በኡስታዝ አቡ ሀይደር
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
ክቡራን ወንድሞቼና እህቶቼ! ዛሬም እንደተለመደው የማስቃኛችሁ ነገር ቢኖር፡ ኢስላም ለሃይማኖትህ ስትል መዋሸትን ይፈቅዳል! የሚለውን የካፊሮችን ከንቱ ክስ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም የራሳቸው ዕውቀትና ተሞኩሮ የሌላቸው፡ እንደ ገደል-ማሚቱ የተነገራቸውን ብቻ የሚያስተጋቡ፡ የጉዳዩን እውነተኝነት ከማጣራት ይልቅ በጥላቻ ስሜት ወሬውን ማሰራጨት የሚወዱ ናቸው፡፡ እስኪ ኢስላም ለሃይማኖትህ ስትል ዋሽ! ብሎ የፈቀደበትን ማስረጃ አሳዩን ስንላቸው ከሼህ ጎግል ያገኙትን ይህን ሐዲሥ አቅርበዋል፡-
ኡሙ ኩልሱም ቢንት-ዑቅባህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- “የአላህ መልከተኛ ሰዎች ከሚናገሩት ውስጥ በጦርነት ጊዜ፣ በሰዎች መሐል እርቅ ለመፍጠር እና ባል ሚስቱን ለማዝናናት፡ እንዲሁም ሚስት ባሏን ለማዝናናት ሲባል እንጂ ውሸትን ሲፈቅዱ አልሰማሁም” (አሕመድ)፡፡
የሐዲሡን መልእክት ወደ ውስጥ ገብተን እንደተለመደው መጠነኛ ማብራሪያ ከመስጠታችን በፊት ጥቂት ስለ ውሸት ንግግር ኢስላም የሚያስተምረውን እንመልከት፡-
ውሸት በኢስላም ውስጥ ምንም አይነት ስፍራ የሌለው ውዳቂና ርካሽ ተግባር መሆኑን ለመረዳት ቀጥሎ ያሉትን መንደርደሪያ ነጥቦች ለናሙና ያህል እንመልከታቸው፡-
1ኛ. ከጌታችን አላህ መለኮታዊ ስሞች ውስጥ አንዱ “አል-ሐቅ” የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትርጉሙ፡- ፍጹም እውነት የሚል ነው፡፡ አላህ መኖሩ የተረጋገጠ በፍጹም እውነትና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ‹አል-ሐቅ› ተብሎ ይጠራል (አል-ሐጅ 6)፡፡ ደግሞም ንግግሩ እውነት ብቻ የሆነ ጌታ ስለሆነ አሁንም ‹አል-ሐቅ› ይባላል (አን-ኒሳእ 87.122)፡፡ በተጨማሪም ለባሪያዎቹም እውነተኛና ታማኝ ጌታ ስለሆነ ‹አል-ሐቅ› ይሰኛል (ዩኑስ 32)፡፡ ለባሮቹ የገባላቸውን ቃል-ኪዳን ስለማያፈርስ ቃሉንም ስለሚጠብቅ (ኢብራሂም 47) “አል-ሐቅ” የሚባል አምላክ ነው፡፡ ታዲያ ባሕሪውና ማንነቱ በዚህ መልኩ የተገለጸው ይህ እውነተኛ አምላክ እንዴት ውሸትን ይፈቅዳል ተብሎ ይታሰባል? (ሱብሐነሁ ወተዓላ ዐምማ የሲፉሁ ዟሊሙን ዑሉወን ከቢራ)፡፡
“…አላህም እውነቱን ይናገራል፤ እርሱም ትክክለኛዉን መንገድ ይመራል” (ሱረቱል አሕዛብ 4)፡፡
2ኛ. ጌታችን አላህ በቅዱስ ቁርኣኑ ያዘዘን በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ከእውነተኞች ጋር እንድንሆን ነው፡-
“እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከዉነተኞቹም ጋር ሁኑ።” (ሱረቱ-ተውባህ 119)፡፡
“ሰው ሁሉ በእርግጥ በከሳራ ውስጥ ነው። እነዚያ ያመኑትና መልካሞችን የሠሩት፣ #በውነትም አደራ የተባባሉት፣ በመታገሥም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ።” (ሱረቱል ዐስር 2-3)፡፡
