(የሕያ ኢብኑ ኑህ)
ሙስሊም ያልሆኑ አካላት በተደጋጋሚ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል ይህ በርዕሱ ያስቀመጥነው ክፍል አብዝቶ የሚቀርብ ነው። “ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ለምን ብዙ ሚስት አገቡ?” የሚለው ጥያቄ ምናልባት ለአንዳንድ ሙስሊም ወገኖቻችንም በውስጣቸው የሚብላላ ጥያቄ ሊሆን ይችላል። ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖቻችን አለፍ ሲልም እነዚህን ጋብቻዎች በመጥቀስ ሙስሊሞች ከተፈቀደላቸው የጋብቻ ኮታ (አራት ማግባት) በላይ እሳቸው ለምን አገቡ? ሲሉ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም አንዳንድ ኢስላምን የሚተቹ አካላት ደግሞ ብዙ የማግባት አላማ “ሴሰኝነት ነው” በሚል ድምዳሜ ረሱልን ”ﷺ” በሴሰኝነት ለመክሰስ ሲዳዳቸው ይስተዋላል (አላህ ይቅር ይበለን)
ይህንን አጀንዳ በሁለት መሠረታዊ ክፍሎች ገምደን ማብራራት እንችላለን። ጉዳዩን በተሟላ መልኩ ለመረዳት የሚከተሉትን ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች በተናጠል ለመመልከት እንሞክር፦
❐ ከጋብቻ ኮታ በላይ ማግባትን በተመለከተ
አላህ ﷻ በቁርአኑ እንደገለፀልን ለምዕመናን ከአንድ በላይ ማግባት ተፈቅዷል። ይህ ፍቃድ ግን ገደብም ጭምር አለው፤ ይኸውም የመጨረሻ ጣራው አራት ብቻ ነው (ከአንድ በላይ ማግባትን/Polygamy/ አስመልክቶ በአላህ ፍቃድ ሌላ ጊዜ ራሱን በቻለ ክፍል እመለስበታለሁ)።
ቁርአን እንዲህ ይላል፦
وَإِنْ خِفْتُمْ أَلَّا تُقْسِطُوا فِي الْيَتَامَىٰ فَانكِحُوا مَا طَابَ لَكُم مِّنَ النِّسَاءِ مَثْنَىٰ وَثُلَاثَ وَرُبَاعَ ۖ فَإِنْ خِفْتُمْ أَلَّا تَعْدِلُوا فَوَاحِدَةً أَوْ مَا مَلَكَتْ أَيْمَانُكُمْ ۚ ذَٰلِكَ أَدْنَىٰ أَلَّا تَعُولُوا
በየቲሞችም (ማግባት) አለማስተካከላችሁን ብትፈሩ (ዝሙትንና ከተወሰነላችሁ በላይ ማግባትንም ፍሩ)፡፡ ከሴቶች ለእናንተ የተዋበላችሁን ሁለት ሁለት ሦስት ሦስትም አራት አራትም አግቡ፡፡ አለማስተካከልንም ብትፈሩ አንዲትን ብቻ ወይም እጆቻችሁ ንብረት ያደረጉትን ያዙ፡፡ ይህ ወደ አለመበደል በጣም የቀረበ ነው፡፡
[ ሱረቱ አል-ኒሳእ – 3 ]
ታዲያ ጥያቄው የሚነሳው ከዚህ ነው። የተፈቀደው የጋብቻ ጣራ አራት ከሆነ ለምን እሳቸው ከዚያ በላይ አገቡ? የሚለው ነው። ይህ እንግዲህ ነብያትና ሌላው አማኝ በተወሰኑ ትዕዛዛት ዙሪያ ያላቸውን ልዩነትና አንድነት ካለመረዳት የመነጨ ጥያቄ ነው። ከዚህ በታች በመጠኑ ላብራራው፦
1- አንዳንድ ተግባራት ነብዩን ”ﷺ” ብቻ በተለየ የሚመለከቱ ትዕዛዛት ሲሆኑ መልእክቱም የሚመለከተውም እሳቸውን ብቻ ነው። ግልጽ ለማድረግ ያክል እሳቸው በነብይነታቸው ሳቢያ ከሌላው ሙስሊም የሚለዩ እንደመሆኑ መጠን ከጠቅላላ የኢስላም ህግጋት ውስጥ በተለየ መልኩ እሳቸውን የሚመለከቱ ፍቃድና ትእዛዛትም ነበሩ።
