በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኛ በሆነው፡፡
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
ይህን ጽሁፍ እንዳዘጋጅ ሰበብ የሆንከኝ ወንድሜ አላህ ኸይር ጀዛህን ይክፈልህ፡፡ በ inbox በኩል፡ አንድ መሃይምነትና ጭፍን ጥላቻ የተቀላቀለበትን የካፊሮችን ጽሁፍ ለጥፎልኝ ምላሽ እንድሰጥበት ጠይቆኝ ነበር፡፡
ጽሁፉ ያተኮረው በነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ላይ ነው፡፡ ጭብጡም፡- ‹‹ለምን ለሳቸው ‹ፊዳከ አቢ ወኡሚ› ይባላሉ? ለምን በየቀኑ ‹ባለውለታዬ ሐቢብ ተምሳሌቴ፣ ስላንቱ ይሰዉ እናቴና አባቴ› በማለት ያስነብቡናል? ደግሞም ጉዳዩ መረጃ የሌለው የስሜት መገንፈልና የመድረክ ሞቅታ የወለደው ነው፡፡ ፊዳ ማለት መስዋእት ነውና፡ መስዋእት የሚገባው ደግሞ ለሕያው አምላክ ነው፡፡ ለእሳቸው መስዋእት ማቅረብ ደግሞ፡ እሳቸውን በአምላክ ቦታ ማስቀመጥ ነው፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አምላክ አድርጋችሁ ይዛችኋል የምንለው፡፡››
ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል፡፡ የኛም መልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
1ኛ. በጽሁፉ ላይ እጅግ የከፋ ጥልቅ ጥላቻና ጭፍን መሃይምነት በጉልህ ይታያል፡፡ በተለይ የአካውንቱን ባለቤት ሙሉ ጽሁፍ ላነበበ ሰው አይደለም ለሙስሊም፡ ገለልተኛ ለሆነ ሰውና በንጹህ አእምሮው ለሚመዝን ሰው ለመስማት የሚሰቀጥጡ ስድቦችን ያገኛል፡፡ ይህም ችግሩ ከጸሀፊው ሳይሆን፡ ከተኮተኮተበት የትምህርት መሰረት ነው፡፡ ችግሩ ዛፉ ላይ ነው፡፡ አጠጥተው ያሳደጉት ውሀ የተመረዘ ነበር፡፡ ታዲያ ከፍሬው ምን መልካም ነገር እንጠብቃለን፡፡ ይህ አይነትና መሰል ስድቦች ደግሞ ለነሱ (ለካፊሮች) አፍ መፍቻ ቋንቋ እስኪመስል ድረስ ተዋህዷቸዋል፡፡ ምን ያድርጉ ሁሌም የሚሰሙት ስብከት ‹‹የምላስ ወለምታ፣ የሐሜት አስከፊነት፣ ነገር ማዋሰድና አደጋው፣ የውሸት አደጋ›› እና መሰል ነገራትን ሳይሆን፡ ገደል ውስጥ የሚከቱ ትምህርቶችን ነው፡፡ ታዲያ የሚገርመን ባይሳደቡ ነው፡፡ እጅጉኑ የሚያስቀውና የሚያስገርመው፡ በዚያው ማንነታቸው ተመልሰው መጥተው ‹‹ክርስትና ፍቅር›› ናት! ይሉናል፡፡ እውነትም ፍቅር! ይኸው በተግባር አየነው እኮ! ለካ አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ብቻ አይደለም፡ ልብም ጭምር ይታያል፡፡ እንዲህ የሚለው የአላህ ቃል መጠቀሱ ተገቢ ነው፡-
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከናንተ ሌላ ምስጢረኛን አትያዙ፤ ማበላሸትን አይገቱላችሁም፤ ጉዳታችሁን ይወዳሉ፥ ጥላቻይቱ ከአፎቻቸዉ በእርግጥ ተገለጸች። ልቦቻቸዉም የሚደብቁት ይበልጥ ትልቅ ነዉ። ልብ የምታደርጉ እንደሆናችሁ ለናንተ ማብራራያዎችን በእርግጥ ገለጽን።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 118)፡፡
2ኛ. ወደ ነጥቡ ስንመለስ፡- ፊዳእ ማለት ቤዛ ማለት ነው፡፡ ይህም አንድን ነገር ለማስቀረትና ለማስተው በምትኩ የሚከፈል ክፍያ ይባላል፡፡ በዕዳ የተያዘ ሙስሊም ወንድምህን ከክስና ከእስር ነጻ ለማውጣት ለባለ መብቱ የገንዘቡን መጠን በመስጠት ወንድምህን ነጻ ብታወጣው ፊዳእ ሆንከው (ተበዤኸው) ይባላል፡፡ ይህንን ሀሳብ የሚገልጹ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችን በመጠኑ እንመልከት፡-
