በአቡ ዩስራ
ጥያቄ ፦
‘’አላህ ለምን 600 አመት ድርስ ጠብቆ ሙሐመድን ( ሰዓወ) ነብይ አድርጎ ላከው ? ለምን ቀደም ብሎ እየሱስ (ዐሰ) እንዳልተሰቀለ ለምን ቀደም ብሎ አልነገረንም ? በዚህም ምክንያት እኛ ክርስቲያኖች አላህ ለክርስትና እምነት መፈጠርና ሁሉንም ሰዎች ሆነ ብሎ በማሳሳት ተጠያቂ ነዉ እንላለን። ምክንያቱም እሱ ባያመሳስልባቸዉ ሰዎቹ ኢሳ ተሰቀለ ብለዉ አያምኑም ነበር! ክርስትናም አይኖርም ነበር ። ነገር ግን በዚያን ግዜ የነበሩ ሰዎች ዒሳ እንደተሰቀለ እና እንደሞተ ሊያምኑ የሚችሉበት በቂ ምክንያት አላቸው። ይህንን ነገር ሲያምኑ ወዲያውኑ ለምንድ ነው ነብይ ወዲያውኑ ያላከላቸዉ ለምን 600 አመታትን ለማስተማር ወሰደበት ? ‘’
ይህ ጥያቄ ብዙ ማለቂያና ምላሽ የሌላቸዉን የአምላክ ውሳኔዎችን ‹ለምን › እንዲህ አደረገ? ለምን እንዲህ ሆነ? ብለን ሰዎች አምላካቸውን እንዲጠይቁ ይጋብዛል፤ ብዙ እኛ የማናውቀዉ የአምላክ ውሳኔዎች በክርስትናውም ዘንድ ይገኛሉ ። አምላካችን አላህ ሱወ በቁርኣን 21፡23 እንዲህ ይላል ‘’ ከሚሠራው ሁሉ አይጠየቅም፡፡ እነርሱ (ፍጥረቶቹ) ግን ይጠየቃሉ ” አዎ እኛ ፍጡራን አምላክን ለምን እንዲህ አደረግክ ? ለምን እንዲህ አላደረግክም ብለን አንጠይቅም ። በተመሳሳይ መልኩ መ/ቅዱስ ወደ ሮሜ ሰዎች 9 ፡20-21 እንዲህ ይላል ‘’20 ነገር ግን፥ አንተ ሰው ሆይ፥ ለእግዚአብሔር የምትመልስ ማን ነህ? ሥራ ሠሪውን፦ ስለ ምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ ይለዋልን?21 ወይም ሸክላ ሠሪ ከአንዱ ጭቃ ክፍል አንዱን ዕቃ ለክብር አንዱንም ለውርደት ሊሠራ በጭቃ ላይ ሥልጣን የለውምን? በማለት አምላክ በሚወስናቸው ውሳኔዎች ላይ ለምን እንዲህ አደረግክ ብለን መጠየቅ እንዴሌለብን ያስተምራል። እንደ ክርስትናው ‘አስተምህሮ’ አምላክ እየሱስን ከመላኩ በፊት ( ወይንም አምላክ ስለሆነ ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ለ 2000 ዓመታትን የሰዉ ልጆች በሙሉ እና እነዚያ ደጋግና የተከበሩ የአምላክ አገልጋዮችና ነብያት (አብራሃም፤ ኢስሃቅ ፤ ሙሴ ወዘተ. . . ) ሰዎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሩትን በወንጀለኛነትና እና በሃጢአተኝነት ሲፈርጃቸዉ እንደቆየ የታወቀ ነው። ከ 2000 አመት በኋላ ከሞቱበት እነሱ በህይወት በሌሉበት አለም ‹ አዳኛችሁ› እሱ ነው ብሎ ከሚያስተምር እምነት ለምን አምላካችሁ 600 አመት ዝም አለ ? ለምንስ ቀደም ብሎ ነብይ አላከም ተብሎ መቅረብ የሚገባዉ ጥያቄ አልነበርም!! ቢያንስ ይህም ‹አምላክ› ለ2000 አመት ሰዎችን ዝም ብሏልና።
ምናልባትም ይህ ጥያቄ ሊከሠት የቻለው ክርስተናዉ እምነት ከፈጠረባችሁ ብዥታ ሊሆን ይችላል።ለ2 ሺህ ዓመታት በኃጢአት ተነክረው ኃጢአታቸው ሳይሰረይ እንዲሁ በከንቱ እንዲዋልሉ ተዋቸው!! ከዚያም ከ2000 አመታት በሗላ ስጋ ለብሶ ወደ ምድር በመምጣት አዳናቸው። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት የነበሩት በርካታ ትውልዶች ከነኃጢአታቸው ዐደፍ ሞተው እስኪቀበሩ ደረስ ለምን በዝምታ አይቶ ተዋቸው?
