በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በኾነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2) የአላህ ውዳሴና ሰላም የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለኾኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ነፍሴ በእጁ በኾነችው ይሁንብኝ! በናንተ ላይ የመርየም ልጅ ፍትሐዊ ዳኛ ኾኖ ሊወርድ ይቃረባል፡፡ መስቀልንም ይሰባብራል፡፡ አሳማዎችንም ይገድላል፡፡ ግብርንም ይተዋል፡፡ ገንዘብንም የሚቀበለው ሰው እስኪጠፋ ድረስ ይበራከታል፡፡ ለአላህ የሚደረግ አንድ ሱጁድ ዱንያና በውስጧ ከያዘችው ኹሉ የበለጠና የተሻለ ይኾናል” ከዚያም አቡ ሁረይራህ፡ ‹‹ከፈለጋችሁ ይህን አንቀጽ አንብቡ›› አለ፡፡ ‹‹ከመጽሐፉም ሰዎች ከመሞቱ በፊት በእርሱ (በዒሳ) በእርግጥ የሚያምን እንጅ (አንድም) የለም፡፡ በትንሣኤም ቀን በነሱ ላይ መስካሪ ይኾናል፡፡››፡፡ (ቡኻሪይ 3448፣ ሙስሊም 406፣ አሕመድ 7471፣ ቲርሚዚይ 2398)፡፡
በዚህ ታላቅ ሐዲሥ ውስጥ ‹‹የመርየም ልጅ ፍትሐዊ ዳኛ ኾኖ ሊወርድ ይቃረባል›› የሚለውን ቃል በመምዘዝ፡ ወገኖቻችን፡- ‹‹እናንተም ሙስሊሞች በመጨረሻው ቀን ዒሳ ፈራጅ እንደኾነ ታምናላችሁ! ሐዲሣችሁም ይናገራል እኮ!›› ይሉናል፡፡ የኛስ መልስ ምንድነው? እውን የሐዲሡ መልእክት እነሱ እንዳሉት ነውን? ፈራጅስ ማነው? መጠነኛ ምላሹን ይከታተሉ፡፡
1/ ፍርድ የአላህ ነው፡፡ የጌትነቱ መገለጫውም ነው፡፡ በባሮቹ ላይ የሚፈርደው እሱ ነው፡፡ ቀድሞውኑም ይህን አድርጉ ትእዛዝ ነው! ያን ደግሞ አትቅረቡ እርም ነው! በማለት በባሮቹ ላይ ህግን ያወጣውና የደነገገው እሱ ነውና፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ህግን አላወጣም አልደነገገምም፡፡ እሱ ራሱ የአምላክ ህግ ከሚመለከታቸው የአምላክ ባሪያና ነቢያት ከኾኑት ውስጥ አንዱ ነውና፡፡ በምን መልኩ ነው ታዲያ፡ ህግ ያወጣው አላህ፡ የሚተሳሰበውና የሚፈርደው ደግሞ ዒሳ የሚኾነው? የመርየም ልጅ ዒሳ በአላህ ባሮች ላይ በመጨረሻው ቀን ይፈርዳል ካልን፡ በምን ህግ ነው የሚፈርድባቸው? ትእዛዝን እሱ አልሰጣቸው! ይህን ሥሩ ዋጂብ ነው! ያን ደግሞ አትቅረቡ ሐራም ነው! ብሎ በሰዎች ላይ ህግን አልደነገገም፡፡ በማያውቀውና ባልደነገገው ህግ ይፈርዳል ማለት ጤናማ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ አላህ ግን በባሮቹ ላይ ከአደም ዘመን ጀምሮ እስከ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂም ወሰለም) ድረስ የነበሩ ነቢያትን፡ የመረጠውና የላከው፣ መጽሐፍትንም ያወረደውና ህግ የደነገገው እሱ ስለነበር፡ በመጨረሻው ቀንም ባሮቹን የሚተሳሰባቸው እሱ ብቻ ነው፡፡ ህጌን የት አደረጋችሁ በማለትም ይጠይቃቸዋል፡ እንደ ሥራቸው መጠንም ይፈርድባቸዋል፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“መልክተኞቻችንን በግልጽ ማስረጃዎች በእርግጥ ላክን፡፡ ሰዎችም በትክክል ቀጥ እንዲሉ መጽሐፎችንና ሚዛንን ወደእነርሱ አወረድን…” (ሱረቱል ሐዲድ 57፡25)፡፡
“አላህ መልክተኞቹን የሚሰበስብበትንና «ምን መልስ ተሰጣችሁ» የሚልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ «ለእኛ ምንም ዕውቀት የለንም አንተ ሩቆችን በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህ» ይላሉ፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡109)፡፡
