የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ–ሰላም) ስም እንኳን 25 ጊዜ 250 ጊዜ ቢጠራም: ከሰብአዊ ፍጡርት ወደ አምላክነት፣ ከመርየም ልጅነት ወደ አላህ ልጅነት አያሻግረውምና!!
በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
” نَحْنُ نَقُصُّ عَلَيْكَ أَحْسَنَ الْقَصَصِ بِمَا أَوْحَيْنَا إِلَيْكَ هَذَا الْقُرْآنَ وَإِنْ كُنْتَ مِنْ قَبْلِهِ لَمِنَ الْغَافِلِينَ ” سورة يوسف 3
“እኛ ይህንን ቁርኣን ወደ አንተ በማውረዳችን በጣም መልካም ዜናዎችን በአንተ ላይ እንተርክልሃለን፡፡ እነሆ ከእርሱ በፊት (ካለፉት ሕዝቦች ታሪክ) በእርግጥ ከዘንጊዎቹ ነበርክ፡፡” (ሱረቱ ዩሱፍ 12፡3)፡፡
በዚህና መሰል የቅዱስ ቁርኣን አንቀጾች መሠረት፡- ጌታ አላህ ለነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ከቀደምት የነቢያትና የሕዝቦቻቸው ታሪክ ውስጥ፡ ለእምነታችን ጠቃሚና አርአያ የሚሆነውን በሳቸው በኩል እንደሚተርክልን መግለጹን እንመለከታለን፡፡ አያይዞም ይህ የነቢያት ዜና ‹‹በጣም መልካም ዜና›› (አሕሰኑል-ቀሶስ) መኾኑን ይገልጽልናል፡፡ ምክንያቱም በነቢያት ሥም የተጻፉ፣ የአምላክ ቃል በሚል ሽፋን የሰው ድርሰት የኾኑ የሀሰት መጽሐፍቶች አሉና!፡፡ ቅዱስ ቁርኣን ግን ቃሉም ሆነ መልእክቱ የአላህ እንጂ፡ የመላእክት ወይም የነቢያት ወይንም የጸሐፍት አይደለምና፡ በውስጡ ያሉት ታሪኮች ሁሉ ፍጹም እውነት ናቸው፡፡ ሌሎች ‹መለኮታዊ› መጽሐፍት የተባሉት በጠቅላላ በሱ ይመዘናሉ እንጂ፡ እሱ በማንም መጽሐፍት አይመዘንም፡፡
በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ እንደ ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሰፊ ምእራፍ (ሱራ) እና ሰፊ ትረካን አግኝቶ፡ ታሪኩ በስፋት የተወሳ አንድም ነቢይም ኾነ ረሱል የለም፡፡ የሙሳን ያህል ሥሙ በተደጋጋሚ የተጠቀሰም አንድም ነቢይ የለም!፡፡ ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሥሙ ብቻ 136 ጊዜ በአላህ ቃል ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሥሙ ከተጠራበት 5 እጥፍ በላይ ማለት ነው!፡፡ የዒሳ ሥም 25 ጊዜ ነውና በአላህ ቃል ውስጥ የተጠቀሰው!፡፡
ታዲያ ክርስቲያን ወገኖቻችን ለምን ይኾን የዒሳን 25 ጊዜ በሥም መጠቀስ፡ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) 5 ጊዜ ከተጠቀሰው ሥማቸው ጋር ማነጻጸር የሚፈልጉት? ምን ዓላማስ አንግቦ ይኾን? ጥያቄው ከዚህ በፊት በተለያዩ ወንድሞች በሰፊው ምላሽ የተሰጠበት ቢኾንም፡ እነሱ ግን እንደ በቀቀን ባገኙት አጋጣሚ ደጋግሞ ከማንሳት አልተቆጠቡምና እኛም ምላሹን ከመስጠት ልንቦዝን አይገባንም፡፡ ሀሳቡን ለመረዳትም እንዲያመች፡ እንዲሁም የወገኖቻችን ሀሳብ ምንም ውሀ መቋጠር እንደማይችል ለማሳየት ቀለል ባለ መንገድ ምላሹ ቀጥሎ ይቀርባል፡፡ መልካም ንባብ፡-
1ኛ/ የሥም ተደጋግሞ መጠቀስ ልይዩ ምስጢር ቢኖረው ኖሮ፡ ለውድድር መቅረብ የነበረበት፡ በሥም ብዛት ከፍተኛውን ስፍራ የያዘው ነቢዩላህ ሙሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ነበር እንጂ፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) አልነበረም፡፡ ጉዳዩ ግን ሰብአዊ ፍጡር የኾነውን ዒሳን፡ ከነቢይነትና ከባርነት በማላቀቅ፡ የአምላክ ልጅና አምላክ እንደሆነ ለማሳየት፡ ከነቢያት የተለየ አድርጎ የማቅረብ ከንቱ ሙከራን የያዘ ተልእኮ በመኾኑ ነው፡፡ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሥም ደግሞ አምስት ጊዜ ብቻ በመጠቀሱ፡ 25 ጊዜ ሥሙ ከተጠቀሰው ነቢይ በደረጃ ያንሳሉ የሚል እሳቸውን ዝቅ አድርጎ ለመመልከት የሚስችል ሀሳብንም ያዘለ ነው፡፡ ግን ደረጃና ክብር መች በሥም ብዛት መጠቀስ ሆነና?
