በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
በተደጋጋሚ ሙስሊም ካልሆኑት ከካፊሮች ዘንድ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ እሱም፡- እናንተ ሙስሊሞች ለምን ወደ ካዕባህ ብቻ ዞራችሁ ትሰግዳላችሁ? አምላክ በሁሉም ቦታ አይደለም እንዴ ያለው? ወይስ የናንተ አምላክ በአንድ አቅጣጫ ብቻ ነው የሚገኘው?
ምላሽ፡-
ይህ አንዱና ዋነኛው መልሳችን ነው፡፡ እኛ ሙስሊሞች ወደ ካዕባህ ዞረን የምንሰግደው ጌታችን አምላካችን አላህ ወደ ካዕባህ አቅጣጫ ዞራችሁ ስገዱ! በማለት ስላዘዘን ነው፡፡ የአላህን ትእዛዝ መፈጸም ደግሞ አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡ ሶላትን የምንሰግደው አላህ ስገዱ ብሎ ስላዘዘን ነው እንደምንለው ሁሉ፡ እንዴት እንሰግዳለን? ለሚለውም ጥያቄ፡ መልስ የሚሆነው፡ አላህ እንዳዘዘን በማለት ነው፡፡ የምንሰግድለት ጌታ አላህ፡ በየትኛውም ስፍራ ሆነን የሶላት ሰዓት ከደረሰብን ለመስገድ ወደ ቂብላ (የሶላት አቅጣጫ) መዞር እንዳለብን እንዲህ በማለት ያዛል፡-
” وَمِنْ حَيْثُ خَرَجْتَ فَوَلِّ وَجْهَكَ شَطْرَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ وَإِنَّهُ لَلْحَقُّ مِنْ رَبِّكَ وَمَا اللَّهُ بِغَافِلٍ عَمَّا تَعْمَلُونَ ” سورة البقرة 149
“ከየትም (ለጉዞ) ከወጣህበት ስፍራ ፊትሀን ወደ ተከበረው መስጊድ አግጣጫ አዙር፡፡ እርሱም ከጌታህ የኾነ እርግጠኛ እውነት ነው፡፡ አላህም ከምትሠሩት ሥራ ዘንጊ አይደለም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 149)፡፡ በተጨማሪም ቁ. 150 ይመልከቱ፡፡
2. የሳቸው ፍላጎት ስለነበር፡-
ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ወደ ካዕባህ ዞረው ከመስገዳቸው በፊት ከሶሐቦቻቸው (ረዲየላሁ ዐንሁም) ጋር ለአስራ ስድስት ወራት ያህል ወደ በይቱል መቅዲስ (ፈልስጢን) ነበር የሚሰግዱት፡፡ ሆኖም ግን በልባቸው ኢብራሂም (ዐለይሂ-ሰላም) ወደገነባው ቤት (ወደ ካዕባህ) መዞርን ይወዱ ነበር፡፡ በሶላታቸውም ላይ ሁነው አላህ ወደ ካዕባህ ፊትህን አዙር በማለት ትእዛዝ ይሰጠኛል በሚል ክጃሎት አይናቸውን ወደ ሰማይ ያነሱ ነበር፡፡ በተጨማሪም አይሁዶች በመመጻደቅ፡- የኛን ቂብላ (በይቱል መቅዲስ) ይከተላል፡፡፡ ሃይማኖታችንን ግን ይተዋል እያሉ አዛ ያደርጓቸው ነበር፡፡ በመጨረሻም አላህ የሳቸውን የልብ ፍላጎት ለመሙላት፡ አይሁዶችም የነሱን ቂብላ እየተከተላቸው እንዳልሆነ ለማሳየት፡ እግረ መንገዱንም አማኞችን በተግባር ለመፈተንና ሙናፊቁን (እሳቸው ወደዞሩበት እሺ ብሎ የሚዞረውንና ከእምነት የሚያፈገፍገውን) ለይቶ ለማውጣት ወደ ካዕባህ ዙሩ! የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ መጣ፡-