እንደ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ ለመጥቀስ ያክል የሌሊት ስግደት (ተሀጁድ) ለሌላው ሙስሊም ማህበረሰብ ቢያደርገው የሚወደድና መልካም ትሩፋትም የሚያገኝበት ነው፤ ነገር ግን የግዴታ ትእዛዝ አይደለም። በተቃራኒው ነብዩን ”ﷺ” በተመለከተ ግን ግዴታና እንዲያደርጉት በተለየ መልኩ ለሳቸው የቀረበ ትእዛዝ ነበር። ካለምንም አሳማኝ ምክንያትም እንዲያልፋቸው አይጠበቅም ነበር። አላህ ﷻ ይህንን በማስመልከት እንዲህ ይላቸዋል፦
وَمِنَ اللَّيْلِ فَتَهَجَّدْ بِهِ نَافِلَةً لَّكَ عَسَىٰ أَن يَبْعَثَكَ رَبُّكَ مَقَامًا مَّحْمُودًا
ከሌሊትም ላንተ ተጨማሪ የኾነችን ሶላት በእርሱ (በቁርኣን) ስገድ፡፡ ጌታህ ምስጉን በኾነ ስፍራ በእርግጥ ያቆምሃል፡፡
(ሱረቱ አል-ኢስራእ – 79)
በተጨማሪ
“ሌሊቱን ሁሉ ጥቂት ሲቀር ቁም፤ (ስገደ)፡፡
ግማሹን (ቁም)፤ ወይም ከርሱ ጥቂትን ቀንስ፡፡ (ቁርአን 73፥2-3)
ሌላው ሙስሊም የግዴታ ሰላቶችን ሰግዶ ማረፍ የሚችል ሲሆን እሳቸው ግን ሌሊቱን በመስገድ እንዲያሳልፉ ታዘዋል። ይህ በተለየ መልኩ ለሳቸው የቀረበ ትእዛዝ ሲሆን በሀዲስ እንደተገለፀልን እሳቸውም ትእዛዙን እግራቸው እስኪያብጥ ድረስ በመስገድ ይጠብቁ ነበር (ሰለዋቱ ረቢ ወሰላሙሁ አለይሂ)
ከዚህም በተጨማሪ በሀዲስ እንደተቀመጠው ነብዩ ሙሐመድ ”ﷺ” ፆምን አከታትለው ይፆሙ ነበር። ይህም ማለት የዛሬ ፆማቸውን ሳይፈቱ ነገም በዛው የረሀብ ሆዳቸው ሌላ ፆምን ይቀጥሉ ነበር ማለት ነው። መሠል ተግባራት የሚመለከቱት በተለየ መልኩ እሳቸውን እንጅ መላውን አማኝም አልነበረም። ጋብቻን አንስቶ “ለራሳቸው እንዲመቻቸው” ነው ብሎ የሚተች ግለሰብ ይህንንስ ምን ይለው ይሆን? የተለየ ተግባራትን ለሳቸው የሚመርጡ ቢሆን ኖሮ የሚመቻቸውን ብቻ በመለየት ለራሳቸው ይሸልሙ ነበርንጅ ራሳቸው ላይ ችግር የሚፈጥሩ ጫናዎችን በማምጣት ህይወታቸውን ባላስጨነቁ ነበር። ነገር ግን የትእዛዙ መሠረት እሳቸው አይደሉምና የሚመጡ ተግባራት ተችዎች እንደሚሉት “የሚመቿቸው” ብቻ አልነበሩም።
በርግጥም ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ነብይ እንደመሆናቸው መጠን ከተራው አማኝ የተለየ ትዕዛዛትን ይቀበሉ ነበር። ነብይ የሆነ ሰው ከአምላክ የተመረጠ ከመሆኑ ጀምሮ ከተራው ማህበረሰብ የሚለዩት መጠነኛ ህግጋቶች ይኖራሉ። የነዚህ ጋብቻዎችን ጥበብ ለተመለከተም ሰው አላህ ﷻ ለምን በተለየ መልኩ ለሳቸው ፍቃድ እንደሰጠ እንረዳለን (የጋብቻዎቻቸውን ጥበብ ስንዘረዝር በሰፊው እንመለከተዋለን)
2- በሁለተኛ ደረጃ የሚቀርበው ጥያቄ “በርግጥ ጋብቻቸውስ ስጋዊ ፍላጎት የታለመበት ነበር?” የሚለው ነው።
ለዚህ ጥያቄ ተገቢው መልስ “በፍፁም” የሚል ነው። ከዚህ በታች በመጠኑ ምክንያቶችን ለማስቀመጥ ልሞክር፦
❐ የመጀመሪያው ነጥብ ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ከአንድ በላይ ሚስቶችን ያገቡት በወጣትነታቸው ሳይሆን እድሚያቸው ከ50 ዓመት ካለፈ በኋላ ነበር። እስከዛው ድረስ የነበረቻቸው ብቸኛ ሚስት ኸዲጃ (ረ.ዐ) ብቻ ነበረች። የሚደንቀው ደግሞ ኸዲጃን ሲያገቡ ከሳቸው በእድሜ 15 አመት ያህል ትበልጣቸው ነበር። ከዚያም በተጨማሪ እሷ ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ያገባች ሴት ነበረች..! እሷ ከሞተች በኃላ እንኳን ትዳር ሲመሰርቱ ለቀጣይ አራት አመታት ብቸኛ ሚስታቸው ሁና የዘለቀችው ሰውዳዕ (ረ.