ሌላው ነጥብ (… አሏህ #ሰዎችን ሆነ ብሎ አሳስቷል ….) የሚለው ዓይን ያወጣ ድፍረት ነው! ምክንያቱም በማንኛውም ግዜ ውስጥ ሰዎች ሁሉ በፈጣሪያቸዉ የካዱበት አንድም አማኝ ሳይኖር አለም በክህደት ብቻ የተሞላችበት ታሪክ የትኛዉ ትዉልድ ላይ እንደሆነ ብትጦቁሙን? ይህ ክስተት በሚከሰትበት ግዜ በግዜዉ አማኛችም ከሀዲዎችም ነበሩ!! ስለዚህ ‹‹ ሁሉንም ሰዎች›› እንደተሳሳቱ መገመቱ የተሳሳተ እይታ ነዉ፡፡ ሌላዉ የሚገርመዉ ነገር በሌላ ንግግራቸዉ ‹‹… በዚህም የተነሳ እኛ ክርስቲያኖች አላህ ለክርስትና እምነት መፈጠር ተጠያቂ ነዉ›› የሚለዉ ክስ አስቂኝም አዝናኝም ነዉ! እኛ ስናዉቅ ስትሰብኩን ‹‹ ክረስትና የነብያት ሃይማኖት ነዉ ስትሉን ነበር ፤ ከአዳም ጀምሮ እግዝአብሔር ለሰዉ ልጆች መዳኛ ያደረገዉ መንገድ ነዉ ›› ትሉናላችሁ ታዲያ ከመቼ ጀምሮ ነዉ ድሮ ቀዳሚ ነዉ ስትሉን የነበረዉ ‹እምነት› ኋለኛ የሆነዉ? ከመቼ ጀምሮ ነዉ ለክርስትና እምነት ‹መፈጠር› እስልምናን ተጠያቂ የሚሆነዉ? እኮ እንዴት?
እስልምና በዚህ ጉዳይ ያለዉ ምላሽ እንደሚከተለው ነው ፦
- አንድ ሰው ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) ተልከው የአሏህን ተባረከ ወተዓላ መልዕክት ለሕዝቡ እስኪያደርሱበት ዘመን ድረስ( # ነብዩ ሰዐወ ከመምጣታቸው በፊት ) ሰለ እየሱስ(ዐሰ) ስቅለት ላይ የነበረው እምነት የተሳሳተ እምነት ቢሆን ( አዎ ተስቅሏል ብሎ ቢያምን ) በዚህ ስህተት ለኩፍር ወይም ለክሕደት አይዳረግም። ምክኒያቱም አልመሲሕ ዐለይሂ ሰላም ሰው ነው ። ሰው እንደመሆኑ ሁሉ ሊሰቀል የማይችልበት ምክኒያት አይኖርም ። ሊሰቀልም ላይሰቅልም ይችላል ። ይህን ነገር አእምሮ ስለሚቀበለው በተሳሳተ እሳቤ ላይ አቋምን በመገንባት አዎን ተሰቅሏል ብለው ሰዎች ሊያምኑ ይችላሉ ። በዉሸት ወሬም ይሁን እንዲሁ ተወናብደው ወሬው ከመናፈሱ ብዛት እውነት ነው ተብሎ ሊታመን ይችላል ። አይሁዶች የነብያት ደመኞች መሆናቸውን ታሪካቸውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሁሉ ያምናል ። በርካታ ነብያቶቸን የገደሉ የግፍ አለቆች ናቸውና ። ስለዚህ እነዚህ የነብያት ገዳይ አልመሲሕን የማይገድሉበት ምክኒያት ስለማይኖራቸው አያሌ ሰዎች አልመሲሕ ተሰቀለ ብለው ሊያምኑ ችለዋል ። ይህን ማመን ወደ ኩፍር (ክህደት) አያዳርስም ። ይልቅ ክርስቲያኖችን ለክሕደት የዳረጋቸው ጉዳይ አልመሲሕን #አምላክ ማድረጋቸው ወይም #የአምላክ ልጅ ነው በማለታቸው ነው እንጂ በስቅለቱ በማመናቸው አይደለም::
