በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ከካፊሮች በኩል የተነሳ አንድ ስሞታ አንብቤ ነው፡፡ እሱም፡- በሙስሊሞች ዘንድ ስለጀነት ሲወሳ ሁሌም የሚያስቡት በውስጧ ሚስቶች መኖራቸውንና የስጋ ፍላጎትም እንደሚከናወንባት ብቻ አድርገው ማሰባቸው ነው፡፡ በርግጥ እነዚህን ሰዎች እስኪ በናንተ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ገነት ጸጋዎች ምን የተዘረዘረ ነገር አልለ? ብለን ብንጠይቃቸው ምንም መመለስ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም መጽሐፉ ይህን ነገር ከመዘርዘር ተቆጥቧልና!!፡፡ እነሱም መመሪያ መጽሐፋቸውን ተከትለው ዝም ማለት ሲገባቸው፡ ጭራሽ በማያውቁት በሌላ ዕምነት ውስጥ ገብተው መዘባረቅ ከጀመሩ የኛ ዝምታ እስከመቼ ነው? ቢያንስ እንኳ ምላሹን ለሙስሊም ወንድሞችና እህቶች በተጠየቁበት ጊዜ እንዲረዳቸው፡ በዛውም አላህ ልቡን የከፈተለት የሌላ ዕምነት ተከታይ ካለም ጉዳዩን በልበ-ሰፊነት እንዲመለከተው ለማገዝ ተዘጋጅቷል፡፡
የጀነትን ጸጋዎች ጠቅለል በማድረግ በሁለት መክፈል እንችላለን፡፡ እነሱም፡- መንፈሳዊ ጸጋና ስጋዊ ጸጋዎች ይባላሉ፡፡ ለዛሬ ቅድሚያ የምንሰጠው ከመንፈሳዊ ጸጋ በመጀመር ይሆናል፡፡ ይከታተሉ መልካም ንባብ፡-
ሀ. ‹‹መንፈሳዊ ጸጋ››
1. አላህን ማየት፡-
ከጸጋዎች ሁሉ በላይና ፍጹም ተወዳዳሪ የሌለው ጸጋ ነው፡፡ አማኞችም በምድራዊ ህይወታቸው የለፉለት፡ ህይወታቸውን መስዋእት እስከማድረግ የታገሉለት፡ የመጨረሻ ግባቸውም ይህን ለማሳካት ነው፡፡ የጌታችንን “መለኮታዊ ፊት” ለማየት የታደለ አንድ አማኝ፡ ለሱ ጀነት ከመኖር የበለጠ ጸጋ እንደሆነ ይረዳል፡፡ ለዚህም ነው ከአራቱ መዝሀብ የአንዱ (የሻፊዒያው) መሪ የነበሩት ሙሐመድ ኢብኑ ኢድሪስ አሽ-ሻፊዒይ ሲናገሩ፡- ‹‹በትንሳኤው ዕለት እኔ (ሙሐመድ ኢብኑ ኢድሪስ አሽ-ሻፊዒይ) ጌታዬን እንደምመለከተው ባለረጋግጥ ኖሮ በዚህ በዱንያ ባልተገዛሁት (ባላመለክሁት) ነበር›› አሉ፡፡
በዛው ተቃራኒ በአላህና በመልክተኛው (በሙሐመድ) ያላመኑ ካፊሮችም ከጀሀነም በላይ የሚያንገበግባቸው ትልቁ ቅጣት ይህንኑ ፈጣሪ አምላካቸውን ለማየት አለመታደላቸው ነው፡፡ የአላህቃል እንዲህ ይላል፡-
” كَلَّا إِنَّهُمْ عَنْ رَبِّهِمْ يَوْمَئِذٍ لَمَحْجُوبُونَ ” سورة المطففين 15
“ይከልከሉ፤ እነሱ በዚያ ቀን ከጌታቸው (ማየት) ተጋራጆች ናቸው።” (ሱረቱል ሙጠፊፊን 15)፡፡
ቅዱስ ቁርኣንና የነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሐዲሥ አላህን አማኞች በመጪው ዓለም እንደሚመለከቱት በበርካታ ቦታዎች ላይ ይናገራሉ፡፡ የተወሰኑትን ለአብነት እንመልከታቸው፡-
” وُجُوهٌ يَوْمَئِذٍ نَاضِرَةٌ * إِلَى رَبِّهَا نَاظِرَةٌ ” سورة القيامة 23-22
“ፊቶች በዚያ ቀን አብሪዎች ናቸው። ወደ ጌታቸው ተመልካቾች ናቸው።” (ሱረቱል ቂያማህ 22-23)፡፡
“ለእነዚያ መልካም ለሠሩት መልካም ነገርና ጭማሪም አላቸው፡፡ ፊቶቻቸውንም ጥቁረትና ውርደት አይሸፍናቸውም፡፡ እነዚያ የገነት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 26)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ለመልካም ሰሪዎች ሁለት ነገር እንደተደገሰላቸው ይገልጻል፡፡ የመጀመሪያው፡- ‹‹መልካም ነገር›› የተባለው ጀነትን ሲሆን፡ ሁለተኛው ‹‹ጭማሪም› የተባለው ደግሞ የጌታቸውን መለኮታዊ ፊት መመልከት መቻል የሚለውን ነው፡፡ ይህንንም ትርጉም ራሳቸው ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለው ገልጸውታል፡-
