አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል!!
በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
በሶስት ጨለማ የተዋጠ ማኅበረሰብ እንዴት ስለ ብርሐን ሊናገር ይችላል? ኩፍር ውስጥ መዘፈቅ በራሱ ትልቅ ጨለማ ነው፡፡ መሃይምነት ደግሞ ሌላ ጨለማ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ጭፍን ጥላቻ ሲታከልበት ድርብርብ ጨለማ ይሆናል፡፡
በዚህ አይነት ጨለማ የተዋጠ ማኅበረሰብ በምንም አይነት መልኩ ስለ ብርሐን መናገር አይችልም፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ ለዓለም ህዝብ ራሕመት እና ብርሐን ሁነው የተላኩ ነቢይ ናቸው (አል-አንቢያእ 107፣ አል-አሕዛብ 45-46)፡፡ ለትዳር አጋሮቻቸው፣ ለሶሐቦቻቸው፣ ለኡማው በጠቅላላ መልካምን የሚመኙና የሚያዝኑ ናቸው (አት-ተውባህ 128)፡፡
እንደዛም ሁኖ ግን ማንም መልክተኛ ወደ ህዝቦቹ ሲላክ መሰደቡ፣ መመታቱ፣ በሱ ላይ በሀሰት መወራቱ አይቀርም (አዝ-ዛሪያት 52)፡፡ አላህ ግን ሐቅ ተሸፍና እንዳትቀር ነቢያቶቹን በማስረጃ በመደገፍ፡ ለሀሰት መልክተኞችም የሐቅ ተጣሪዎችን በማዘጋጀት እውነቱን በቃሉ ያረጋግጣል (ዩኑስ 82)፡፡ ሀሰት እውነት ፊት ለመቆም አቅሙ የላትምና (አል-ኢስራእ 81)፡፡
ለዛሬ አላህ ፈቃዱ ከሆነ በአንድ መሃይምነትና ጭፍን ጥላቻ በተቀላቀለበት የቅጥፈት ወሬ ላይ አብረን እንቆያለን፡፡ መልካም ንባብ፡-
عن عائشة قالت:- كانت إحدانا إذا كانت حائضا فأراد رسول الله صلى الله عليه و سلم أن يباشرها أمرها أن تتزر في فور حيضتها ثم يباشرها . قالت وأيكم يملك إربه كما كان النبي صلى الله عليه و سلم يملك إربه. رواه البخاري ومسلم.
Narrated ‘Abdur-Rahman bin Al-Aswad: (on the authority of his father) ‘Aisha said: “Whenever Allah’s Apostle wanted to fondle anyone of us during her periods (menses), he used to order her to put on an Izar and start fondling her.” ‘Aisha added, “None of you could control his sexual desires as the Prophet could.” Bukhari :: Book 1 :: Volume 6 :: Hadith 299
‘A’isha reported: When anyone amongst us (amongst the wives of the Holy Prophet) menstruated, the Messenger of Allah (may peace be upon him) asked her to tie a waist-wrapper over her (body) and then embraced her. Muslim :: Book 3 : Hadith 577