” قَدْ نَرَى تَقَلُّبَ وَجْهِكَ فِي السَّمَاءِ فَلَنُوَلِّيَنَّكَ قِبْلَةً تَرْضَاهَا فَوَلِّ وَجْهَكَ شَطْرَ الْمَسْجِدِ الْحَرَامِ وَحَيْثُ مَا كُنْتُمْ فَوَلُّوا وُجُوهَكُمْ شَطْرَهُ وَإِنَّ الَّذِينَ أُوتُوا الْكِتَابَ لَيَعْلَمُونَ أَنَّهُ الْحَقُّ مِنْ رَبِّهِمْ وَمَا اللَّهُ بِغَافِلٍ عَمَّا يَعْمَلُونَ ” سورة البقرة 144
“የፊትህን ወደ ሰማይ መገላበጥ በእርግጥ እናያለን፡፡ ወደምትወዳትም ቂብላ እናዞርሃለን፡፡ ስለዚህ ፊትህን ወደ ተከበረው መስጊድ (ወደ ካዕባ) አግጣጫ አዙር፡፡ የትም ስፍራ ብትኾኑም (ስትሰግዱ) ፊቶቻችሁን ወደርሱ አግጣጫ አዙሩ፡፡ እነዚያም መጽሐፉን የተሰጡት እርሱ ከጌታቸው ሲኾን እውነት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ አላህም ከምትሠሩት ሥራ ዘንጊ አይደለም፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 144)፡፡
3. የኡማውን አንድነት ለማሳየት፡-
ሙስሊሙ ኡምማ (ህዝብ) አንድ ኡምማ ነው፡፡ የአንድነቱ ትልቁ ቁልፍ ‹‹ላ ኢላሀ ኢለሏህ ሙሐመዱን ረሱሉሏህ›› የሚለው የምስክርነት ቃል ነው፡፡ በዚህ የምስክርነት ቃል ‹ካፊር› የነበረው ግለሰብ ወይም ማኅበረሰብ ሙስሊም በመሆን ወደ አማኞች ጎራ ይቀላቀላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የሙስሊምነታችን ተግባራዊ መገለጫ የሆነው ‹ሶላት› ነው፡፡ ይህን ሶላት ከመስገድ የኮራ ወይም የተወ ሰው ወደ ኩፍር (ክህደት) ተመለሰ ማለት ነው፡፡ ታዲያ የጌታቸውን የአላህን ትእዛዝ ተቀብለው በሶላታቸው የጸኑ መልካም ባሪያዎቹ፡ ይህን ኢስላማዊ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ወደ አንድ ቂብላ መስገድ አለባቸው፡፡ ሁሉም ሰው በግልም ይሁን በቡድን ሆኖ ወደ ተለያየ አቅጣጫ የሚሰግድ ከሆነ፡ አንድነቱ ምኑ ላይ ነው? ደግሞስ በዚህ መልክ እንዲሰግድ ማን አዘዘው? ጌታ አንድ ከሆነ፡ ከአንዱ ጌታ የሚወጣው ትእዛዝ አንድ እንጂ የተለያየ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኡምማው አንድነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ቂብላውም አንድ መሆን አለበት፡-
” إِنَّ هَذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاعْبُدُونِ ” سورة الأنبياء 92
