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 117)፡፡
” إِنَّمَا أَمْرُهُ إِذَا أَرَادَ شَيْئًا أَنْ يَقُولَ لَهُ كُنْ فَيَكُونُ ” سورة يس 82
“ነገሩም አንዳች ባሻ ጊዜ ሁን ማለት ነው ወዲያው ይሆናልም።” (ሱረቱ ያሲን 82)፡፡
በነዚህ ሶስት የቁርኣን አንቀጾች መሰረት፡ አላህ ሊያስገኘው የሻውን ነገር በጠቅላላ ‹‹ሁን›› በሚለው ቃሉ አማካኝነት ማስገኘት እንደሚችል በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
ለ/ ወደ መርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ስንመጣ ደግሞ ጌታ አላህ እሱን ከመርየም (ዐለይሃ-ሰላም) በድንግልናዋ ወንድ ሳይነካት ‹‹ሁን›› በሚለው መለኮታዊ ቃሉ ፈጥሮታል፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የሱረቱ አሊ-ዒምራን 45ኛ አንቀጽ መሰረት ‹‹ከርሱ በሆነው ቃል›› በማለት፡ ‹‹ሁን›› በሚለው መለኮታዊ ቃሉ አማካኝነት እንደሚፈጥረው ለመርየም ብስራት መነገሩን እንረዳለን፡፡ ይህንን ሀሳብ ይበልጥ እንዲያጠናክርልን ደግሞ ወደታች ወረድ ብለን አንቀጽ 47ትን እንመልከተው፡-
” قَالَتْ رَبِّ أَنَّى يَكُونُ لِي وَلَدٌ وَلَمْ يَمْسَسْنِي بَشَرٌ قَالَ كَذَلِكِ اللّهُ يَخْلُقُ مَا يَشَاء إِذَا قَضَى أَمْرًا فَإِنَّمَا يَقُولُ لَهُ كُن فَيَكُونُ ” سورة آل عمران 47
“ጌታዬ ሆይ! ሰዉ ያልነካኝ ስሆን ለኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል? አለች፤ ነገሩ እንደዚህሽ ነዉ፤ አላህ የሚሻዉን የፈጥራል፤ አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ሁን ይለዋል ወድያዉኑም ይሆናል፥ አላት።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 47)፡፡
መርየም ያለ ትዳር-አጋር ሰው የመውለዷ ነገር አስገርሟት፡ እንዴት ሊሆን እንደሚችል በጠየቀች ጊዜ የተሰጣት ምላሽ፡- ‹‹ነገሩ አላህ የሚሻውን ይፈጥራል›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ማለት አላህ አንድን ነገር ከሻው (ከፈለገው) ለመፍጠር የሚከለክለው ነገር የለም! ያለ ምንም ሰበብም (እናትና አባትም ሳይኖሩ) መፍጠር ይችላል ነው፡፡ ከዛም አንቀጹ ይቀጥልና፡- ‹‹አንዳችን በሻ ጊዜ ለርሱ ሁን ይለዋል ወድያዉኑም ይሆናል፥ አላት›› በማለት፡ ከሷ የሚገኘውም ፍጥረት (ዒሳ) “ሁን” በሚለው የአላህ መለኮታዊ ቃል አማካኝነት መሆኑን አበሰራት፡፡ ስለዚህም ዒሳ (ዐለይሂ-ሰለም) ‹‹ሁን›› የሚለው የአላህ መለኮታዊ ቃል ውጤት እንጂ እርሱ ራሱ ‹ሁን› የሚለው ቃል አይደለም፡፡
በተጨማሪም የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂማ-ሰላም) በዚሁ ‹‹ሁን›› በሚለው መለኮታዊ ቃል አማካኝነት መፈጠሩን ለመረዳት ቀጣዩን ጥቅስ መመልከት ጠቃሚ ነው፡-