የምእመናን እናት ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- “ከእኛ ውስጥ አንዳችን በሐይድ (የወር አበባ) ላይ ከሆነችና የአላህ መልክተኛም እሷን ለመንካት(ለማቀፍ) ከፈለጉ ከሐይድ ወቅት ጀምሮ ልብስን እንድታሸርጥ ያዟት ነበር፡፡ ከዛም ገላዋን ይዳብሷት፡ ይነኳት ነበር፡፡ የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ስሜታቸውን ይቆጣጠሩ እንደነበረው ማንኛችሁ ነው ስሜቱን መቆጣጠር የሚችለው? አለች፡፡” (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
በነዚህ የጨለማው ዓለም ተጓዦች አገነዛዘቡ ከተበደለው ሐዲሥ አንዱ ይህ ነበር፡፡ እነሱ መልክቱን ገልብጠው፡- የሙስሊሞች ነቢይ ከሚስቶቻቸው ጋር በወር አበባ ወቅት እንኳ ይገናኙ ነበር በማለት የሳቸውን ክብር ለመንካት ምላሳቸውን አሾሉ፡፡ እስኪ ምላሹን በአላህ ፈቃድ እንከታተል፡-
1ኛ. በሐዲሡ ውስጥ የሰፈረው ኃይለ ቃል ‹‹ዩባሺሩሃ›› የሚል እንጂ ‹‹ዩጃሚዑሃ›› የሚል አይደለም፡፡ ሙባሸራህ ማለት ቀጥታ ፍቺው፡- አካላዊ ንክኪ እንጂ የግብረ ስጋ ግኑኝነት አይደለም፡፡ ወደ ግብረ-ስጋ ግንኙነት ሊወስደው የሚችል ተያያዥ ሀሳብ ከሌለ በዛ መተርጎሙ ፍጹም ስህተት ነው፡፡ የሐዲሡ ሃሳብ ደግሞ ከንክኪ ጋር እንጂ ከግብረ-ስጋ ግንኙነት ጋር እንደማይገናኝ ለመግለጽ ‹‹ሽርጥን እንድታሸርጥ ያዟት ነበር›› የሚለው በራሱ አስረጂ ነው፡፡ የተፈለገው የግብረ-ስጋ ግኑኝነት ከሆነ ለምን በላይዋ ላይ ልብስን እንድትለብስ ማዘዙ ተፈለገ?
2ኛ. እነዚህ ወገኖች ዐረብኛ ስለማይችሉ (አሊፍ ይቁም ይተኛ ስለማያውቁ) በቋንቋ ሸውዳችሁን ነው እንዳይሉ ወደ እንግሊዘኛው ደግሞ እንግባ (እሱንም ካወቁት ማለቴ ነው)፡፡ በእንግሊዘኛው ላይ የተቀመጠው ቃል ‹‹fondle›› እና ‹‹embraced›› የሚለው ነው፡፡
‹‹fondle›› ማለት ‹መደባበስ፣ መነካካት› ማለት ነው፡፡ ‹‹embrace›› ማለት ደግሞ፡- ‹ማቀፍ፣ መያዝ› ማለት ነው፡፡ የሁለቱም ትርጉም ተመሳሳይ ነው፡፡ አንዳቸውም የግብረ-ስጋ ግኑኝነትን (Sexual Intercourse) አያመለክትም፡፡
3ኛ. በሐዲሡ ማብቂያ ላይ እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) ‹‹የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ስሜታቸውን ይቆጣጠሩ እንደነበረው ማንኛችሁ ነው ስሜቱን መቆጣጠር የሚችለው?›› ማለቷ በራሱ ጉዳዩ ከግብረ-ስጋ ፍላጎት ጋር ምንም ግኑኝነት እንደሌለው ያስረዳል፡፡ እሳቸው ምንም ባለቤቶቻቸውን ቢነካኩና ቢዳብሱም ይህ ፍላጎታቸው ሚስቶቻቸውን ወደ መገናኘት እንዳይወስዳቸው ስሜታቸውን ይቆጣጠሩ እንደነበር በተወዳጅ ባለቤታቸው ተመስክሮላቸዋል፡፡
4ኛ. የትዳር አጋርን በወር አበባ ወቅት ከግብረ-ስጋ ግኑኝነት መራቅ እንደሚገባን የአላህ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ያስረዳል፡-
” وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ وَلَا تَقْرَبُوهُنَّ حَتَّى يَطْهُرْنَ فَإِذَا تَطَهَّرْنَ فَأْتُوهُنَّ مِنْ حَيْثُ أَمَرَكُمُ اللَّهُ إِنَّ اللَّهَ يُحِبُّ التَّوَّابِينَ وَيُحِبُّ الْمُتَطَهِّرِينَ ” سورة البقرة 222