” وَفَدَيْنَاهُ بِذِبْحٍ عَظِيمٍ ” سورة الصافات 107
“በታላቅ ዕርድም (መስዋእት) ተቤዠነው” (ሱረቱ-ሷፍፋት 107)፡፡
ጌታ አላህ ለነቢዩላህ ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) ልጁን ኢስማዒልን (ዐለይሂ-ሰላም) እንዲያርደው በህልሙ በማሳየት ትእዛዝን ይሰጠዋል፡፡ ኢብራሂምም የጌታውን ትእዛዝ ለልጁ ባሳወቀው ጊዜ፡ ኢስማዒልም ለአላህ ትእዛዝ ፈቃደኛ ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ አባት የመጀመሪያ ልጁን ለማረድ፡ ልጅም ለመታረድ በዝግጅት ላይ ሳሉ፡ ‹ኢብራሂም ሆይ!› የሚልን ጥሪ ይሰማሉ፡፡ ኢብራሂምም ህልሙንም በተግባር በማረጋገጡ፡ ለጌታውም ትእዛዝ እጅ በመስጠቱ፡ ፈተናውን ማለፉ ይነገረውና ልጁን እንዳያርድ በመከልከል በምትኩ እጅግ የደለበ የበግ ሙክት ቤዛ ሆኖ ይሰጠዋል፡፡ በተጨማሪም በሚስቱ በሳረት በኩል ኢስሐቅንም እንደሚወልድ ብስራት ይደርሰዋል፡፡(ሱረቱ-ሷፍፋት 101-113)፡፡
አሁን የሆነው ነገር፡ በኢስማዒል ምትክ በጉ ቤዛ ሆነ፡ ታረደ ነው እንጂ፡ አላህ ለኢብራሂም መስዋእትን አቀረበ እንላለን እንዴ? አላህ እንታዘዘው ዘንድ መስዋእትን የምናቀርብለት አምላክ እንጂ፡ እራሱ መስዋእት የሚያቀርብ አይደለም፡፡
” يُبَصَّرُونَهُمْ يَوَدُّ الْمُجْرِمُ لَوْ يَفْتَدِي مِنْ عَذَابِ يَوْمِئِذٍ بِبَنِيهِ ” سورة المعارج 11
“ዘመዶቻቸውን) ያዩዋቸዋል አመጠኛው ከዚያ ቀን ስቃይ፣ (ነፍሱን) በልጆቹ ሊበዥ ይመኛል።” (ሱረቱል መዓሪጅ 11)፡፡
በዕለተ ቂያማህ በፍርዱ ቀን፡ አመጠኛ (ከሀዲ) የሆነ ሰው፡ ቤተሰቦቹ በሱ ቦታ ቤዛ ሁነው፡ እነሱ የሱን ኃጢአትና ቅጣት ተሸክመው ቢቀጡና፡ እሱ ነፍሱን ቢያድን እንደሚመኝ ጌታ አላህ ይነግረናል፡፡ ያ ማለት ግን ሰውየው ቤተሰቡን መስዋእት አድርጎ ያቀርባል ማለት አይደለም፡፡ በሁለቱም ቦታዎች የገባው የዐረብኛ ቃል ግን ‹ፊዳእ› መሆኑን ልብ በሉ፡፡
ታዲያ አንድ ሙስሊም ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ‹‹ፊዳከ አቢ ወኡምሚ›› (አባቴም እናቴም ለእርስዎ ይሰዉሎት) ቢል፡ ትርጉሙ ምንድነው ካሉ፡- የእርሶን ክፋት አያሳየኝ፣ እንዲሁም አያሰማኝ፡፡ የእርሶን መጥፎ ነገር ከምሰማ በምትኩ እናቴና አባቴ ለእርስዎ ቤዛ ይሁንልዎ ማለት ነው፡፡ እንግዲያውስ ይህ ለሳቸው ያለን ፍቅር፡ ያቃጠላቸው ካፊሮች፡ መልክቱን ሳያውቁና በአግባቡ ጠይቀውም ሳይረዱ፡ ይህ ለእሳቸው መስዋእት ማቅረብ ነው! ይሉናል፡፡ በክርስትና አስተሳሰብ ተመልክታችሁት ከሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ እውነታውና እንደ ኢስላም ከሆነ ግን ስህተት ነው፡፡ የፊትን ትክክለኛ ገጽታ ለማወቅ በተስተካከለ መስታወት እንጂ በተሰነጠቀና በቆሸሸ መስታወት መመልከቱ አግባብ አይደለም፡፡ ውጤቱ ጥሩ ስለማይሆን፡፡
