በኡስታዝ አቡ ሐይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
عَنْ أَبِي سَعِيدٍ الخُدْرِيِّ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ، خَرَجَ رَسُولُ اللَّهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فِي أَضْحًى أَوْ فِطْرٍ إِلَى المُصَلَّى، ثُمَّ انْصَرَفَ، فَوَعَظَ النَّاسَ، وَأَمَرَهُمْ بِالصَّدَقَةِ، فَقَالَ: «أَيُّهَا النَّاسُ، تَصَدَّقُوا»، فَمَرَّ عَلَى النِّسَاءِ، فَقَالَ: «يَا مَعْشَرَ النِّسَاءِ، تَصَدَّقْنَ، فَإِنِّي رَأَيْتُكُنَّ أَكْثَرَ أَهْلِ النَّارِ» فَقُلْنَ: وَبِمَ ذَلِكَ يَا رَسُولَ اللَّهِ؟ قَالَ: «تُكْثِرْنَ اللَّعْنَ، وَتَكْفُرْنَ العَشِيرَ، …» رواه البخاري ومسلم.
አቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በዒደል አድሓ (ዒደል ፊጥር) ወደ መስገጃው ስፍራ ሄዱ፡፡ ከዛም ወደ ህዝቡ በመዞር ሰዎችን መከሯቸው፡፡ ሶደቃንም (ልገሳ) እንዲያወጡ አዘዟቸው፡፡ እንዲህም አሉ፡- ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! ሶደቃን አብዙ››፡፡ በሴቶች በኩልም አለፉና፡- ‹‹እናንተ ሴቶች ሆይ! ሶደቃን አብዙ፡፡ እኔ ከጀሀነም ሰዎች አብዛኛዎቹ ሆናችሁ አይቻችኋለሁና›› አሉ፡፡ ሴቶቹም፡- ‹‹አንቱ የአላህ መልክተኛ ሆይ! ይህ የሆነው በምን ምክንያት ነው?›› ብለው ጠየቁ፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹እርግማንን ታበዛላችሁ፣ የባለቤታችሁን ውለታ ትክዳላችሁ…›› አሉ፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ይህንን ነቢያዊ ሐዲሥ መሰረት በማድረግ አንዳንድ ክርስቲያን ወገኖች፡ በእስልምና አብዛኞቹ መስሊም ሴቶች ጀሀነም እንደሚገቡ ይታመናል በማለት የተሳሳተ ምልክታ ይዘው ሌላውንም ለማሳሳት ይሞክራሉ፡፡ ጭራሹኑ የሴቶችን የመዳን ተስፋ ያደበዝዘዋልም ሲሉ ይከሳሉ፡፡ ከኛ ሙስሊሞች ደግሞ የሚጠበቀው አገነዛዘቡ የተበደለውን ሐዲሥ የተቃና ማድረግ ስለሆነ፡ እውነትን ለሚፈልግ ሰው ይኸው ትክክለኛውን ማብራሪያ እንካችሁ ብለናል፡-
1ኛ. በሐዲሡ ላይ የተቀመጠው ኃይለ ቃል ‹‹ሴቶች›› የሚል እንጂ ‹ሙስሊም ሴቶች› የሚል እንዳልሆነ ልብ ይበሉ፡፡ ‹‹ሴት›› ከተባለ የአደምን ዘሮች፡ የሐዋእን ልጆች በጠቅላላ የሚመለከት እንጂ፡ ሙስሊሞችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ስህተት እሱ ነውና፡፡ በሌላም ሐዲሥ ላይ እንደተነገረው፡- ‹‹እኔ እሳትን ተመለከትሁ፡፡ አብዝኃኛው ነዋሪዎቿ ሴቶች ናቸው›› ይላል እንጂ ‹ሙስሊም ሴቶች› አይልም፡፡
2ኛ. ምክንያቱስ ምንድነው? ብለንም ከጠየቅን፡ መልስ የሚሆነው፡- ከላይ በሐዲሡ ላይ እንደተገለጸው ሁለት የኃጢአት ባሕሪዎች እነሱ ላይ ጎልቶ መታየቱ ነው፡፡ እሱም፡- ‹‹እርግማንን ማብዛት›› እና ‹‹የባልን ውለታ መካድ›› ናቸው፡፡ ሴት ሆና መፈጠሯ አይደለም ችግር ያመጣባት፡፡ ሙስሊም መሆኗ አይደለም እንቅፋት የሆነባት፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ኃጢአት ላይ መዘፈቋ እንጂ!፡፡
ይህንን ስራ ‹እርግማንና ውለታ መካድ› ወንዱም ሊሰራው ይችላል፡፡ የሴቶች የግል መለያቸው አይደለም፡፡ ሆኖም በብዛት ጎልቶ የሚታየው እነሱ ላይ ነውና፡፡
