በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
ለ. ‹‹ስጋዊ ጸጋዎች››
ባሳለፍናቸው ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ስለ ጀነት ጸጋዎች ‹‹ኒዕማ›› ጀምረን፡ የመጀመሪያውን አይነት ኒዕማ ማለትም ‹መንፈሳዊ ጸጋ› ለመግለጽ አስር ምሳሌዎችን ለአብነት ተመልክተናል፡፡ አላህ ፈቃዱ ከሆነ ደግሞ ስለ ስጋዊ ጸጋዎችም እንደዚሁ የተወሰነ ነገር እንመለከታለን ኢንሻአላህ፡-
1. መብልና መጠን፡-
የአላህ ባሮች በጀነት ውስጥ ከተዘጋጀላቸው የክብር ስጦታና መስተንግዶ መሐከል አንዱ ‹መብልና መጠጥ› መኖሩ ነው፡፡ እነዚህን የመብና የመጠጥ አይነቶች ከመዘርዘራችን በፊት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን ቀድሞ መመልከቱ ጠቃሚ ነው፡፡ እነሱም፡-
– በጀነት ውስጥ ለአማኞች የተዘጋጀው መብልና መጠጥ የክብር መገለጫና የድሎት መጠቀሚያ እንዲሆን እንጂ ለረኃብና ለጥም ማስታገሻ እንዲሆን ታስቦ አለመዘጋጀቱን ነው፡፡ ምክንያቱም በጀነት ውስጥ ረኃብም ሆነ ውሀ ጥም የለምና፡፡ የተዘጋጁት መጠጦችም ሆኑ መብሎች ‹የቅንጦት› መገለጫዎች ናቸው፡፡ ለአምሮት የተዘጋጁ ስጦታዎች ናቸው፡፡
የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን (አደምና ሐዋእን) ዐለይሂማ ሰላም፡ ምሳሌ አድርገን ብንወስድ ፡ እነሱ በጀነት በነበሩበት ወቅት የውሀ ጥምም ሆነ ረኃብ የሚባል ነገር አልነበረባቸውም፡፡ በውስጡ የነበሩት ጸጋዎች ሁሉ የድሎትና የቅንጦት እንጂ የረኃብ ማስታገሻና የጥም መቁረጫ አይደለም፡፡ ቁርኣን እንዲህ ይላል፡-
” إِنَّ لَكَ أَلَّا تَجُوعَ فِيهَا وَلَا تَعْرَى * وَأَنَّكَ لَا تَظْمَأُ فِيهَا وَلَا تَضْحَى ” سورة طه 119-118
“ለአንተ በእርሷ ውስጥ አለመራብና አለመታረዝ አለህ። አንተም በእርሷ ውስጥ አትጠማም፤ በፀሃይ አትተኮስም።” (ሱረቱ ጣሀ 118-119)፡፡
– ሌላው ደግሞ ከመብላትና ከመጠጣት በኋላ ያን ተከትሎ የሚመጣው ስርአት (መሽናትና ቆሻሻን ማስወገድ) ፈጽሞ በጀነት አለመኖሩ ነው፡፡ አማኞች የበሉትና የጠጡት ነገር ከሰውነታቸው የሚወጣው በላብና በትንፋሽ አማካይነት ብቻ ነው፡፡ ይህ ላብና ትንፋሽ ደግሞ ከሚስክ ሽታ የበለጠ መዓዛ ያለው ነው፡፡ እንደ-ምድራዊ ህይወት ጠረኑ የሚገማ አይደለም፡፡