2ኛ/ በአላህ ቃል ውስጥ ታሪካቸው ከተወሱት ቀደምት የአላህ ነቢያት ውስጥ ሥማቸው ከ25 ጊዜ በላይ ተደጋግሞ የተወሳ አልለ፡፡ ይህ ማለት በነዚህ ወገኖቻችን ግንዛቤ መሠረት እነዚህ ነቢያት ደግሞ በክብርና በደረጃ ከመርየም ልጅ ይበልጣሉ ማለት ነው፡፡ አንዱን በሰፈርንበት ሚዛን ሌላውንም መስፈር ግድ ይለናልና!፡፡ የሙሳ (136)፣ የኢብራሂም (69)፣ የኑሕ (50) የዩሱፍ እና ሉጥ ሥም (27) ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ ለምን እነዚህን ነቢያት ዘንግተው ወደ ዒሳ መሄድ ፈለጉ? ለምን ከነሱስ ጋር ዒሳን ማወዳደር አልፈለጉም? ጉዳዩ በኢስላም ላይ የተከፈተ ዘመቻ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የነቢዩ ሙሐመድን ክብር ዝቅ ለማድረግና የመርየምን ልጅ ከደረጃው በላይ ለመስቀል የሚደረግ መፍጨርጨር እንጂ ሌላ አይደለም!፡፡
3ኛ/ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሥሙ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ 25 ጊዜ መጠቀሱ ምንም ምስጢር የለውም፡፡ እንግዳ ነገርም አይደለም፡፡ ባይሆን በተጠቀሰባቸው 25 ቦታዎች ላይ ከሥሙ ጋር ተያይዞ ስለ-ማንነቱ ምን መልእክት ለማስተላለፍ ተፈለገ? ብሎ ጥያቄ ማንሳቱ ብልህነት ነው፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ በተጠቀሰባቸው ቦታዎች ሁሉ ላይ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት፡-
ሀ/ እሱም እንደሌሎች መልክተኛ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ ለመግለጽ!፡- ይህ አንዱ እና ዋናው ነጥብ ነው፡፡ የመርየም ልጅ ዒሳ ከሱ በፊት እንዳለፉት መልክተኞች የኾነ መልክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም!፡፡ ምግብንም ተመጋቢ ነበር፡፡ የበላው ነገር ከሰአታት በኋላ ከሰውነቱ ማውጣቱና ማስወገዱም ግዳጁ ነው፡፡ ከተፈጥሮ ህግ ሊወጣ አይችልምና!፡፡ ይህ ደግሞ ሰብአዊ ፍጡር መኾኑን የሚያሳይ ነው፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“የመርየም ልጅ አልመሲሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ እናቱም በጣም እውነተኛ ናት፡፡ (ሁለቱም) ምግብን የሚበሉ ነበሩ፤ አንቀጾችን ለነርሱ (ለከሓዲዎች) እንዴት እንደምናብራራ ተመልከት ከዚያም (ከእውነት) እንዴት እንደሚመለሱ ተመልከት፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡75)፡፡
ለ/ አምላክ እንዳልሆነና ነኝ ማለትም እንደማይገባው ለማስረዳት፡- ዒሳን (ዐለይሂ-ሰላም) ከሰብአዊ ፍጡርነቱ በማውጣት መለኮታዊ ባሕሪን ማላበስ ፍጹም ክህደት ነው፡፡ የቂያም ቀንም ለጀሀነም እሳት የሚዳርግ ታላቅ ኃጢአት ነው፡፡ በመኾኑም እሱ አምላክ አለመኾኑን ለማስተማር ሥሙና ታሪኩ ተወሳ፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“እነዚያ «አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ አልመሲህም አለ፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ፡፡» እነሆ! በአላህ የሚያጋራ ሰው አላህ በርሱ ላይ ገነትን በእርግጥ እርም አደረገ፡፡ መኖሪያውም እሳት ናት፡፡ ለበዳዮችም ምንም ረዳቶች የሏቸውም፡፡” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡72)፡፡
