በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፥ ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
‹‹አላህ አንድ ነው!›› የሚለው መሪ ቃል የእምነታችን ዋና መገለጫ ነው፡፡ የጌታችንን አላህ አሐዳዊነት የሚገልጽ፣ ሁለትዮሽ፡ ሶስትዮሽና የብዜት እምነትንም የሚቃወም አስተምህሮ ነው፡፡
አንድ ሙስሊም ‹‹አላህ አንድ ነው!›› ብሎ አመነ ማለት፡ እሱ አላህ ሁለት ወይም ሶስት ወይም ከዛ በላይ አይደለም ብሎ ተቀበለ ማለት ነው፡፡ በሌላ መልኩ የአላህን ሁለትነት፣ ሶስትነትና ብዜትን አምነው የሚቀበሉ ሰዎችን ተቃወመ፡ በእምነታቸውም ካደ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ከዚህ ሙስሊም የሚፈለገው እምነት ‹‹አላህ አንድ ነው!›› የሚለው እምነት ብቻ ነውን? የአላህ ነቢያትና ሩሱሎችስ የተላኩት፡ አላህ ‹‹አንድ አምላክ›› ነው የሚለውን ትምህርት ብቻ ለማስተማር ነውን? በፍጹም አይደለም!፡፡ ይህ አይነት ንግግር ከአላዋቂዎች አንደበት እንጂ ከማንም አይጠበቅም፡፡ ጉዳዩን በማስረጃ ዘርዝረን እንመልከተው፡-
1ኛ. ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ነቢይ ሆነው የተነሱበት የዐረቡ ማኅበረሰብ ‹ሙሽሪክ› (በአላህ የሚያጋራ) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያን ማኃበረሰብ ሙሽሪክ ያሰኘው ግን በአላህ ላይ ሌሎች አካላትን በማምለኩና፡ ለአላህ ብቻ የሚገባውን የአምልኮ ክፍል ለፍጡራንም አሳልፎ በመስጠቱ ነው፡፡
ታዲያ ‹አላህ አንድ ነው!› ካልን፡ ይህ ብቻ ይበቃል የማለት አዝማሚያ ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎችን የምንጠይቃቸው ጥያቄ፡- እነዚህ ሙሽሪኮች አላህ ሁለት ወይም ሶስት ነው ብለው ያምኑ ነበርን? ሙሽሪክ ያሰኛቸውስ እሱ ነበርን? የሚል ይሆናል፡፡ አይ እንደዛ ብለው አያምኑም ነበር ከተባለ፡ እንግዲያውስ ሙስሊም ለመሰኘት የከለከላቸውና ሙሽሪክ ያደረጋቸው ምንድነው? ብለን በድጋሚ ልንጠይቃቸው ይገባናል፡፡
በአላህ ላይ ማጋራታቸው! የሚል መልስ ከተሰጠን፡ እነሱ እኮ በአላህ አንድነት ያምናሉ፡፡ ያጋሩት በምኑ ላይ ነበር? የሚል ጥያቄ እናስከትላለን፡፡ ያጋሩትማ በአላህ አንድነቱ ላይ ሳይሆን፡ ብቻውን በመመለኩ ላይ ነው ካሉን ደግሞ፡ ስለዚህ አላህ አንድ ነው ብሎ ማመን እና አላህን በብቸኝነት ማምለክ ይለያያሉ ማለት ነው፡፡
እነዚህ ሙሽሪኮች አላህ አንድ አምላክ መሆኑን ብቻ ሳይሆን፡ የሁሉ ነገር ፈጣሪና አስገኚ ጌታ መሆኑንም ያምኑ ነበር፡፡ ከአላህ ጋር አብሮ ዓለማትን የፈጠሩ አሉ ብለው እንኳ አያምኑም፡፡ ቅዱስ ቁርኣን እንዲህ ይመሰክርላቸዋል፡-
“ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ማን እንደ ሆነ ብትጠይቃቸው አላህ ነው፣ ይሉሃል።ከአላህ ሌላ የምትግገዟቸውን (ጣዖታት) አያችሁን? (ነገሩኝ) አላህ በጉዳት ቢፈልገኝ እነሱ ጉዳቱን ገላጮች ናቸውን? ወይስ በችሮታው ቢፈቅደኝ እነርሱ ችሮታውን አዘጋጆች ናቸውን? በላቸው። አላህ በቂዬ ነው፤ በርሱ ላይ ተመኪዎች ይመካሉ፤ በል።” (ሱረቱ-ዙመር 38)፡፡
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ሁለት የተለያዩ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪው፡- እነዚህ ሙሽሪኮች አላህ የሰማያትና ምድር ፈጣሪ መሆኑን አምነው መቀበላቸው፡ መቀበልም ብቻ አይደለም በአንደበታቸው መመስከራቸው ሲሆን፡ ሁለተኛው ደግሞ፡- የአላህን ፈጣሪነት በመሰከሩት አንደበታቸው ጣኦታትንም ያመልኩና ይገዙ እንደነበር ነው፡፡
ስለዚህም የአላህን አንድነት አምኖ ተቀብሎ፡ ግን አላህን ብቻ አለመገዛት ዋጋ የለውም፡፡ ግለሰቡንም ሙስሊም አያደርገውም፡፡ እምነታችን አንድ አምላክና አንድ አምልኮ እንጂ፡ አንድ አምላክ የሚለው ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ የአይሁዶች እምነት ነው፡፡ እነሱ አላህ አንድ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ግን ብቻውን አያመልኩትም፡፡
2ኛ. ቁርኣን እራሱ በሩቡቢያህ (የአላህን ጌትነት አምኖ መቀበል) እና በኡሉሂያህ (አላህን በብቸኝነት መገዛት) መካከል ልዩነት አድርጓል፡፡ ታዲያ እኛ ማን ሆነን ነው ስለ ‹‹ተውሒድ አር-ሩቡቢያህ›› እና ስለ ‹‹ተውሒዱል ኡሉሂያ›› ሲነገረን፡ ይህ አላህን መከፋፈል ነው የምንለው? እስኪ ተከታዮቹን የቁርኣን አንቀጾች እንመልከታቸው፡-
” قُلْ لِمَنِ الْأَرْضُ وَمَنْ فِيهَا إِنْ كُنْتُمْ تَعْلَمُونَ * سَيَقُولُونَ لِلَّهِ قُلْ أَفَلَا تَذَكَّرُونَ * قُلْ مَنْ رَبُّ السَّمَاوَاتِ السَّبْعِ وَرَبُّ الْعَرْشِ الْعَظِيمِ * سَيَقُولُونَ لِلَّهِ قُلْ أَفَلَا تَتَّقُونَ * قُلْ مَنْ بِيَدِهِ مَلَكُوتُ كُلِّ شَيْءٍ وَهُوَ يُجِيرُ وَلَا يُجَارُ عَلَيْهِ إِنْ كُنْتُمْ تَعْلَمُونَ * سَيَقُولُونَ لِلَّهِ قُلْ فَأَنَّى تُسْحَرُونَ ” سورة المؤمنون 89-84
“«ምድርና በውስጥዋ ያለው ሁሉ የማን ነው የምታውቁ ብትኾኑ (ንገሩኝ)» በላቸው፡፡ «በእርግጥ የአላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «ታዲያ አትገሰጹምን» በላቸው፡፡ «የሰባቱ ሰማያት ጌታና የታላቁ ዐርሽ ጌታ ማን ነው» በላቸው፡፡ «በእርግጥ አላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «እንግዲያ አትፈሩትምን» በላቸው፡፡ «የነገሩ ሁሉ ግዛት በእጁ የኾነ እርሱ የሚጠብቅ በእርሱ ላይ የማይጠበቅ ማን ነው የምታውቁ እንደኾናችሁ (መልሱልኝ)» በላቸው፡፡ «በእርግጥ አላህ ነው» ይሉሃል፡፡ «ታዲያ እንዴት ትታለላላችሁ» በላቸው፡፡” (ሱረቱል ሙእሚኑን 84-89)፡፡
