በኡስታዝ አቡ ሐይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
ሀ. ‹‹መንፈሳዊ ጸጋ››
በክፍል አንድ ትምሕርታችን ላይ ለአማኞች ከተዘጋጁ ‹‹መንፈሳዊ ጸጋዎች›› መሐከል አራቱን ለአብነት ተመልክተናል፡፡ እነሱም፡-
1. የጌታችንን አላህ መለኮታዊ ፊት መመልከት
2. የጌታችንን አላህ ውዴታ መጎናጸፍ
3. የጌታችንን አላህ መለኮታዊ ሰላምታ መስማት
4. የጌታችንን አላህ የምስጋና ቃል ማዳመጥ
አላህ ፈቃዱ ከሆነ ዛሬም ከዛው የሚቀጥለውን እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡፡
5. የነቢያትን ጉርብትና ማግኘት፡-
የጀነት ሰዎች ከሚያገኙት መንፈሳዊ እርካታ መሀል አንድ የነቢያትን ጉርብትና ማግኘት ነው፡፡ አማኞች በጀነት ከነቢያት ጋር በመሆን፡ በአንድ ላይ የመሰብሰብን ዕድል ይጎናጸፋሉ፡፡ በተለይ ከነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ጋር መሆን፡፡ አላህ ይወፍቀን፡-
” وَمَنْ يُطِعِ اللَّهَ وَالرَّسُولَ فَأُولَئِكَ مَعَ الَّذِينَ أَنْعَمَ اللَّهُ عَلَيْهِمْ مِنَ النَّبِيِّينَ وَالصِّدِّيقِينَ وَالشُّهَدَاءِ وَالصَّالِحِينَ وَحَسُنَ أُولَئِكَ رَفِيقًا ” سورة النساء 69
“አላህንና መልክተኛውንም የሚታዘዝ ሰው፤ እነዚህ ከነዚያ አላህ በነርሱ ላይ ከለገሰላቸው ከነቢያት፣ ከጻድቃንም፣ ከሰማዕታትም ከመልካሞቹ ጋር ይኾናሉ። የነዚያም ጓደኝነት አማረ!” (ሱረቱ-ኒሳእ 69)፡፡
6. ቤተሰባዊ ግኑኝነት፡-
በምድራዊ ህይወታቸው አንድ ቤተሰብ ሁነው፡ በአንድ የእምነት ጥላ ስር የነበሩ፡ በድንገት ግን ያልታሰበ አደጋ (ሞት) የነጠቃቸው፡ ቀሪውን የቤተሰብ አካል ሀዘን የዋጣቸው ስንቶች አሉ!!፡፡ አላህ እነዚህን የቤተሰብ አካላት ሁሉም በኢስላም ላይ ጸንተው እስከሞቱ ድረስ በጀነት ሊያገናኛቸው ቃል ገብቷል፡፡ ዳግመኛ ተመልሶ አይመጣም በሚል ስሜት በምድር ላይ ተስፋ ቆርጠውበት የነበረው ‹መለየት› በጀነት ውስጥ እንደ አዲስ ሊቀጥልላቸው ማለት ነው፡፡ ከዚህስ የበለጠ ምን የሚያስደስት መንፈሳዊ ጸጋ አልለ? ሰው በሞት የተለየውንና የሚወደውን የቤተሰብ አካል ዳግም ለማግኘት መታጨት? ጌታ አላህ በቁርኣኑ እንዲህ ይላል፡-
” وَالَّذِينَ آمَنُوا وَاتَّبَعَتْهُمْ ذُرِّيَّتُهُمْ بِإِيمَانٍ أَلْحَقْنَا بِهِمْ ذُرِّيَّتَهُمْ وَمَا أَلَتْنَاهُمْ مِنْ عَمَلِهِمْ مِنْ شَيْءٍ كُلُّ امْرِئٍ بِمَا كَسَبَ رَهِينٌ ” سورة الطور 21
“እነዚያም ያመኑትና ዝርያቸውም በእምነት የተከተለቻቸው፣ ዝርያቸውን በነሱ እናስጠጋለን፤ ከሥራቸውም ምንም አናጎድልባቸውም፤ ሰው ሁሉ በሰራው ሥራ ተያዢ ነው።” (ሱረቱ-ጡር 21)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ‹‹ዝርያቸውን በነሱ እናስጠጋለን›› የሚለው፡ በእምነት የተከተሏቸውን የቤተስ አካላት በጀነት እንደሚያገናኛቸው የሚያስረዳ ነው፡፡