ዐ) ነበረች። በነዚህ የወጣትነታቸው ጊዜያት ሁሉ የነበራቸው አንድና አንድ ሚስት ብቻ ነበር። አስቡት የጋብቻዎቻቸው መንስኤ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ሴሰኝነትና ተያያዥ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ይበልጥ ተገቢው ጊዜ ወጣትነታቸው ይሆን ነበር። ክስተቱ ግን ከዚህ የተለየ ነበር።
❐ ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ሁሉም የነብዩ ”ﷺ” ሚስቶች ከአኢሻ በስተቀር ባሎቻቸው የሞቱባቸው ወይንም የተፈቱ ነበሩ፡፡ አሁንም በተመሳሳይ የምንጠይቀው ጥያቄ እንደተባለው እውን ነብዩ ”ﷺ” ፍላጎታቸው ሴሰኝነት ቢሆን ኖሮ ያገባሉ ተብሎ የሚታሰበው የተመረጡ ደናግላንና ቆነጃጅት ሴቶችን ነው ወይንስ ባሎቻቸው የሞቱባቸውና አጋዥ አልባ ሚስኪኖችን? የሚለው ነው። ይህ ከጤነኛ አእምሮ የሚፈልቅ አመክንዬ ሊሆን አይችልም። “ሴሰኛ” ተብሎ የሚወቀስ ሰው መገለጫዎቹ በርግጥም ይታወቃሉ። ሴሰኛ ሰው ከመነሻው ወደ ትዳር የመምጣት እድሉ ጠባብ ነው። ቢመጣም ለስሜቱ ቅርብ የሆኑ ምርጫዎች ይታወቃሉ። ነብዩ ሙሀመድ ”ﷺ” ከነዛ ባህርያት ሁሉ ፈጽሞ የራቁ ነበሩ። ይህንን አስመልክቶ ሊኖር የሚችለው ቀጣይ ጥያቄ “ታዲያ ለምን አገቡ?” የሚለው ነው። ይህንንና ከጋብቻዎቻቸው ጀርባ ያሉ ጥበቦችን ደግሞ ከዚህ በታች እንመለከታለን፨
የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋብቻዎችን በተመለከተ ብዙ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ቢሆኑም በዋናነት ግን በነዚህ ሶስት ምክንቶች ውስጥ ይጠቃለላሉ
- ትምህርት አዘል ምክንያቶች
- ህግ-ነክ ምክንያቶች
- ፖለቲካዊ-ነክ ምክንያቶች
እነዚህን ጠቅለል አድርገን እያንዳንዳቸውን ለመመልከት እንሞክር
ትምህርት አዘል ምክንያቶች
የመጀመሪያ መርህ አላማ ያደረገው የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሚስቶችን ለሴቶች ልክ እንደ መምህር ኢስላማዊ ህግጋተ-ትምህርቶችን እንዲያስተምሩ ከምንጩ ስልጠና መስጠት ነው። እንደሚታወቀው ሴቶች የህብረተሰቡ ግማሽ አካል ናቸው፡፡ በዚህም እንደማንኛውም ወንድ የተጣለባቸውን ኢስላማዊ ሃላፊነቶችን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ አብዛኛው ሴቶች ጥያቄዎቻቸውን ለነብዩ ሙሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ለማቅረብ ያፍሩ ነበር በይበልጥ ደግሞ እነሱን የሚመለከቱ (ፆታዊ ጥያቄዎች) ሲሆኑ
ለምሳሌ፡- እንደወር አበባ፤ በወሊድ ጊዜ ስለሚደረጉ ተግባራት ፤ እንዲሁም ሌሎች የጋብቻ አጀንዳዎችን በተመለከተ ሴቶች በግልጽ ለመጠየቅ ሀፍረት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሌላው ከመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ባህሪይ ውስጥ አንዱ ደግሞ አይናፋርነታቸው ነበር፡፡ እሳቸው በሃዲስ እንደተጠቀሰው ‹‹ጫጉላ ውስጥ ካለች ልጃገረድ ይበልጥ አይናፋር ነበሩ›› እነዚህ ጥያቄዎች በድፍረት በሴቶች ቢጠየቁ እንኳን በግልጽ ለመመለስ ያፍሩ ነበር፡፡ አንዳንዴ ግልጽና ቀጥተኛ ያልሆኑ ቃላትን ይጠቀማሉ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ሴቶች የተጠቀሙበትን ድብቅ ቃል ላይረዱት ይችላሉ፡፡
