በኡስታዝ አቡ ሐይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
” إِنَّ الْأَبْرَارَ لَفِي نَعِيمٍ * عَلَى الْأَرَائِكِ يَنْظُرُونَ * تَعْرِفُ فِي وُجُوهِهِمْ نَضْرَةَ النَّعِيمِ * يُسْقَوْنَ مِنْ رَحِيقٍ مَخْتُومٍ * خِتَامُهُ مِسْكٌ وَفِي ذَلِكَ فَلْيَتَنَافَسِ الْمُتَنَافِسُونَ ” سورة المطففين 26-22
“እውነተኞቹ ምእመናን በእርግጥ በድሎት (ገነት) ውስጥ ናቸው። በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ሆነው ይመለከታሉ። በፊቶቻቸው ላይ የድሎትን ውበት ታውቃለህ። ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጥጠጣሉ። ማተሚያው ሚስክ ከሆነ፤ በዚህም ተሽቀዳዳሚዎች ይሽቀዳደሙ።” (ሱረቱል ሙጠፊፊን 22-26)፡፡
አንድ ክርስቲያን ወገኔ በዚህ የቅዱስ ቁርኣን ክፍል ውስጥ ‹‹ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጠጣሉ›› የሚለው ቅዱስ ቃል ላይ በመመርኮዝ ሁለት ጥያቄዎችን ጠይቆኛል፡፡ እነሱም፡-
1ኛ. አላህ በናንተ ላይ እርም ያደረገው አልኮሆል መጠጦችን መጠጣት ነው ወይስ መስከር?
2ኛ. ደግሞስ በዚህ ዓለም የተከለከላችሁትን መጠጥ እንዴት በጀነት ተፈቀደላችሁ? በማለት ጥያቄውን አስከተለ፡፡
ለእነዚህ ጥያቄዎች እኔ ያለኝ ምላሽ እንዲህ ይቀርባል፡-
1ኛ. ኢስላም አስካሪ መጠጥን በጽኑ ያወግዛል፡፡ ከታላላቅ ኃጢአቶችም ይመድበዋል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! የሚያሰክር መጠጥ፣ ቁማርም፣ ጣዖታትም አዝላምም (የመጠንቆያ እንጨቶች) ከሰይጣን ሥራ የሆኑ እርኩስ ብቻ ናቸው፤ (እርኩስን) ራቁትም ልትድኑ ይከጀላልና። ሰይጣን የሚፈልገው በሚያሰክር መጠጥና በቁማር በመካከላችሁ ጠብንና ጥላቻን ሊጥል፣ አላህን ከማውሳትና ከስግደትም ሊያግዳችሁ፣ ብቻ ነው ታዲያ እናንተ (ከነዚህ) ተከልካዮች ናችሁን? (ተከልከሉ)።” (ሱረቱል ማኢዳህ 90-91)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ፡ ጌታ አላህ አስካሪ መጠጥን ከቁማር ጨዋታና ጣኦታት አምልኮ ተርታ በመመደብ የተወገዘ የሰይጣን ሥራ የሆነ እርኩስ ተግባር አድርጎ ነው የሚገልጸው፡፡ ከዛም በተጨማሪ ከአስካሪ መጠጥ የሚገኘው ትርፍ፡ በወዳጆች መሐከል ጸብና ጥላቻን ማትረፍ፣ አላህን ከመዘከርና ከማምለክ መራቅ መሆኑን በመግለጽ ከዚህ መጥፎ ስራ እንድንርቅ ይመክረናል፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ ዑመር (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንደነገረን የአላህ ነቢይ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ አስካሪ መጠጥን፣ ጠጪውንም፣ ቀጂውንም፣ ሻጩንም፣ የሚገዛለትንም፣መጠጡን ጠማቂ፣ አስጠማቂውን፣ ተሸካሚውን፣ የሚሸከሙለትንም ሰው ከራሕመቱ ያርቃቸው ” (ቡኻሪይ)፡፡
ከዚህ ነቢያዊ ትምህርትም የምንወስደው ቁም ነገር፡ መጠጥ መጠጣቱ ብቻ ሳይሆን የሚያስረግመው፡-
ሀ. መጠጥ በራሱ የተረገመ መሆኑን
ለ. ለራስ መጥመቅም
ለ. እንዲሁም ማስጠመቅ
ሐ. መጠጥ ቤት ከፍቶ መነገድ
መ. የመጠጥ ቀጂና አስተናጋጅ ሁኖ ለመስራት መቀጠር
ሠ. በመጠጥ ቤቱ ውስጥ ገብቶ መጠጣት
ረ. በመሀል የመጠጥ አመላላሽ ሁኖ መስራት….