ጃቢር ኢብኑ ዐብዲላህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “የጀነት ሰዎች በውስጧ ይበላሉ ይጠጣሉ፡፡ ሆኖም አይተፉም፣ አይሸኑም፣ ቆሻሻቸውን (ከኋላ) አያስወጡም፣ አይናፈጡም፡፡ ሶሐቦችም (ረዲየላሁ ዐንሁም)፡- የበሉትና የጠጡትስ? ብለው ሲጠይቁ፡ እሳቸውም፡- የበሉት ምግብ ተመልሶ የሚስክ መዓዛ አይነት ሽታ ባለው ትንፋሻቸውና ላባቸው አማካኝነት ይወጣል፡፡ መተንፈስን የለገሳቸው አላህ በምትኩ ተስቢሕንና ተሕሚድን (ሱብሐነላህ ማለትንና አልሐምዱ ሊላህ ማለትን) ይለግሳቸዋል” (ሙስሊም 7331)፡፡
ይህንን ከተረዳን ከተዘጋጀው የመጠጥና የመብል አይነት በከፊል እንመልከት፡-
‹‹መጠጦች››፡-
በጀነት ውስጥ አማኞች አራት አይነት የመጠጥ ወንዝ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡
እነሱም በቀጣዩ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ተገልጸዋል፡-
” مَثَلُ الْجَنَّةِ الَّتِي وُعِدَ الْمُتَّقُونَ فِيهَا أَنْهَارٌ مِنْ مَاءٍ غَيْرِ آسِنٍ وَأَنْهَارٌ مِنْ لَبَنٍ لَمْ يَتَغَيَّرْ طَعْمُهُ وَأَنْهَارٌ مِنْ خَمْرٍ لَذَّةٍ لِلشَّارِبِينَ وَأَنْهَارٌ مِنْ عَسَلٍ مُصَفًّى وَلَهُمْ فِيهَا مِنْ كُلِّ الثَّمَرَاتِ وَمَغْفِرَةٌ مِنْ رَبِّهِمْ كَمَنْ هُوَ خَالِدٌ فِي النَّارِ وَسُقُوا مَاءً حَمِيمًا فَقَطَّعَ أَمْعَاءَهُمْ ” سورة محمد 15
“የዚያች ጥንቁቆች ተስፋ የተሰጧት ገነት ምስል፡- በውስጧ ሺታው ከማይለወጥ ውሃ ወንዞች፣ ጣዕሙ ከማይለውጥ ወተትም ወንዞች፣ ለጠጪዎች ሁሉ ጣፋጭ ከኾነች የወይን ጠጅም ወንዞች፣ ከተነጠረ ማርም ወንዞች አሉባት፤ ለነሱም በውስጧ ከፍሬዎች ሁሉ (በያይነቱ) ከጌታቸው ምሕረትም አላቸው፣ (በዚች ገነት ውስጥ ዘውታሪ የሆነ ሰው) እርሱ በእሳት ውስጥ ዘውታሪ የሆነ ሰው ሞቃትንም ውሃ እንደ ተጋቱ፣ አንጀቶቻቸውንም ወዲያውኑ እንደ ቆራረጠው ነውን? (አይደለም)።” (ሱረቱ ሙሐመድ 15)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ አራት አይነት ወንዞችን እናገኛለን፡፡ እነሱም፡-
1. የውሀ ወንዞችን፡- ይህ የውሀ ወንዝ ጣዕሙ ፈጽሞ የማይቀየር፡ መጥፎ ሽታ የሌለው ሁሌም ንጹህ የተደረገ መሆኑ ከምድራዊው ፈጽሞ ይለየዋል፡፡ የምድሩ ውሀ በአንድቦታ ላይ ከመቆየቱ የተነሳ የሚገማ፣ መልኩ የሚቀየር ነው፡፡