ሐ/ የአላህ ባሪያ እንጂ ልጁ እንዳልሆነ ለመግለጽ፡- ፍጥረታት በጠቅላላ የአላህ ባሪያ ናቸው (ሱረቱ መርየም 19፡93)፡፡ የመርየምን ልጅ ከዚህ ባርነት ሊያስወጣው የሚችል ምንም ማንነት የለውም፡፡ እሱም ቢሆን የአላህ ባሪያ በመሆኑ በፍጹም አይጠየፍም፡፡ ስለዚህ የአላህ ባሪይ እንጂ ልጁ ተብሎ እንደማይጠራ ለማስረዳት ተጠቀሰ፡፡ ጌታ አላህ እንዲህ ይላል፡-
“አልመሲሕ (ኢየሱስ) ለአላህ ባሪያ ከመኾን ፈጽሞ አይጠየፍም፡፡ ቀራቢዎች የኾኑት መላእክትም (አይጠየፉም)፡፡ እርሱን ከመገዛት የሚጠየፍና የሚኮራም ሰው (አላህ) ሁሉንም ወደ እርሱ በእርግጥ ይሰበስባቸዋል፡፡ እነዚያማ ያመኑት መልካሞችንም የሠሩት ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል፡፡ ከችሮታውም ይጨምርላቸዋል፡፡ እነዚያን የተጠየፉትንና የኮሩትንማ አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል፡፡ ከአላህም ሌላ ለእነሱ ዝምድንና ረዳትን አያገኙም፡፡” (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡171-172)፡፡
“እርሱ በርሱ ላይ የለገስንለት ለእስራኤለም ልጆች ተዓምር ያደረግነው የኾነ ባሪያ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 43፡59)፡፡
መ/ መጽሐፍና ተአምራት እንደተሰጠው ለመግለጽ፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እንደቀደሙት የአላህ መልክተኞች እሱም መልክተኛ በመሆኑ መጽሐፍ (ኢንጂል) ተሰጥቶታል፡፡ ቀደምት ነቢያት ተአምራት እንደተሰጣቸው ለሱም ተአምራት የማድረግ ችሎታ ተሰጥቶታል፡፡ ማንኛውም የአላህ መልክተኛ በአላህ ፈቃድ ካልሆነ በቀር በገዛ ፈቃዱ ተአምርን ማድረግም ሆነ ማምጣት አይችልም (ሱረቱ-ረዕድ 13፡38)፡፡
“ሙሳንም መጽሐፍን በእርግጥ ሰጠነው፡፡ ከበኋላውም መልክትኞችን አስከታተልን፡፡ የመርየምን ልጅ ዒሳንም ግልጽ ታምራቶችን ሰጠነው፡፡ በቅዱሱ መንፈስም አበረታነው፡፡ ነፍሶቻችሁ በማትወደው ነገር መልክተኛ በመጣላችሁ ቁጥር (ከመከተል) ትኮራላችሁን? ከፊሉን አስተባበላችሁ፤ ከፊሉንም ትገድላላችሁ፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡87)፡፡
ይህ ነው እውነታው!፡፡ የቁርኣኑ ዋና ዓላማ፡- በመርየም ልጅ ላይ ወሰን በማለፍ የተሳሳቱትን ሁለት ጠርዘኛ ቡድኖች በመገሰጽ፡ ትክክለኛ ማንነቱን ደግሞ በማብራራትና በመግለጽ ሚዛናዊነትን ማሳየት ነው!፡፡ አንደኛው ጠርዘኛ ቡድን፡ አላህ ከሰጠው የነቢይነትና የመልክተኝነት ሚና፡ ደረጃውን ዝቅ በማድረግና ክብሩን በማሳነስ፡ በሀሰተኝነትና በደጋሚነት ሲወነጅለው፣ እንዲሁም ከድንግል በተአምር መወለዱን ጥያቄ ውስጥ በመክተት የዝሙት ልጅ ብሎ ሲከሰው እናያለን (ሱረቱ-ኒሳእ 4፡156፣ አል ማኢዳህ 5፡110፣ አል-ሶፍ 61፡6)፡፡