“ይህች (ሕግጋት) አንዲት መንገድ ስትኾን በእርግጥ ሃይማኖታችሁ ናት፤ እኔም ጌታችሁ ነኝና ተገዙኝ።” (ሱረቱል አንቢያእ 92)፡፡
وَإِنَّ هَذِهِ أُمَّتُكُمْ أُمَّةً وَاحِدَةً وَأَنَا رَبُّكُمْ فَاتَّقُونِ ” سورة المؤمنون 52 “
“ይህችም (በአንድ አምላክ የማመን ሕግጋት) አንድ መንገድ ስትኾን ሃይማኖታችሁ ናት፡፡ እኔም ጌታችሁ ነኝና ፍሩኝ፡፡” (ሱረቱል ሙእሚኑን 52)፡፡
4. በሌላም አቅጣጫ መሰገድ መቻሉ፡-
ሌላው ወደ ካዕባህ ዙረን መስገዳችን የአላህን ትእዛዝ በማክበር እንጂ ካዕባን በማምለክ ላለመሆኑ መረጃችን፡ ቂብላ በጠፋብን ጊዜ ቂብላ ነው ብለን ባሰብነው አቅጣጫ መስገድ መቻላችን ነው፡፡ እሱም፡- ሙስሊሞች በጉዞ ላይ ሁነው ሳለ ሶላት ወቅት ቢደርስባቸውና መኪናቸውን አቁመው ለመስገድ ሲፈልጉ ትክክለኛውን የቂብላ አቅጣጫ የሚጠቁማቸውን ኮምፓስም ይሁን ሰው ቢያጡ፡ ሁሉም ሰው ቂብላ ነው ብለው ወዳሰቡት አቅጣጫ በአንድነት መስገድ ይችላሉ፡፡ ሶላታቸውን ከጨረሱ በኋሏ አንድ መንገደኛ መጥቶ የሰገዳችሁት ሶላት ቂብላው የተሳሳተ ነው ቢላቸው እንኳ ሶላታቸውን እንዲደግሙ አይጠየቁም፡፡ ስግደቱ ለአላህ እንጂ ለቂብላው ስላልሆነ፡፡ እዛው ሶላት ውስጥ እያሉ ከሆነ ግን ወደተነገራቸው አቅጣጫ ፊታቸውን ማዞር ይገባቸዋል፡፡ እንዲሁም በአየር ጉዞ ላይ እያለን ሶላት ወቅቱ ቢደርስብን በተክቢረተል ኢሕራም (ወደ ሶላት መግቢያ ተክቢራ) ወቅት ፊታችንና ደረታችንን ወደ ካዕባህ አዙረን መነየት (መሐረም) አለብን፡፡ ከዛ በኋላ ግን ሶላቱ እስኪያልቅ በተቀመጥንበት ወንበር ላይ ሁነን ሶላቱን ማጠናቀቅ እንችላለን፡፡ አይሮፕላኑ ወደፈለገው አቅጣጫ ቢሽከረከር የሰጋጁን ሶላት አያበላሸውም፡፡
” وَلِلَّهِ الْمَشْرِقُ وَالْمَغْرِبُ فَأَيْنَمَا تُوَلُّوا فَثَمَّ وَجْهُ اللَّهِ إِنَّ اللَّهَ وَاسِعٌ عَلِيمٌ ” سورة البقرة 115
“ምሥራቁም ምዕራቡም የአላህ ነው (ፊቶቻችሁን) ወደ የትም ብታዞሩ የአላህ ፊት እዚያ ነው፡፡ አላህ ችሮታው ሰፊ ዐዋቂ ነውና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 115)፡፡
5. አምላክ በሁሉም ቦታ የለም!!
ሌላው የተሳሳተው አመለካከት፡- አምላክ በሁሉም ቦታ አልለ የሚለው ነው፡፡ ፈጣሪ አምላክ አላህ በመለኮታዊ ክብሩ ከሰማያት በላይ ያለ አምላክ እንጂ፡ በሁሉም ስፍራ ያለ አምላክ አይደለም፡፡ አላህ ሁሉንም ስፍራዎች የሚመለከት፣ የሚቆጣጠር ጌታ በመሆኑ፡ በዕውቀቱና በእይታው በሁሉም ስፍራ አልለ ማለት እንችላለን፡፡ ከሱ እይታና ቁጥጥር ውጭ ሊሆን የሚችል የዓለም ክፍል የለምና፡፡
