በኡስታዝ አቡ ሐይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ርኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
አንዳንዶች ባለማወቅ ለመረዳት፣ ሌሎች ደግሞ ግራ ተጋብቶ ሌላውንም ግራ ለማጋባት አላህ ለምን የፈለገውን ያጠማል? የሚል ጥያቄ ያለሳሉ፡፡ ጭራሽ የአላህን ፍትሐዊነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ለማስገባት ይሞክራሉ፡፡ ይህን ሀሳብ በአግባቡ ለመረዳት ሙስሊሞች ዘንድ መጥተው ጠይቆ መማር ሲገባ፡ ጭራሽ በመለኮታዊ አሰራሩ ጣልቃ ገብተው፡ እነሱ ከሱ በላይ ለፍጡሩ ተጨንቀው፡ አላህን ተከሳሽ እራስን ከሳሽ ማድረጉ ምን የሚሉት ዕብደት ነው? ዕብድም ደፍሮ እንደዚህ መናገሩን እንጃ!! ለማንኛውም ቅዱስ ቃሉ ‹በመልክተኛው ላይ ያለበት መልክቱን ማድረስ ብቻ ነው› ስለሚል፡ እኛም እውነታውን በመግለጽ፡ በነሱ ላይ ማስረጃውን በማቆም ከሐቅ የጠፋም ከማስረጃ በኋላ እንዲጠፋ፣ በሐቁ ሰበብም ወደ እውነት የሚመጣ እንዲመጣ የበኩላችንን እንወጣለን፡፡ ‹‹ወማ ተውፊቂ ኢልላ ቢላህ›› (ለማንኛውም መልካም ነገር ገጠመኛችን ከአላህ እንጂ ከማንም አይደለም››!! እንዲል ቃሉ፡፡ ጉዳዩ ግልጽ እንዲሆንም በአራት ነጥቦች በመከፋፈል በጥያቄ መልክ አቀርበዋለሁ፡-
1. አላህ ማንን ነው የሚያጠመው ?
2. ለምንድነው የሚያጠመው?
3. መጀመሪያውኑ ለጀሀነም ለምን ፈጠራቸው?
4. ጌታህ ቢሻ ኖሮ የሚለውስ?
በጽሁፋቸው ውስጥ የተንጸባረቁት ጥያቄዎች ከሞላ ጎደል እነዚህን ይመስላሉ፡፡ ወደ ዝርዝር ምላሹ በአላህ ፈቃድ በመታገዝ እንግባ፡-
1. አላህ ማንን ነው የሚያጠመው? ፡-
ፈጣሪ አምላካችን አላህ ለጥመት የሚዳርጋቸው፡ ቀድሞውኑ ከእምነት ጎራ ያፈገፈጉ፡ እውነትን አምኖ ከመቀበል እራሳቸውን ያገለሉ ባሪያዎቹን ነው፡፡ እውነትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ በመልካም ስራ ላይ የተሰማሩ ባሮቹን በፍጹም ለጥመት አይዳርጋቸውም፡፡ ‹‹አል-ጀዛኡ ሚን-ጂንሲል ዐመል›› (የዋጋ መጠን በስራው ልክ ነው) እንዲሉ፡ ለነዚህ ኃጢአተኞችና በተውበት ወደ አላህ መንገድ መመለስን ላልፈለጉት አላህ የሂዳያ በሩን ቢዘጋባቸውና ለጥመት ቢዳርጋቸው ፍትሐዊነት እንጂ አድሎአዊነት አይደለም፡፡ ጌታ አላህ ለጥመት የሚዳርጋቸው እነዚሁኑ ለመሆኑ ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች ለናሙና እንመልከታቸው፡-
