በኡስታዝ አቡ ሐይደር
አቢ ደርዳእ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈው፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አላህ አደምን በፈጠረው ጊዜ፡ ቀኝ ጀርባውን አበሰው፡፡ ከሱም ልክ እንደ ቀይ ጉንዳን ያነሱ የኾኑ ነጭ ዘሮችን አወጣ፡፡ ከዛም ግራ ትከሻውን አበሰው፡፡ ከሱም ልክ እንደ ፍም የመሰሉ ጥቁር ዘሮችን አወጣ፡፡ ለነዚያም በቀኝ በኩል ለነበሩት፡- ‹‹ወደ ጀነት ሂዱ! ምንም አይገደኝም!››፣ በግራ በኩል ለነበሩት ደግሞ፡- ‹‹ወደ እሳት ሂዱ! ምንም አይገደኝም›› አለ፡፡” (ሙስነድ ኢማሙ አሕመድ 28250)፡፡
የዚህን ሐዲሥ መልእክት በቀጥታ በመረዳት፡ ሃሳቡን ለማግኘት የተቸገሩ (ወይም እውነታውን መረዳት የማይሹ) ሰዎች፡ ጥቁር ሰዎች ለእሳት፣ ነጮች ደግሞ ለጀነት እንደተፈጠሩ ያሳያል ይላሉ፡፡ እውነት እናንተ እንደምትሉት፡ የሐዲሡ መልእክት ጥቁር ዘሮችን ለእሳት፣ ነጮችን ደግሞ ለጀነት እንደታጩ ለመናገር ከኾነ፡ ቀይ የሰው ዘሮችና በዚህ መሐል ሌላ መልክ ያላቸው ሰዎችስ ለምንድነው የተፈጠሩት? ከላይ ባየነው ሐዲሥ መሠረት፡ የአደም ዝርያዎች ነጭና ጥቁር ብቻ ሳይኾኑ፡ ቀይ እንዲሁም ሌላ አይነት መልክ ያላቸውም ጭምር እደኾኑ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሐዲሥ ውስጥ ለምን እነሱ ተዘለሉ? እውነታው ግን፡- በዚህ ሐዲሥ ውስጥ ነጭና ጥቁር የሰው ዘር ተብለው የተጠቀሱት፡ እምነትና ክህደትን በሱ ምሣሌ ለመግለጽ እንጂ፡ ስለ መልክ ለማውራት አይደለም፡፡ ነጭ ብርሃናማ በመኾኑ፡ እምነትና መልካም ሥራ በሱ ይመሰላሉ፡፡ ጥቅር ጨለማ በመኾኑ፡ ክህደትና ኃጢአት በሱ ይመሰላሉ፡፡ ይህንን የሚያስረዳ ምሣሌ ከአላህ ቃል እንመልከት፡-
“ፊቶች የሚያበሩበትን ፊቶችም የሚጠቁሩበትን ቀን (አስታውስ)፡፡ እነዚያ ፊቶቻቸው የጠቆሩትማ «ከእምነታችሁ በኋላ ካዳችሁን? ትክዱት በነበራችሁት ነገር ቅጣቱን ቅመሱ» (ይባላሉ)፡፡እነዚያም ፊቶቻቸው ያበሩትማ በአላህ ችሮታ (ገነት) ውስጥ ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡106-107)፡፡
ይህ የቁርኣን አንቀጽ፡ በትንሳኤው ዓለም ፊቶች እንደሚያበሩና እንደሚጠቁሩ ይነግረናል፡፡ አያይዞም፡- ፊቶቻቸው የሚያበሩት፡ በምድረ ዓለም ሳሉ፡ ነጭ የሰው ዘር የነበሩት ሳይኾኑ፡ በእምነታቸውና በመልካም ሥራዎቻቸው ጌታቸውን ያስደሰቱት እንደኾኑ ይገልጻል፡፡ እነዚያ ፊቶቻቸው የሚጠቁረው ደግሞ፡ በምድረ ዓለም ሳ፡ የጥቁር ዘር የነበሩት ሳይኾኑ፡ በክህደታቸውና በኃጢአታቸው ምክንያት ጌታቸውን ያስቆጡት እንደኾኑ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ ጥቁረትና ንጻትም፡ እምነትንና ክህደትን ለመግለጽ እንደሚመጣ መረዳት ይቻላል፡፡
