(የሕያ ኢብኑ ኑህ)
በመጽሀፍ ቅዱስ የተነገረለትና የሚመጣው የተባለውን “አፅናኝ” በተመለከተ ከሙስሊሞች ለሚነሱ መከራከሪያዎች ክርስቲያኖች የሚያቀርቧቸው መልሶች ሁሌም በቀዳዳ የተሞሉ ናቸው። ይህ አጽናኝ ተብሎ የተተነበየለት አካል ነብዩ ሙሐመድ “ﷺ” እንዳልሆኑ ለማስረዳት የሚያደርጉት ክርክር ክፍተቶቻቸውን እና ደካማነታቸውን የሚያጋልጥ ነው። ይህንን አጀንዳ በተመለከተ “አፅናኙ ማነው?” በሚል ርእስ ከአመታት በፊት በድምፅ የሰጠሁትን ትምህርት ብትከታተሉት አሁን ለሚወራው መከራከሪያ እንደ መግቢያ ሙሉ ምስል ያስጨብጣችኃል።
ዛሬ ታዲያ ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የኛን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚል የሚያቀርቧቸውን “ማስረጃዎች” በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን። እስኪ ከዚህ በታች ከሚነሱት ሙግቶች ውስጥ ተደጋግሞ የሚጮህላቸውን የተወሰኑ ምላሾች ለያይተን በክፍል እንቃኛቸው፦
፩)
የሚልከው ኢየሱስ ከሆነ “በተዘዋዋሪ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን መስክራችኃል” ይሉናል። ለዚህ የሚያነሱት መከራከሪያ የሚከተለውን የዮሐንስ ወንጌል አንቀፅ ነው፦
ነገር ግን፣ እውነት እላችኋለሁ፤ መሄዴ ይበጃችኋል። እኔ ካልሄድሁ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድሁ ግን እርሱን ወደ እናንተ እልካለሁ፤ዮሐንስ 16፥7 (አዲሱ መ.ት)
በዚህ አንቀፅ ኢየሱስ “ወደናንተ እልካለሁ” ስላለ በተዘዋዋሪ እርሱ ላኪ አምላክ መሆኑን መስክራችኃል የሚል ነው። በመሠረቱ መከራከርያው ከተነሳው “የተተነበየተለት ማነው?” ከሚለው ነጥብ ጋር የሚገናኝ ባይሆንም ለቀረበው ጥያቄም ቢሆን አውዱን የሳተ በመሆኑ በቀላሉ የሚታረም ነው። ይህንን አንቀፅ ብቻውን ነጥሎ ለተመለከተው ሰው እንደተባለውም እርሱ በፍቃዱ ላኪ የሆነ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ይህንን ክስተት በተመለከተ ቀደም ብሎ ኢየሱስ የተናገረውን መልዕክት ለተመለከተ አስተዋይ ሰው ግን ሀሳቡ እንደተባለው እንዳልሆነ ይረዳል። ዋናው ነጥብ “ኢየሱስ እልካለሁ” ሲል በምን መልኩ ነው የሚልከው? የሚል ነው። ልክ እንደ አምላክ በራሱ ችሎታና ውሳኔ ነው ወይንስ ሌላ መንገድ አለ? ለሚለው እራሱ ኢየሱስ መልሱን ሰጥቶን መከራከሪያውን አፈርድሜ ያበላዋል። ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦
እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ዮሐንስ 14፥16 (አዲሱ መ.ት)
ኢየሱስ በዚህ አንቀፅ በግልፅ የሚከተሉትን መልዕክቶች አስተላልፏል፦
ሀ) የኢየሱስ የ”መላክ” አገላለፅ ልመና ከማድረግና በዚያ ምክንያት ፀሎቱ ከመፈጸም የዘለለ ስልጣን የሌለው እንደሆነ፣
ለ) ሰጭው እርሱ ሳይሆን ሌላ አካል እንደሆነ “ይሰጣችኃል” ሲል በሶስተኛ ወገን ያስቀመጣል።
ስለዚህም ከላይ በመጀመሪያው ነጥብ እንደገለፅነው የኢየሱስ “እልካለሁ” ንግግር የፀሎቱን ውጤት የገለፀ እንጅ የባለቤትነትን መለያ የያዘ አይደለም። መሠል ቃላትን መጠቀሙን በተመለከተ ደግሞ ከመነሻውም በዚህ መልኩ በምሳሌ እንደሚናገር በዮሐንስ ወንጌል 16፥25 ተናግሯል።
በነገራችን ላይ “አፅናኙን” በተመለከተ አሁን ክርስትያኖች በሚከራከሩን መልኩ “መንፈስ ስለሆነ ማንነት” ወዘተ ሳይሆን በጥንታዊ ክርስቲያኖች ዘንድ ስጋ የለበሰ ሰው እንደሆነ ነበር የሚረዱት። በዚህም ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ከህዝቡ መካከል “እኔ አፅናኙ ነኝ” በሚል ብዙ ሐሰተኛ ግለሰቦች ይነሱ እንደነበር በሰፊው ተጠቅሷል። (1)
ሬይመንድ ብራውን እንዴውም ሀሳቡን ከዚያም በማሻገር ተራው አማኝ ብቻ ሳይሆን ብዙ ሊቃውንትም ጭምር አፅናኙ የሰው ስጋን የለበሰ አካል እንደሆነ ያምናሉ ሲል ፅፏል (2)
፪)