ሌላኛው ጠርዘኛ ቡድን ደግሞ፡ አላህ ከሰጠው የነቢይነትና የመልክተኝነት ሚና በላይ፡ ደረጃውን ከፍ በማድረግና ክብሩን በማላቅ፡ እሱን ጌታና አምላክ አድርጎ መያዝ፣ እንዲሁም ያለ አባት ከድንግል ብቻ መወለዱን በማንሳት የአምላክ ልጅ እንደሆነ አድርጎ መስበኩ ነው፡፡
ሁለቱም አመለካከቶች በስህተት ላይ ያሉ መሆናቸውን ለመግለጽ፡ እውነታውም የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የአላህ መልክተኛና ባሪያው፡ ከመርየም በይኹን ቃሉ የፈጠረው ፍጥረቱ መሆኑን ለማስረዳት፡ በሱ ላይ ወሰን ያለፉ የእምነት ግሩፖችም ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱ ለመርዳት የዒሳ ማንነት በሥሙ 25 ጊዜ፣ በኩንያው 23 ጊዜ፣ በለቀቡ (ቅጽል ሥሙ) 11 ጊዜ ተጠራ፡፡ ሌላ ምንም ስውር ምስጢር የለውም፡፡
4ኛ/ ወደ ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ስንመለስ ደግሞ፡- የሳቸው ሥም በአላህ ቃል ውስጥ አምስት ጊዜ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ለምን እንደ ዒሳ 25 ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ አልተወሱም? የሚል ጥያቄ ከተነሳም፡ መልሳችን የሚሆነው፡-
ሀ/ ቅዱስ ቁርኣኑ ራሱ ይወርድ የነበረው በሳቸው ልብ ላይ ነው፡፡ የሚያናግረውም እሳቸውን ነው፡፡ እንደነ ዒሳና ሙሳ በታሪክ ኖረው ያለፉ ነቢይ ሳይሆኑ፡ በዘመኑ የነበሩ ሕያው ነቢይ ነበሩና፡ የሳቸውን ሥም ደጋግሞ መጥቀሱ ምንም አስፈላጊነት አልነበረውም፡፡ እነደቀደሙት ነቢያት ‹‹እንዲህ ነበሩ›› እየተባለ ሊወራላቸው የሚችለው፡ ምድራዊ ተልእኮዋቸውን ፈጽመው፡ ወደ ዘላለማዊው ዓለም ቢሻገሩ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከሳቸው መሞት በኋላ በተጻፉት የሲራ መጻሕፍት ላይ ነው የሚገኘው፡፡
ለ/ ጌታ አላህ በቅዱስ ቁርኣን ውስጥ ነቢዩ ሙሐመድን (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በቀጥታ በመጥራት አናግሯቸዋል፡፡ ሲጠራቸው የነበረው ግን ‹‹ያ አዩኸ-ረሱሉ፣ ያ አዩኸ-ነቢዩ›› (አንተ መልክተኛ ሆይ! አንተ ነቢይ ሆይ!) በማለት ከአላህ ዘንድ በተመረጡበትና በተሰጣቸው የክብር ሥም ነው (አል-ማኢዳህ 5፡41፣ 5፡67፣ አል-አንፋል 8፡64፣ አል-አሕዛብ 33፡45)፡፡ አንድም ስፍራ ላይ ‹‹ሙሐመድ ሆይ!›› የሚል ጥርሪን ባዘለ መልኩ ሲያናግራቸው አናገኝም፡፡ ይህ የሚያሳያው እሳቸው ከቀደምት ነቢያት የበለጠ ክብርና ደረጃ ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም እኛም የሳቸው ተከታይ የሆንን ሙስሊሞች እሳቸውን በስማቸው ብቻ መጥራትን አላህ ከለከለን፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“በመካከላችሁ የመልክተኛውን ጥሪ ከፊላችሁ ከፊሉን እንደ መጥራት አታድርጉት፡፡ ከእናንተ ውስጥ እነዚያን እየተከለሉ በመስለክለክ የሚወጡትን አላህ በእርግጥ ያውቃቸዋል፡፡ እነዚያም ትዕዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳትደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ፡፡” (ሱረቱ-ኑር 24፡63)፡፡
