በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ሰሞኑን የመርየምን ልጅ ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) በተመለከተ፡ ተከታታይ ትምሕርቶችን እየዳሰስን ነው፡፡ በተለይ ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) ከነቢይነትና ከሰብአዊ ፍጥረት ክልል አውጥቶ እሱን አምላካዊ ማንነት ለማላበስ የሚደረገውን ከንቱ ሙከራ ምላሽ እየሰጠንበት ነው፡፡ ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) ከነቢያት ኹሉ በላይ ከፍ ለማድረግ ያግዙናል የሚሏቸውን አንዳንድ ቅዱስ ቁርኣናዊ አንቀጾችንም በማንሳት የአንቀጹን ትክክለኛ መልእክት እና የነሱን የተሳሳተ ግንዛቤ እየተመለከትን ነው፡፡ ዛሬም አላህ ፈቃዱ ከኾነ የምንመለከተው የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) አምላክ እንዳልነበረ፣ እንዳልኾነና ፈጽሞም ሊኾን እንደማይቸል የሚያስረዱትን ቀጥታና ግልጽ የኾኑ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾችን በመጠቀም ነው፡፡ መልካም ንባብ፡-
ሀ/ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም!
ይህ አንዱና ዋነኛው መረጃችን ነው፡፡ የአላህ ቃል የኾነው ቅዱስ ቁርኣን ከአላህ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ በግልጽ ይናገራል፡፡ ‹‹ሌላ የለም›› በሚለው ቃል ውስጥ ከአላህ ውጭ የኾነው ፍጥረት ኹሉ ይካተታል፡፡ የመርየም ልጅም ከነዚህ ‹‹ሌላ›› ተብለው ከተጠቀሱት አካላት አንዱ ነው፡፡ እሱ አላህ አይደለምና፡ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም! ከተባለ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) አምላክ አለመኾኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል ማለት ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“አምላካችሁም አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ (እርሱ) እጅግ በጣም ርኅሩህ አዛኝ ነው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡163)፡፡
“ከባሮቹ በሚሻው ሰው ላይ መላእክትን ከራእይ ጋር በፈቃዱ ያወርዳል (ከሓዲዎችን በቅጣት) አስጠንቅቁ፤ እነሆ ከኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ፍሩኝም ማለትን (አስታውቁ በማለት ያወርዳል)፡፡” (ሱረቱ-ነሕል 16፡2)፡፡
“እኔ አላህ እኔ ነኝ ያለ እኔ አምላክ የለምና ተገዛኝ፡፡ ሶላትንም (በእርሷ) እኔን ለማውሳት ስገድ፡፡” (ሱረቱ ጣሀ 20፡14)፡፡
ለ/ ዒሳ ጠፊ ነው፡-
ይህ ደግሞ ሌላኛው ማስረጃችን ነው፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ፍጹም ዘላለማዊነትን አልተላበሰም፡፡ ፈጣሪ አምላኩ አላህ በፈለገ ጊዜ ሊያጠፋው ይችላል፡፡ ከዚህ ጥፋት እራሱም ሆነ ሌላው አካል በመተባበር ሊያድነው የሚችል አንድም ኃይል የለም አይኖርምም፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ የመርየምን ልጅ አልመሲሕን፡ እናቱንም፡ በምድር ያለንም ሁሉ #ለማጥፋት ቢሻ ከአላህ ማዳንን የሚችል ማን ነው? በላቸው፡፡ የሰማያትና የምድር ንግስና የአላህ ብቻ ነው የሚሻውን ይፈጥራል አላህም በነገሩ ሁሉ ላይ ቻይ ነው፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡17)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሰረት፡ ጌታ አላህ ዒሳንም ሆነ እናቱን እንዲሁም በምድር ላይ ያለን ሁሉ ለማጥፋት ቢፈልግ፡ ማንም ሊያድናቸው የሚችል እንደሌለ ያስረዳል፡፡ አያይዞም በመቀጠል ‹‹የሚሻውን ይፈጥራል›› በማለት ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ከፍጥረታዊ ማንነት ውጪ የዘለለ ሌላ ነገር እንደሌለው ያስረዳል፡፡ እውነተኛ አምላክ የሆነው አላህ ግን አይጠፋም፡፡ ሁሌም ቀሪ ነው፡፡ ቃሉም የሚለው እንዲህ ነው፡-