” الَّذِينَ يُجَادِلُونَ فِي آيَاتِ اللَّهِ بِغَيْرِ سُلْطَانٍ أَتَاهُمْ كَبُرَ مَقْتًا عِنْدَ اللَّهِ وَعِنْدَ الَّذِينَ آمَنُوا كَذَلِكَ يَطْبَعُ اللَّهُ عَلَى كُلِّ قَلْبِ مُتَكَبِّرٍ جَبَّارٍ ” سورة غافر 35
“እነዚያ፤ የመጣላቸው አስረጅ ሳይኖር፣ በአላህ ታምራቶች የሚከራከሩ (ክርክራቸው) አላህ ዘንድና እነዚያም ያመኑት ዘንድ መጠላቱ፣ በጣም ተለቀ፤ እንደዚሁ አላህ #በኩሩ ጨካኝ (ሰው) ልብ ሁሉ ላይ ያትማል።” (ሱረቱ-ጋፊር 35)፡፡
” وَإِذْ قَالَ مُوسَى لِقَوْمِهِ يَا قَوْمِ لِمَ تُؤْذُونَنِي وَقَدْ تَعْلَمُونَ أَنِّي رَسُولُ اللَّهِ إِلَيْكُمْ فَلَمَّا زَاغُوا أَزَاغَ اللَّهُ قُلُوبَهُمْ وَاللَّهُ لَا يَهْدِي الْقَوْمَ الْفَاسِقِينَ ” سورة الصف 5
“ሙሳም ለሕዝቦቹ ሕዝቦቼ ሆይ! እኔ ወደ እናንተ የአላህ መልክተኛ መሆኔን በእርግጥ የምታውቁ ስትሆኡ ለምን ታሰቃዩኛላችሁ? ባለ ጊዜ (አስታውስ፤ ከውነት) በተዘነበሉም ጊዘ አላህ ልቦቻቸውን አዘነበላቸው አላህም አመጠኞችን ሕዝቦች አያቀናም።” (ሱረቱ-ሶፍ 5)፡፡
” مِنْ دُونِ اللَّهِ قَالُوا ضَلُّوا عَنَّا بَلْ لَمْ نَكُنْ نَدْعُو مِنْ قَبْلُ شَيْئًا كَذَلِكَ يُضِلُّ اللَّهُ الْكَافِرِينَ ” سورة غافر 74
“ከአላህ ሌላ (የምታጋሩዋቸው) ከኛ ተሰወሩን፤ ከቶ ከዚህ በፊት ምንንም የምንግገዛ አልነበርንም ይላሉ፤ እንደዚሁ አላህ #ከሀዲዎችን ያሳስታል።” (ሱረቱ-ጋፊር 74)፡፡
” وَلَقَدْ جَاءَكُمْ يُوسُفُ مِنْ قَبْلُ بِالْبَيِّنَاتِ فَمَا زِلْتُمْ فِي شَكٍّ مِمَّا جَاءَكُمْ بِهِ حَتَّى إِذَا هَلَكَ قُلْتُمْ لَنْ يَبْعَثَ اللَّهُ مِنْ بَعْدِهِ رَسُولًا كَذَلِكَ يُضِلُّ اللَّهُ مَنْ هُوَ مُسْرِفٌ مُرْتَابٌ ” سورة غافر 34
“ዩሱፍም ከዚህ በፊት ግልጽ ማስረጃዎችን በእርግጥ አመጣላችሁ፤ ከዚያም እርሱ ካመጣላችሁ ነገር ከመጠራጠር አልተወገዳችሁም፤ በጠፋም ጊዜ አላህ ከርሱ ኋላ መልክተኛን በጭራሽ አይልክም፣ አላችሁ፤ አላህ እንደዚሁ #ድንበር አላፊ፣ #ተጠራጣሪ የሆነን ሰው ያሳስታል።” (ሱረቱ ጋፊር 34)፡፡