አኢሻ (ረ.ዐ) እንዳስተላለፈችው አንድ ከአንሷር የሆነች ሴት ረሱልን ከወር አበባ ስለመጽዳት (ጉስል) ጠየቀቻቸው እሳቸውም እንዴት መጽዳት /መታጠብ/ እንዳለባት አስተማሯት ከዚያም በቁራጭ ጨርቅና ዝባድ ራሷን እንድታፀዳ ነገሯት እሷም ‹‹የአላህ መልዕክተኛ ሆይ!! እንዴት ነው በዛ እራሴን የማፀዳው??›› አለቻቸው እሳቸውም
‹‹ሱብሃነሏህ! በዛ ራስሽን አጽጅ!›› አሏት
ከዚያም አኢሻ እንዲህ አለች ‹‹ወደ እኔ ወሰድኳትና ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ያሉት ግልጽ ሆኖልኝ ስለነበር በሚገባ አብራራሁላት እንዲህ አልኳት
‹‹ምንም አይነት የደም ምልክት እንዳይኖር በዚህ ቁራጭ ጨርቅና በዝባድ አጽጅው ከዚያም የት ቦታ ላይ ማጽዳት እንደሚገባትም ግልጽ ሆኘ አስረዳኋት፡፡››
መልዕክተኛው(ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን በግልጽ ለመመለስ ያፍሩ ነበር፡፡ ይህ ብቻም አልነበረም እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን በግልጽና ሰው በተሰበሰበበት ለመጠየቅ የሚደፍሩም ጥቂት ሴቶች ብቻ ነበሩ፡
እንደዚህ አይነት እሳቸውን የሚሳፍሩ ጥያቄዎች ይመለሱ የነበሩት በሚስቶቻቸው ነበር፡፡
አኢሻ (ረ.ዐ) እንዲህ ትል ነበር
‹‹የመዲና ሴቶች ምንኛ መልካም ናቸው ሀፍረታቸው ዲናቸውን ከመማር አላገዳቸውም››
ማንኛውም ሴት ወደ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሚስቶች በመሄድ ስለ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች፤ ስለወር አበባ ህግጋት ከመውለድ ጋር በተያያዙ መደረግ ያለባቸው አስተምህሮቶች፤ ከወር አበባና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ስለመጽዳት ወ.ዘ.ተ መጠየቅና መረዳት ትችል ነበር፡፡ እነሱም መልካም መምህርና ቅን መንገድ አመላካች ነበሩ በዚህም ለሴቶች ጥሩ መምህር እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው ሱና ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የተናገሩት ብቻ አይደለም የሰሩትም ጭምር እንጂ፡፡ ይህ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ዘንድ የሸሪአ አንዱ አካል ነው፡፡ ታዲያ ከቤት ውስጥ ያለውን የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ኢስላማዊ ክንውኖች ማን ያስተላልፍልን ነበር? በዚህም ምክንያት የኃላኃላ ሚስቶቻቸው የሙስሊሙ ኡማ መምህርና የሀዲስ አስተላላፊ ነበሩ፡፡ እንዲሁም በነበራቸው ብሩህ የማስታወስ ችሎታ ታዋቂ ነበሩ፡፡
ህግ-ነክ ምክንያቶች
ከረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ጋብቻዎች ጀርባ ያሉ ህግ-ነክ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑት ከእስልምና በፊት የነበሩ የአረብ ማህበረሰብ በተለምዶ የሚፈፅሟቸውን ተግባራት በእስልምና መሰረት የለሽ መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ጉዲፈቻ በአረቦች ዘንድ ከእስልምና በፊት በሰፊው የሚተገበር ልማድ ነበር፡፡ ይህም አንድ ሰው አንድ የራሱ ያልሆነን ልጅ በጉደፈቻነት ከወሰደ በኋላ ልክ እውነተኛ ልጅ አድርጎ ‹‹አንተ ልጄ ነህ፤ ንብረቴንም ለአንተ አወርሳለሁ አንተም የእኔን ንብረት ትወርሳለህ›› የሚልበት ሁኔታ ነበር፡፡ በዚህም የውርስ ህግጋት፤የፍች ህግጋት፤ጋብቻና የተከለከለ የጋብቻ ጥምረትን የሚመለከቱ ህግጋት ወ.ዘ.ተ በአጠቃላይ ለዚህ በጉዲፈቻ ለሚያደርገው ልጅም ያገለግሉ ነበር፡፡ እስልምና እንደዚህ አይነት መሰረት የለሽ ህግጋት በሰው ልጅ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ አያጸድቅም፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ተግባር ማቆሚያ ይኖረው ዘንድ አላህ (ሱ.ወ) ለተልዕኮ ነብዩ( ሰ.ዐ.ወ)ን ከመምረጡ በፊት ዘይድ ኢብኑ ሀሪስን (ረ.ዐ) በማደጎነት እንዲያሳድጉ የአላህ (ሱ.ወ) ፍላጎት ሆነ ፡፡ ከዚያ በኋላ ዘይድ ስሙ ‹‹ዘይድ ኢብኑ ሙሀመድ ›› ሆነ፡፡ ቡኻሪና ሙሰሊም በዘገቡት ሀዲስ አብደላህ ኢብኑ ኡመር እንዲህ ይላል፡-
‹‹ዘይድ ኢብኑ ሀሪስን ይህ የቁርአን አንቀጽ እስከሚወርድ ድረስ ዘይድ ኢበኑ ሙሀመድ እያልን እንጠራው ነበር፡፡
ادْعُوهُمْ لِآبَائِهِمْ هُوَ أَقْسَطُ عِندَ اللَّهِ ۚ
‹‹ለአባቶቻቸው (በማስጠጋት) ጥሯቸው እሱ ከአላህ ዘንድ ትክክለኛ ነው፡፡…..››335
ከዚያም መልዕክተኛው (ሱ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉት ‹‹አንተ ዘይድ ኢብኑ ሀሪስ ኢብኑ ሸራሀል ነህ›› አሉት፡፡
በመቀጠልም የሱ ዘመድ የነበረችውን ዘይነብ ቢንት ጀህሽን (ረ.ዐ) አጋቡት፡፡ ነገር ግን ትዳራቸው ረጅም ጊዜን ሊዘልቅ አልቻለም ለዚህም ምክንያቱ ዘይድ ኢብኑ ሀሪስ ረሱልን (ሱ.ዐ.ወ) ከማግኘቱ በፊት ባሪያ የነበረ መሆኑና እሷ ደግሞ የዘር ግንዷ ከተከበሩ ሰዎች ከመሆኑ አንፃር ዘይነብ (ረ.ዐ) እራሷን ከፍ አድርጋ በመመልከቷ እና እሱን በማንገላታቷ ነበር፡፡ ከእስልምና በፊት የነበሩ መሰረት የለሽ ድንጋጌዎችን ለማምከንና ትክክለኛ እስላማዊ ህግጋትን ለማሳወቅ አላህ (ሱ.ወ) መልክተኛው (ሱ.ዐ.ወ) ዘይነብ ቢንት ጀህሽን እንዲያገቧት አዘዙ፡፡
የአላህ መልዕክተኛ(ሱ.ዐ.ወ) የቁረይሾችን ‹‹ሙሀመድ የልጁን ሚስት የነበረችውን ሴት አገባ›› የሚለው ወቀሳና ሀሜት አስፈራቸው፡፡ ቁርአን ይህን ይህን የሳቸውን ስጋት ወቀሰ
وَإِذْ تَقُولُ لِلَّذِي أَنْعَمَ اللَّهُ عَلَيْهِ وَأَنْعَمْتَ عَلَيْهِ أَمْسِكْ عَلَيْكَ زَوْجَكَ وَاتَّقِ اللَّهَ وَتُخْفِي فِي نَفْسِكَ مَا اللَّهُ مُبْدِيهِ وَتَخْشَى النَّاسَ وَاللَّهُ أَحَقُّ أَن تَخْشَاهُ ۖ فَلَمَّا قَضَىٰ زَيْدٌ مِّنْهَا وَطَرًا زَوَّجْنَاكَهَا لِكَيْ لَا يَكُونَ عَلَى الْمُؤْمِنِينَ حَرَجٌ فِي أَزْوَاجِ أَدْعِيَائِهِمْ إِذَا قَضَوْا مِنْهُنَّ وَطَرًا ۚ وَكَانَ أَمْرُ اللَّهِ مَفْعُولًا [٣٣:٣٧]