እነዚህ ሰዎች ከዚህ ድርጊታቸው በፍጥነት ወደ አላህ ተውበት በማድረግ ካልተመለሱ የቂያም ቀን ከተጠያቂነት እንደማይድኑ ነው፡፡ ኢስላም ሁለንተናዊ በመሆኑ፡ አትጠጡ ወይም አትስከሩ ብቻ ሳይሆን፡ ከላይ የተዘረዘሩትንም በሙሉ ያወግዛል፡፡
ዐሥማን ኢብኑ ዐፋን (ረዲየላሁ ዐንሁ) ደግሞ በመጠጥ ዙሪያ ድንቅ ንግግርን ተናግሯል፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡- ‹‹አስካሪ መጠጥን ራቋት፡፡ እሷ የኃጢአት ሁሉ እናት ናትና…›› (ነሳኢይ 317)፡፡
እውነቱን ነው!! ድሮስ የማን ተማሪ ሆንክና፡፡ አስካሪ መጠጥ ፡- ዝሙት እንዲስፋፋ፣ ሰዎች እንዲጋደሉ፣ የቤተሰብ ኑሮ እንዲናጋ፣ አላህን ከማምለክ እንዲዘናጉ የሚያደርግ፣ ኢኮኖሚን የሚያቃውስ የኃጢአቶች ሁሉ ‹እናት› ቢባል አይበዛበትም፡፡
2ኛ. አማኞች በእምነታቸውና በመልካም ስራቸው ምክንያት፡ በአላህ ራሕመት ጀነትን ሲገቡ መንፈሳዊና ስጋዊ ደስታዎችን ይጎናጸፋሉ፡፡ ከስጋዊ ደስታዎች ውስጥ ለመጠጥነት የሚያገለግሉ (የማር፣ የወተት፣ የውሀና የመጠጥ) ወንዞች መኖራቸው ነው (ሱረቱ ሙሐመድ 15)፡፡
ሌሎቹን መጠጦች ለጊዜው እናቆያቸውና ‹‹የመጠጥ ወንዞች›› የተባለው ላይ ቆይታ እናድርግ፡፡ ከላይ እንዳየነው ኢስላም አስካሪ መጠጥን በጽኑ ካወገዘ፡ እንዴት ተመልሶ ያንኑ መጠጥ በጀነት ለአማኞች ሊፈቅድ ቻለ? የሚለውን ሁለተኛውን ጥያቄ እንመልከተው፡-
በጀነት ውስጥ ለአማኞች የክብርና የጸጋ መጠጥ ሆኖ የተዘጋጀው በዚህ ምድር ካለው ጋር በፍጹም አይመሳሰሰልም፡፡ በይዘትም ሆነ በጥፍጥና፣ በውጤትም ሆነ በመንስኤ ግንኙነት የላቸውም፡፡ እንዴት ከተባለም፡-
ሀ. የጀነቱ መጠጥ ሽታው ከምድር ላይ ካሉ መዓዛዎች ሁሉ እጅጉኑ የሚበልጠውን የሚስክ መዓዛን የያዘ ሲሆን፡ የምድሩ መጠጥ ግን መጥፎ ጠረን ያለውና ሰውን የማያቀርብ ነው፡፡
ለ. የጀነቱ መጠጥ መልኩ ከወተት የነጻ፣ ጣእሙ እጅጉኑ የሚጣፍጥ ሲሆን፡ የምድሩ ግን እንደ ወተትም ያልነጻ፣ ጣእሙም መራራ ነው፡፡
ሐ. የጀነቱ መጠጥ ከተጠጣ በኃላ ደስታንና ሀሴትን እንጂ፡ ስካርንና ሀዘንን የማያስከትል ሲሆን፡ የምድሩ ግን ውጤቱ ስካርንና እራስን መሳት፣ ጸብንና ጥላቻን፣ ቤትን ረስቶ ትቦ ውስጥ ማደርን ነው የሚያስከትለው፡፡
መ. የጀነቱ መጠጥ የተዘጋጀው በአምላካችን አላህ መለኮታዊ ኃይልና ቃል ሲሆን፣ የምድሩን ግን ጠማቂው ሰው ነው፡፡ እሱም ከጌሾ፣ ከብቅል፣ ከወይንና ከመሳሰሉት፡፡