ከነዚህ አራት የቅዱስ ቁርኣን ጥቅሶች እንደምንረዳው፡ ከሐቅ የኮሩ፣ ከእውነት የተዘነበሉ፣ በካዱና በተጠራጠሩ ህዝቦች ልብ ላይ እውነትን እንደሚጋርድባቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ ቅጣት ነው፡፡ ማመን እና በተውበት መመለስ ሲችሉ ማን በጥመታቸው ስር ዘውትሩ አላቸው? ያለ ምክንያት ግን ሰዎች የእውነት መልክት ሳይደርሳቸውና በሱም ሳያስተባብሉ በፊት ለጥመትና ለቅጣት እንደማይዳርጋቸው እንዲህ በማለት ይነግረናል፡-
” وَمَا كَانَ اللَّهُ لِيُضِلَّ قَوْمًا بَعْدَ إِذْ هَدَاهُمْ حَتَّى يُبَيِّنَ لَهُمْ مَا يَتَّقُونَ إِنَّ اللَّهَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ ” سورة التوبة 115
“አላህም ሕዝቦችን ከአቀናቸው በኋላ፣ የሚጠነቀቁትን (ሥራ) ለርሱ እስከሚገልጽላቸዉ፣ (እስከሚተዉትም) ድረስ ጥፋተኛ የሚያደርግ አይደለም፤ አላህ በነገሩ ሁሉ ዐዋቂ ነውና።” (ሱረቱ-ተውባህ 115)፡፡
ከዛ ይልቅ በንሰሀና በተውበት ወደ አላህ መንገድ መመለስ የሚፈልጉትን ይመራቸዋል እንጂ አያጠማቸውም፡-
” وَيَقُولُ الَّذِينَ كَفَرُوا لَوْلَا أُنْزِلَ عَلَيْهِ آيَةٌ مِنْ رَبِّهِ قُلْ إِنَّ اللَّهَ يُضِلُّ مَنْ يَشَاءُ وَيَهْدِي إِلَيْهِ مَنْ أَنَابَ ” سورة الرعد 27
“እነዚያም የካዱት፥ በርሱ ላይ ከጌታው ታምር ለምን አልተወረደም ይላሉ፤ አላህ የሚሻውን ያጠማል፤ የተመለሰውንም ሰው ወደርሱ ይመራል፥ በላቸው።” (ሱረቱ-ረዕድ 27)፡፡ የአንደኛው ጥያቄ መልስ በመጠኑ ይህን ይመስላል፡፡
2. ለምንድነው የሚያጠመው?
የዚህ ጥያቄ መሰረቱ ‹‹አላህ የሚሻውን ያጠማል›› የሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ አዎ አላህ የፈለገውን ያጠማል፡፡ እንዲሁ በግልቡ ስናየው ለምን? የሚል ጥያቄ ልናነሳ እንችል ይሆናል፡፡ ዋና ሃሳቡንና መልክቱን ከመግለጻችን በፊት ግን እንደው እንደዚህ ብለን መልስ ብንሰጥስ ምን ይመጣ ይሆን! አላህ የፈለገውን የሚያጠመው፡ የፈለገውን የማጥመም መብት ስላለው! ሁሉም ነገር የሱ ንብረት ስለሆነ! ብንባል ይህ ብቻ በቂ አይሆንም ነበር? ፍጥረታዊ የሆነ ሰው ፍጥረታዊ በሆነ አሰራሩና አሳቡ እንዴት ፈጣሪ አምላኩን አላህን እንዴት እንደሚሰራና ለምንስ ይህን ያደርጋል? ብሎ ጥያቄ ሊያቀርብ ይገባልን? የሱ ስልጣንና የኛ ድክመት፡ የሱ ጥበብና የኛ ሞኝነት በምን ተገናኘና?