“የሚጠራቸውንና ለመልክተኞቹስ ምንን መለሳችሁ» የሚልበትን ቀን (አስታውስ)፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡65)፡፡
“…ፍርዱ ለአላህ ብቻ ነው፡፡ እውነትን ይፈርዳል፡፡ እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው» በላቸው፡፡” (ሱረቱል አንዓም 6፡75)፡፡
“ከእርሱ ሌላ እናንተና አባቶቻችሁ (አማልክት ብላችሁ) የጠራችኋቸውን ስሞች እንጅ አትገዝዙም፡፡ አላህ በእርሷ ምንም አስረጅ አላወረደም፡፡ ፍርዱ የአላህ እንጅ የሌላ አይደለም፡፡ እርሱን እንጅ ሌላን እንዳትገዙ አዟል፡፡ ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት ነው፡፡ ግን አብዛኞቹ ሰዎች አያውቁም፡፡” (ሱረቱ ዩሱፍ 12፡40)፡፡
“እርሱም አላህ ነው፡፡ ከእርሱ ሌላ አምላክ የለም፡፡ ምስጋና በመጀመሪያይቱም በመጨረሻይቱም ዓለም ለእርሱ ብቻ ነው፡፡ ፍርዱም የእርሱ ብቻ ነው፡፡ ወደእርሱም ትመለሳላችሁ፡፡” (ሱረቱል ቀሶስ 28፡70)፡፡
2/ የፍርድ ቀን የሚባለው ሁላችንም እንደምናውቀው የውሙል ቂያም (የትንሳኤው ዕለት) ነው፡፡ ማለትም፡- በምድር ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት በጠቅላላ ሞተው፡ ከአፈር በታች (በመቃብር) ኾነው፡ ከዚያም በኋላ መልአኩ ኢስራፊል (ዐለይሂ-ሰላም) በጡርንባው አንዴ ሲነፋ ምድር ሸክሞቿን በጠቅላላ ታራግፋለች፡፡ ሙታን በጠቅላላ ዳግም ነፍስ ዘርተው ሕያው ኾነው ይቀሰቀሳሉ፡፡ ወደ ጌታቸው አላህ ፍርድ ሚዛንም ለምርመራና ለፍርድ ይቀርባሉ፡፡ ይህ ቀን ነው የፍርድ ቀን የሚባለው፡፡ የዚህ የፍርዱ ቀን ባለቤት ደግሞ አላህ ብቻ ነው (ማሊኪ የውሚ-ዲን) የተባለው እርሱ አይደለምን?፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ግን ወደዚህ ምድር የሚወርደው ከቂያም ቀን መከሰት በፊት ነው፡፡ እንደውም የሱ መምጣትና መውረድ፡ ለቂያም ቀን እጅግ መቃረብ ምልክት ነው ተብሎ በቁርኣን ተነግሮናል (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡61 ተመልከት)፡፡ ታዲያ ከፍርዱ ቀን በፊት፡ በምድር ያሉ ሕያዋንም ጨርሰው ከመሞታቸው፡ ሙታንም ከመቃብራቸው ከመቀስቀሳቸው በፊት ወደዚህ ምድር ዒሳ የሚመጣው በሰዎች ላይ ለመፍረድ ነው ብሎ ማሰብ ምንኛ ነው? የትንሳኤው ፍርድ ቀኑ ተቀየረ እንዴ? ደግሞስ ሊፈርድ ከመጣ በወቅቱ በሕይወት ባሉት ሰዎች ላይ ብቻ ሊኾን ነውን? በመቃብር ከዚህ በፊት የሞቱትስ ከፍርድ አመለጡ ማለት ነውን? እነዚህ ፍርድን የተቀበሉትስ ሞት ሊቀርላቸው ነው ወይስ ከፍርድም በኋላ ድጋሚ ሞት ይኖር ይኾን? ይህ ሁሉ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የሚመጣው በሰዎች ላይ ለመፍረድ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ራቁቱን የሚያስቀር ነው፡፡
3/ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በአላህ ቃል ውስጥ እንደተገለጸው፡ በትንሳኤው ቀን በባሮቹ ላይ የሚፈርደው አላህ ራሱ መኾኑን በአንደበቱ መመሥከሩን ነው፡፡ የአላህ ቃል ስለ ዒሳ ምሥክርነት ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
“«በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም፡፡ በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በነርሱ ላይ ተጣባበቂ ነበርኩ፡፡ በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ፡፡ አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ፡፡» «ብትቀጣቸው እነርሱ ባሮችህ ናቸው፡፡ ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ» (ይላል)፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡117-118)፡፡