“ለእነዚያ መልካም ለሠሩት መልካም ነገርና ጭማሪም አላቸው፡፡ ፊቶቻቸውንም ጥቁረትና ውርደት አይሸፍናቸውም፡፡ እነዚያ የገነት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡ ለእነዚያም ኃጢአቶችን ለሠሩት የኃጢኣቲቱ ቅጣት በብጤዋ አለቻቸው፡፡ ውርደትም ትሸፍናቸዋለች፡፡ ለእነሱ ከአላህ (ቅጣት) ጠባቂ የላቸውም፡፡ ፊቶቻቸው ከጨለመ ሌሊት ቁራጮች እንደ ተሸፈኑ ይኾናሉ፡፡ እነዚያ የእሳት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱ በውስጧ ዘለዓለም ነዋሪዎች ናቸው፡፡” (ሱረቱ ዩኑስ 10፡26-27)፡፡
በዚህም አንቀጽ መሠረት፡ አማኞችና መልካም ሰሪዎች፡ ፊቶቻቸውን ጥቁረትና ውርደት እንደማይሸፍቸውና የጀነት ሰዎች መኾናቸውን በመግለጽ፣ ኃጢአተኞችን ደግሞ፡ በጨለመ ለሊት ቁራጭ ፊቶቻቸው እንደሚሸፈኑ ይገልጻል፡፡ ስለዚህ የመዳኑና የመጥፋቱ ጉዳይ፡ ከእምነትና ክህደት ጋር እንጂ፡ ከፊት መጥቆርና መንጻት ጋር እንደማይያያዝ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ የአማኞች ፊት መንጻቱና መብራቱ የእምነታቸው ውጤት ሲኾን፣ የከሀዲያን ፊት መጥቆሩ ደግሞ፡ የክህደታቸውና የኃጢአታቸው ውጤት ነው ማለት ነው፡፡ ከዛ ውጭ በዘር መቅላትም ኾነ መጥቆር በእምነት ላይ የሚያሳድረው ምንም ተጽእኖ የለም!፡፡
“በትንሣኤ ቀንም እነዚያን በአላህ ላይ የዋሹትን ፊቶቻቸው የጠቆሩ ኾነው ታያቸዋለህ፡፡ በገሀነም ውስጥ ለትዕቢተኞች መኖሪያ የለምን?” (ሱረቱ-ዙመር 39፡60)፡፡
በዚህም አንቀጽ ሥር፡ በአላህ ላይ ሲዋሹ የነበሩ አመጸኞች፡ በትንሳኤው ቀን ፊቶቻቸው የጠቆረ ይኾናል በማለት፡ ጥቁረትና ከክህደት ጋር አያይዞ ሲያቀርበው እንጂ፡ ከዘር ጋር ሲያገናኘው አናይም፡፡
የሐዲሡም መልእክት፡ ከአደም ጀርባ የወጡትና የጀነት የተባሉ ነጭ የሰው ዘሮች፡ ነጭ የተሰኙት በእምነታቸው ምክንያት ሲኾን፣ በግራ በኩል የነበሩትና የጀሀነም የተባሉት ጥቁር የሰው ዘሮች ደግሞ፡ ጥቁር የተሰኙት በክህደታቸው ምክንያት ነው ማለት ነው፡፡
ይህንን ጥቁረትና ንጻት፡ መልክን ከመግለጽ ባሻገር፡ ጥሩንና መጥፎን ነገር ለመጠቆም እኛም እንደ ምሣሌ እንጠቀምበታለን፡፡ ለምሣሌ፡- ፊቱ ተበሳጭቶና አዝኖ የምናገኘውን ሰው፡- ‹‹ምነው ዛሬ ፊትህ ጠቆረ?›› ስንለው፣ በልቡ ክፋትንና ተንኮልን ያሰበ ሰውን ደግሞ፡- ‹‹ይህ ሰው ልቡ ጥቁር ው!›› ስንል፡ የፈለግነው መልኩን ለመግለጽ ሳይኾን፡ መጥፎ ገጽታንና ክፉ ሀሳብን እንደያዙ ለማስረዳት ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ፡- ፊቱ ላይ ደስታንና ፈገግታን ያየንበትን ሰው፡ ምንም መልኩ ጥቁር ቢኾንም ‹‹ዛሬ ፊትህ በርቷል!›› ብለን እንናገረዋለን፡፡ የተፈለገው መልክ አይደለምና፡፡ ታዲያ ሐዲሱንስ በቀና መንፈስ ለመረዳት ምን ከለከለን?