“ከወር አበባም ይጠይቁሃል፡፡ እርሱ አስጠያፊ ነው፡፡ ሴቶችንም በወር አበባ ጊዜ ራቋቸው፡፡ ንጹሕ እስከሚኾኑም ድረስ አትቅረቡዋቸው፡፡ ንጹሕ በኾኑም ጊዜ አላህ ካዘዛችሁ ስፍራ ተገናኙዋቸው፡፡ አላህ (ከኃጢኣት) ተመላሾችን ይወዳል፤ ተጥራሪዎችንም ይወዳል በላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 222)፡፡
‹‹ሴቶችን ራቋቸው›› እና ‹‹አትቅረቧቸው›› የሚለው የቁርኣን ክፍል፡ እነሱ መጽሐፍ ውስጥ በተቀመጠው መልኩ ነው ብለን እንዳናስብ የአላህ መልክተኛ ራሳቸው እንዲህ በማለት አብራርተውታል፡-
عَنْ أَنَسٍ أَنَّ الْيَهُودَ كَانُوا إِذَا حَاضَتِ الْمَرْأَةُ فِيهِمْ لَمْ يُؤَاكِلُوهَا، وَلَمْ يُجَامِعُوهُنَّ فِي الْبُيُوتِ فَسَأَلَ أَصْحَابُ النَّبِيِّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ النَّبِيَّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فَأَنْزَلَ اللهُ تَعَالَى {وَيَسْأَلُونَكَ عَنِ الْمَحِيضِ قُلْ هُوَ أَذًى فَاعْتَزِلُوا النِّسَاءَ فِي الْمَحِيضِ} [البقرة: 222] إِلَى آخِرِ الْآيَةِ، فَقَالَ رَسُولُ اللهِ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ: «اصْنَعُوا كُلَّ شَيْءٍ إِلَّا النِّكَاحَ» فَبَلَغَ ذَلِكَ الْيَهُودَ، فَقَالُوا: مَا يُرِيدُ هَذَا الرَّجُلُ أَنْ يَدَعَ مِنْ أَمْرِنَا شَيْئًا إِلَّا خَالَفَنَا فِيهِ،…” رواه المسلم.
አነስ ኢብኑ-ማሊክ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ አለ፡- “አይሁዶች ሚስቶቻቸው ሐይድ ላይ ሲሆኑ፡ አብረዋቸው አይመገቡም፣ በቤት ውስጥም አብረዋቸው አይተኙም ነበር፡፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሶሐባዎችም ስለ ጉዳዩ ጠየቁ፡፡ ከዛም ከላይ የተጠቀሰው የቁርኣን አንቀጽ ወረደ፡፡ የአላህ መልክተኛም፡- ‹‹ከግብረ-ስጋ ግንኙነት በስተቀር ሁሉንም አድርጉ›› በማለት መለሱ፡፡ ይህ ነገርም አይሁዶች ዘንድ ደረሰ፡፡ እነሱም፡- ይህ ሰው (ታላቁን ነቢይ) ከጉዳያችን ላይ ቢቃረነን እንጂ ምንም አልተወም አሉ፡፡” (ሙስሊም )፡፡ Muslim :: Book 3 : Hadith 592
በዚህ የቅዱስ ቁርኣን ነቢያዊ ማብራሪያ መሰረትም እሳቸው ግብረ-ስጋ ግንኙነትን በወር አበባ ወቅት ይከለክሉ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ታዲያ እሳቸው ተከታዮቻቸውን ከልክለው ለራሳቸው ግን ይጠቀሙ ነበር ብሎ ማሰብ የጤና ነውን?
5ኛ. ከላይ ባየናቸው አራት መንገዶች መሰረት የመሃይማኖቹ ጭፍን ክስ መሰረት አልባ እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ አሁንም በድጋሚ ክሳቸው ውሀ መቋጠር እንደማይችል እነሱ ባሉት መልኩ እንሂድና ጥያቄ እናቅርብላቸው፡-
እናንተ እንዳላችሁት የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በወር አበባ ወቅት ከባለቤታቸው ጋር ይገናኙ ነበር እንበል (ምንም ውሸት ቢሆንም)፡፡ ታዲያ ምንድነው ጥፋቱ? እኮ ምን?