እንደዛም ሆኖ ግን ‹‹አላህ የፈለገውን ያጠማል›› ሲባል እኛ በጥሬው እንደምንረዳው አይደለም፡፡ ዋና መልእክቱ፡- ማን ከልቡ ትክክለኛ አማኝ እንደሆነና ማን አስመሳይ እንደሆነ፣ ማን በሚሰራው ስራና በልፋቱ ለሂዳያ ወይም ለጥሜት ተገቢ እንደሆነ ከሁሉም በላይ አላህ አዋቂና ጥበበኛ እንዲሁም ፍትሐዊ ጌታ ስለሆነ እሱ ያውቃል፡ ስለሆነም ለፈለገው ሂዳያን በመለገስ ያልፈለገውን በመረጠው ጥመት ይከተዋል ማለት ነው፡፡ ወይስ እሱ አላህ የፈለገውን ሳይሆን እኛ የፈለግነውን እንዲያጠም ነው ጥያቄው? በኒ አደም እንዲህ ብሎ አይጠይቅም አይባል! ሰዎች የአላህን መንገድ ከልባቸው እየፈለጉ በስራም እየገለጹ አላህ ግን መንገዱን ዘጋባቸው ሐቅን እንዳይቀበሉ አጠመማቸው ማለት ነው ብለን በፍጹም ልንረዳው አይገባም፡፡ ቀጣዩ አንቀጽ ይህንን ያስረዳል፡-
” إِنَّكَ لَا تَهْدِي مَنْ أَحْبَبْتَ وَلَكِنَّ اللَّهَ يَهْدِي مَنْ يَشَاءُ وَهُوَ أَعْلَمُ بِالْمُهْتَدِينَ ” سورة القصص 56
“አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ አታቀናም፡፡ ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 56)፡፡
በዚህ አንቀጽ ስር፡- አላህ ሰዎችን ማቅናትና ልባቸው እውነትን አምኖ እንዲቀበል ማድረግ የሱ ስልጣን እንጂ የማንም እንዳልሆነ ከገለጸ በኋላ፡ ምክንያቱን ሲያብራራ ደግም ‹‹እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው›› በማለት፡ ቅናቻ (ሂዳያ) የሚገባቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ የማውቀው እኔ ብቻ ነኝ አለ፡፡ እኛ የሰዎችን ውጪያዊ ገጽታ አይተን ከመፍረድ ውጪ ልባቸውን አናውቅም፡፡ ስለዚህ ማን ለጌታው መንገድ ተገቢ እንደሆነና ማን ለጥመት የሚገባው እንደሆነ ልብን ለሚያውቀው አላህ መተው ለራሳችንም መልካም ነው፡፡ ያለሙያችን በአላህ ስራ ገብቶ ለምን ይህን ያደርጋል? ለምን ይህን ይተዋል? ከማለት፡ እኛንም በራሕመቱ አይቶን ከተመሩት ባሮቹ እንዲመድበን፡ በወንጀላችን ብዛት ለጥመት እንዳይዳርገን መማጸን ነው የሚገባን፡፡
3. ለጀሀነም የተፈጠሩ፡-
የጥቅሱ መልክት ሳይገባቸው፡ ቀጥሎ ያለውን ተያያዥ ሃሳብ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ ያነሱት ጥያቄ ነው፡፡ የጥቅሱ መልእክት፡- አላህ በሰጣቸው ልብ እውነትን መገንዘብና መቀበል ባለመቻላቸው፣ በተሰጣቸው መስሚያ ሐቅን ፈልጎ መስማትና ማዳመጥን ባለመፈለጋቸው፣ እንዲሁም በተቸራቸው አይን እውነትን ለማየት ባለመውደዳደቸው ሰበብ ለጀሀነም የተፈጠሩ ተብለው ተገለጹ እንጂ ያለነሱ ጥፋትና ክህደት ቀድሞውኑ ጀሀነም የተደገሰላቸው አልተባሉም፡፡ እስኪ ጥቅሱን በድጋሚ እንመልከተው፡-
” وَلَقَدْ ذَرَأْنَا لِجَهَنَّمَ كَثِيرًا مِنَ الْجِنِّ وَالْإِنْسِ لَهُمْ قُلُوبٌ لَا يَفْقَهُونَ بِهَا وَلَهُمْ أَعْيُنٌ لَا يُبْصِرُونَ بِهَا وَلَهُمْ آذَانٌ لَا يَسْمَعُونَ بِهَا أُولَئِكَ كَالْأَنْعَامِ بَلْ هُمْ أَضَلُّ أُولَئِكَ هُمُ الْغَافِلُونَ ” سورة الأعراف 179