አንድ ሚስት ባለቤቷ ለብዙ ጊዜያት መልካም ሲውልላት ቆይቶ አንድ ቀን እሷን የሚጎዳ ነገር ቢፈጽም፡- እስከ-ዛሬ ምን አድርገህልኝ ታውቃለህ? በማለት ያለፉ ጣፋጭ ዘመናትን ትክዳቸዋለች (አላህ በእዝነቱ የጠበቃት ስትቀር)፡፡
3ኛ. ታዲያ መፍትሄው ምንድነው ምንድነው? ብለን ጥያቄ ማንሳቱ አግባብነት አለው፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ይህንን ለሴቶች የተናገሩት፡ ለነሱ ከነፍሳቸው በላይ በማዘን ከወዲሁ እንዲጠነቀቁ እንጂ፡ ተስፋ ለማስቆረጥ አይደለም፡፡ ደካማ ጎኑ የተነገረው ሰው አስተዋይ ከሆነ፡ ድክመቱን ለመሸፈን ይጥራል እንጂ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ በዚህ ሐዲሥ ላይ ደግሞ ችግሩ ብቻ ሳይሆን የተወሳው መፍትሄውም ጭምር ነው፡፡ መፍትሄውም፡- ሶደቃን አብዙ ብለዋል፡፡ አዎ! ሶደቃ ኃጢአትን ያጠፋልና፡፡
ጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ(ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “…ሶደቃህ ውሀ እሳትን እንደሚያጠፋው ኃጢአትን ያጠፋል…” (ሶሒሑ ተርጊብ ወት-ተርሒብ 866)፡፡
ደግሞም እህቶች ሆይ! ባለቤቶቻችሁን በውለታቸው አመስጋኝ ሚስቶች ሁኑ፡፡ ከመራገምም እራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ሐዲሡ፡- ‹ሙስሊም ተሳዳቢም ተራጋሚም አይደለም› ይላልና፡፡
አላህን የምትፈራ ሙስሊም ሴት እራሷን ከነዚህ ሁለት መጥፎ ባሕሪያት ማራቅና ማግለል ትችላለች፡፡ እሱም፡- ሃይማኖቷን በአግባቡ በመማር፣ እንዲሁም ጥሩ አርአያ መሆን ከሚችሉ እህቶቿ ጋር ወዳጅነትን በመመስረት፡፡ ስለዚህ ሐዲሡ ተስፋ አስቆራጭ ሳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ በማድረግ የተነገራችሁን ነገር በማስተዋል እንድትፈጽሙ ለናንተ በማሰብና በመጨነቅ የተሰጠ ነቢያዊ ትምህርት ነው፡፡ (ፊዳከ አቢ ወኡሚ ያረሱለሏህ)፡፡
4ኛ. ትልቁ ቁም ነገር እዚህ ጋር ነው፡፡ አንዲት ሙስሊም ሴት በኃጢአቷ ምክንያት አላህ በቀብር ቅጣት፣ ወይም በቂያም ቀን ጭንቀት፣ ወይም በነቢያችን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሸፋዐህ (ምልጃ) ያ ካልሆነም ከራሱ በመነጨ ራሕመት ልማርሽ ባይላትና በእሳት ሊቀጣት እንኳ ቢወስን፡ በእሳት ውስጥ ዘውታሪ አይደለችም አትሆንምም፡፡ የጥፋቷን ያህል ተቀጥታ ወደ ጀነት መመለሷ የማይቀር ነው፡፡ በጀሀነም መዘውተር የከሀዲያን እንጂ የሙስሊሞች አይደለምና፡፡ ጀነትን ከሙስሊም ውጪ ማንም አይገባትምና፡፡ ተከታዩ ሐዲሥ ይህን ይገልጻል፡-
عَنْ عَبْدِ اللَّهِ، قَالَ: كُنَّا مَعَ النَّبِيِّ فِي قُبَّةٍ، فَقَالَ: «أَتَرْضَوْنَ أَنْ تَكُونُوا رُبُعَ أَهْلِ الجَنَّةِ» قُلْنَا: نَعَمْ، قَالَ: «أَتَرْضَوْنَ أَنْ تَكُونُوا ثُلُثَ أَهْلِ الجَنَّةِ» قُلْنَا: نَعَمْ، قَالَ: «أَتَرْضَوْنَ أَنْ تَكُونُوا شَطْرَ أَهْلِ الجَنَّةِ» قُلْنَا: نَعَمْ، قَالَ: «وَالَّذِي نَفْسُ مُحَمَّدٍ بِيَدِهِ، إِنِّي لَأَرْجُو أَنْ تَكُونُوا نِصْفَ أَهْلِ الجَنَّةِ، وَذَلِكَ أَنَّ الجَنَّةَ لاَ يَدْخُلُهَا إِلَّا نَفْسٌ مُسْلِمَةٌ،