‹‹ለዚያም አላህ በርሱ ላይ ለለገሰለትና (አንተም ነፃ በማውጣት) በርሱ ላይ ለለገስክለት ሰው (ለዘይድ) አላህ ገላጭ የሆነን ነገር በነፍስህ ውስጥ የምትደብቅና አላህ ልትፈራው ይልቅ የተገባው ሲኾን ሰዎችን የምትፈራ ኾነህ ፡- ሚስትህን ባንተ ዘንድ ያዝ (ከመፍታት) አላህንም ፍራ በምትል ጊዜ (አስታውስ) ዘይድም ከርሷ ጉዳይን በፈፀመ ጊዜ በመዕምናኖች ላይ ልጅ አድረገው ባስጠጓቸው (ሰዎች) ሚስቶች ከነሱ ጉዳይን በፈፀሙ (በማግባት) ችግር እንዳይኖርባቸው እርሷን አጋባንህ የአላህም ትዕዛዝ ተፈፃሚ ነው፡፡ 33፡37
በዚህ መልኩ ከእስልምና በፊት የነበረው የጉዲፈቻ ስርዓት ፍፃሜውን አገኘ፡፡ ቁርአንም ይህንን አዲስ ህግ ደነገገ፡፡
مَّا كَانَ مُحَمَّدٌ أَبَا أَحَدٍ مِّن رِّجَالِكُمْ وَلَٰكِن رَّسُولَ اللَّهِ وَخَاتَمَ النَّبِيِّينَ ۗ وَكَانَ اللَّهُ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمًا [٣٣:٤٠]
‹‹ሙሀመድ ከወንዶቻችሁ የአንድም ሰው አባት አይደለም ግን የአላህ መልዕክተኛና የነብዮች መደምደሚያ ነው፤አላህም በነገሩ ሁሉ አዋቂ ነው፡፡›› 33፤40
ቡኻሪ በዘገቡት ሀዲስ ዘይነብ (ረ.ዐ) ለሌሎች የረሱል(ሰ.ዐ.ወ) ሚስቶች በፉክክር ቃና እንዲህ ትላቸው ነበር፡
‹‹እናንተን ያጋቧችሁ ቤተሰቦቻችሁ ሲሆኑ እኔን ግን ከሰባት ሰማያት በላይ ያለው አላህ (ሱ.ወ) ነው፡፡›› ቡኻሪ
ማህበራዊ ምክንያቶች
ከጋብቻው ጀርባ ያሉትን ማህበራዊ ምክንያቶች በተመለከተ ግልጽ የሚያደርግልን የሳቸው ቅርብ ሰው የነበሩትን የአቡበክር (ረ.ዐ)ና የኡመርን(ረ.አ) ሴት ልጆች ያገቡበትን ሁኔታ በትኩረት ከተመለከትን ነው፡፡ ይህ ጋብቻ የተከናወነውም ከተለያዩ የቁረይሽ የዘር ግንድ አባላት ጋር በመሆኑ የተለያዩ ጎሳዎችና ነገዶች የሳቸውን ሃይማኖት ከጥቃት በመከላከልና በመርዳት ረገድ አጋዦች እንዲሆኑ አድርጓቸው ነበር፡፡
መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የወዳጃቸውንና የጠንካራ ባልደረባቸውን የአቡበክርን(ረ.ዐ) ልጅ ማግባታቸው ለርሱ እንደ ሽልማት ነበር፡፡ አቡበክር ማለት እስልምናን በመጀመሪያ ከተቀበሉ እንዲሁም ህይወቱንና ገንዘቡን ለእስልምናና ለረሱል ጥበቃ ያዋለና ሁሉንም ነገሩን ለእስልምና የሰጠ ሰው ነበር፡፡
ቲርሚዚ እንደዘገቡት መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የአቡበክርን (ረ.ዐ) ምንዳ እሳቸው በዚህ ምድራዊ ቆይታ ሊከፍሉ እንዳልቻሉና አላህ (ሰ.ወ) የፍርዱ ቀን ምንዳውን እንዲሰጠው አላህን እንደለመኑለት ተገልጻል፡፡ መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ለአቡበክር (ረ.ዐ) እስልምናን ሲያቀርቡለት በጭራሽ አላንገራገረም እሳቸው ቋሚ ወዳጅ (ጓደኛ) እንዳይዙ ቢፈቀድላቸው ያ ሰው አቡበክር እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ)ለ አቡበክር (ረ.