” وَالَّذِينَ صَبَرُوا ابْتِغَاءَ وَجْهِ رَبِّهِمْ وَأَقَامُوا الصَّلَاةَ وَأَنْفَقُوا مِمَّا رَزَقْنَاهُمْ سِرًّا وَعَلَانِيَةً وَيَدْرَءُونَ بِالْحَسَنَةِ السَّيِّئَةَ أُولَئِكَ لَهُمْ عُقْبَى الدَّارِ * جَنَّاتُ عَدْنٍ يَدْخُلُونَهَا وَمَنْ صَلَحَ مِنْ آبَائِهِمْ وَأَزْوَاجِهِمْ وَذُرِّيَّاتِهِمْ وَالْمَلَائِكَةُ يَدْخُلُونَ عَلَيْهِمْ مِنْ كُلِّ بَابٍ ” سورة الرعد 23-22
“እነዚያም የጌታቸውን ውዴታ ለመፈለግ የታገሡ፥ ሶላትንም አዘውትረው የሰገዱ እኛ ከሰጠናቸው ሲሳይም በምስጢርም ሆነ በግልጽ የመጸወቱ፥ ክፉውንም ነገር በበጎ የሚገፈትሩ ናቸው፤ እነዚያ ለነሱ መጨረሻይቱ ምስጉን አገር አለቻቸው። (እርሷም) የመኖሪያ ገነቶች ናት፤ ይገቡባታል፤ ከአባቶቻቸውም ከሚስቶቻቸውም ከዝርያቸውም መልካም የሠራ ሰው (ይገባታል)፤ መላእክትም በነሱ ላይ ከየደጃፉ ሁሉ ይገባሉ።” (ሱረቱ-ረዕድ 22-23)፡፡
“ወዳጆች በዚያ ቀን ከፊላቸው ለከፊሉ ጠላት ነው፤ አላህን ፈሪዎች ብቻ ሲቀሩ፤ (ለነርሱስ)፦ ባሮቼ ሆይ! ዛሬ ቀን በናንተ ላይ ፍርሃት የለባችሁም፤ እናንተም የምታዝኑ አይደላችሁም (ይባላሉ)።እነዚያ በአንቀጾቻችን ያመኑና ፍጹም ታዛዦች የነበሩ (ባሮቼ ሆይ!) ገነትን ግቡ እናንተም ሚስቶቻችሁም፣ ትደሰታላችሁ፤ (ይባላሉ)።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 67-70)፡፡
“ጌታችን ሆይ! እነርሱንም ከአባቶቻቸውና ከሚስቶቻቸውም ከዝርዮቻቸውም የበጀውን ሁሉ፣ እነዚያን ቃል የገባህላቸውን የመኖሪያ ገነቶች አስገባቸው፤ አንተ አሸናፊው ጥበበኛው አንተ ነህና።” (ሱረቱ-ጋፊር (ሙእሚን) 8)፡፡
7. የጓደኛሞች መገናኘት፡-
በዚህ ምድር ላይ በመሐከላቸው ምንም አይነት የስጋ ዝምድና ሳይኖር በአላህ መንገድ (በኢስላም) የተዋወቁና መንፈሳዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን የመሰረቱ ሙስሊሞች፡ በእምነታቸው ጸንተው ከሞቱ፡ ነጌም በጀነት አላህ ያገናኛቸዋል፡፡ በክብር ወንበር ላይም ተቀምጠው ይጨዋወታሉ፡፡ ስላሳለፉት ምድራዊ ህይወት ይነጋገራሉ፡፡ ከኢስላም ሊያስወጧቸው የነበሩ የጀሀነም ተጣሪዎችንም አንስተው ያወሳሉ፡፡ እንዲሁም ሌሎችን የደስታ ጨዋታዎችን፡-
“የሚጠያየቁም ሆነዉ ከፊላቸዉ ወደ ከፊሉ ይመጣሉ። ከእነርሱ የሆነ ተናጋሪ ይላል፡- እኔ ጓደኛ ነበረኝ። በእርግጥ አንተ ከሚያምኑት ነህን?” የሚል። በሞትንና ዐፈር አጥንቶችም በሆን ጊዜ እኛ በእርግጥ እንመረመራለን?” (የሚል)።እናንተ ተመልካቾች ናችሁን? ይላሉ። ይመለከታልም፤ በገሀነም መካከልም (ጓደኛዉን) ያየዋል። ይላል “በአላህ እምላለሁ፤ በእርግጥ ልታጠፋኝ ቀርበህ ነበር። የጌታየም ጸጋ ባልነበረ ኖሮ ወደ እሳት ከሚቀርቡት እሆን ነበር።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 50-57)፡፡
8. ጸብና ጥላቻ አለመኖር፡-