በዚህ የቁርኣን አንቀጽ ውስጥ ሙሽሪኮች፡- ምድርና በውስጧ ያለው የአላህ ንብረት መሆኑን፣ እንዲሁም አላህ የዐርሽ፡ የሰማያትና የምድር ጌታቸው (ረብ) መሆኑን መመስከራቸውን እንረዳለን፡፡ በሌላ አንቀጽ ላይ ደግሞ በተቃራኒው እንዲህ እናገኛቸዋለን፡-
” إِنَّهُمْ كَانُوا إِذَا قِيلَ لَهُمْ لَا إِلَهَ إِلَّا اللَّهُ يَسْتَكْبِرُونَ * وَيَقُولُونَ أَئِنَّا لَتَارِكُو آلِهَتِنَا لِشَاعِرٍ مَجْنُونٍ ” سورة الصافات 36-35
“እነርሱ ከአላህ ሌላ አምላክ የለም በተባሉ ጊዜ ይኮሩ ነበሩ። እኛ ለዕብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተዉ ነን? ይሉም ነበር።” (ሱረቱ-ሷፍፋት 35-36)፡፡
ከላይ እንዳየነው አላህ የዐርሽ፡ የሰማያትና የምድር ጌታ መሆኑን የመሰከሩ ሙሽሪኮች፣ ምድርና በውስጧ ያሉ ነገራት በጠቅላላ የአላህ ንብረት መሆናቸውን የመሰከሩ ሙሽሪኮች፣ ነገራትን ሁሉ በግዛቱ አድርጎ ሁሉን የሚጠብቅና የሚቆጣጠር ጌታ አላህ ብቻ መሆኑን የመሰከሩ ሙሽሪኮች፡ አሁን ግን ‹‹ላ ኢላሀ ኢልለሏህ›› በሉ ሲባሉ፡ እምቢ አሉ ኮሩ፡፡ ግን ለምን?
አዎ! መልሱ ቀላል ነው፡፡ የላኢላሀ ኢልለሏህ ትርጉምና መልእክት (ኡሉሂያ) የአላህን ጌትነትና በፍጥረታቱ ላይ የበላይ ተቆጣጣሪ መሆኑን (ሩቡቢያህ) ከመመስከር የሚለይና የሚሰፋ በመሆኑነው፡፡
ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ማለት፡- አምልኮን ለአላህ ብቻ ማድረግን ይጠይቃል፡፡
ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ማለት፡- ከአላህ ውጪ የሚመለኩ ነገራትን በጠቅላላ መካድና ከነሱ መራቅን ይጠይቃል፡፤
ላ ኢላሀ ኢልለሏህ ማለት፡- ከአላህ ውጪ ያሉ አካላትን የሚያመልኩ ሰዎችን ሙሽሪኮች መሆናቸውን በማመን፡ ከነሱ ድርጊት መገለልን (በራእ) እንዲሁም የዲን ጠላት አድርጎ መያዝን ይጠይቃልና፡፡
ለዚህም ነው እነሱ ይህን ምስክርነት መናገር ያልፈለጉት፡፡ በቁርኣኑም ላይ እንዳየነው፡- ‹‹እኛ ለዕብድ ባለቅኔ ብለን አማልክቶቻችንን የምንተዉ ነን?›› ማለታቸው፡ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ የሚለው ምስክርነት የነሱን የሀሰት አምልኮ የሚቃወምና እንዲተው የሚጠይቅ፡ አላህን በብቸኝነት ማምለክን የሚጠይቅ መሆኑን መረዳታቸውን ያሳየናል፡፡
የሰማያትና የምድር ጌታ ማን እንደሆነ መመስከሩ ላይ ግን አላህ ከማለት አልተቆጠቡም፡፡ የአላህን ጌትነት ብቻ (ሩቡቢያህ) መመስከር ሰውን ካለበት ሺርክ አውጥቶ ሙስሊም አያደርገውም ማለት ነው፡፡ የግድ አላህን በህይወት ዘመኑ በብቸኝነት ማምለክም (ኡሉሂያ) ይጠበቅበታል፡፡ ታዲያ ይህ በራሱ በ ‹ሩቡቢያህ› እና ‹ኡሉሂያህ› መካከል የትርጉምና የመልእክት ልዩነት መኖሩን አይጠቁመንምን?