3ኛ. ውሸተኞች በተለይም በአላህና በአንቀጾቹ ላይ ሀሰትን የሚቀጥፉ አላህ ዘንድ እጅግ የተጠሉ መሆናቸው በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በተደጋጋሚ ተገልጾአል፡፡ ለአብነት ያህል፡-
“በአላህም ላይ ውሸትን ከቀጣጠፈ ወይም በአንቀጾቹ ካስተባበለ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማነው? እነሆ በደለኞች አይድኑም” (ሱረቱል አንዓም 24)፡፡
“በአላህም ላይ እብለትን ከቀጣጠፈ ወይም ወደርሱ ምንም ያልተወረደለት ሲኾን «ወደኔ ተወረደልኝ» ካለና፡- «አላህም ያወረደውን ብጤ በእርግጥ አወርዳለሁ» ካለ ሰው ይበልጥ በዳይ ማን ነው?…” (ሱረቱል አንዓም 93)፡፡
“…ሰዎችንም ያለ ዕውቀት ሊያጠም በአላህ ላይ ውሸትንም ከቀጠፈ ሰው ይበልጥ በደለኛ ማን ነው አላህ በደለኞችን ሕዝቦች (ቅኑን መንገድ) አይመራም፡፡»” (ሱረቱል አንዓም 144)፡፡
“በአላህ ላይም ውሸትን ከቀጣጠፈ ሰው ወይም እውነቱ በመጣለት ጊዜ ከአስዋሸ ይበልጥ በዳይ ማነው? በገሀነም ውስጥ ለከሐዲዎች መኖሪያ የለምን?” (ሱረቱል ዐንከቡት 68)፡፡
እነዚህ አናቅጾች በአንድ ድምጽ የሚያስተጋቡት በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጥፉ ሰዎች አላህ ዘንድ ምን ያህል እንደተጠሉና በደላቸውም እጅግ የከፋ መሆኑን ነው፡፡ ታዲያ ለባሪያዎቹ ውሸትን ይፈቅዳል ብለን ማሰብ እንችላለን?
4ኛ. በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጥፉ ሰዎች ፈጽሞ እንደማይድኑና ለጥፋት የተወሰኑ ሰዎች መሆናቸውን ጌታችን በቃሉ ይነግረናል፡-
“«እነዚያ በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉ ፈጽሞ አይድኑም፤» በላቸው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 69)፡፡
“በአላህም ላይ ውሸትን ልትቀጣጥፉ፣ ምላሶቻችሁ በሚመጥኑት ውሸት፥ ይህ የተፈቀደ ነው፤ ይህም እርም ነው፣ አትበሉ፤ እነዚያ በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉ፣ አይድኑም።” (ሱረቱ-ነሕል 116)፡፡
“በትንሣኤ ቀንም፣ እነዚያን በአላህ ላይ የዋሹትን፣ ፊቶቻቸው የጠቆሩ ሆነው ታያቸዋለህ፤ በገሀነም ውስጥ ለትዕቢተኞች መኖሪያ የለምን?” (ሱረቱ-ዙመር 60)፡፡
5ኛ. እንዲሁም በነቢያችን ላይ ያላሉትን ብለዋል በማለት እያወቀ የሚዋሽባቸው ሰው ነጌ የሚጠብቀውን አስፈሪ ቅጣት እንዲህ ሲሉ መልክተኛው ገልጸውታል፡-
“በኔ ላይ መዋሸት በአንዳቹ ላይ እንደመዋሸት አይደለም፡፡ በኔ ላይ የዋሸ ሰው መቀመጫውን ከእሳት ያድርግ” (ሙስሊም)፡፡
6ኛ. ውሸት እጅግ የተጠላ መሆኑን ለመግለጽ ሌላው መንገድ ውሸትን ራቁት ብሎ ቅዱስ ቁርኣን ማስጠንቀቁ ነው፡፡ እንደውም ከጣኦት አምልኮ ጋር አቆራኝቶ ነው አላህ ያስጠነቀቀን፡-
“…ከጣዖታት ርክሰት ተጠንቀቁ፤ የሀሰትንም ቃል ራቁ።” (ሱረቱል ሐጅ 30)፡፡