2. የወተት ወንዞች፡- ይህ የወተት ወንዝ ከመቆየቱ የተነሳ ጥፍጥናው የማይቀየር፡ መልኩም እጅግ የነጣ ነው፡፡ ዛሬ በምድር ያለው ወተት ግን ከረጋ ጥፍጥናው የሚቀየርና የሚበጣጠስ፡ መልኩና ሽታውም የሚለወጥ ነው፡፡
3. የወይን-ጠጅ ወንዞች፡- ይህ የመጠጥ ወንዝ ደግሞ ለመቅመስ ሽታው የማያስቸግር፡ ለጠጪዎችም ጣፋጭ የተደረገ፡ ከጠጡትም በአናት ላይ ወጥቶ ለስካር እና ለችግር የማይዳርግ ነው፡፡ ደግሞም የታተመው (የታሸገው) ራሱ በሚስክ ነው፡፡ ሌሎች ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችም ይህን ሀሳብ የበለጠ ያጠናክራሉ፡፡
“በድሎት ገነቶች ዉስጥ። ፊት ለፊት የሚታያዩ ሲሆኑ በአልጋዎች ላይ (ይንፈላሰሳሉ)።ከሚመነጭ ወይን ጠጅ በያዘ ብርጭቆ በእነርሱ ላይ ይዞርባቸዋል። ነጭ ለጠጪዎች ጣፋጭ ከኾነች። በእርሷ ዉስጥም ራስ-ምታት የለባትም። እነርሱም ከእርሷ የሚሰክሩ አይደሉም።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 43-47)፡፡
“ከጠጅ ምንጭም፣ በብርጭቆዎችና በኩስኩስቶች በጽዋም (በነሱ ላይ ይዞራሉ)። ከርሷ የራስ ምታት አያገኛቸውም፤ አይሰክሩምም።” (ሱረቱል ዋቂዓህ 18-19)፡፡
“እውነተኞቹ ምእመናን በእርግጥ በድሎት (ገነት) ውስጥ ናቸው። በባለ አጎበር አልጋዎች ላይ ሆነው ይመለከታሉ። በፊቶቻቸው ላይ የድሎትን ውበት ታውቃለህ። ተጣርቶ ከታተመ ጠጅ ይጥጠጣሉ። ማተሚያው ሚስክ ከሆነ፤ በዚህም ተሽቀዳዳሚዎች ይሽቀዳደሙ።” (ሱረቱል ሙጠፊፊን 22-26)፡፡
የምድሩ መጠጥ ግን ሽታው ሰው አለማቅረቡ፡ ተጠጥቶም ማስከሩ፡ጥቅምንም ሳይሆን ጉዳትን ማስከተሉ ፈጽሞ ከጀነቱ ጋር አያመሳስለውም፡፡
4. የማር ወንዞች፡- ይህ የማር ወንዝም ለማጣራት የሰው ኃይል ሳያስፈልገው በራሱ ፍጹም የተጣራ ነው፡፡ እዚህ ምድር ያለው ግን በራሱ የተጣራ አለመሆኑ ነው፡፡
ሌሎች አይነት መጠጦችም (ተስኒም፣ ካፉር፣ ዘንጀቢል…) ተብለው የሚጠሩ ምንጮች አሉ፡፡
“በጎ አድራጊዎች፥ መበረዣዋ ካፉር ከሆነች ጠጅ ይጠጣሉ። ከርሷ የአላህ ባሮች፥ የሚጠጡላት፥ (ወደፈለጉበት) ማንቧቧትን የሚያንቧቧት ከሆች ምንጭ (ይጠጣሉ)።” (ሱረቱ-ደህር(ኢንሳን) 5-6)፡፡
“በእርሷም መበረዣዋ ዘንጀቢል የሆነችን ጠጅ ይጠጣሉ። በውስጧ ያለችውን ሰልሰቢል ተብላ የምትጠራውን ምንጭ።” (ሱረቱ-ደህር(ኢንሳን) 17-18)፡፡
ስለ ጀነት የክብር መጠጦች በተወሰነ መልኩ ከተነጋገርን፡ ቀጣዩን ነጥብ ‹‹ስለ-መብል›› ደግሞ በሌላ ጊዜ እንመለከተዋለን ኢንሻአላህ፡፡ አላሁመ ወፍፊቅነል-ጀንናህ፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