“በርሷ (በምድር) ላይ ያለው ሁሉ ጠፊ ነው፡፡ የእልቅናና የልግስና ባለቤት የሆነው የጌታህ ፊትም ይቀራል (አይጠፋም)” (ሱረቱ-ረሕማን 55፡26-27)፡፡
“ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትገዛ ከርሱ በቀር አምላክ የለም ነገሩ ሁሉ ከአላህ በቀር ጠፊ ነው ፍርዱ የርሱ ብቻ ነው ወደርሱም ትመለሳላችሁ” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡88)፡፡
ሐ/ ዒሳ ምግብን ይመገብ ነበር፡-
ሰዎች በዚህ ምድር ላይ በሕይወት ለመቆየት ከሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ነገራት አንዱ መብል ነው፡፡ ያለ መብል በሕይወት መቆየት አይችሉም፡፡ ይህም ደካማ ፍጡር መኾናቸውን ያሳያል፡፡ የመርየም ልጅም ከተመጋቢዎቹ አንዱ ነበር፡፡ ታዲያ እንዴት ኾኖ ነው ከአፈር የወጣንና የበቀለን ነገር እንደምግብነት የሚጠቀም አካል የኔ አምላክ ሊኾን የሚችለው? ደግሞስ የበላውና የጠጣው ነገር ተመልሶ በሌላ መልክ (በሽንትና በቆሻሻ) ከሰውነቱ መውጣቱ ይቀራልን? እንግዲያውስ ይህን ስርአት የሚፈጽም አካል አምላኬ ነው ብዬ ልቀበለው? እሱም ደፍሮ አይለኝም!!
“የመርየም ልጅ አል መሲሕ፡ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የሆነ መልክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም እናቱም በጣም እውነተኛ ናት (ሁለቱም) ምግብን #የሚበሉ ነበሩ፡፡ አንቀጾችን ለነርሱ (ለካሀዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት ከዚያም (ከእውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡75)፡፡
እውነተኛው አምላክ አላህ ግን አይበላም፡፡ ባይሆን ፍጡራኑን (ሰውን፣ እንሰሳትን፣ ነፍሳትን፣ በራሪዎችን…) ያበላል እንጂ፡፡ እርሱ መጋቢ እንጂ ተመጋቢ አይደለም! የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ከሆነው አላህ፡ እርሱ የሚመግብ፣ #የማይመገብም ሲሆን ሌላን አምላክ እይዛለሁን? በላቸው፡፡ እኔ መጀመሪያ ትእዛዝን ከተቀበለ ሰው ልሆን ታዘዝኩ ከአጋሪዎችም ፈጽሞ አትሁን (ተብያለሁ) በላቸው” (ሱረቱል አንዓም 6፡14)፡፡
“ጋኔንና ሰውንም ሊግገዙኝ እንጂ ለሌላ አልፈጠርኳቸውም፡፡ ከነርሱም ምንም ሲሳይ አልፈልግም #ሊመግቡኝም አልሻም አላህ እርሱ ሲሳይን ሰጪ የብርቱ ኃይል ባለቤት ነው፡፡” (ሱረቱ-ዛሪያት 56-58)፡፡
መ/ ዒሳ ወደፊት ሟች ነው፡-
መሞት የፍጡራን ባሕሪ እንጂ የአምላክ አይደለም፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳም (ዐለይሂ-ሰላም) ፍጡር በመኾኑ ከሞት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ቂያማ ከመቆሙ በፊት ወደዚህ ምድር በጌታው ፈቃድ ከወረደና ተልእኮውን ከፈጸመ በኋላ እሱም ይሞታል፡፡ ሟች መሆኑን ገና በእናቱ እቅፍ ሳለ በልጅነቱ እንዲህ ተናግሯል፡-
“ሰላምም በኔ ላይ ነው በተወለድኩ ቀን #በምሞትበትም ቀን ህያው ሆኜ በምቀስቀስበት ቀን” (ሱረቱ መርየም 19፡33)፡፡
እውነተኛው ጌታና አምላክ አላህ ግን ፈጽሞ የማይሞት ነው፡፡ ደግሞስ የሞት ፈጣሪና አምላክ እንዴት በፈጠረው ሞት ይያዛል?