ለዚህ ልዩነቶች ያሉን ማስረጃዎች ቀጥሎ ያሉት የቅዱስ ቁርኣን ክፍሎች ናቸው፡-
“በድሎት ገነቶች ዉስጥ። ፊት ለፊት የሚታያዩ ሲሆኑ በአልጋዎች ላይ (ይንፈላሰሳሉ)።ከሚመነጭ ወይን ጠጅ በያዘ ብርጭቆ በእነርሱ ላይ ይዞርባቸዋል። #ነጭ ለጠጪዎች #ጣፋጭ ከኾነች። በእርሷ ዉስጥም ራስ-ምታት የለባትም። እነርሱም ከእርሷ #የሚሰክሩ አይደሉም።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 43-47)፡፡
“ከጠጅ ምንጭም፣ በብርጭቆዎችና በኩስኩስቶች በጽዋም (በነሱ ላይ ይዞራሉ)። ከርሷ የራስ ምታት አያገኛቸውም፤ #አይሰክሩምም።” (ሱረቱል ዋቂዓህ 18-19)፡፡
3ኛ. አሁን የቀረው ጥያቄ፡- በጀነት ለአማኞች የተዘጋጀው የክብር መጠጥ ከላይ እንደተገለጸው አስካሪ ካልሆነ፡ ለምን ‹ጠጅ› የሚል ስያሜ ተሰጠው? የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም ‹ጠጅ› ሲባል እኛ የምናውቀው የሚያሰክር የሆነ መጠጥን ነው የሚል መነሻ ሃሳብን ያቀፈ ነው፡፡
ለዚህ ጥያቄ ደግሞ ምለሹ እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ሀ. በአማርኛው የቅዱስ ቁርኣን ትርጉም ላይ ‹ጠጅ› የሚለው ቃል፡ በዐረብኛው ላይ ለተጠቀሰው ‹‹ረሒቅ›› ለሚለው ቃል ፍቺ ነው፡፡‹ረሒቅ› የሚለው ቃል ፍቺው፡- ከቆሻሻ ፍጹም የተጣራ መጠጥ ማለት ነው፡፡ (ተፍሲር ፈትሑል በያን)፡፡
ጠጅ የሚለው ስም በዚህ ምድር ላይ አስካሪ የሆነውን መጠጥ ለመግለጽ የሚገባ ስም ነው፡፡ ነገር ግን ስሙን ብቻ በመያዝ የጀነቱንም መጠጥ በአማርኛው የቁርኣን ትርጉም መሰረት ‹ጠጅ› ስለተባለ እዛም ያለው ያሰክራል ብለን እንዳንሳሳት፡፡ የስም መመሳሰል የባሕሪ መመሳሰልን አይገልጽምና፡፡ ውሀም እኮ ‹መጠጥ› ተብሎ ይጠራል፡፡ አስካሪ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
ለ. በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ከተጠቀሱት የጀነት መጠጦች ውስጥ አንድ ‹‹የወተት ወንዝ›› ነው፡፡ በሁላችንም ዘንድ እንደሚታወቀው ወተት የሚገኘው ደግሞ (ከላም፣ ግመልና ፍየል…) ነው፡፡ ታዲያ በጀነት ወተት አልለ ቢባል፡ እዛ የሚታለቡ ላሞች፡ ግመሎችና ፍየሎች አልሉ ማለት ነው ለማለት ያስችለናልን? እንደዛ ማለት አይደለም ከተባለ ደግሞ፡ ለምን የጀነቱን መጠጥ በምድራዊው ስሌት ማየት አስፈለገ ታዲያ?