“ከጋኔንም ከሠዎችም ብዙዎችን ለገሀነም በእርግጥ ፈጠርን፡፡ ለእነርሱ በሳቸው የማያውቁባቸው ልቦች አሏቸው፡፡ ለእነሱም በሳቸው የማያዩባቸው ዓይኖች አሏቸው፡፡ ለእነሱም በሳቸው የማይሰሙባቸው ጆሮዎች አሏቸው፡፡ እነዚያ እንደ እንሰሳዎች ናቸው፡፡ ይልቁኑም እነርሱ በጣም የተሳሳቱ ናቸው፡፡ እነዚያ ዘንጊዎቹ እነርሱ ናቸው” (ሱረቱል አዕራፍ 179)፡፡
ከዚህ ሙሉ አንቀጽ የምንወስደው መልክት በተሰጣቸው የሰውነት መሳሪያ (ልብ፣ አይን፣ ጆሮ) ባለመጠቀማቸው ምክንያት ለእሳት የተፈጠሩ መሆናቸውን ነው፡፡ ‹‹ለእሳት በርግጥ ፈጠርን›› ማለት ለዚያ ዓላማ ታስቦ ማለት አይደለም፡፡ ‹‹ሊጀሀነመ›› የሚለው የዐረብኛው ቃል ውስጥ ያለችዋ የመጀመሪያ ፊደል ‹ላም› ‹ላሙል-ዓቂባህ› ትባላለች፡፡ ፍጻሜያቸውና መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ቀድሞ በመታወቁ ምክንያት ለዚያ የተፈጠሩና የተዘጋጁ ማለት ነው፡፡ ይህንን ሀሳብ የሚደግፍ አንድ የቅዱስ ቁርኣን ጥቅስ እንመልከት፡-
” فَالْتَقَطَهُ آلُ فِرْعَوْنَ لِيَكُونَ لَهُمْ عَدُوًّا وَحَزَنًا إِنَّ فِرْعَوْنَ وَهَامَانَ وَجُنُودَهُمَا كَانُوا خَاطِئِينَ ” سورة القصص 8
“የፈርዖን ቤተሰቦችም (መጨረሻው) ለእነርሱ ጠላት ሐዘንም ይሆን ዘንድ አነሱት፡፡ ፈርዖንና ሃማንም ሰራዊቶቻቸውም ሀጢአተኞች ነበሩ” (ሱረቱል ቀሶስ 8)፡፡
እውነት ፊርዐውንና የሱ ቤተሰቦች (በክህደት አምሳዮቹ ባለቤቱ ስትቀር) ሙሳን (ዐለይሂ-ሰላም) ከባሕሩ ያነሱትና ያሳደጉት ጠላትና ሐዘን ይሆንባቸው ዘንድ ነው እንዴ? በፍጹም አይደለም!! እነሱ አንስተው ያሳደጉት፡ ልጅ ስላልነበራቸው እንደ ልጅ ለመያዝና ደግሞም ነገ ይጠቅመናል በማለት ነው፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” وَقَالَتِ امْرَأَتُ فِرْعَوْنَ قُرَّتُ عَيْنٍ لِي وَلَكَ لَا تَقْتُلُوهُ عَسَى أَنْ يَنْفَعَنَا أَوْ نَتَّخِذَهُ وَلَدًا وَهُمْ لَا يَشْعُرُونَ ” سورة القصص 9
“የፈርዖንም ሚስት ‹‹ለእኔ የዓይኔ መርጊያ ነው፡፡ ለአንተም፡፡ አትግደሉት፡፡ ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና›› አለች፡፡ እነሱም (ፍጻሜውን) የማያውቁ ሆነው (አነሱት)” (ሱረቱል ቀሶስ 9)፡፡
የነሱ ዓላማ ይህ ነበር፡፡ ግን ጥበበኛው ጌታ አላህ ሙሳን (ዐለይሂ-ሰላም) በጠላቱ ቤት በጥሩ እንክብካቤ እንዲያድግ አደረገውና ኃላም ላይ በአሳዳጊው በፊርዐውን ላይ ጠላት ሁኖ እንዲነሳበት አደረገው፡፡ ይህም ፊርዐውን በክህደቱ ምክንያት ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ጠላት እንደሚሆንበት ቀድሞውኑ ያላወቀው ፊርዐውን አንስቶ አሳደገው በማለት የመጀሪው አንቀጽ ስለፍጻሜው ያወራል ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዛው በሱረቱል አዕራፍ ቁጥር 179 ላይ የተጠቀሱት ሰዎችና ጂኒዎች የተፈጠሩበት ዓላማ አላህን ለመገዛት ነው (ሱረቱ-ዛሪያት 56)፡፡ ይህንን ዓላማ በፈቃደኝነት ለማሳካት እሺ የማይሉና በክህደት ተግባራቸው የሚዘወትሩ የሰውና የጂኒ ጭፍሮች እንዳሉ ገና ከመፈጠራቸው በፊት አላህ ቀድሞ ያውቃልና፡ እነዚህን ለገሀነም ፈጠርኋቸው ቢል ምንም የሚደንቅ አይደለም፡፡ ለኛ የሚያሳየን ነገር ቢኖር፡ በደልን ሳይሆን የሰዎችን ስራ፡ ገና ሰዎቹ ከመምጣታቸው በፊት ቀድሞ የማወቅ ችሎታ ያለው ጌታ መሆኑን ነው፡፡