“ፊቶችም ሁሉ #ሕያው አስተናባሪ ለሆነው (አላህ) ተዋረዱ በደልንም የተሸከመ ሰው በእርግጥ ከሰረ” (ሱረቱ ጣሀ 20፡111)፡፡
“በዚያም #በማይሞተው ሕያው አምላክ ላይ ተመካ…” (ሱረቱል ፉርቃን 25፡58)፡፡
ሠ/ የትንሳኤ ቀን ጥያቄና መልስ
ነገ በየውሙል ቂያም (በዕለተ ትንሳኤ) ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በጌታው ፊት በሰዎቹ ይመሰክርባቸውና ይክዳቸው ዘንድ ይጠየቃል፡፡ አንተ ለሰዎቹ እኔና እናቴን ከአላህ ሌላ አምላክ አድርጋችሁ ያዙ ብለህ አስተምረህ ነበርን? ተብሎ ይጠየቃል፡፡ የሱም መልስ፡- በፍፁም! የሚል ይሆናል፡፡ ይህም አምላክ አለመሆኑን ፍንትው አድርጎ ያስረዳል፡-
“አላህም የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብለሀልን? በሚለው ጊዜ (አስታውስ) ጥራት ይገባህ ለኔ ተገቢዬ ያልሆነን ነገር ማለት ለኔ #አይገባኝም፡፡ ብዬው እንደሆነም በእርግጥ አውቀኸዋል በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም፡፡ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም አዋቂ አንተ ብቻ ነህና” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡116)፡፡
እውነተኛ አምላክ የሆነው አላህ ግን እኔን ተገዙኝ፡ አምልኩኝ ይላል፡-
“ከአንተ በፊትም፣ እነሆ ከኔ ሌላ አምላክ የለምና ተገዙኝ፣ በማለት ወደርሱ የምናወርድለት ቢሆን እንጅ ከመልክተኛ አንድንም አልላክንም።” (ሱረቱል አንቢያእ 21፡25)፡፡
ረ- የሐዋሪያት እምነትስ?
የዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ተከታይ የነበሩት ሐዋሪት እንኳ እሱ አምላክ አለመሆኑን ያውቁ ስለነበር፡ ለምልክት የሚሆን ማእድ (መብል) ከሰማይ እንዲወርድላቸው ጌታህን ለምንልን ብለው እሱን ጠየቁት እንጂ፡ አንተ አውርድልን አላሉትም፡፡ እንደማይችል ያውቃሉና፡-
“ሐዋሪያት፡- የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ #ጌታህ በኛ ላይ ከሰማይ ማእድን ሊያወርድልን ይችላል? ባሉ ጊዜ ( አስታውስ) ምእመናን እንደሆናችሁ አላህን ፍሩ አላቸው” (አል-ማኢዳህ 5፡112)፡፡
የመርየም ልጅ ዒሳም (ዐለይሂ-ሰላም) ይህንን ማድረግ የሚችለው አላህ ብቻ እንደሆነ ያውቅ ስለነበር፡ ጌታውን አላህ እንዲህ ብሎ ለመነ፡-
“የመርየም ልጅ ዒሳ አለ ፦ጌታችን አላህ ሆይ! ለኛ ለመጀመሪያዎቻችንና ለመጨረሻዎቻችን በአል (መደሰቻ) የምትሆንን ከአንተም ተአምር የሆነችን ማእድ ከሰማይ በኛ ላይ አውርድ፤ ስጠንም፤ አንተ ከሰጪዎች ሁሉ በላጭ ነህና። አላህም፦ እኔ (ማእድዋን) በናንተ ላይ አውራጅዋ ነኝ፤ በኋላም ከናንተ የሚክድ ሰው እኔ ከዓለማት አንድንም የማልቀጣውን ቅጣት እቀጣዋል አለ።” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡114-115)፡፡