3ኛ. እኛ ነቢዩ ሙሐመድንም ሆነ ዒሳን (ዐለይሂማ-ሰላም) አናመልክም፡፡ ሁለቱም የአላህ ፍጥረቶችና ባሪያዎች ስለሆኑ አምልኮ አይገባቸውም፡፡ እንዲሁም መላእክትን አናመልክም፡፡ በስማቸው ቀናትን መድበን፡ ጅብሪል ድረስልኝ፣ ሚካኢል እርዳኝ፣ እገሌ ተከተለኝ፣ እንትና ጥበቃህ አይለየኝ የመሳሰሉትን ሁሉ አንጠቀምም፡፡ ጥበቃውንና እርዳታውን፣ መከተሉንና ማገዙን ለመላእክት፣ ለጻድቃን፣ ለሰማእታትና ለቅዱሳን ከሰጠናቸው፡ ታዲያ አላህ ምን ቀረው? በጣም የሚገርመው በዚህ አይነት የተሳሳተ አምልኮ ውስጥ የተዘፈቀ ሰው፡ ተመልሶ ሙስሊሙን ሌላ ታመልካላችሁ ማለቱ ነው፡፡ ሰው እራሱን በከንቱ አምልኮ ተብትቦ፡ ከተተበተበበት ገመድ ሳይላቀቅ፡ ሌላውን በሌለበት ጥፋት መክሰስ ምን የሚሉት ድፍረት ነው?
እናንተ በዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሰላም ላይ ወሰንን አልፋችሁ፡ ከአላህ ባርነት ወደ ልጅነት፣ ከነቢይነትና መልክተኝነት ወደ አምላክነት እንዳሸጋገራችሁትና በዚሁ ስራችሁም ኩፍር (ክህደት) ውስጥ እንደገባችሁት፡ እኛም በነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ላይ ከፍቅርና ከውዴታ የተነሳ ወሰን አልፈን እንዳንሳሳት፡ ከነፍሳችን በላይ ለኛ የሚራሩት ታላቁ ነቢይ እንዲህ አሉን፡-
عَنِ ابْنِ
عَبَّاسٍ، سَمِعَ عُمَرَ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ، يَقُولُ عَلَى المِنْبَرِ: سَمِعْتُ النَّبِيَّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ يَقُولُ: «لاَ تُطْرُونِي، كَمَا أَطْرَتْ النَّصَارَى ابْنَ مَرْيَمَ، فَإِنَّمَا أَنَا عَبْدُهُ، فَقُولُوا عَبْدُ اللَّهِ، وَرَسُولُهُ» البخاري 3445
ዐብዱላህ ኢብኑ አባስ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ዑመር ኢብኑል-ኸጣብን (ረዲየላሁ ዐንሁ) በሚንበር ላይ ሁኖ እንዲህ ሲል ሰማው፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ሲሉ ሰማሁ፡- “ክርስቲያኖች ዒሳን ያለ ደረጃው ከፍ እንዳረጉት እኔንም ከፍ እንዳታረጉኝ፡፡ እኔ የአላህ ባሪያው ነኝና የአላህ ባሪያና መልክተኛው በሉኝ”›› (ቡኻሪይ)፡፡
4ኛ. ትንሽ ያሳቀኝ ደግሞ ይህ ነው፡፡ ፊዳከ የምትለው በመድረክ ሞቅታ የተፈበረከች እንጂ ምንም ማስረጃ የላትም፡፡ በርግጥ ጥያቄው ከሙስሊም ቢመጣ ምነው እስከዛሬ የት ነበርክ? ያስብላል፡፡ ግን የራሱን መጽሐፍ እንኳ በወጉ ካላነበበ ሰው መገኘቱ ብዙም እንዳልገረም አድርጎኛል፡፡ ለማንኛውም የዚህን ቃል መሰረት ከየት እንደሆነ ማወቁ ለሙስሊሞች ጠቃሚ በመሆኑ እንመልከተው፡-
ሀ. ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም)
ይህን ቃል ከተጠቀሙት ሰዎች የመጀመሪያው ታላቁ ነቢይ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እራሳቸው ናቸው፡፡ በእሁድ ዘመቻ ወቅት ሰዕድ ኢብኑ ማሊክን (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አሉት፡-
عَنْ عَلِيٍّ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ، قَالَ: مَا سَمِعْتُ النَّبِيَّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ جَمَعَ أَبَوَيْهِ لِأَحَدٍ إِلَّا لِسَعْدِ بْنِ مَالِكٍ، فَإِنِّي سَمِعْتُهُ يَقُولُ يَوْمَ أُحُدٍ: «يَا سَعْدُ ارْمِ فِدَاكَ أَبِي وَأُمِّي» رواه البخاري 4059 ومسلم 2411
ዐሊይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- “የአላህ ነቢይ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ወላጆቻቸውን (አባትና እናት) በመሰብሰብ ለሰዕድ ኢብኑ ማሊክ እንዳሉት ለማንም ሲሉ አልሰማኋቸውም፡፡ እኔ የእሑድ (ዘመቻ) ቀን እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡- ‹‹ሰዕድ ሆይ! (በጠላት ላይ በትርህን) ወርውር፡፡ እናቴና አባቴ ፊዳእ ይሁኑልህ››” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ጉዳዩ የፍቅርን ደረጃ ለመግለጽ እንጂ መስዋእት ለማቅረብ አለመሆኑን ይበልጥ የምንረዳው፡ የአላህ ነቢይ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ለሰዕድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ይህን በተናገሩ ጊዜ፡ ሁለቱም ወላጆቻቸው በህይወት አልነበሩም፡፡ ታዲያ ፊዳከ ማለት ፍቅርን ለመግለጽ እንጂ መስዋእት ለማቅረብ ነውን? ነገሩ አንድን ከሶስት መለየት ላልቻለ አእምሮ ይሄ ለመረዳት ቢከብደው የሚደንቅ አይደለም፡፡
ለ. አቡ በክር አስ-ሲዲቅ (ረዲየላሁ ዐንሁ)፡-
ከነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በኋላ የኸሊፋነቱን ቦታ በመያዝ ኡምማውን የመሩት አቡ በክር (ረዲየላሁ ዐንሁ) ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሚንበር ላይ ይቀመጡና፡- ‹‹አላህ ባሪያውን፡- ከፈለገ የዚህ ዓለምን ጌጦች የፈለገውን ያህል ሊሸልመው፣ ወይንም አላህ ዘንድ ያለውን ሊሰጠው አማረጠው፡፡ (ያ ባሪያም) አላህ ዘንድ ያለውን መረጠ›› ሲሉ፡ አቡበክር (ረዲየላሁ ዐንሁ) በጣም አለቀሱ፡፡ እንዲህም አሉ፡- ‹‹አባቶቻችንና እናቶቻችን ለርሶ ፊዳእ (ቤዛ) ይሁንልዎት›› ለካ ያ የአላህ ባሪያ የተባለውና ምርጫ የተሰጠው ነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) መሆናቸው ለአቡበክር ተገልጾላቸው ነበር፡፡ ስለዚህም የሳቸው መለየት ስላላስቻላቸው ‹‹በርሶ ምትክ አባቶቻችንና እናቶቻችን ፊዳእ ይሁንልዎት›› አሉ፡፡ (ቡኻሪይ፣ ሙስሊም፣ ቲርሚዚይ)፡፡ የዚህን ሙሉ ቃል በዐረብኛ ለሚፈልግ ሰው ደግሞ ይኸው፡-
عَنْ أَبِي سَعِيدٍ الخُدْرِيِّ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ، أَنَّ رَسُولَ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ جَلَسَ عَلَى المِنْبَرِ فَقَالَ: «إِنَّ عَبْدًا خَيَّرَهُ اللَّهُ بَيْنَ أَنْ يُؤْتِيَهُ مِنْ زَهْرَةِ الدُّنْيَا مَا شَاءَ، وَبَيْنَ مَا عِنْدَهُ، فَاخْتَارَ مَا عِنْدَهُ» فَبَكَى أَبُو بَكْرٍ وَقَالَ: فَدَيْنَاكَ بِآبَائِنَا وَأُمَّهَاتِنَا، فَعَجِبْنَا لَهُ، وَقَالَ النَّاسُ: انْظُرُوا إِلَى هَذَا الشَّيْخِ، يُخْبِرُ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ عَنْ عَبْدٍ خَيَّرَهُ اللَّهُ [ص:58] بَيْنَ أَنْ يُؤْتِيَهُ مِنْ زَهْرَةِ الدُّنْيَا، وَبَيْنَ مَا عِنْدَهُ، وَهُوَ يَقُولُ: فَدَيْنَاكَ بِآبَائِنَا وَأُمَّهَاتِنَا، فَكَانَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ هُوَ المُخَيَّرَ، وَكَانَ أَبُو بَكْرٍ هُوَ أَعْلَمَنَا بِهِ، وَقَالَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: «إِنَّ مِنْ أَمَنِّ النَّاسِ عَلَيَّ فِي صُحْبَتِهِ وَمَالِهِ أَبَا بَكْرٍ، وَلَوْ كُنْتُ مُتَّخِذًا خَلِيلًا مِنْ أُمَّتِي لاَتَّخَذْتُ أَبَا بَكْرٍ، إِلَّا خُلَّةَ الإِسْلاَمِ، لاَ يَبْقَيَنَّ فِي المَسْجِدِ خَوْخَةٌ إِلَّا خَوْخَةُ أَبِي بَكْرٍ» البخاري 3904 ومسلم 2382 والترمذي.
ሐ. አባ ጠልሓህ (አል-አንሷሪይ)፡-
የአላህ ነቢይ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከባለቤታቸው ሶፊያህ ቢንት ሑየይ (ረዲላሁ ዐንሃ) ጋር በአንድ ግመል ተፈናጠው ወደ አንድ ጉዞ እየተጓዙ ሳለ፡ የአላህ ቀደር ይሆንና እሳቸውና ባለቤታቸው ከግመሉ ላይ ይወድቃሉ፡፡ አባ ጠልሐም በድንገት ተወርውሮ ከራሱ ግመል ላይ ይወርድና በፍጥነት ወደ መልክተኛው በመምጣት፡- ‹‹አላህ እኔን ለርሶ ፊዳእ (ቤዛ) ያርገኝ፡፡ ምን የተጎዱት ነገር አልለ? ሲላቸው፡ እሳቸውም፡- እኔ ምንም አልሆንኩም፡ ግን እሷን አደራ ተጎድታ ከሆነ›› ብለው መለሱለት፡፡ (ቡኻሪይ 6185)፡፡
አንባቢን ላለማድከም እንጂ በጉዳዩ ላይ ብዙ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ታዲያ የመጽሐፋቸውን መግቢያውንና መውጫውን በቅጡ ያልተረዱ ሰዎች፡ ከምን ተነስተው ነው ይህ አባባል የመድረክ ላይ ሙቀትና የጋለ ስሜት እንጂ መረጃ አልባ ነው ያሉት? ለነገሩ መሃይም አፉ እንደ መቀመጫው ነው፡ ንግግሩ ደግሞ እንደ ቆሻሻው ነው አይደል የሚባለው?
5ኛ. በመጨረሻም ለነዚህ ልባቸው በጥላቻ ለታወረ ወገኖች የምንላቸው ነገር ቢኖር፡- ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንኳን ወላጆቻችን ዓለሙ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ቢቀርብ አላህ ዘንድ ካላቸው ደረጃ፡ አንድ እጁንም አይሞላም፡፡ ምክንያቱም ይህቺ ምድር ውበቷ፡ እሷንና በላይዋ ላይ ያሉትን የፈጠረውን አንድ አምላክ ስናመልክባት ነው፡፡ ይህ ትምሕርት ደግሞ እሳቸው ነቢይ ሆነው ባይላኩ ኖሮ መች ይገኝ ነበር?፡፡ እኛም በክህደት ጨለማ ተውጠን፡ በአምላክ ፈንታ ሰውን አምልከን፡ የክህደት ጉድጓድ ውስጥ በወደቅን ነበር፡፡ ዓለሙም በጨለመ ነበር፡፡ አልሐምዱ ሊላህ እሳቸውን ነቢይ አድርጎ ለላከልን አላህ፡፡
“ከኢስላም ሌላ ሃይማኖትን የሚፈልግ ሰዉ፣ ፈጽሞ ከርሱ ተቀባይ የለዉም፤ እርሱም በመጨረሻይቱ ዓለም ከከሳሪዎች ነዉ።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 85)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