4. ብንሻ ኖሮ፡-
አዎ አላህ ቢፈልግ ኖሮ የዓለምን ህዝብ ሁሉ አማኝ ማድረግ ይችላል፡፡ የሰዎች ልብ ሁሉ በቁጥጥሩ ስር ነውና፡፡ ያ ያልሆነበት ምክንያት ግን ሰዎች በምርጫቸው አላህን እንዲያመልኩ ስለፈቀደ ነው፡፡ የፈለገ ሰው ጌታውን በፈቃደኝነት ያመልካል፡፡ ያልፈለገ ደግሞ በመረጠው ክህደት ይዘወትራል፡፡ አላህ ቢሻ ግን ከሀዲውን ሁሉ አማኝ ሙስሊም ማድረግ ይችላል፡፡ ግን ማስገደድን አልፈለገም፡፡ ይህም የፍጹም ፍትሐዊነቱ መገለጫ ነው፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” وَلَوْ شَاءَ رَبُّكَ لَآمَنَ مَنْ فِي الْأَرْضِ كُلُّهُمْ جَمِيعًا أَفَأَنْتَ تُكْرِهُ النَّاسَ حَتَّى يَكُونُوا مُؤْمِنِينَ ” سورة يونس 99
“ጌታህም በሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሰዎች ሁሉም የተሰበሰቡ ሆነው ባመኑ ነበር፡፡ ታዲ አንተ ሰዎችን አማኞች እንዲሆኑ ታስገድዳለህን” (ሱረቱ ዩሱፍ 99)፡፡
አላህ ማስገደድን የሚሻ አምላክ ቢሆን ኖሮ በምድር ላይ ያሉትን ሁሉ ልባቸውን በመቀየር ወደ እምነት ጎራ በማምጣት ሁሉንም አማኝ ማድረግ እንደሚችልና ይህም ለሱ ቀላል እንደሆነ አስረዳ፡፡ ነገር ግን በዚህ መልክ እንዲሆን ያልፈለገው አምላካችን አላህ ነቢያችንንም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አንተስ ሰዎችን አማኝ እስኪሆኑ ድረስ ታስገድዳቸዋለህን? በማለት ማስገደድ እንደማይገባ ገለጸ፡፡ እናም ይህ ጥግ የደረሰ የፍትሕ መገለጫ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ወገኖች ሆይ! እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንዴት ልትፈቱት ነው?፡-
‹‹የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል?›› (መጽሐፈ መክብብ 7፡13)፡፡
‹‹እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም እልከኛ ያደርገዋል። እንግዲህ ስለ ምን እስከ አሁን ድረስ ይነቅፋል? ፈቃዱንስ የሚቃወም ማን ነው? ትለኝ ይሆናል። ነገር ግን፥ አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን። ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን? ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን?›› (ወደ ሮሜ ሰዎች 9፡18-21)፡፡
“አንተን ብቻ እንግገዛለን፤ አንተንም ብቻ ርዳታን እንለምናለን። ቀጥተኛውን መንገድ ምራን። የነዚያን በነርሱ ላይ በጎ የዋልክላቸውን፣ በነሱ ላይ ያልተቆጣህባቸውንና ያልተሳሳቱትንም ሰዎች መንገድ (ምራን፤ በሉ)።” (ሱረቱል ፋቲሓ 5-7)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