‹ጠጅ› ከተባለ የሚያሰክረውን እንጂ ሌላ አናውቅም ከተባለ፡ እንግዲያውስ ወተት ከተባለም ከነዚሁ እንሰሳቶች የሚገኘውን እንጂ ሌላ አናውቅና እዛም የእንሰሳት እርባታ አልለ ብለን ልንደመድም ነውን? ዝግጅቱ እኮ የአምላክ እንጂ የሰው አይደለም፡፡
ሌላኛውን የማር ወንዝንም ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚር ምድር ላይ ‹ማር› ሲባል እኛ የምናውቀው ንብ የምትቀስመው፡ ከሆዷ የሚወጣውን ነው፡፡ ታዲያ የጀነቱንም ማር በዚሁ ምድራዊው አይን ተመልክተን ንቦችም እዛ ይሰፍራሉ ልንል ነው?
ሶስተኛው መጠጥ ‹የውሀ ወንዝ› የተባለው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ውሀን ማንም ሰው የሚያውቀው ካረገዙ ዳመናዎች ከበላያችን የሚዘንበውን ነው፡፡ ዝናብ ከሌለ ውሀ የለም፡፡ በጀነት ያለውን በመቆየት ብዛት ሽታ የማያመጣውን ‹የውሀ ወንዝም› ከዝናብ የተገኘ ነው ማለት ይቻላልን? እንግዲያውስ ዝናብ ካልዘነበ ውሀው ተጠጥቶ ያልቃል ማለት ነዋ?
ታዋቂው የቅዱስ ቁርኣን ተንታኝና የኒቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሐባ የነበረው ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) እንዲህ ይላል፡- ‹‹በጀነት ውስጥ ያለው ጸጋ በምድር ካለው ስሙ እንጂ ሌላ የለም›› (ተፍሲሩ-ጠበሪይ ሱረቱል በቀራህ 25)፡፡
አዎ! በጀነት ውስጥ ስሙ ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ ወተት፣ ማር፣ ዉሀ፣ መጠጥ፣ ፍራፍሬ….፡፡ መዓዛውና ጥፍጥናው፣ ቅርጽና ይዘቱ፣ ውጤቱና ጥቅሙ ምንም በዚህ ዓለም ካለው ጋር አይመሳሰልም፡፡ ጠጅ የሚለውንም በስምነቱ ብቻ እንረዳው፡፡
4ኛ. እንደ ወገናችን ጥያቄ መሰረት ‹ጠጅ› አስካሪ መጠጥ ከሆነ፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በዮሀንስ ወንጌል ምእ 2፡ ቁ1-11 ላይ እንደተጻፈው፡ ኢየሱስ በቃና ዘገሊላ ላይ በተደረገው ሰርግ ከሀዋሪያቶቹ ጋር ተገኝቶ ነበር፡፡ በስፍራውም የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ እናቱ ማሪያም ወደሱ መጥታ እንዳለቀባቸው ስትነገረው፡ እሱም ጋኖቹን ውሀ እንዲሞሏቸውና ከዛም ለአሳዳሪው እንዲሰጡት አዘዛቸው፡፡ ውሀው በተቀዳ ጊዜ ግን የወይን ጠጅ ሁኖ ተገኘ፡፡ ኢየሱስም የተአምራት ስራዎቹን መጀመሪያ በቃና ዘገሊላ አደረገ ይላል፡፡
ታዲያ ኢየሱስ የቀየረው ውሀ ‹ወይን ጠጅ› ከነበረ፡ አስካሪ መጠጥን ለሰው ማቅረብ ምኑ ላይ ነው አግባብነቱ? ውሀን ወደ ወይን-ጠጅ ቀይሮ በማጠጣት ሰውን ማስከር ተአምር ነውን?
5ኛ. ክርስቲያኑ ወገኔ ሆይ! እኔም በተራዬ ሁለት ጥያቄዎችን ልጠይቅህ፡-
1. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አስካሪ መጠጥ ያለው አቋም ምንድነው?
2. በገነት ውስጥ ለአማኞች የተዘጋጀ መብልና መጠጥ መኖርና አለመኖርን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ምንድነው?
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