በዚህ አንቀጽ መሠረት፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በዚህ ምድር ላይ አላህ የሱና የሰዎቹ ጌታቸው እንደኾነ ማስተማሩን ይመሠክራል፡፡ ወደ አላህም ከመነሳቱ (ከመወሰዱ) በፊት በሰዎቹ ጉዳይ ተጠባባቂ እንደነበርና፡ አላህ ወደራሱ ካነሳው በኋላ ግን ምንም የሚውቀው ነገር እንደሌለ፡ ይልቁኑ አላህ ተጠባባቂ እንደነበረና አላህም በሁሉም ነገር ዐዋቂ መኾኑን ይመሠክራል፡፡ አያይዞም፡- እነዚህን እስራኤላውያን አመጸኞቹን ቢቀጣቸው የራሱ ባሮች ስለኾኑ መብቱ እንደኾነ፡ ቢምራቸው ደግሞ አሸናፊውና ጥበበኛው እሱ ብቻ እንደኾ በመግለጽ ፍርድ የአላህ ብቻ መኾኑን ይናገራል፡፡ የፈለገውን የሚምር የፈለገውን የሚቀጣ አላህ ብቻ ከኾነ፡ የመርየም ልጅ ወደዚህ ምድር የሚወርደው ሊፈርድ ነው ማለት ፍጹም ስህተት ነው!፡፡
4/ ከላይ መግቢያችን ላይ ወደጠቀስነው ሐዲሥ ስንመለስ፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ወደዚህ ምድር ሲወርድ ‹‹ፍትሐዊ ዳኝ›› ወይም ‹‹ፍትሐዊ ፈራጅ›› ኾኖ ይወርዳል የሚለው፡ በአላህ ሸሪዐና ህግ ማስተዳደሩን ለመግለጽ እንጂ፡ የጀነት እና የጀሀነም ጉዳይን በኃላፊነት ተሸክሞ፡ አንዱን ለጽድቅ አንዱን ለኩነኔ አድርጎ በመለየት ለመፍረድ አይደለም አይኾንምም፡፡ በዚህ በቡኻሪይ ሐዲሥ ላይ የተጠቀሰውን፡ ኢማም አል-ቀስጦላኒይ፡ ኢርሻዱ-ሳሪይ በተሰኘው የቡኻሪይ መጽሐፍ ማብራሪያቸው ላይ፡ ይህን ሐዲሥ እንዲህ ይፈቱታል፡-
(حكمًا) بفتحتين أي حاكمًا (مقسطًا) عادلاً يقال أقسط إذا عدل وقسط إذا جار أي حاكمًا من حكام هذه الأمة بهذه الشريعة المحمدية لا نبيًّا برسالة مستقلة وشريعة ناسخة. إرشاد الساري 105/4.
‹‹ፍትሐዊ ዳኛ/ፈራጅ›› ማለት፡- በነቢዩ ሙሐመድ ሸሪዓህ ከሚፈርዱ የዚህ ኡምመት ዳኞችና አስተዳዳሪዎች ውስጥ እሱም አንዱ ዳኛ ይኾናል፡፡ በዚሁ ሸሪዓህ እንጂ፡ በአዲስ መልኩ ነቢይና መልክተኛ ኾኖ አዲስ ሸሪዓም ይዞ አይደለም›› ይላሉ፡፡
5/ በአላህ ቃል ውስጥ፡ በጌታቸው ሸሪዓህ እንዲፈርዱ ስልጣን የተሰጣቸው ብዙ ነቢያቶች አሉ፡፡ ከሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በኋላ የመጡ ትእዛዝን የተቀሉ የእስራኤል ነቢያቶች በተውራት ህግ እንዲፈርዱ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡44 ተመልከት)፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አላህ ባወረደው በቁርኣን ህግ እንዲፈርዱ ታዘዋል (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡48-49 ተመልከት)፡፡ እነዚህ ነቢያቶች ‹‹ይፈርዳሉ›› ማለት ግን፡ መዳኘትና ማስተዳደር፡ ህዝቡን ወደ ቀናው ጎዳና ማመላከት እንጂ፡ ስለ ጀነት እና ጀሀነም ፍርድ መስጠት አይደለም፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳም (ዐለይሂ-ሰላም) ‹‹ይዳኛል ይፈርዳል›› ማለት ፡ በአላህ ህግና ስርአት ህዝቦቹን መምራት እንጂ፡ በሙታን እና በሕያዋን ላይ ለፍረድ አቅርቦ ውሳኔ መስጠት አይደለም፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