- ከዚህ በተቃራኒው ነብዩ ሙሐመድ ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም #ከመጡ #በኋላ አልመሲሕ ዒሳ (ዐሰ) ከተከበሩት የአሏህ መልክተኞች አንዱ መልክተኛ አይደለም ብሎ ያመነ ፣ ሰውም አይደለም ፣ እርሱ የመጣው የአምላክ ልጅ ወልድ መሆኑን ለማስተማር እንደሆነ የሚያምን ግለሠብ #በመሰቀሉ ጉዳይ ላይ የተሳሳተ ግንዛቤ #ቢኖረውም #ባይኖረውም እርሱ #ከሐዲ #የሆነ ግለሰብ ነው ።
ቁርአን ስለስቅለት ቀለል ባለ ጥቆማ መልዕክቱን ከማስተላለፍ በስተቀር በጥልቀት ጉዳዩን ያላወሳበት ምክኒያት የኢየሱስ (ዐሰ) መሰቀል/አለመሰቀል መሰረታዊ የእምነት ጉዳይ ስላልሆነ ነዉ። መሰረታዊ ጉዳይ ላይ የአላህን አሀዳዊነት በሚፃረር ላይ ግን በግልፅ ከሀዲነታቸውን እንዲህ በማለት አስቀምጧል፡-
➊ ቁርአን 5፡73 እነዚያ «አላህ የሦስት ሦስተኛ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡ ከአምላክም አንድ አምላክ እንጅ ሌላ የለም፡፡ ከሚሉትም ነገር ባይከለከሉ ከነሱ እነዚያን የካዱትን አሳማሚ ቅጣት በእርግጥ ይነካቸዋል፡፡
➋ ቁርአን 5፡72 እነዚያ «አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው» ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡
➌ ቁርአን 5፡17 እነዚያ አላህ እርሱ የመርየም ልጅ አልመሲሕ ነው ያሉ በእርግጥ ካዱ፡፡
➍ ቁርአን 10፡68-70 «አላህ ልጅን ያዘ (ወለደ)» አሉ፡፡ (ከሚሉት) ጥራት ተገባው፡፡ እርሱ ተብቃቂ ነው፡፡ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የርሱ ነው፡፡ እናንተ ዘንድ በዚህ (በምትሉት) ምንም አስረጅ የላችሁም፡፡ በአላህ ላይ የማታውቁትን ትናገራላችሁን «እነዚያ በአላህ ላይ ውሸትን የሚቀጣጥፉ ፈጽሞ አይድኑም፤» በላቸው፡፡(እነሱ) በቅርቢቱ ዓለም መጠቀም አላቸው፡፡ ከዚያም መመለሻቸው ወደእኛ ነው፡፡ ከዚያም ይክዱ በነበሩት ምክንያት ብርቱን ቅጣት እናቀምሳቸዋለን፡፡
የአሏህ አሐዳዊነት በቁርአን ውስጥ በሙሉ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው ። ነብያትም መልክተኞችም የተላኩበት ዋነኛ ዓለማ ይህንኑ ግብ ለማሳካት ነው ። በመሆኑም አሏህ ተባረከ ወተዓላ የአልመሲሕ ዐለይሂሰላም አምላክነት ወይም የአምላክ ልጅነት ውድቅ እንደሆነ ግልጽ በሆኑ አንቀጾች ገልጾ አስረድቷል ። ክርስቲያኖችንም ሆነ አይሁዶችን ሊያግባባን ወደሚችለው የአንድነት ቃል ኑ! ማለት አሏህን ተባረከ ወተዓላ ብቻ ያለተቀናቃኝ እናምልከው ወደሚለው ጥሪ መጣራት ነው ። ይህ ጥሪ ደግሞ አልመሲሕ ዐለይሂ ሰላም ሰው እንደሆነና የአምልኮ ድርሻ በፍጹም እንደሌለው የሚያረጋግጥ ቃል ነው፡በተጨማሪም ወደ አንድነት ቃል ኑ! ብሎ ቁርአን ለክርስቲያኖች ጥሪ ማቅረቡ ‹‹ በስቀለት እኛም እናምናለን ነገር ግን አሏህን ብቻ እናምልከው ›› የሚል መልክት አልያዘም ። በሌላ አገላለጽ ‹‹ ለስቅለት መከሠት ዕውቅና ሰጥተን እናረጋግጥላችኋለን ብቻ እናንተ በአሏህ እመኑ›› የሚል መልዕክት በውስጡ አልያዘም ። በአጭሩ ከቁርአን በፊት ዒሳ(አሰ) ተስቅሏል ሞቷል ብለዉ ሊያምኑ ይችላሉ ፤ ምንም አስገራሚ ነገር የለዉም ከዒሳ(አሰ) በፊትም ነብያት በህዝቦቻቸዉ የሞትን ፅዋ ቀምሰዋልና የዒሳ(አሰ) በዚህም እምነታቸዉ በይቅርታ ሊታለፍ ይችላል ዋናዉ ነብያቱ ያመጡትን መልዕክት ማደረሳቸዉ እንጂ ! ይህ እምነታቸዉ መሰረታዊዉን የተዉሂድ /የአምላክን አሀዳዊነት/ አይቃወምም ነገር ግን ነብዩ(ሰአወ) ቁርአንን ይዘዉ ከመጡ በኋላ እና ይህ ነገር ስህተት መሆኑን የተረዳ እና መልእክቱ የደረሰዉ ማንኛዉም ሰዉ እንደበፊቶቹ ህዝቦች ዒሳ(አሰ) የአላህ መልእክተኛ ሳይሆን አምላክ ነዉ ወይንም የአምላክ ልጅ ነዉ ወይንም የአምላክ አንድ ሲሶ ነዉ ብሎ የሚያምን ከሆነ ከሃዲ ነዉ፡፡
በመጨረሻም ነጥብ ደግሞ እንደዉ ለመግባባት ያህል ‹‹ ቁርአን ዒሳ(አሰ) ተሰቅሏል ሞቷል ብሎ ›› ያስተምራል ብለን እንበል! - ታዲያ በየትኛዉ የቁርአን ወይንም የሐዲስ አስተምህሮ ነዉ ‹ዒሳ የተሰቀለዉ ለሰዉ ልጆች ሁሉ ሀጢኣት ነዉ › ብሎ የሚያስተምረዉ?
- በየትኛዉስ የቁርአን ወይንም የሐዲስ ዘገባ ነዉ ዒሳ(አሰ) ከሞተ በኋላ ‹‹ በሶስተኛዉ ቀን›› ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ የሚለዉ! እዉን ወገኖቻችን እንደሚሉት አላህ ‹ለክርስትና እምነት › መፈጠር ተጠያቂ የሚሆን ከሆነ ቁርአን ‹ የእየሱስን መሰቀል እና መሞት ብቻ›› ሳይሆን ለሰዉ ልጆች ሀጢአት ብሎ መሰቀሉን እንዲሁም በሶተኛዉ ቀን መነሳቱንም ጭምር መናገር አለበት!
ጳዉሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው ደብዳቤ መሰረት አንደ ሰው በእየሱስ መሰቀል ብቻ ማመኑ ብቻ ‹ክርስቲያን› ሊያስብለዉ እንደማይስችልና መሰቀሉን ከሐጢአት መንፃት ጋር ካላቆራኘ ፤ ስብከቱም እምነቱም ከንቱ እንደሆነ ተናግሯል።
- 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥14 ክርስቶስም #ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው #እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት››
- 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15፥17 ክርስቶስም #ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ #በኃጢአታችሁ #አላችሁ።
በዚህ ጥቅስ መሰረት እየሱስ ከሞት ካልተነሳ ፤ እየሱስ ሀጢአታችንን ሊያስተሰርይ ነዉ የመጣዉ ብሎ ካላመነ እየሱስ መስቀል ላይ ሞቷል ብሎ ብቻ ማመኑ እንደማይጠቅም ያስረዳል፤ አላመንም እያለ ነዉ!!