ሰ ነቢይ መሆኑ፡-
“(ሕፃኑም) አለ እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ፤ መጽሐፍም ሰጥቶኛል #ነቢይም አድርጎኛል።” (ሱረቱ መርየም 30)፡፡
ጌታ አላህ ደግሞ ነቢይን ጌታ አድርገን እንድንይዝ አይመክረንም፡ አያዘንምም፡፡ ደግሞም ነቢይ የሆነ አካል ሰዎችን ለኔ ባሪያ ሁኑ የማለት ስልጣንም አልተሰጠውምም፡-
“ለማንም ሰዉ አላህ መጽሐፍንና ጥበብን ነቢይነትንም ሊሰጠዉና ከዚያም ለሰዎች ከአላህ ሌላ ለእኔ ባሮች ሆኑ ሊል አይገባዉም፤ ግን መጽሐፍን የምታስተምሩ በነበራችሁትና የምታጠኑም በነበራችሁት በዕዉቀታችሁ ሠሪዎች ሁኑ (ይላቸዋል)። መላእክትንና ነቢያትንም አማልክቶች አድርጋችሁ እንድትይዙ ሊያዛችሁ (አይገባዉም)፤ እናንተ ሙስሊሞች ከሆናችሁ በኋላ በክሕደት ያዛችኋልን?” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡79-80)፡፡
ሸ. ባሪያ መሆኑ፡-
የአምላክ ቃል የሆነው ቅዱስ ቁርኣን እንደሚያስተምረው በሰማያትና በምድር ያለው ነገር በጠቅላላ የአላህ ባሪያ ነው (መርየም 19፡93)፡፡ ፍጥረታት በጠቅላላ በፈቃዱ ስር የተገዙ ናቸው (አር-ሩም 30፡26)፡፡ ለአፍታ ያህል ከሱ መለኮታዊ ቁጥጥር መውጣት የሚቻለው የለም፡፡ በይሁንታው የፈቀደው ነገር ሁሉ ይኾናል፡፡ እሱ ያልሻው ነገር በመላ ከንቱ ሆኖ ይቀራል እንጂ መሆንና መገኘት አይችልም፡፡
‹‹ባሪያ›› ማለት ትርጉሙ፡- በጌታው ላይ ጥገኛ የሆነ፣ ከጌታው ተነጥሎ እራሱን በመቻል ነጻነቱን ያላወጀ፣ ጌታው በፈለገው ጊዜ ያለምንምና ያለማንም ተቃውሞ እንደፈለገ ሊያደርገው የሚችል ማለት ነው፡፡ ታዲያ በዚህ አይነት የ‹‹አላህ ባሪያ›› ያልኾነ ማን አልለ?
ስንፈጠር፡- እሱ ፈጣሪያችን አላህ በፈለገው ጊዜና ዘመን፣ በፈለገው ሀገርና መንደር፣ ከፈለገው እናትና አባት፣ በፈለገውና በወሰነው ጾታና መልክ ሠራን፡፡ በዚህ ውስጥ ምን የኛ ድርሻ አለበት? ማነው ጥቁር አፍሪካዊ መሆንን መርጦ የተወለደ?
ስንኖር፡- በሕይወት ለመቆየት የሚያስችሉንን መሰረታዊ ነገራት (አየር፣ መብልና መጠጥ፣ መጠለያ) አላህ እራሱ ፈልጎ ካዘጋጀቸው ነገሮች ብቻ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ማነው ይህን የሚተነፍሰውን አየር አልተስማማኝም ብሎ በሰው ሠራሽ አየር ለመቀየር የሞከረና መኖር የቻለ?
ማነው ይህን የሚመገበውን ምግብ (ከእጽዋትና ከእንሰሳት የሚገኙትን) አልተስማሙኝም ብሎ በምትኩ ሰው ሰራሽ ምግብ ማምረትና፡ የእጽዋትንና የእንሰሳትን ቦታ መሸፈን የቻለ?
ማነው በዝናብ አማካኝነት የወረደለትን ውሃ ጠልቶ፡ ለመጠጥ ግልጋሎት የሚውል ሌላ አይነት መጠጥ ያዘጋጀና እራሱን የቻለ?
ስንሞት፡- ሁላችንም አላህ በፈቀደውና በሻልን ሰዓት እንሞታለን፡፡ ከተመደበልንና ከተወሰነልን ሰዓት ለሰከንድ ያክል ማቅረብም ሆነ ማዘግየት አንችልም፡፡ አይሞከርምም፡፡ ታዲያ ማነው ለሞት መድኃኒትን ሊያገኝ የቻለ ፍጡር? ወይም ጊዜውን ማራዘም የሚችል?