” يَا أَهْلَ الْكِتَابِ لاَ تَغْلُواْ فِي دِينِكُمْ وَلاَ تَقُولُواْ عَلَى اللّهِ إِلاَّ الْحَقِّ إِنَّمَا الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ رَسُولُ اللّهِ وَكَلِمَتُهُ أَلْقَاهَا إِلَى مَرْيَمَ وَرُوحٌ مِّنْهُ…” سورة النساء 171
“እላንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ፤ በአላህም ላይ እውነትን እንጂ አትናገሩ፤ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ፣ የአላህ መልክተኛ፣ ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም ከርሱ የሆነ መንፈስም ብቻ ነው…” (ሱረቱ-ኒሳእ 171)፡፡
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ‹ወደ መርየም የጣላት (የሁን) ቃሉም› የሚለው የሚያስረዳን፡- ጌታ አላህ ‹‹ሁን›› በሚለው ቃሉ ያስገኘውና የፈጠረው መሆኑን ነው፡፡
ሐ/ የሃይማቱ ሊቃውንት በተለይም የቅዱስ ቁርኣን ተንታኞች (ሙፈሲሪን) ከቁርኣኑ ጥቅስ የተገነዘቡት ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ‹‹ሁን›› በሚለው የአላህ ቃል መፈጠሩን እንጂ፡ እርሱ ራሱ ቃል መሆኑን አይደለም፡፡ የተወሰኑትን ለአብነት እንመልከታቸው፡-
1/ ኢማሙ አሕመድ ኢብኑ ሐንበል፡-
يقول الإمام أحمد – رحمه الله – : ” المعنى في قوله جل ثناؤه { إِنَّمَا الْمَسِيحُ عِيسَى ابْنُ مَرْيَمَ رَسُولُ اللَّهِ وَكَلِمَتُهُ أَلْقَاهَا إِلَى مَرْيَمَ } (النساء : 171) . فالكلمة التي ألقاها إلى مريم : حين قال له كن ، فكان عيسى بكن وليس عيسى هو كن ، ولكن بكن كان . فالكن من الله قول ، وليس الكن مخلوقًا . الرد على الجهمية والزنادقة 43.
ኢማሙ አሕመድ (ረሒመሁላህ) እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ወደ መርየም የጣላት (የኹን) ቃሉ የሚለው፡ ‹‹ሁን›› ባለው ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ እናም ዒሳ ሁን በሚለው ቃል ተገኘ እንጂ፡ ‹ሁን› የሚለው ቃላ እራሱ ዒሳ አልነበረም፡ ነገር ግን ‹‹ሁን›› በሚለው ቃል አማካኝነት ተገኘ:: ‹‹ሁን›› የሚለው ከአላህ ዘንድ የሆነ ቃል ነው እንጂ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ››
2/ ኢብኑ ጀሪር አጥ-ጠበሪይ፡-
10854- حدثنا به الحسن بن يحيى قال، أخبرنا عبد الرزاق قال، أخبرنا معمر، عن قتادة:”وكلمته ألقاها إلى مريم”، قال: هو قوله:”كن”، فكان. جامع البيان-سورة النساء 171
ቀታዳህ (ረሒመሁላህ) ‹‹ወደ መርየም የጣላት (የኹን) ቃሉ›› የሚለውን ሲፈታው እንዲህ አለ፡- እሱ ‹‹ሁን›› አለው ሆነም፡፡ (ተፍሲር ጃሚዑል በያን፡ ሱረቱ-ኒሳእ 171: ቁ 10854)፡፡
3/ ኢብኑ ከሢር፡-
قال شاذان بن يحيى: “ليس الكلمة صارت عيسى ولكن بالكلمة صار عيسى” تفسير ابن كثير: سورة النساء 171.