ሌላኛዉ ተያያዥ ክስ ‹‹ ቁርአን በሱራ 4፡156-159 በዒሳ ቦታ ሌላ ሰው እንዲሰቀል አላህ ሁኔታዎችን ባያመቻችና የሰውየውን መልክ ከዒሳ መልክ ጋር ባያመሳስል ኖሮ ተሰቅሏል የሚል ትምህርት ባልተስፋፋ ነበር፡፡ ታዲያ አላህ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ሕይወት አያሳዝነውምን? የሚል ነዉ፡፡
እንደሚታወቀዉ አንድ ሰዉ ክርስቲያን ነኝ ካለ ቢያንስ ከስር የተቀመጡትን መሰረታዊ ነገሮች ማመን አለበት!
➊እየሱስ በመሰቀል ላይ ሲሞት ዝም ብሎ ሞት አልሞተም ለኛ ‹‹ ሀጢአት› ሲል ነዉ የሞተዉ ብሎ ማመን አለበት
➋እየሱስ ከሞት ተነስቷል ብሎ ማመን አለበት
➌እየሱስ አምላክ ነዉ ብሎ ማመን አለበት
➍እየሱስ የስላሴ አካል ነዉ ብሎ ማመን አለበት
➎በሱ ሞት ከኦሪት ህግ ነፃ ወጥተናል አሁን በህግ ሳይሆን በምህረት የምኖርበት ግዜ ነዉ ብሎ ማመን አለበት!
አንድ ሰዉ አላህ እየሱስ ሲሰቀል ያዩ ሰዎችን አሳሳቷል ብሎ የሚያስብ ከሆነ ከላይ ለተቀመጡ አምስት ነጥቦች ምናልባትም ሁለተኛዉን ነጥብ ሊያምኑ ይችሉ ይሆናል ምክንያቱም ‹ሲሰቀል › ስላዩ ተነስቶ ይሆናል ብለዉ ሊያምኑ ይችላሉና፡፡ ነገር ግን ከ ሁለተኛ ዉጪ ያሉትን ነጥቦች (1፣3፣4 እና 5) በየትኛዉም አይነት አምክኒዮ ሰዎች አላህን ተጠያቂ ሊያደርጉ የሚችሉትበት ምንም መክንያት የለም!!
በርግጥም አላህ እየሱስ ለሰዉ ልጆች ሃጢአት ይሞታል፤ በ3ኛዉም ቀን ይነሳል የሚል ትምህርት አላስተማረ – ወይንም ዒሳ ዐለይሂሰላም አምላክ ነዉ ብሎም አላስተማሪ — ይህ ደግሞ የክረስትናዉ መሰረታዊ ነገር ነዉ ፡፡ እንደ እኛ እምነት ይህን ያስተማሩት ሰዎች ናቸዉ፡፡ ስለዚህ አላህ የሚወቀስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ምናልባትም አንተ/ቺ በግዜዉ ብትኖር/ሪ ይህ ሰዉ የፈጣሪ ሰማእት ነዉ ትል/ይ ይሆናል፡፡ ሰዎች ከዚያ በኋላ በፈጠሩት ነገር (ከሞተ በኋላ ተነስቷል -እሱ የሞተዉ ለሃጢኣትችሁ ነዉ! እራሱም አምላክ ነዉ ፤ የስላሴም አንድ አካል ነዉ ወዘተ…) ብለዉ ያላስተማረዉን ትምህርት በሱ ስም ቢሰብኩ አላህ ሊጠየቅበት የሚችል ምንም አይነት ምክንያት የለም!! ሌሎች ይህን አጋጣሚ ተጠቅመዉ የራሳቸዉን ነገርች በመጨማመር እምነቱን ፈጥረዋል፡፡
ነገር በምሳሌ .. እንደሚባለዉ ነገሩን ግልፅ ለማደረግ ምሳሌ እንጠቀም፡-