ዐብዱላህ ኢብኒ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ጋር (በሚና) ድንኳን ስር እያለን እንዲህ አሉን፡- ‹‹የጀነት ሰዎች ሩብ እናንተ ብትሆኑ ትወዳላችሁን?›› አዎን ! አልናቸው፡፡ በድጋሚ ‹‹የጀነት ሰዎች 1/3 እናንተ ብትሆኑ ትወዳላችሁን?›› ሲሉን፡ አዎን! አልናቸው፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ‹‹የጀነት ሰዎች ግማሹ እናንተ ብትሆኑ ትወዳላችሁን?›› ሲሉን አዎን! አልናቸው፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹የኔ ነፍስ በእጁ በሆነችው በአላህ እምላለሁ፡፡ እናንተ የጀነት ሰዎች ግማሹ እንደምትሆኑ ባለ ሙሉ ተሰፋ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ጀነትን ሙስሊም የሆነ ነፍስ እንጂ ሌላው አይገባትምና›› አሉ፡፡ (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
5ኛ. እነዚህ ክርስቲያን ወገኖች እንደሚሉት ‹‹በጀሀነም ውስጥ ሴቶች በዝተው አየሁ›› የሚለው ሐዲሥ ፡ ሴቶችን ለተውበትና ለመልካም ስራ ከማነሳሳት ይልቅ ተስፋ የሚያስቆርጥ ከሆነ (አይደለም እንጂ)፡ ታዲያ በእናንተ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የሐብታሞችን ገነት የመግባት ተስፋ የሚያሟጥጥ አነጋገርን ምን ልትሉት ነው?፡፡ አንድ ሐብታም ወደ መንግስተ ሰማያት መግባትን ፈልጎ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በጠየቀው ጊዜ የኢየሱስ ምላሽ ምን እንደነበር ከመጽሐፉ እናንብብ፡-
‹‹እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው። እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።
ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው። ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው። ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ። ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው። ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ። ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ። ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።›› (የማቴዎስ ወንጌል ምዕ 19 ቁ 16-26)፡፡
ስለዚህ ሐብታም ክርስቲያኖች የግመልን በመርፌ መግባት ተስፋ ያድርጉ ወይስ…?
6ኛ. በመጨረሻም እህቶቼ ሆይ! እነዚህን የጌታችሁን ምክር ስሙና በስራ ላይ አውሉት፡፡ መዳንን ከፈለጋችሁ፡፡
“ከወንድ ወይንም፣ ከሴት፣ እርሱ አማኝ ሆኖ ከበጎ ሥራዎች አንዳች የሚሠራም ሰው እነዚያ ገነትን ይገባሉ፤ በተምር ፍሬ ላይ ያለችን ነጥብ ያህል እንኳ አይበደሉም።” (ሱረቱ-ኒሳእ 124)፡፡
“ከወንድ ወይም ከሴት እርሱ አማኝ ሆኖ በጎን የሠራ መልካም ኑሮን በእርግጥ እናኖረዋለን፤ ይሠሩትም ከነበሩት ነገር በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።” (ሱረቱ-ነሕል 97)፡፡
“መጥፎን የሠራ ሰው፣ ብጤዋን እንጅ አይመነዳም፤ እርሱ መእምን ሆኖ ከወንድ ወይም ከሴት በጎን የሠራም ሰው፣ እነዚያ ገነትን ይገባሉ፤ በርሷ ውስጥ ያለ ቁጥጥር ይመገባሉ።” (ሱረቱ ጋፊር (ሙእሚን) 40)፡፡
አምላካችን አላህ ሆይ! በኢስላም ላይ ጽናትን፣ በሞት ጊዜ ሸሀደተይንን፣ በቀብር ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽን ወፍቀን፡፡ በራሕመትህ ከቂያም ቀን ንዳድ እና ከእሳትም ጠብቀን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