ሻዛን ኢብኑ የሕያ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- ‹‹ቃሉ እራሱ ዒሳ አልሆነም፡፡ ነገር ግን በቃሉ አማካኝነት ዒሳ ተገኘ›› (ተፍሲር ኢብኑ ከሢር፡ ሱረቱ-ኒሳእ 171)
መ/ ‹‹ከርሱ በሆነው ቃል›› በማለት፡ ጉዳዩን ወደ አላህ አስጠግቶ ‹ከርሱ› ብሎ መናገሩ የሚያስገነዝበን፡- ግኝቱና ስሪቱ ከአላህ የሆነ፣ ባለቤቱና ምንጩ አላህ ሆነ ማለት ነው እንጂ፡ ከአላህ ሀልዎት (ዛት) ቃል ተከፍሎ ወጥቶ በመርየም ማኅፀን አድሮ ሰው ሁኖ ስጋ ለብሶ የመጣ ማለት አይደለም፡፡ አምላካችን አላህ የሚከፋፈል ጌታ አይደለምና፡፡ ይህን ሀሳብ ሊገልጹ የሚችሉ የቁርኣን አንቀጾችን እንመልከት፡-
” وَسَخَّرَ لَكُم مَّا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ جَمِيعًا مِّنْهُ إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآيَاتٍ لَّقَوْمٍ يَتَفَكَّرُونَ ” سورة الجاسية 13
“ለናንተም በሰማያት ያለውንና በምድርም ያለውን ሁሉ በመላ ከርሱ ሲኾን የገራላችሁ ነው፤ በዚህ ለሚያስተነኑ ሕዝቦች ታምራት አለበት።” (ሱረቱል ጃሲየህ 13)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ጌታ አላህ በሰማያትና በምድር ያሉትን በጠቅላላ ለኛ ያገራልን አምላክ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ ታዲያ በገለጻው ውስጥ ‹‹ከርሱ ሲኾን›› የሚል ቃል አልለ፡፡ ይህ ማለት፡ ከአላህ ሀልዎት ተቆርሶ ለኛ የተሰጠን ማለት አይደለም (ሱብሐነሁ ወተዓላ አምማ የሲፉሁ-ዟሊሙን)፡፡
ከዛ ይልቅ ‹‹ከርሱ ሲኾን›› ማለት፡- በሰማያትም ሆነ በምድር ያሉ ነገራት በጠቅላላ ፈጣሪያቸውና ባለቤታቸው አላህ ነው፡፡ ምንጭነታቸውም ከሱ ዘንድ ነው ለማለት ነው፡፡
” وَمَا بِكُم مِّن نِّعْمَةٍ فَمِنَ اللّهِ ثُمَّ إِذَا مَسَّكُمُ الضُّرُّ فَإِلَيْهِ تَجْأَرُونَ ” سورة النحل 53
“ማንኛውም በናንተ ላይ ያለው ጸጋ ከአላህ ነው፤ ከዚያም ችግር በደረሰባቸሁ ጊዜ፣ ወደርሱ ብቻ ትጮሃላችሁ።” (ሱረቱ-ነሕል 53)፡፡
እዚህም ተመሳሳይ ሀሳብ እናገኛለን፡፡ በኛ ላይ የተዋለው ጸጋ በጠቅላላ ከአላህ ነው ተብሎ እየተነገረን ነው፡፡ “ከአላህ ነው” ማለት ግን፡- ከርሱ ዘንድ የተሰጠ፡ አስገኚውና ፈጣሪው እሱ ብቻ የሆነ ማለት እንጂ፡ ከህላዌው የተቆረሰ ማለት አይደለም፡፡
በዛው መልኩ የመርየም ልጅ አል-መሲሕ ዒሳም (ዐለይሂማ-ሰላም) በአላህ መለኮታዊ ቃል አማካኝነት መፍፈጠሩን ለመግለጽ ‹‹ከርሱ በሆነው ቃል›› ማለቱ፡- ከአላህ ዘንድ በሆነው ቃል የተገኘና የተፈጠረ ማለት እንጂ: ከአላህ የወጣ ቃል ነው ማለት አይደለም፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡ ወሰለላሁ ወሰለመ ኣላ ነቢዪና ሙሐመድ፣ ወዐላ ኣሊሂ፣ ወሳሕቢሂ ወሰለም፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