አበበ በጓደኛዉ በቀለ ላይ ፕራንክ (ቧልት /ቀልድ) መስራት ፈለገና ለበቀለ ሄዶ ‹‹በቀለ የ10 ሚሊዮን ብር ሎተሪ እንደደረሰዉ›› እንዲያስብ ያደረገዋል! ከዚያም በቀለ በደስታ ብዛት በሚቀጥለዉ ቀን ስራ ይሄድና አለቃዉ ጋር በመጣላት ስራ ይለቃል፤ ወደ ቤቱም ይመልስና ባለቤቱን ከዛሬ ጀምሮ ከአንቺ ጋር አልኖርም ስንት ቆንጆ ቆንጆ ሴት በሞላበት ምን ወጣኝ ይልና ያባርራታል፤ ወደ መኪናዉም ዞር ብሎ ከእንግዲህ በቃ በዚህ አሮጌ መኪና መሄድ ቀረ ዘመናዊ መኪና ስለምገዛ ይልና መኪናዉን ይሰባብራል፤ጓደኛቹን በመጥራት እናንተ መናጢ ድሃዎች ከእንግዲህ ቦታችሁን ፈልጉ እኔ ለናንተ አልመጥናችሁም ብሎ በማቅራራት ጓደኝነታቸዉን ይቆርጥባቸዋል ይህን ሁሉ ካደረገ በኋላ አበበ ያለዉ ነገር ለቀልድ መሆኑን ይደረስበታል በዚህም ስራዉን፤ ባለቤቱን፤ ንብረቱን እና ጓደኛቹን ያጣል!! በቀለ አበበን በተከሰተዉ ሀሉ ጥፋተኛ ያደረገዋል፡፡
☞ ጥያቄዉ፡ በቀለ ለሰራዉ ያንን ሁሉ ጥፋት ተጠያቂዉ አበበ ነዉ ወይንስ እራሱ በቀለ? ሁለት ምላሽ ይኖራል፡-
➊ አበበ ሎተሪ እንዳሸነፈ እንዲያስብ ባያደረገዉ ኖሮ በቀለ ይህንን ሁሉ ጥፋት አይፈፅምም ነበር ስለዚህ በቀለ ለፈፀመዉ ተግባራቶች በሙሉ አበበ ነዉ ጥፋተኛ፡፡
➋ አበበ በመቀለዱ ምክንያት የበቀለን ጥፋቶች አስከትሏል ነገር ግን በቀለ ለፈፀመዉ ጥፋት ሁሉ ግን አበበ መወቀሰ የለበትም ፤ በቀለ ሎተሪ ማሸነፉ የፈፀማቸዉን ድርጊቶች ከተጠያቂነት አያድነቱም! ይህ የሚያሳየዉ በቀለ ዉስጡ ያለዉን መጥፎ ስሜት አጋጣሚዉን ተጠቅሞ ግልፅ መዉጣቱን ያመለክታል እንጂ ፤ ሎተሪ ማሸነፉ በራሱ ወንጀል እንዲሰራ አይገፋፋዉም ፤ በማሸነፉ ምክንያት ግን ተደብቆ የነበረዉ የክፉ ማንነት ባህሪዉን ግለፅ!! በሎተሪዉ ምክንያት ግልፅ ወጣ!! በቀለ ከዚህ ደርጊቱ ዉጪ አማራጭ ነበረዉ! ለግዜዉ በደስታ ሊፈነጥዝ ይችል ነበር ምናልባትም መልሶ ዉሸት መሆኑን ሲያዉቅ ደግሞ ሊናደድ ፤ ከዚህ ዉጪ ያንን ሁሉ ወንጀል ለፈፀምና አበበን የሚችልበት ምንም አይነት ምክንያት ማቅረብ አይችልም!! ማንም ሚዛናዊ የሆነ ሰዉ ሁለተኛዉን መልስ ይመልሳል እንጂ የበቀለን ጥፋት በአበበ አያላክክም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አላህ (ሱወ) ሰዎችን አሳሰስቷል ብለዉ እንኳን ቢያስቡ ሀዋሪያቶቹና በግዜዉ የነበሩ አማኛች ሊሄዱ የሚችሉት ርቀት ነቢዩላህ ዒሳ ዐለይሂሰላም እንደቀደምት ነብያት የአላህ መልእክተኛ ነበር ፤ ነገር በጠላቶቹ እጅ ተገደሎ ሰማአት ሆኖ ሞተ ። ብሎ ያስባል እንጂ ከዚህ መስመር ዘሎ እሱ የሞተዉ ለሐጢአቴ ነዉ! እሱ የአምላክ ልጅ ነዉ! እሱ የስላሴ አካል ነዉ ወዘተ…. ብሎ እንዲያምን የሚገፋፋዉ ምንም አይነት ምክንያት የለም!!
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት –1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