ስንቀሰቀስ፡- አሁንም አላህ እራሱ በፈለገው ቀንና ጊዜ ከመቃብራችን፡ በሞትንበት ሁኔታ ላይ እንደነበርነው ይቀሰቅሰናል፡፡ እኔ መቀስቀስ የለብኝም ብሎ በዛው አፈር ሆኖ የሚቀር የለም፡፡ ወይም ከሰዓቱ በፊት ከመቃብር ሆድ አፈትልኮ የሚወጣ የለም፡፡
እንግዲያውስ ሁላችንም የአላህ ‹‹ባሮች›› አይደለንምን? እንዴታ! ነን እንጂ፡፡ በትንሳኤው ዕለትም (የውሙል ቂያም) ወደ ጌታችን አላህ ስንቀሰቀስ ባሪያ ሆነን እንጂ ሌላ ኾነን አንመጣም፡፡
“በሰማያትና በምድር ያለዉ ሁሉ (በትንሣኤ ቀን)፣ ለአል-ረሕማን #ባሪያ ኾነዉ የሚመጡ እንጂ ሌላ አይደሉም።” (ሱረቱ መርየም 19፡93)፡፡
የመርየም ልጅ ዒሳም (ዐለይሂ-ሰላም) በምድር ከሚኖሩት ከአላህ ባሪያዎች አንዱ እንደነበር፡ ገና የእናቱን ማኅፀን እንደከፈተ (እንደተወለደ) በአንደበቱ የተናገረው ምስክርነት ነበር፡-
“በርሱም የተሸከመቺዉ ኾና ወደ ዘመዶችዋ መጣች ፦ መርየም ሆይ ከባድን ነገር በእርግጥ ሠራሽ አሏት። የሃሩን እኅት ሆይ አባትሽ መጥፎ ሰዉ አልነበረም፤ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም አሉዋት። ወደርሱም ጠቀሰች ፤ በአንቀልባ ያለን ሕፃን እንዴት እናናግራለን! አሉ። (ሕፃኑም) አለ እኔ የአላህ #ባሪያ ነኝ፤ መጽሐፍም ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል።” (ሱረቱ መርየም 19፡27-30)፡፡
በርግጥም ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የአላህ ባሪያ በመሆኑ ይኮራ እንደሆን እንጂ በፍፁም ሊጠየፍ አይችልም፡ መጠየፍም አይገባውም፡-
“አልመሲሕ፣ ለአላህ #ባሪያ ከመኾን ፈጽሞ አይጠየፍም፤ ቀራቢዎች የሆኑት መላእክትም (አይጠየፉም)…” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡172)፡፡
ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የአላህ ባሪያ እንጂ ልጁ አይደለም፡፡ አላህ ዘንድ ባሪያ እንጂ ልጅ ወይም አምላክ ተደርጎ አይቆጠርምና፡-
“እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤል ልጆች ታምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጂ ሌላ አይደለም።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡59)፡፡
እንግዲውስ የአላህ ባሪያ የኾነ አካል እንዴት ነው ተመልሶ ጌታና አምላክ የሚሆነው?
ቀ/ ጌታ እንዳለው መናገሩ፡-
አምላክ በራሱ ላይ ሌላ አምላክ የለበትም፡፡ አምላክ አንድ ብቻ ነውና፡፡ ጌታም እሱ ብቻ ስለሆነ፡ በራሱ ላይ ሌላ ጌታ የለበትም፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ ግን በአራት የቅዱስ ቁርኣን ምእራፎችና ስድስት አንቀጾች ላይ አላህ ጌታውና ጌታችን መሆኑን በማስተማር እሱን ብቻ ልናመልከው እንደሚገባ መናገሩን አላህ እንዲህ ነግሮናል፡-
“እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፤ አልመሲሕም አለ፦ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፤ እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ጀነትን በእርግጥ እርም አደረገ፤ መኖሪያውም እሳት ናት፤ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም።” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡72)፡፡ በተጨማሪም፡- (አሊ-ዒምራን 3፡51፣ አል-ማኢዳህ 5፡117፣ መርየም 19፡36፣ ዙኽሩፍ 43፡64) ይመልከቱ፡፡