ሱሀይብ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን አላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የጀነት ሰዎች ጀነት ከገቡ በኋላ፡ ጌታችን አላህም፡- እንድጨምርላችሁ የምትፈልጉት ነገር አለን? ይላቸዋል፡፡ እነሱም፡- ፊቶቻችንን አበራህልን፣ ከጀሀነም ቅጣትም አዳንከን፣ ጀነትንም አስገባኸን (ታዲያ የምን ጭማሬ ያስፈልጋል?) ይላሉ፡፡ የዛኔም በነሱና በጌታቸው አላህ መሀል እንዳይመለከቱት ተሸፍኖባቸው የነበረውን ግርዶሽ ያነሳዋል፡፡ እነሱም ጌታቸውን አላህን ያዩታል፡፡ አላህን ከማየትም የበለጠ ጸጋ አልተሰጣቸውምና፡፡ ከዚያም የአላህ ነቢይ ይህን የቁርኣን አንቀጽ አነበቡ” (ሶሒሕ ሙስሊም 467-468)፡፡
ጀሪር (ረዲየላሁ ዐንሁ) በነገረን ሌላ ዘገባ ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- “የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በለይለቱል በድር (በጨረቃ አቆጣጠር 14ኛው ቀን ሙሉ ሆና ደምቃ በምትታይበት) ወደኛ መጡና፡- ‹‹እናንተ የውሙል ቂያም ጌታችሁን በሚገባ ታዩታላችሁ፡፡ ልክ ይህቺን ጨረቃ እንደምታዩት፡፡ አላህን በማየትም መጨናነቅና መጣበብ የለም›› አሉን” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
አዎ! አማኞች አንዱ ሌላውን በመውቀስ አጭሩ ረጅሙን ከለልከኝ አይልም፣ ጌታቸውን ለማየት መገፋፋት የለም፣ ለአይኔ ርቆብኛል የሚል ስሜትም አይኖርም፡፡ ሁሉም ባለበት ቦታ ሆኖ ጌታውን ይመለከታል፡፡ አላህ በራሕመቱ ከነሱ ያድርገን፡፡
2. ውዴታውን መጎናጸፍ፡-
ሌላው ትልቁ መንፈሳዊ ጸጋ ‹‹የአላህን ውዴታ›› መጎናጸፍ ነው፡፡ አላህ ውዴታውንና ፍቅሩን በአማኞች ላይ ያሰፍረዋል፡፡ ቁጣ የሚባል ነገር ለዘልዓለም ፈጽሞ አያገኛቸውም፡፡ ቀጣዮቹ ማስረጃዎች ይህንን ይገልጻሉ፡-
” وَعَدَ اللَّهُ الْمُؤْمِنِينَ وَالْمُؤْمِنَاتِ جَنَّاتٍ تَجْرِي مِنْ تَحْتِهَا الْأَنْهَارُ خَالِدِينَ فِيهَا وَمَسَاكِنَ طَيِّبَةً فِي جَنَّاتِ عَدْنٍ وَرِضْوَانٌ مِنَ اللَّهِ أَكْبَرُ ذَلِكَ هُوَ الْفَوْزُ الْعَظِيمُ ” سورة التوبة 72
“አላህ ምእምናንንና ምእምናትን ከስሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶችም ዉስጥ መልካም መኖሪያ ቤቶችን ቃል ገብቶላቸዋል፤ ከአላህም የሆነዉ ዉዴታ ከሁሉ የበለጠ ነው፤ ይህ እርሱ ታላቅ ዕድል ነው።” (ሱረቱ-ተውባህ 72)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹‹ከአላህም የሆነዉ ዉዴታ ከሁሉ የበለጠ ነው›› በማለት፡ የአላህን ውዴታ ለማግኘት መታደል ጀነትና በውስጧ ከያዘቻቸው ጸጋዎች በላይ እንደሆነ ያስረዳል፡፡