ከዚህ ውጭ ጥቁር የሰው ዘሮች፡ በክህደታቸው ሳይኾን በጥቁረታቸው ብቻ፡ እሳት የሚገቡ ቢኾን ኖሮ፡ እንዴት የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሙአዚን የኾነው ሐበሻዊው ቢላል የጀነት ሰው ሊኾን ቻለ?
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዳስተላለፈው፡ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ቢላልን (ረዲየላሁ ዐንሁ) በፈጅር ሶላት ወቅት፡- ቢላል ሆይ! በእስልምና ውስጥ ትልቅ ተስፋ የምታደርግበትን መልካም ሥራህ ምን እንደኾነ ንገረኝ፡፡ እኔ ያንተን የጫማህን እንቅስቃሴ ከፊት ለፊቴ በጀነት ውስጥ ሰምቼአለሁና!›› አሉት፡፡ እሱም፡- ‹‹እኔ ብዙም ተስፋ የማደርግበት መልካም ሥራ የለኝም፡፡ ግን በለሊቱም ኾነ በቀኑ ክፍል ሁሌም ዉዱእ (የትጥበት ስርአት) ባደረግሁ ቁጥር፡ አላህ ያገራልኝን ያህል ሳልሰግድ አልተውም›› አላቸው፡፡ (ቡኻሪይ 1098)፡፡
ዐጣእ ኢብኒ አቢ-ረባሕ (ረሒመሁላህ) እንዲህ አለ፡- ዐብዱላህ ኢብኑ ዐብባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ከጀነት ነዋሪዎች የኾነችን ሴት አላሳይህምን! አለኝ፡፡ እኔም እንዴታ አሳየኝ እንጂ! አልኩት፡፡ እሱም፡- ይህቺ ጥቁር ሴት፡ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ዘንድ መጥታ፡- እኔ አዙሪት በሽታ አለብኝና፡ ስወድቅ ልብሴ ይገለጥብኛል፡፡ እባክዎትን አላህን ይለምኑልኝ! አለች፡፡ መልክተኛውም፡- ከፈለግሽ ታገሺ! በመታገስሽ ጀነት አለሽና!፡፡ ካልኾነም አላህ ጤናሽን እንዲመልሰው ዱዓእ አደርጋለሁ አሏት፡፡ እሷም፡- እሺ እታገሳለሁ! ግን በሚጥለኝ ጊዜ፡ ልብሴ እንዳይገለጥ ዱዓእ ያድርጉልኝ አለች፡፡ እሳቸውም ዱዓእ አደረጉላት፡፡ (ቡኻሪይ 5652)፡፡
በዚህ ሐዲሥ ላይ ገና በሕይወት ሳለች የጀነት እንስት መኾኗ የተመሰከረላት ሴት፡ ጥቁር መኾኗን ልብ ይበሉ፡፡ የመልኳ መጥቆር ጀነት ከመግባት አላገዳትምና፡፡
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንዲህ ይላል፡- መስጂድን የምታነጻ የኾነች አንዲት ጥቁር ሴት ነበረች፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) አጧት፡፡ ስለሷም ሲጠይቁ፡- ሞታለች! በማለት ነገሯቸው፡፡ እሳቸውም፡- አትነግሩኝም ነበርን! አሉ፡፡ እነሱ ግን የሴትየዋን ማንነት አቅለለው ነበር ለመልክተኛው ያልነገሩት፡፡ ከዛም መልክተኛው፡- ቀብሯን አሳዩኝ! አሉ፡፡ ቀብሯ እንደደረሱም፡ ለሷ ዱዓእ አደረጉላት፡፡ እንዲህም አሉ፡- ይህቺ ቀብር በባለቤቷ ላይ በጨለማ የተሞላች ነበረች፡፡ ነገር ግን አላህ በኔ ዱኣእ ሰበብ ለባለቤቷ ያበራላታል›› (ሙስሊም 2259)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