አዎ! ዒሳንም ሆነ ማንኛውንም ነቢይ እንዲሁም መልአክ ጌታ በማድረግ በአላህ ላይ ማጋራት ለጀሀነም የሚዳርግ ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡ ጀነትንም በፍጹም አያስወርስም፡፡ እኛ የምናመልከው እውነተኛው አምላክ አላህ እርሱ የሁሉ ጌታ የሆነ እንጂ፡ ለራሱ ጌታ ያለው አይደለም፡-
“በላቸው «እርሱ (አላህ) የሁሉ ጌታ ሲኾን ከአላህ በቀር ሌላን ጌታ እፈልጋለሁን? ነፍስም ሁሉ በራሷ ላይ እንጅ (ክፉን) አትሠራም፡፡ ተሸካሚም (ነፍስ) የሌላይቱን ሸክም (ኃጢአት) አትሸከምም፡፡ ከዚያም መመለሻችሁ ወደ ጌታችሁ ነው፡፡ ወዲያውም በእርሱ ትለያዩበት የነበራችሁትን ሁሉ ይነግራችኋል፡፡»” (ሱረቱል አንዓም 6፡164)፡፡
በ/ የራሱ ሆነ ኃይልና ስልጣን ስለሌለው፡-
የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በሚያደርጋቸው ማንኛውም ነገራት፡ የጌታው ፈቃድና ጥበቃ ያስፈልገው ነበር፡፡ እንዲሁም በመልአኩ ጂብሪል ይታገዝ ነበር፡፡ ተአምራትንም በራሱ ኃይልና ስልጣን ሳይሆን፡ በጌታው አላህ ፈቃድና ኃይል ሰጪነት ነበር የሚያከናውነው፡፡ ይህም አምላክ አለመሆኑን በግልጽ ያሳያል፡-
“ወደ እሥራኤልም ልጆች መልክተኛ የደርገዋል፤ (ይላልም) ፡-እኔ ከጌታዬ ዘንድ በታምር መጣኋችሁ። እኔ ለናንተ ከጭቃ አንደ ወፍ ቅርጽ እፈጥራለሁ፤ በርሱም እተነፍስበታለሁ፤ #በአላህም ፈቃድ ወፍ ይሆናል። በአላህም ፈቃድ ዕዉር ሆኖ የተወለደን፥ ለምጸኛንም፥ አድናለሁ፤ ሙታንንም አስነሳለሁ። የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት።” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡49)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ በግልጽ እንደሰፈረው ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ወደ የዕቁብ ዝርያዎች (ቤተ እሥራኤል) መልክተኛ ሆኖ ሲላክ፡ በተአምራት እንደታገዘና፡ እነዚህንም ተአምራት በአላህ ፈቃድ ያከናውን እንደነበር መረዳት ይቻላል፡፡ እሱ አምላክ ከነበር የማንን ፈቃድ ነው የሚጠብቀው? ደግሞስ መልአክ እንዴት ሊያበረታታውና ሊያጸናው ቻለ?
“አላህ በሚል ጊዜ (አስታውስ) ፦ የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! በአንተና በእናትህ ላይ (የዋልኩላችሁን) ጸጋዬን አስታውስ፤ በሕጻንነትና በከፈኒሳነት (የበሰለ ሰው ሆነህ) ሰዎችን የምትናገር ስትሆን በቅዱስ መንፈስ (በጂብሪል) ባበረታሁህ ጊዜ…” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡110)፡፡
በጥቅሉ በዚህ ክፍል ያየናቸው፡ በአሥር መንገድ የተጠቀሱ ቅዱስ ቁርኣናዊ ማስረጃዎች ያለምንም ጥርጥር ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የአላህ ባሪያና መልክተኛ እንጂ፡ አምላክና የአምላክ ልጅ እንዳልነበረ፣ እንዳልሆነምና ፈጽሞም ሊሆን እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ ጌታ አላህም እንዲህ ይለናል፡፡ የኛስ መልስ ምንድነው?፡-
“እርሱ እውነተኛ ጌታችሁ አላህ ነው፡፡ ከእውነትም በኋላ ጥመት እንጂ ሌላ ምን አለ? (ከውነት) እንዴት ትዞራላችሁ” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡32)፡፡
“ከአላህም ጋር ሌላን አምላክ አትግገዛ፡፡ ከእርሱ በቀር አምላክ የለም፡፡ ነገሩ ሁሉ ከአላህ በቀር ጠፊ ነው፡፡ ፍርዱ የርሱ፤ ብቻ ነው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡88)፡፡
አላሁምመ ሠቢትና ዐለል-ኢስላም፣ ወአሚትና አላ ከሊመቲ-ሸሀዳህ፣ ወሠብቢትና ዒንደ-ሱአሊል መለከይኒ ፊል-ቀብር፣ ወወፊቅነል ጀንናህ፣ ወጀንኒብና አኒ-ናር፡፡ ቢራሕመቲከ ያ አርሐመ-ራሒሚን፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