በሐዲሥ ላይም የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “እጅግ በጣም የከበደ ኃጢአትን ልንገራችሁን? ሲሉ፡ ሶሐቦችም፡- ‹‹እንዴታ ይንገሩን እንጂ!›› አሉ፡፡ እሳቸውም፡- ‹‹በአላህ ማጋራት፣ ወላጆችን መጨቆን›› አሉ፡፡ ተደግፈው ነበርና ቁጭ ብለው፡- ‹‹አዋጅ! የሐሰት ቃል፣ የውሸት ምስክርነትም፣ አዋጅ! የሐሰት ቃል፣ የውሸት ምስክርነትም›› አሉ፡፡” (ቡኻሪይ)፡፡
ዐብዱላህ ኢብኑ-መስዑድ(ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “…ውሸትን ተጠንቀቁ፡ ውሸት ወደ ጥመት ይመራል፡ ጥመት ደግሞ ወደ እሳት ይወስዳል” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
7ኛ. ሌላው ኢስላም የውሸትን አስከፊነት የገለጸበት መንገድ፡- ሀሰትን መናገር የሙናፊቅ ባሕሪ ነው ብሎ ማስተማሩ ነው፡-
አቢ ሁረይራህ(ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ(ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “የሙናፊቅ ምልክት ሶስት ናቸው፡- ሲናገር ይዋሻል፣ ቀጠሮ ያፈርሳል፣ ሲታመን ይከዳል” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
8ኛ. ነጌ የቂያም ቀንም ጠቃሚነቱ በእምነታቸውና በስራቸው እውነተኛ ለሆኑ ለአላህ ባሮች ብቻ እንደሆነ ቅዱስ ቁርኣን ያስተምራል፡-
“አላህ ይላል ፦ ይህ እውነተኞችን እውነታቸው የሚጠቅምበት ቀን ነው፤ ለነርሱ በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው በውስጣቸው ሁልጊዜ ዘውታሪዎች ሲሆኑ የሚኖሩባቸው ገነቶች አሉዋቸው፤ አላህ ከነሱ ወደደ፤ እነርሱም ከርሱ ወደዱ፤ ይህ ታላቅ ዕድል ነው።” (ሱረቱል ማኢዳህ 119)፡፡
“አላህም እውነተኞችን በውነተኛነታቸው ሊመነዳ፣ መናፍቃንንም ቢሻ ሊቀጣ፣ ወይም (ቢመለሱ) በነሱ ላይ ጸጸታቸውን ሊቀበል፥ (ይህን አደረገ)፤ አላህ መሐሪ አዛኝ ነውና።” (ሱረቱል አሕዛብ 24)፡፡
9ኛ. እጅግ በጣም የሚገርመው ደግሞ ኢስላም ውሸትን ለቀልድና ሰውን ለማሳቅ ብሎ እንኳ አለመፍቀዱ ነው፡-
የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “ወየውለት! ለዚያ ሲናገር ሰዎችን ለማሳቅ ብሎ ለሚዋሽ ሰው፡ ወየውለት! ወየውለት!” (አቡ-ዳዉድ 4992፣ አሕመድ 20055)፡፡
አቢ ኡማማህ(ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል፡- “በጀነት ውስጥ ላለው መሐከለኛ ቤት ውሸትን ለቀልድም እንኳ ቢሆን ለተወ ሰው ተሟጋች ነኝ” (ሶሒሑ ተርጊብ-ወተርሂብ 6/3)፡፡
10ኛ. የታላቁ ሮም ንጉስ የነበረው ሒረቅል አባ ሱፍያንን(ረዲየላሁ ዐንሁ) ነቢያችሁ በምን ያዛችኋል? ብሎ በጠየቀው ጊዜ እንዲህ ብሎ መለሰለት፡- “አላህን ብቻውን ተገዙት፡ በርሱም ምንንም አታጋሩ፣ አባቶቻችሁ የሚሉትን ነገር ተዉ፣ ሶላት እንድንሰግድ፣ እውነትን እንድንናገር፣ ዝምድናን እንድንቀጥል ያዘናል” (ቡኻሪይ)፡፡
ታዲያ ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢስላም ውሸትን መናገር ይፈቅዳል ብሎ ወሬ ማናፈስ የጤና ነውን?
ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ እንግዲያውስ ከላይ መግቢያ ላይ እንደ ርዕስ የተጠቀሰው ሐዲሥ መልእክቱ ምንድነው? የሚል ጥያቄ ስለሚነሳ እስኪ ወደሱ እንመለስ፡-
ሀ. በሰዎች መሐል እርቅ ለመፍጠር፡-
ሰዎች ተጣልተው እርቅ ለመፍጠር የሚፈልግ ሽማግሌ እውነቱን ተናግሮ የጥሉን ግድግዳ ማፍረስ የማይችል ቢሆንና ሌላ አማራጭ ቢጠፋበት፡ ሰላሙን ለማውረድ አስቦ የአንደኛውን ጥፋት መግለጹ የባሰ ጥሉን እንደሚያባብሰው ከተረዳ፡ ዋሽቶ ቢያስታርቃቸው እንደ ኃጢአተኛ አይቆጠርም፡፡ ምክንያቱም ዓላማው የግል ጥቅሙን ለማስጠበቅ፣ ተወዳጅነትን ለማትረፍና ምድራዊ ጥቅሙን ለማግኘት ሳይሆን በሰዎች መሐል እርቅ ለማውረድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተጨባጩ ዓለም ላይ የምናየውና የምንኖረው እውነት ነው፡፡ ባልና ሚስት ተጣልተው ትዳሩ ሊፈርስ ቢቃረብና ጉዳዩን የተረዳ ሽማግሌ የአንዳቸውን ነውር ደብቆ ዋሽቶ ቢያስታርቃቸው ጥፋቱ ምኑ ላይ ነው? ወይስ እውነቱን አውጥቶ ያፍረጥርጠውና ትዳሩም ይፍረስ፡ ቤተሰቡም ይበተን?
ጉዳዩን የበለጠ ለመረዳት ምሣሌን እንመልከት፡-
ምሣሌ አንድ፡- አንድ ተበዳይ የሆነ ሰው ከበዳዩ ለማምለጥ እየሮጠ ወደ አንድ ግቢ ሲሸሸግ በአይንህ ተመልክተኸዋል፡፡ በዳዩ ሰው ወዳንተ መጥቶ፡- አሁን በዚህ ጋ የሮጠውን ልጅ አይተኸዋል? የት ነው የተሸሸገው? ብሎ ቢጠይቅህ ምን ብለህ ትመልሳለህ? አሁን አንተ ሁለት አጣብቂኝ ነገር ውስጥ ገብተሀል፡፡
1ኛ. አላየሁም ብለህ መዋሸት
2ኛ. አይቼዋለሁ ብለህ የተደበቀበትን ቦታ ማሳየትና ልጁን ማስገደል ወይም ማስመታት
ታዲያ ውሸት ኃጢአት ነው ብለህ ልጁ የተደበቀበትን ቦታ አሳይተህ ማስገደሉ ፍትህ ነው? አእምሮህስ ይቀበለዋል? ወይንስ የተደበቀውን ሰው እንዳላየህ ገልጸህ ልጁን ማዳን? በተለይ ሊገደል የሚፈለገው ሰው የቤተሰብህ አካል ቢሆን ምን ልታደርግ እንደምትችል አስብ፡፡ ‹‹አኸፉ-ደረረይን›› ከሁለት ጉዳቶች፡ ጉዳቱ የተሻለውን መርጦ መጠቀም አግባብነት ያለው ድርጊት ነው፡፡
ምሣሌ ሁለት፡- የህክምና ባለሙያ ነህ እንበል፡፡ አንድን በሽተኛ እያከምኸው ሳለ፡ ህመሙ በጣም እንዳገረሸበትና በከፋ አደጋ ላይ እንዳለ ታውቃለህ፡፡ ይህን ሁኔታ ለበሽተኛው ብትነግረው፡ ምናልባትም መቋቋም አቅቶት የባሰ ህመሙ አገርሽቶበት ይሞታል ብለህ ትሰጋለህ፡፡ እናም ይህ ህመምተኛ፡- ዶክተር አሁን እንዴት ነኝ? በምን ሁኔታ ላይ ነው የምገኘው? የጤናዬ ነገር ያስፈራልን? ቢልህስ ያንተ ምላሽ ምንድነው የሚሆነው?