ዐ) ልጃቸውን ከማግባት የተሻለ ሽልማት በዚህች ምድር አላገኙለትም፡፡ በዚህም ወዳጅነታቸው እንዲጠናከርና ግንኙነታቸውም ይበልጥ ጥልቅ እንዲሆን አስቻሉት፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) በተመሳሳይ የኡመር (ረ.ዐ) ልጅ የነበረችውን ሀፍሷን(ረ.ዐ) አግብተዋል፡፡ አባቷ በእስልምና ውስጥ ላሳየው ሀቀኝነትና ታማኝነት ታላቅ ሽልማት ነበር፡፡ ዑመር በእስልምና ታሪክ ውስጥ ታላቅ ጀግና ነበሩ፡፡ አላህ (ሱ.ወ) በሱ ሰበብ እስልምናን የላቀና አይነኬ አድርጎት ነበር፡፡ የመልዕክተኛውም ጋብቻ ለአቡበክርና (ረ.ዐ) ለኡመር (ረ.ዐ) የነበራቸውን ክብርና ፍቅር ለመግለጽ ነበር፡፡ በተጨማሪም ለኡስማንና (ረ.ዐ) ለአልይ (ረ.ዐ) የነበራቸውን ክብር ደግሞ የነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) ሴት ልጆችን ለነሱ በማጋባት ገልፀውላቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው አራቱ አቡበክር (ረ.ዐ)፤ ኡመር(ረ.ዐ)፤ ኡስማንና አሊይ (ረ.ዐ) የረሱል ታላላቅ ባልደረቦች የነበሩና ኸሊፋ በመሆን እስልምናን ያስፋፉና ለእስልምና ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው፡፡
ፖለቲካዊ ምክንያቶች
ከመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ዋነኛ የጋብቻ ምክንቶች አንዱ በዙሪያቸው ከነበሩ ህዝቦች ጋር የጠበቀ ግንኙነት መመስረት ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ከአንድ ጎሳ ወይም ነገድ ጋር አንድ ሰው በጋብቻ ከተሳሰረ አዲስ የሆነ ዝምድና ይመሰረታል፡፡ ይህም አስቸኳይ እርዳታ በሚስፈልግበት ወቅት ግንባር ቀደም ተሰላፊ ይሆኑለታል፡፡ ከዚህ በታች ይህን የሚያጠናክሩ ጥቂት ምሳሌዎችን እናያለን
የመጀመሪያ ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) የበኒ ሙስጠላቅ ጎሳ መሪ የነበረውን አል-ሀሪስን ልጅ ጁወይራህን አገቡ፡፡ በወቅቱ እሷን ጨምሮ ሙሉ የጎሳው አባላት በመልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) አንዱ ዘመቻ ላይ የሙሰሊሙ የጦር ምርኮኛ ነበሩ፡፡ እሷም የጎሳው መሪ ልጅ እንደመሆኗ መጠን ምርኮ ስለሆኑት ወገኖቿ ማስለቀቂያ ገንዘብ ለመጠየቅ ወደ መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) መጣች፡፡ የአላህ መልዕክተኛም(ሰ.ዐ.ወ) ለእሷ የሚሆነውን የምርኮ ማስለቀቂያ ገንዘብ እሳቸው ሊከፍሉና ከዛም እሷ እሳቸውን እንድታገባ ሀሳብ አቀረቡ በሀሳቡ ተስማማች፡፡ ከዚያም ይህ ጉዳይ ማለትም ከመልዕክተኛው ጋር በጋብቻ የተጣመረን ጎሳ በምርኮ ማቆየታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ሙስሊሞች አመኑ ከዚያም ሁሉንም በነፃ ለቀቋቸው፡፡ ይህን የሙስሊሞች መልካም ተግባር ሲመለከቱ ሙሉው የበኒ ሙስጠለቅ ጎሳ እስልምናን ተቀበለ፡፡
ሁለተኛ የሁየይ ቢን አህጧብ ልጅ የሆነችው ሰፍያህ (ረ.ዐ) በኸይበር ዘመቻ ወቅት ባሏ ከተገደለ በኋላ በሙስሊሞች ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሁለት ምርጫን ሰጥቷት
ሀ) ነፃ አውጥተዋት እሳቸውን እንድታገባ