ጥፋቱማ፡- በሐይድ ወቅት ከባለቤት ጋር መገናኘት ኃጢአት መሆኑ ነው!!፡፡
ማነው ኃጢአት ነው ብሎ ያስተማራችሁ? በወንጌል ውስጥ በወር አበባ ወቅት ሚስትን መገናኘት የሚከለክል ጥቅስ ልታሳዩን ትችላላችሁ? ወንጌላችሁ እንደሆነ ይህን ነገር አያስተምራችሁም፡፡ ታዲያ ምን መሰረት ይዛችሁ ነው እኛን የምትቃወሙት? ሰው ባዶ ቤት ውስጥ ሆኖ የሰው ቤት ዕቃን ከመቁጠርና ከመተቸት ለምን የራሱን ቤት በዕቃ አይሞላም?
አይ! በወንጌል ሳይሆን በኦሪት ህግ የተከለከለ ስለሆነ ነው የምትሉ ከሆነ ደግሞ፡ የኦሪቱን ህግ ትቀበሉታላችሁ ወይ? በማለት እንጠይቃችኋለን፡፡ ምላሻችሁም አዎ! የሚል ከሆነ፡ እንግዲያውስ ኦሪት በወር አበባ ላይ ያለችን ሴት አትገናኛት ብቻ ሳይሆን የሚለው ሌላም ስላለው አብረን እንየው፡፡ አንዱን ጥሎ ሌላኛውን አንጠልጥሎ መሄድ የለምና፡፡ እንዲህ ይላል የዛሬው ዘመን ኦሪት፡-
19፤ ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ #ርኩስ ነው። 20፤ መርገምም ስትሆን የምትተኛበት ነገር ሁሉ #ርኩስ ነው፤ የምትቀመጥበትም ነገር ሁሉ #ርኩስ ነው። 21፤ መኝታዋንም የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ #ርኩስ ነው። 22፤ የምትቀመጥበትንም ነገር ሁሉ የሚነካ ሁሉ ልብሱን ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም #ርኩስ ነው። 23፤ በመኝታዋም ላይ ወይም በምትቀመጥበት ነገር ላይ ቢሆን ሲነካው እስከ ማታ ድረስ #ርኩስ ነው። 24፤ ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን #ርኩስ ነው፤ የሚተኛበትም መኝታ ሁሉ #ርኩስ ነው። 25፤ ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፥ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፥ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ #ርኩስ ናት። 26፤ ደምዋም በሚፈስስበት ወራት ሁሉ የምትተኛበት መኝታ ሁሉ በመርገምዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ያለ ይሆንባታል፤ የምትቀመጥበት ነገር ሁሉ እንደ መርገምዋ ርኵስነት #ርኵስ ነው። 27፤ እነዚህንም ነገሮች የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው፤ ልብሱንም ያጥባል፥ በውኃም ይታጠባል፥ እስከ ማታም #ርኩስ ነው። 28፤ ከፈሳሽዋም ብትነጻ ሰባት ቀን ትቈጥራለች ከዚያም በኋላ ንጹሕ ትሆናለች። 29፤ በስምንተኛውም ቀን ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ይዛ ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ታመጣቸዋለች።
30፤ ካህኑም አንደኛውን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል፤ ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ #ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል።
(ኦሪት ዘሌዋውያን ምእ15፡ ቁ 19-30)፡፡
ወገኖች ሆይ! ይኸው መመሪያችሁ! ለካ እናንተም ነቢዩ ሙሐመድ ሚስቶቻቸውን ለምን እንደዚህ አልተጸየፉም በማለት ተቆጭታችሁ ነውን የምትቃወሙ የነበረው? ምነው ሴት ልጅ ይህን ያህል እንደ እንደ እቃ የረከሰች ናትን? ባለቤቷ ወደሷ መቅረብ የሚችለው ንጹህ ስትሆን ብቻ ነውን? በጣም የሚገርመው ደግሞ የሷ መርከስ ብቻ ሳይሆን እሷ የነካችው፣ ያረፈችበት፣ እሷንም የነካት ማንኛውም ነገር የረከሰ መሆኑ ነው፡፡ እንዴት ነው ታዲያ ቤተሰባዊ ህይወት መምራት የሚቻለው?