ለ. ባለቤቱን ለማስደሰት፡-
በትዳር ዓለም በባልና ሚስት መሐል የፍቅር ጨዋታዎች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ ታዲያ ባል የባለቤቱን ፍቅር ለመጨመርና በመሐከላቸው መዋደድ እንዲኖር ውሸትን ያዘሉ የጨዋታ ቃላቶች መጠቀም ተፈቅዶለታል፡፡ አንቺ ከዓለማት ሴቶች ሁሉ በላይ ለኔ ውድ ነሽ! እና የመሳሰሉትን፡፡ ምናልባት እሷ የዚያን ያህል የተወደደች ላትሆን ትችላለች፡፡ በውስጥዋ ደስታን ለመዝራትና ፍቅሩን ለማጠንከር ግን መጠቀም ይችላል፡፡ አንድ ምሣሌ እንመልከት፡-
ባለቤትህ አንተ ቤት ስትገባ እንድትበላና እንድትደሰት ቀኑን ሙሉ ምግብ ሰርታ ለፍታ አዘጋጅታ ጠበቀችህ፡፡ አንተም ወደ ቤት በገባህ ጊዜ የተዘጋጀህልን ምግብ መብላት ጀመርክ፡፡ ግን ምግቡ ላይ ጥፍጥና አላገኘህበትም፡፡ እናም ላንተ ብላ የለፋችው ባለቤትህ ወዳንተ በመምጣት፡ በፍቅር ቋንቋ፡- እንዴት ነው ምግቡ? ብትልህ፡ ምንም አይጣፍጥም! ነው ያንተ መልስ፡ ወይስ መስተካከል ያለበትን ሌላ ቀን እነግራታለሁ ብለህ ለዛሬ ሞራሏን ላለመንካት፡- በጣም አሪፍ ነው የሰራሽው ምግብ፡ ይጣፍጣል ውዷ ባለቤቴ! ነው የምትላት?
ሐ. በጦርነት ጊዜ፡-
ለወረራ የመጣን የጠላት ጦር በማዘናጋትና በማሳሳት ጥቃት ለመፈጸም በፍጥጫው ሌላ አቅጣጫ እንዳለን አድርጎ ማታለል የተፈቀደ ተግባር ነው፡፡ ካልሆነም የት እንዳለህ፡ የጦር ሰራዊቶችህን ብዛትና ቁጥር፡ የታጠቃችሁትን የመሳሪያ አይነት፡ ጦርነቱ መቼ እንደሚጀመር ከጠየቁህ እውነቱን ግለጽላቸውና መጥተው ይጨርሱት፡፡
ወንድምና እህቶች ከላይ እንዳነበብነው ኢስላም ውሸትን ምን ያህል እንዳወገዘና የተጠላ ተግባር እንደሆነ በሰፊው ተመልክተናል፡፡ ውሸተኞችም የማይድኑ መሆኑን አንብበናል፡፡ ለሶስት ምክንያቶች ግን ፡ እሱም ለማኃበረሰቡ ጥቅምና ግልጋሎት ሲባል እንጂ ልግል ጥቅም ታስቦ ባልሆነበት ቦታ ላይ መዋሸት መቻሉን አይተናል፡፡ የኢስላም ጠላቶች ግን፡ አንድም የተሟላ ዲን ስለሌላቸው ፡ ሌላም በጥላቻ ስሜት በመነሳት እነዚህን ሶስቱን ነጥቦች ብቻ አጉልተውና አጋነው ሊያሳዩን ይሞክራሉ፡፡ ጭራሹኑ ለሃይማኖትህ ስትል መዋሸት በኢስላም ይቻላል ይላሉ፡፡ ይህ ትልቅ ቅጥፈት ነው፡፡ ለሃይማኖቴና ለጌታዬ አላህ ክብር ስል እንድዋሽ አልተፈቀደልኝም፡፡ ይልቁኑ ይህ ያለው በናንተ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፋችሁ እንዲህ ይላል፡-
‹‹በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል? ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና። የእነርሱም ፍርድ ቅን ነው።›› (ወደ ሮሜ ሰዎች 3፡7-8)፡፡
“ቀጥተኛውን መንገድ ምራን።” (ሱረቱል ፋቲሓ 6)፡፡
ወላሁ አዕለም
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