ሁለተኛው መሟገቻ “ከናንተ ጋር እንዲኖር ለዘላለም እሰጣችኃለው ስላለ ነብዩ ﷺ አያመለክትም” በሚል የሚቀርበው ነው። እንደ ክርስቲያኖች ገለፃ መሠረት ነብዩ ሙሐመድ ﷺ ዘላለም አልኖሩምና ትንቢቱ እሳቸውን አይመለከትም የሚል ነው። ታዲያ ማንን ይመለከታል? ስንላቸው አንቀፁ የሚመለከተው መንፈስ ቅዱስን እንደሆነ ይነግረናል። እስኪ ስለ ነብዩ መሐመድ ያቀረቡትን መቃረኒያ ለጊዜው እናስቀምጠውና በንግግሩ መሠረት መንፈስ ቅዱስን እንፈትሸው። አንቀፁን በማስቀመጥ እንጀምር፦
እኔ አብን እለምናለሁ፤ እርሱም ከእናንተ ጋር ለዘላለም የሚኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ዮሐንስ 14፥16 (አዲሱ መ.ት)
ይህንን አንቀፅ መሠረት አድርገን እስኪ ስለመንፈስ ቅዱስ የተወሰነ ነገር እንነጋገር፦
ሀ) አንቀፁ የሚለው “ሌላ” አፅናኝ ነው። እንደ ክርስቲያኖች እምነት መሠረት መንፈስ ቅዱስ አንድ አካል እንጅ የሚለዋወጥና በሌላ ቃል የሚጠቀስ ተጨማሪ ማንነት ያለው አይደለም። ኢየሱስ “ሌላ” ሲል የነበረው መንፈስ ቅዱስን የተለየ ማለቱ ነው? መንፈስ ቅዱስ ያለው ባህርይ እንዲህ ነው?
ለ) ከኢየሱስ ማረግ በፊት መንፈስ ቅዱስ ከደቀመዛሙርት ጋር አልነበረምን? ከነበረስ ያ የነበረው መንፈስ ቅዱስስ ጊዜያዊ እንጅ ዘላለማዊ አልነበረም ማለት ነው?
ሐ) ኢየሱስ በሌላ ቦታ ላይ ስለዚህ አፅናኝ ሲናገር፦
እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።ዮሐንስ 16፥7
በዚህ አንቀፅ ኢየሱስ ለአፅናኙ መምጣት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የሱን መሄድ ነው። አፅናኙ ሊመጣ የሚችለውም እርሱ ከሄደ ብቻ ነው። ይህ አፅናኝ መንፈስ ቅዱስ ነበረ ካልን ግን ብዙ ነገር እናፋልሳለን። የመጀመሪያው ነገር ኢየሱስ ገና ከእናቱ ማህፀን ሳይወጣ በፊት ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ ነበር። ኢየሱስ እራሱ የተፀነሰው በመንፈስ ቅዱስ ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።ማቴዎስ 1፥18 (አዲሱ መ.ት)
ሲጠመቅም መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ነበር።
ከውሃው በሚወጣበትም ጊዜ፣ ሰማያት ተከፍተው፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ሲወርድ አየ፤ማርቆስ 1፥10 (አዲሱ መ.ት)
ሌሎችንም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በጥቅሉ ግን ከላይ እንዳየነው መንፈስ ቅዱስ ከኢየሱስ በኃላ የሚላክና የማይታወቅ አካል ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበረና ለመምጣትም “እኔ ካልሄድኩ ወደናንተ አይመጣም” የሚባልለት አካል አይደለም።
ይህንን ካልን ታዲያ ወደተነሳንበት የነብዩ ሙሐመድ ﷺ መከራከርያ እንለፍ። ለዘላለም የሚኖሩ አይደሉምና መልዕክቱ እሳቸውን የሚመለከት አይደለም የሚለው መከራከሪያ አስቂኝና አስገራሚ ነው። እዚህ ጋር ቃልበቃል የሳቸውን ህልውና ብቻ የሚገልፅ አድርጎ መውሰድ ትክክል አይደለም። እሳቸው እንደመላዕክት ወይንም ሰይጣን እስከፍፃሜው ድረስ የሚቅዩ ልዩ ፍጡር አይደለም። እሳቸው እስከ ፍፃሜው ድረስ በአካል ባይኖሩም በመልዕክታቸው ግን ዝንተ አለም እስከፍፃሜው ድረስ ህያው ናቸው። የተቀበሉት መልዕክት ዛሬም ነገም ሁሌም ቢሆን ለዘላለም ከኛ ጋር የሚኖር ህያው ነው። የዘላለም መኖር ሁሌ የአካል ህልውናን የሚጠቁም ከመሰልዎት ፈጽሞ ተሳስተዋል። መጽሀፍ ቅዱስ ለአብነት እንዲህ ይላል፦
ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።1ኛ ዮሐንስ 2፥17 (አዲሱ መ.ት)
ስለዚህም የነብዩ ሙሐመድ መልዕክት ለዘላለም ከኛ ጋር አብሮ ይኖራል፤ ይህ ግልፅና የተብራራ መልዕክቱም በተግባር የሚረጋገጥ እውነታ ነው።
ማስታወሻዎች
(1) Institute of Ecclesiastical History, ancient and modern. Volume 1 Page 153-155 ,Page 201
(2) The paraclete in the fourth Gospel Raymond E. Brown pg 113