ሐ/ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ክቡር ሥም የሆነው ‹‹ሙሐመድ›› እና ‹‹አሕመድ›› በአላህ ቃል ውስጥ አራት ጊዜና አንድ ጊዜ በጥቅሉ አምስት ጊዜ ተጠቀሶአል፡፡ በነዚህ ቦታዎችም ላይ ለማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት፡- እሳቸው እነደቀደሙት ነቢያትና መልክተኞች ሰው የሆኑ ነቢይና መልክተኛ በመሆናቸው ዘላለማዊ ሕያው አይደሉምና ሊሞቱ እንደሚችሉ በመግለጽ፡ በሳቸው ሞት ሰበብ ማንም ከእምነት ማፈግፈግ እንደሌለበት በማስተማር ለመገሰጽ (አሊ-ዒምራን 3፡164)፣ እሳቸው ላልወለዷቸው ልጆች አባት ተብለው እንደማይጠሩና የአላህ መልክተኛና የነቢያት መደምደሚያ መሆናቸውን ለመግለጽ (አል-አሕዛብ 33፡40፣ አል-ፈትሕ 48፡29)፣ የሳቸውን ነቢይነት አምኖ የተቀበለ ሰው የኃጢአት ስርየትን እንደሚያገኝ ለማስተማር (ሱረቱ ሙሐመድ 47፡2)፡፡ እንዲሁም በመርየም ልጅ በዒሳ የተበሰሩ (ትንቢት የተነገረላቸው ነቢይ) መሆናቸውን ለማሳየት ነው (አል-ሶፍ 61፡6)፡፡
5ኛ/ እኛ እንደ ሙስሊምነታችን የመርየም ልጅ ዒሳም ሆነ ነቢዩ ሙሐመድ (ዐለይሂማ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) የአላህ ነቢይ እና መልክተኛ መሆናቸውን አምነናል፡፡ የሁለቱን ብቻ ሳይሆን በነቢያትና በመልክተኞች በጠቅላላ አምነናል (አል-በቀራህ 2፡285)፡፡ የእምነታችንም አንድ አካል ነው፡፡ (አል-በቀራህ 2፡177)፡፡ እናንተ ግን የነቢዩ ሙሐመድን ነቢይነት አምናችሁ ካልተቀበላችሁ፡ ለምን በሥም ብዛት የተጠቀሰውን በመፈለግ ማወዳደርን መረጣችሁ? ነቢይ መሆናቸውን አምናችሁ ካልተቀበላችሁ ሥማቸው አርባ ጊዜ ተጠቀሰ ወይም አራት ጊዜ ለናንተ ምን ይፈይድላችኋል? ለዚህ ነው ሙግታችሁ ውሀ የማያነሳ ከንቱ ሀሳብ ያልነው፡፡ ወገኖቻችን በእሳት ላይ ነው ያላችሁት፡፡ በዕድሜያችሁ አትቀልዱ፡፡ በፍጹማዊ አንድነቱ ሶስትነት የሌለበት፣ በአምላካዊ ማንነቱ ሰዋዊነት ያልተቀላቀለበት፣ በፍጹም ሕያውነቱ ሞትና እንቅልፍ የማይከተለው፣ በእኔነት እራሱን የሚገልጥ፣ በአንተነት የሚጠራና የሚለመን፣ በእሱነት ለሰዎች የሚሰበክ፣ በእኛት ሥራዎቹን የሚያሳይ፣ በእነሱነት ፈጽሞ የማይጠራ የኾነውን አንዱንና እውነተኛውን አምላካችንን አላህ ታመልኩ ዘንድ በአክብሮት ጥሪ እናቀርብላችኋለን፡፡ አላህ ወደ ሐቅ ይምራችሁ!
“የመጽሐፉ ባለቤቶች ሆይ! በእኛና በእናንተ መካከል ትክክል ወደ ኾነች ቃል ኑ፡፡ (እርሷም) አላህን እንጅ ሌላን ላንገዛ፣ በርሱም ምንንም ላናጋራ፣ ከፊላችንም ከፊሉን ከአላህ ሌላ አማልክት አድርጎ ላይይዝ ነው፤ በላቸው፡፡ እምቢ ቢሉም፡- እኛ ሙስሊሞች መኾናችንን መስክሩ በሏቸው፡፡” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡64)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