በነዚህ የጀነት ሰዎች መሀል ለዘልዓለሙ ዳግመኛ ጠብና ጥላቻ እንዳይከሰት፣ ምቀኝነትና ቅናት እንዳይኖር፡ አላህ እነዚህን በሽታዎች ከልባቸው ያስወግደዋል፡፡ ሁሌም ወንድማሞችና እህትማሞች እንጂ፡ ጠላቶችና ዘረኞች ሁነው አይተያዩም፡፡ ይህም ታላቅ ጸጋ ነው፡-
“በደረቶቻቸው ውስጥ ያለውንም ጥላቻ እናስወግዳለን፤ ወንዞች በሥሮቻቸው ይፈሳሉ፤ ለዚያም ወደዚህ (ላደረሰን ሥራ) ለመራን አላህ ምስጋና ይገባው፤ አላህ ባልመራንም ኖሮ አንመራም ነበር፤ የጌታችን መልክተኞች በእውነት ላይ ሲኾኑ በእርግጥ መጥተውልናል ይላሉ ይህቻችሁም ገነት ትሰሩት በነበራችሁት ተሰጣችኋት በማለት ይጠራሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 43)፡፡
“ባልጋዎችም ላይ ፊት ለፊት የሚቀጣጩ ወንድማማቾች ኾነው በደረቶቻቸው ውስጥ ከቂም ያለውን ሁሉ እናስወግዳለን፡፡ በእርሷም ውስጥ ድካም አይነካቸውም፡፡ እነሱም ከእርሷ የሚወጡ አይደሉም፡፡” (ሱረቱል ሒጅር 47-48)፡፡
9. ሰላም እንጂ ረብሻ የለውም፡-
የጀነት ነዋሪዎች በጀነት ውስጥ የሚሰሙት ቃሉ ‹ሰላም› የሆነውን ብቻ ነው፡፡ ጫጫታና ረብሻ፣ አመጽና ችግር የሚባል ነገር ፈጽሞ አይከሰትም፡-
“ግን የተጸጸተና ያመነም በጎንም ሥራ የሠራ ሰዉ እነዚህ ገነትን ይገባሉ፤ አንዳችንም አይበደሉም። የመኖሪያን ገነቶች፣ ያችን አልረሕማን ለባሮቹ በሩቅ ኾነዉ ሳሉ ተስፋ ቃል የገባላቸዉን፣ (ይገባሉ) እርሱ ተስፋዉ ተፈጻሚ ነዉና፤ በርሷ ሰላምን እንጂ ዉድ ቅን ነገር አይሰሙም፤ ለነሱም በርሷ ዉስጥ፣ ጧትም ማታም ሲሳያቸዉ አላቸዉ።” (ሱረቱ መርየም 60-62)፡፡
“በውስጧ ትርፍ ቃልንም ማስዋሸትንም አይሰሙም።” (ሱረቱ-ነበእ 35)፡፡
“በውስጥዋ ውድቅ ንግግርንና መውወንጀልን አይሰሙም። ግን ሰላም መባባልን፣ (ይሰማሉ)።” (ሱረቱል ዋቂዓህ25-26)፡፡
10. ፍጹም ዘላለማዊ መሆናቸው፡-
የጀነት ሰዎች በጀነት ውስጥ የሚቆዩት ለተገደበ ዓመትና ዘመን ሳይሆን፡ ፍጹም ማብቂያ ለሌለው ዘላለማዊ ህይወት ነው፡፡
“እነዚያንም ያመኑትንና መልካም ሥራዎችን የሠሩትን ከስራቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውን ገነቶች ዘለዓለም በውስጣቸው ዘውታሪዎች ሲኾኑ በእርግጥ እናስገባቸዋለን…” (ሱረቱ-ኒሳእ 57)፡፡
“እነዚያ ያመኑትና መልካሞችንም የሠሩት፣ እነዚያ እነሱ ከፍጥረት ሁሉ በላጭ ናቸው። በጌታቸው ዘንድ ምንዳቸው ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው የመኖሪያ ገነቶች ነው፤ በውስጣቸው ዘለዓለም ዘውታሪዎቹ ሲኾኑ (ይገቡባቸዋል)። አላህ ከነሱ ወደደ፤ ከርሱም ወደዱ፤ ይህ ጌታውን ለፈራ ሰው ነው።” (ሱረቱል በይናህ 7-8)፡፡
አቢሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ አሉ፡- “አንድ ተጣሪ (መልአክ) እንዲህ በማለት ይጣራል፡- (የጀነት ሰዎች ሆይ!) ከአሁን በኋላ ሁሌም ጤነኛ ናችሁ፡ ለዘልዓለም አትታመሙም፣ ሁሌም ህያው ናችሁ ፈጽሞ አትሞቱም፣ ሁሌም ወጣት ናችሁ ፈጽሞ አታረጁም፣ ሁሌም ተጠቃሚዎች ናችሁ ፈጽሞ አትቸገሩም” (ሙስሊም የዘገበው)፡፡
አላህ በራሕመቱ ከጀነት ሰው ይበለን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