-አቶ ባል ከስራ ስትመጣ ባለቤትህን እንኳን ልትስማት፡ ከነካሀት ራሱ ትረክሳለህ፡፡ እሷ የነካችውን የምትነካም ከሆነ ትረክሳለህ፡፡ መርከስም ብቻ አይደለም ልብስህንና ገላህን ትታጠባለህ፡፡ ታጥበህም አይወርድልህ እስኪመሽም ድረስ ረክሰህ ትውላለህ፡፡
እሷ ባረፈችበት ወንበርም ሆነ መኝታ ላይ አርፋለሁ ብትል አሁንም ትረክሳለህ፡፡ ገላህን ታታጠባለህ ልብስህንም ታጥባለህ፡፡ አብረሀት ከተኛህና ከርክሰትዋ ቢነካህ አንተም አብረህ ሰባት ቀን የረከስክ ትሆናለህ፡፡ አጂብ!፡፡ ታዲያ ሴት እህቶቼ አላህ ሙስሊም ስላደረጋችሁ አልሐምዱ ሊላህ አትሉም?
አዎ! አልሐምዱ ሊላህ፡፡ ኢስላም እንደዚህ አላስተማረንም፡፡ በወር አበባ ወቅት አንድ ባል ከሚስቱ የተከለከለው ነገር አንድና አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም ግብረ-ስጋ ግኑኝነት! በቃ ይሄ ነው፡፡ ከዛ ውጪ አብሯት ቢቀመጥ፣ ቢጫወታት፣ ቢያጎርሳት፣ ቢያቅፋትና ቢስማት፣ በአንድ መኝታም አብሯት ቢተኛ አልተከለከለም፡፡ ቀጣዩን ነቢያዊ ሞዴል እንከታተል፡-
ሀ. አብሮ መተኛት፡-
እናታችን መይሙናህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹የአላህ መልክተኛ እኔ በሐይድ ላይ እያለሁ በሳቸውና በእኔ መሐከል ልብስ ይደረግና አብረውኝ ይተኙ ነበር›› (ሙስሊም)፡፡ Muslim :: Book 3 : Hadith 580
ለ. አብሮ መብላት፡-
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹እኔ በሐይድ ላይ ሁኜ ሳለ በእቃ እጠጣና ከዛም የጠጣሁበትን እቃ ለአላህ መልክተኛ እሰጣቸውና፡ አፋቸውን እኔ በጠጣሁበት ቦታ በማድረግ ይጠጡበት ነበር፡፡ በወር አበባ ላይ ሁኜ አጥንትንም (ስጋ ያለውን) እመገብ ነበር፡፡ ከዛም ለሳቸው እሰጣቸውና እሳቸውም የኔ አፍ የነካበት ቦታ ላይ አፋቸውን ያደርጉበት ነበር›› (ሙስሊም)፡፡Muslim :: Book 3 : Hadith 590
ሐ. መታጠብና ጸጉርን ማበጠር
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹እኔ በሐይድ ላይ ሳለሁ የአላህ ነቢይም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ይነኩኝ ነበር፡፡ በመስጂድ ውስጥም ኢዕቲካፍ አድርገው ሳለ፡ ከመስጂዱ ራሳቸውን ወደ ውጭ ያወጡና እኔ አጥባቸው ነበር›› (ቡኻሪና ሙስሊም) Bukhari :: Book 3 :: Volume 33 :: Hadith 247
አሁንም በድጋሚ እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ ትላለች፡- ‹‹እኔ በሐይድ ወቅት ሆኜ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በመስጂድ ውስጥ ሆነው ራሳቸውን ወደኔ ያስጠጉትና ጸጉራቸውን አበጥርላቸው ነበር፡፡›› (ቡኻሪና ሙስሊም ) Bukhari :: Book 3 :: Volume 33 :: Hadith 245