” أَلَمْ تَرَ أَنَّ اللَّهَ يَعْلَمُ مَا فِي السَّمَاوَاتِ وَمَا فِي الْأَرْضِ مَا يَكُونُ مِنْ نَجْوَى ثَلَاثَةٍ إِلَّا هُوَ رَابِعُهُمْ وَلَا خَمْسَةٍ إِلَّا هُوَ سَادِسُهُمْ وَلَا أَدْنَى مِنْ ذَلِكَ وَلَا أَكْثَرَ إِلَّا هُوَ مَعَهُمْ أَيْنَ مَا كَانُوا ثُمَّ يُنَبِّئُهُمْ بِمَا عَمِلُوا يَوْمَ الْقِيَامَةِ إِنَّ اللَّهَ بِكُلِّ شَيْءٍ عَلِيمٌ ” سورة المجادلة 7
“አላህ በሰማያት ውስጥ ያለውን፣ በምድርም ውስጥ ያለውን፣ ሁሉ የሚያውቅ መሆኑን አታይምን? ከሶስት ሰዎች መንሾካሾክ አይኖርም፣ እርሱ አራተኛቸው ቢሆን እንጂ፤ ከአምስትም (አይኖርም)፣ እርሱ ስድስተኛቸው ቢሆን እንጂ፤ ከዚያ ያነሰም የበዛም (አይኖርም)፣ እርሱ የትም ቢሆኑ አብሮዋቸው ቢሆን እንጂ፤ ከዚያም በትንሳኤ ቀን የሰሩትን ሁሉ ይነግራቸዋል። አላህ ነገሩን ሁሉ አዋቂ ነው።” (ሱረቱል ሙጃደላህ 7)፡፡
ይህ አንቀጽ ሲጀምር የአላህን ሁሉን ዐዋቂነት በመግለጽ ይጀምራል፡፡ ሲያጠናቅቅም እንደዚሁ የሱን ሁሉን ዐዋቂነት በመግለጽ ይዘጋዋል፡፡ በመሐል ደግሞ ዐዋቂነቱን በተጨባጭ የሚያሳይ ትምሕርት አለ፡፡ እሱም፡- ሶስት ሰዎች በአንድ ሆነው ሚስጥርን ቢያወሩ አራተኛው አላህ ነው ይለናል፡፡ ይህ ማለት፡ የነዚህ ሰዎች መመሳጠር ከአላህ እንደማይሰወርና እሱ አላህ የሶስቱን ሚስጥር የሚሰማና የሚያውቅ ጌታ መሆኑን ዕወቁ ማለቱ ነው፡፡ እንደዛውም አምስትም ብንሆን የአምስታችንን ሚስጥር የሚሰማና የሚያውቅ ስድስተኛው፡ ጌታ አላህ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በማያያዝም ከዚህ ያነሰ ቁጥር ሆነን ብንመሳጠር ወይም የበዛ ቁጥር ቢኖረንም እሱ ከኛ ጋር መሆኑን ይነግረናል፡፡
አላህ ‹‹ከኛ ጋር አብሮ ያለ ነው›› የሚለው አንቀጽ የሚያስረዳን፡ ከአንቀጹ መግቢያና መቋጫ በመነሳት፡ እሱ በዕውቀቱ ከኛ ጋር መሆኑን እንደሚቆጣጠረንና እንደሚመለከተን የሚያሳይ ነው እንጂ በመለኮታዊ ክብሩ ከኛ ጋር መሆኑን ለማሳየት አይደለም፡፡
በሌሎች አንቀጾች ላይ ደግሞ አላህ ‹‹ከአማኞች ጋር መሆኑን›› የሚያስረዱ ሀሳቦች አሉ፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ደግሞ የሚያሳየው በእርዳታውና በእገዛው እንዲሁም በመለኮታዊ ጥበቃው ከአማኝ ባሪያዎቹ ጋር መሆኑን የሚያሳይ ነው፡-
” إِنَّ اللَّهَ مَعَ الَّذِينَ اتَّقَوْا وَالَّذِينَ هُمْ مُحْسِنُونَ ” سورة النحل 128
“አላህ ከነዚያ ከሚፈሩትና ከነዚያም እነሱ መልካም ሠሪዎች ከሆኑት ጋር ነውና።” (ሱረቱ-ነሕል 128)፡፡