እነዚያ ሙሽሪኮች የተረዱትን የ ላ ኢላሀ ኢልለሏህ መልእክት መረዳት የተሳናቸው ግን (ሩቡቢያውና ኡሉሂያውን) በአንድ ደባልቆ መጥራት እውቀት ይመስላቸዋል፡፡ ወል-ዒያዙ ቢላሂ ሚነል-ጀህል፡፡
3ኛ. በ ‹ሩቡቢያህ› እና በ ‹ኡሉሂያህ› መካከል የትርጉምና የመልእክት ልዩነት መኖሩን በተጨማሪ መረዳት የሚፈልግ ሰው የቃላቶቹን ትርጓሜ ማወቁ ብቻ በቂ ነው፡፡ እንዴት ከተባለም፡-
ሀ. ሩቡቢያህ የአላህ ስራ ነው፡፡ አላህ ረብ (ጌታ) ነው ብለን ስናምን፡- ብቻውን ዓለማትን የፈጠረ፣ ለሁሉም ነገር ህልውና የሰጠ፣ ዓለሙን ብቻውን የሚመራና የሚያስተዳድር፣ ለሁሉም ፍጥረት ሲሳይን የሚለግስ ጌታ ነው ብለን አመንን ማለት ነው፡፡ ይህ በአላህ ስራና ድርጊት ማመን ማለት ነው፡፡
ለ. ኡሉሂያ ግን የኛ ስራ ነው፡፡ ኢላህ ማለት፡- የሚመለክ አምላክ ማለት ነው፡፡ በማን የሚመለክ? ከተባለም፡ በኛ በባሮቹ ተብሎ ይመለሳል፡፡ ስለዚህ ኡሉሂያ፡- አላህን ብቻ መገዛት፣ ከሱ ውጭ ያለን ነገር ሁሉ ከማምለክ መራቅን የሚጠይቅ የባሮች ስራ ነው፡፡
ታዲያ አንድ የአላህ ባሪያ አላህን በስራዎቹ አጋር የሌለው ብቸኛ ፈጣሪና የዓለሙ ንጉስ፣ የፍጥረቱ ጌታና አስተዳዳሪ መሆኑን መስክሮ፡ በራሱ ስራ ግን የሚጠበቅበትን አምልኮ ለአላህ ካልሰጠ፣ ጌታውን በህይወት ዘመኑ ካላመለከ በምኑ ነው ሙስሊም የሚባለው?
4ኛ. የሥላሴ አባዜ፡- በምን መነጽር ቢመለከቱት ነው የተውሒድን ዘርፎች በሶስት ከፍሎ ማስተማሩ ከሥላሴ አስተምህሮ ጋር የተመሳሰለባቸው፡፡ የሥላሴ አስተምህሮ እኮ እንኳን ለነዚህ ወንድሞች ለባለቤቶቹም ሚስጥር የሆነ ነገር ነው፡፡ እናንተ ሚስጥሩ ተገልጾላችሁ ነው ከተውሒድ ክፍያ ጋር የተመሳሰለባችሁ? ወይስ ተውሒዱም እንደ ሥላሴ ሚስጥር ሆኖባችሁ?