ለ) ነፃ አውጥተዋት በሰላም ወደ አይሁድ ቤተሰቦቻ መመለስ፡፡
ነገር ግን እሷ የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ስነ-ምግባር ከምንም በላይ ተመልክታ ስለነበር ይህ አጋጣሚ እንዲያመልጣት አልፈለገችምና እሳቸውን ማግባትን መረጠች ከዚህም በላይ እሷን ጨምሮ በብዙዎቹ እስልምናን ተቀበሉ፡፡
በአንድ ወቅት የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ለሶፊያ (ረ.ዐ) እሳቸውን ጠላት አድርጎ በመያዝ ረገድ ከሌሎች ይልቅ አይሁዶች እንደሚበልጡ ሲነግሯት እሷም
‹‹….የአላህ መልዕክተኛ ሆይ? አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል
‹‹……ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላቶቹን ሸክም (ሀጢያት) አትሸከምም….››
የአላህ መልዕክተኛ(ሰ.ዐ.ወ) ኢስላምን ከመረጠች እንዲያገቧትና አይሁዳዊነትን ከመረጠች ግን ወደ ቤተሰቦቿ መሄድ እንደምትችል ሲያማርጧት እሷ ኢስላምን መምረጧንና በእሳቸውም ማመኗን ከአይሁድ ቤተሰቦቿ ጋር ከዚህ በኋላ የሚገናኛት ነገር እንደሌለ ነበር የገለፀችው (አላህ መልካም ስራዎቿን ይውደድላት) በዚህም የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሊያገቧት ችለዋል፡፡
ሶስተኛ፡–
የአላህን መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ሌላው የጋብቻ ጥበባቸው ውስጥ ኡሙ ሀቢባን ያገቡበት ክስተት ነበር፡፡ የኡሙ ሀቢባ (ረምላ) አባት አቡ ሱፊያን በወቅቱ የጠላቶቻቸው የመካ አጋሪዎች መሪ ነበሩ፡፡ እሷ መካ በነበረችበት ወቅት እስልምናን ተቀብላለች ከዚያም ወደ ኢትዮጰያ ከባለቤቷ ጋር ተሰደደች፡፡ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) የባሏን በኢትዮጵያ ውስጥ መሞት ሲሰሙ ኡሙ ሃቢባን ያጋቡት ዘንድ ለሀበሻ ንጉስ ለነጃሺ መልዕክት ላኩ፡፡ ኡሙ ሃቢባ ይህ ዜና እጅጉኑ አስደሰታት ምክንያቱም ወደ ቤተሰቦቿ ብትመለስ አባቷ በግዳጅ እስልምናን እንድትተው የተለያየ ስቃይ ሊፈፅምባት ይችል ስለነበር ነው፡፡ 400 ዲናር መኽር ከተቀበለች በኋላ ወደ መዲና ተመልሳ አላህ መልዕክተኛን (ሰ.ዐ.ወ) አገባች፡፡ የኃላኃላ የነብዩ ጠላት የነበረው አባቷ አቡ ሱፍያን እስልምናን ሲቀበል በድርጊቱ ደስተኛ ሁኖ ነበር፡፡ ከአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር ልጁ በትዳር መጣመሯንም በጉራ ይናገርና ክብር እንደሚሰማው ይገልፅ ነበር፡፡
ይህ ጋብቻ የኢስላም ታላቅ ጠላት የነበረውን አቡ ሱፍያንን ጠላትነቱንና በሙስሊሞች ላይ ይፈጽም የነበረውን ጭካኔ ሊያለዝበው ችሏል፡፡ ከዚህም በላይ ጋብቻው ለኡሙ ሀቢባ (ረ.ዐ) ከአባቷ ጋር ታግላ በአቋሟ ጽኑ በመሆኗ እንደሽልማትም ነበር፡፡
(ይህ ጹሁፍ በዋናነት ምንጭ ያደረገው ከሸኽ ሙሀመድ አሊ አሳቦኒ ትምህርታዊ ገለፃ ተወስዶ Fallacies & misconceptions about the messenger’s marriages በሚል ርዕስ በዶ/ር አህመድ አሰይድ አቡ ዘይድ ወደ እንግሊዘኛ ከተመለሰችው አነስተኛ መጽሐፍ ነው)
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