በዚህ ጥቅስ መሰረት፡ አላህ ከኩራተኞችና ከኃጢአተኞች ጋር እንዳልሆነ ነው የምንረዳው፡፡ እሱ እራሱ ‹‹ከሚፈሩኝና መልካምንም ከሚሰሩት ጋር ነኝ›› ብሏልና፡፡ ታዲያ ቅድም ባየነው አንቀጽ ‹የትም ብትሆኑ እኔ ከናንተ ጋር ነኝ› በማለት፡ አላህ ከባሪያዎቹ ጋር በጠቅላላ እንደሆነ ገልጾልን አልነበረምን? ቢባል፡ መልሱም አዎ! የሚል ይሆናል፡፡ በቅድሙ አንቀጽ ላይ የነበረው ‹አብሮነት› በቁጥጥሩና በዕውቀቱ ሁሉን ተመልካችነቱን የሚያሳይ አንቀጽ ሲሆን፡ አሁን ደግሞ ከፈሪዎችና ከመልካም ሰሪዎች ጋር ያለው አብሮነት፡ የእርዳታና የእገዛ እንዲሁም የጥበቃ አብሮነትን ነው፡፡ አላህ መልካም ሰሪዎችን በማገዝ (ተውፊቅ በመስጠት) በመለኮታዊ ጥበቃውም በመጠበቅ ከዕውቀቱና ከቁጥጥሩም በተጨማሪ በእርዳታውም አብሯቸው መሆኑን እያስረዳ ነው ማለት ነው፡፡
” قَالَا رَبَّنَا إِنَّنَا نَخَافُ أَنْ يَفْرُطَ عَلَيْنَا أَوْ أَنْ يَطْغَى * قَالَ لَا تَخَافَا إِنَّنِي مَعَكُمَا أَسْمَعُ وَأَرَى ” سورة 46-45
“ጌታችን ሆይ! እኛ በኛ ላይ ክፋት በመስራት መቸኮሉን፣ ወይም ኩራትን መጨመሩን እንፈራለን፣ አሉ። (አላህም) አለ፦አትፍሩ፤እኔ በእርግጥ ከናንተ ጋር ነኝና፤ እሰማለሁ፤ አያለሁም።” (ሱረቱ ጣሀ 45-46)፡፡
ሙሳና ወንድሙ ሀሩን (ዐለይሂማ ሰላም) ለዳዕዋ ስራና በኒ ኢስራኢሎችን ከግብጻውያን ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ፊርዐውን በተላኩ ጊዜ፡ የፊርዐውንን ወሰን ማለፍ በማሰብ ስጋት ገብቷቸው ነበር፡፡ ጌታችን አላህም ‹አትፍሩ! እኔ ከናንተ ጋር ነኝ› በማለት ዕርዳታውና ጥበቃው እንደማይለያቸው በመግለጽ አጽናናቸው፡፡ ‹ከናንተ ጋር ነኝ› የሚለው አብሮነት፡ በዕውቀቱ ወይም በቁጥጥሩ የሚለውን የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ፡ ሙሳና ሀሩንን ብቻ ለይቶ ለምን ‹ከናንተ ጋር ነኝ› ማለት አስፈለገ? ፊርዐውንና ሰራዊቱስ ከአላህ ዕውቀትና ቁጥጥር ውጭ ነበሩ እንዴ? (ሱብሐኑ ወተዓላ ዑሉወን ከቢራ!)፡፡ መልእክቱ ግን ጌታ አላህ ምንም በዕውቀቱና በቁጥጥሩ ከሁሉም ጋር ቢሆንም፡ በእገዛውና በእርዳታው ግን ከሙሳና ከሀሩን ጋር እንደነበረ ለማሳየት ነው፡፡
እኛም እንኳ በስልክ የምንሰናበተውን ወንድማችንን ‹በል እንግዲህ አላህ ካንተ ጋር ይሁን!› እንለው አይደል? ማለት የፈለግነውስ የአላህ ጥበቃና እርዳታ አይለይህ ለማለት አይደል?
ለማጠቃለል፡- ጌታችን አላህ በመለኮታዊ ክብሩ (በዛቱ) ከዐርሽ በላይ ፡ ከሰማያት በላይ ያለ አምላክ ነው፡፡ ለዚህም ነው ልባችን ከጌታዋ አንድ ነገር በፈለገች ጊዜ እንዲሳካላት እጆችዋን ወደፈጠራት ወደ አላህ የምታነሳው፡፡
በዕውቀቱና በቁጥጥሩ ደግሞ ከሁሉም ጋር ነው እንላለን፡፡ በእርዳታውና በእገዛው ደግሞ ከአማኝ ባሮቹ ጋር ነው፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