አቢ ሰዒድ አል-ኹድሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ የጀነት ነዋሪዎችን እንዲህ ይላቸዋል፡- የጀነት ነዋሪዎች ሆይ! እነሱም፡- አቤት ጌታችን ሆይ! ሁሌም ለጥሪህ ታዛዦች ነን፡ ረዳታችንም አንተው ነህ ይላሉ፡፡ እሱም፡- በሰጠኋችሁ ጸጋ ተደሰታችሁን? ሲላቸው፡ እነሱም፡- ከዓለማት ለማንም ያልሰጠኸውን ጸጋ ሰጥተኸን እንዴት አንደሰትም!በማለት ይመልሳሉ፡፡ አላህም፡- ከዛ የበለጠ ነገር ልሰጣችሁ ነኝ ሲላቸው፡ እነሱም፡- ጌታችን ሆይ! ከዚህ የበለጠ ምን ጸጋ ኖሮ ነው? በማለት ይጠይቃሉ፡፡ እሱም፡- ውዴታዬን በናንተ ላይ አሰፍረዋለሁ፡ ከዚህ በኋላ ለዘልዓለም አልቆጣባችሁም ይላቸዋል” (ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡት)፡፡
ጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የጀነት ሰዎች ጀነት እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ፡ ጌታ አላህም፡- እንድጨምርላችሁ የምትፈልጉት ነገር አለን? ይላቸዋል፡፡ እነሱም፡- ጌታችን ሆይ! ከሰጠኸን በላይ የሆነ ነገር ምን አለና? ይላሉ፡፡ አላህም፡-እንዴታ! አለ እንጂ፡፡ ውዴታዬ ከዛ የበለጠና የበዛ ነው ይላቸዋል” (ሶሒሕ ኢብኑ-ሒባን ቁ 7439)፡፡
3. ሰላምታውን ማዳመጥ፡-
የጀነት ሰዎች ከሚጎናጸፉት መንፈሳዊ ጸጋዎች ውስጥ ሌላው የጌታቸውን ‹ሰላምታ› መስማታቸው ነው፡፡ ሰው ከባለ ስልጣናትና ከባለ ሐብት እንዲሁም ከታዋቂና ዝነኛ ሰዎች ሰላምታ ቢቀርብለት ምን ያህል ነው የሚያስደስተው? ታዲያ የፍጡራን ሁሉ አምላክ የሆነውን አላህ፡ ሰላምታውን መስማት እንዴት ያስደስት ይሆን!
“እነሱ ያ በናንተ ላይ እዝነትን የሚያወርድ ነው፤ መላእክቶችም ( እንደዚሁ ምሕረትን የሚለምኑላችሁ ናቸው) ፣ ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ያመጣችሁ ዘንድ (ያዝንላችኋል)፤ ለአማኞችም በጣም አዛኝ ነው። በሚገናኙት ቀን መከባበሪያቸው ሰላም በመባባል ነው፤ ለነርሱም የከበረን ምንዳ አዘጋጅቶላቸዋል።” (ሱረቱል አሕዛብ 43-44)፡፡
በዚህ አንቀጽ ስር ‹‹በሚገናኙት ቀን መከባበሪያቸው ሰላም በመባባል ነው›› በማለት አማኞች ጌታቸውን አላህን ሲገናኙ ‹ሰላም› በማለት እንደሚያከብራቸው ይገልጻል፡፡
“የገነት ሰዎች ዛሬ በእርግጥ በሥራዎች ውስጥ ተደሳቾች ናቸው…(ለነሱም) አዛኝ ከሆነው ጌታ ቃል በቃል ሰላምታ አላቸው።” (ሱረቱ ያሲን 55.58)፡፡
4. የሱን ምስጋና መስማት፡-
የጀነት ሰዎች በአላህ ቸርነት፡ በእምነታቸውና በመልካም ስራቸው ምክንያት አላህ ጀነትን ሲወፍቃቸው (ሲለግሳቸው) ይህ የእምነታችሁና የመልካም ስራችሁ ውጤት ነውና ስራችሁም የተመሰገነ ነው በማለት በአክብሮት ይገልጽላቸዋል፡፡ ታዲያ የጌታውን የምስጋና ቃል ከማዳመጥ በላይ ምን አስደሳች ነገር ይኖራል?
” وَمَنْ أَرَادَ الْآخِرَةَ وَسَعَى لَهَا سَعْيَهَا وَهُوَ مُؤْمِنٌ فَأُولَئِكَ كَانَ سَعْيُهُمْ مَشْكُورًا ” سورة الإسراء 19
“መጨረሻይቱንም ዓለም የፈለገ ሰው፣ እርሱ አማኝ ሆኖ ለርሷ (ተገቢ) ሥራዋን የሠራም ሰው እነዚህ ሥራቸው የተመሰገነ ይሆናል።” (ሱረቱል ኢስራእ 19)፡፡
” إِنَّ هَذَا كَانَ لَكُمْ جَزَاءً وَكَانَ سَعْيُكُمْ مَشْكُورًا ” سورة الإنسان 22
“ይህ በእርግጥ ለናንተ ዋጋ ሆነ፤ ሥራችሁም ምስጉን ሆነ፤ (ይባላሉ)” (ሱረቱል ኢንሳን (ደህር) 22)፡፡
ለዛሬ እዚህ ላይ ላቁምና በተከታታይ ክፍሎች የተወሰኑ የጀነት ጸጋዎችን በአላህ ፈቃድ እንዳስሳለን፡፡ አላህ በራሕመቱ ከጀነት ሰው ይበለን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