ይህ ነበር የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አስተምህሮትና ሞዴል!!፡፡ በጣም ከገረሙኝ የመጽሐፍ ቁዱስ የወር አበባ ፍርድ ላይ ‹‹ማንም ከእርስዋ ጋር ቢተኛ መርገምዋም ቢነካው፥ ሰባት ቀን #ርኩስ ነው›› የሚለው ነው፡፡ ከዚህ የወር አበባ ደም ነካው ተብሎ ሰባት ቀን ሙሉ የሚረክስ ባል!!፡፡ ታዲያ ምኑ ገረመህ ካላችሁኝም፡ የአላህ መልክተኛም ይህ ነገር ገጥሟቸው ነበር፡፡ ታዲያ ምን ሆኑ? ካላችሁኝ ቀጣዩን ሐዲሥ አብረን እንከታተል፡-
እናታችን ዓኢሻህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንዲህ አለች፡- ‹‹እኔና የአላህ መልክተኛ በወር አበባ ላይ ሁኜ ሳለ በአንድ ልብስ (አንሶላ ወይም ሌላ) እንተኛ ነበር፡፡ ከኔ አንዳች ነገር (ከደሙ) ቢያገኛቸው፡ የነካውን ቦታ ያጥቡት ነበር፡፡ ወደሌላው ክፍልም (ለማጠብ) አያሰፉትም፡፡ ከዛም በዛው ልብስ (ገላ) ሶላትን ይሰግዱ ነበር›› (አቡ ዳዉድ 269) Dawud :: Book 1 : Hadith 269
ይህ ነው አርአያነት! ደሙ የነካውን የሰውነትም ሆነ የልብስ ክፍል በማጠብ መብቃቃት፡፡ የምን ሰባት ቀን መርከስ? ልብሱን ከሆነ የነካው የምን ገላ መታጠብ? ገላቸውን ከሆነ የነካው የምን ልብስ ማጠብ? ደግሞም ልብሱም ሆነ ገላው ሲታጠብ ደሙ የነካው ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ሴቷ ከወር አበባዋ በነጻች ጊዜ (በስምንተኛው ቀን) የኃጢአት ማስተሰረያ የሚሆን መስዋእት እንድታቀርብ መታዘዟ ነው፡፡ ‹‹ካህኑም ስለ ፈሳሽዋ #ርኵስነት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል›› በማለት የወር አበባ ማየቷንም እንደ ኃጢአት መመልከቱና ከደሟ በነጻች ግዜ ለመስዋእትነት የሚሆን ነገር እንድታቀርብ ማዘዙ እጅጉኑ አስገራሚ ነው፡፡ የወር አበባ አላህ በአደም ልጆች (ሴቶች) ላይ የወሰነው ተፈጥሮአዊ ፍርድ እንጂ የኃጢአት ውጤት አይደለም፡፡ ማን በሰራው ኃጢአት ማን ይረገማል?
ይህ የኦሪት ህግ ተሸሯል የምትሉ ወገኖች ካላችሁ ደግሞ በምትኩ የተተካውን አዲሱን ህግ አሳዩን፡፡ በባዶ ሜዳ ተሸሯል ማለት የትም አያደርስም፡፡
የሴት ልጅ ስብእና ይከበር!! እንደ እርኩስ መቆጠሯ ይብቃ!!
አምላካችን አላህ ሆይ! በኢስላም ላይ ጽናትን ለግሰን፡፡ በጨለማ ለሚመላለሱ ወገኖቻችንም ልባቸውን ለኢስላም ክፈተው፡፡ ዕውቀትንም ለግሰን፡፡ ከጠሞ አጥማሚዎችም በራሕመትህ ጠብቀን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