ሀ. ሥላሴ የሚያውጠነጥነው በሶስት አካላት ላይ ነው፡፡ እነዚህ አካላትም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ማንነት የሆነ አካል እንዳላቸው በአማኞቹ ዘንድ ይነገራል፡፡ በሥላሴዎችም ዘንድ አንተ፣ እኔ እና እሱ የሚባል ማንነት እንዳለ ይነገራል፡፡
ሶስቱም የተውሒድ ክፍሎች ግን የሚያውጠነጥኑት በአላህ አንድነት ዙሪያ እንጂ በሁለትነት ወይም በሶስትነት አይደለም፡፡
- ተውሒድ-አር-ሩቡቢያህ ማለት፡- አላህ በሚሰራው ስራ ብቸኛ ማድረግ፡ ለስራው ተጋሪን አለማበጀት ማለት ነው፡፡
- ተውሒዱል ኡሉሂያህ ማለት፡- አላህን በባሮቹ ስራ (በአምልኮ) መነጠልና አንድ ማድረግ፡ እሱን ብቻ ማምለክና ከሱ ውጪ ያሉትን አምልኮቶች መራቅ ማለት ነው፡፡
- ተውሒዱል አስማኢ-ወስ-ሲፋት ማለት፡- አላህን በመልካም ስሞቹም ሆነ በውብ ባሕሪያቱ አምሳያ የሌለው፡ ብጤ የማይገኝለት ጌታ መሆኑን አምኖ መቀበል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ከሥላሴ ጋር የተመሳሰለው የቱ ጋር ነው?
ለ. የሥላሴ አካላት የሚባሉት ሶስቱም የግል ስም ያላቸው ናቸው፡፡ በአንዱ ስም ሌላውን መጥራት አይቻልም፡፡ ይህም ስም አባት አብ ሲባል፣ ልጁ ደግሞ ወልድ ይባላል፡፡ ሰራጺው ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ይባላል፡፡ አባትን ወልድ፡ ልጅን መንፈስ ቅዱስ፡ ሰራጺውን ደግሞ አብ ብሎ መጥራት አይቻልም ይባላል፡፡
እዚህ ግን በሶስቱም የተውሒድ ክፍሎች የሚጠራው አንዱ አላህ ብቻ ነው፡፡ ሩቡቢያህ (ጌትነት) የርሱ ብቻ እንደሆነ ሁሉ፡ አምልኮትም (ኡሉሂያ) ለርሱ ብቻ የሚገባ ነው፡፡ ፍጹም አምሳያ አለመኖርም (አስማኡ ወስ-ሲፋት) የአላህ ብቸኛ ባሕሪ ነው፡፡ የታለ መመሳሰሉ ታዲያ?
ሐ. በሥላሴዎች ዘንድ የስራ ክፍፍል አለ፡፡ እሱም፡- የአብ ስራ መውለድ፣ የወልድ ደግሞ መወለድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ደግሞ መስረጽ ነው፡፡
በተውሒድ አስተምህሮ ላይ ግን ምንም የስራ ክፍፍል የለም፡፡ ምኑን ከምን አገናኝተን ነው ተውሒድን በሶስት ዘርፍ ከፍሎ ማስተማሩን ከሥላሴ ጋር የምናመሳስለው? እሱም አልበቃ ብሎ፡- ኡሉሂያ የሚሉት አብን ነው፡፡ ሩቡቢያ የሚሉት ወልድን ነው ማለት ከየት የመጣ ነው? ምነው እንዲህ የሚለው የአላህ ቃል ተረሳ እንዴ፡-
“…سَتُكْتَبُ شَهَادَتُهُمْ وَيُسْأَلُونَ ” سورة الزخروف 19
“…መመስከራቸው በርግጥ ትጻፋለች፤ ይጠየቃሉም።” (ሱረቱ-ዙኽሩፍ 19)፡፡
እኛ አምላክና ፈጣሪ እንዲሁም ጌታ የሆነ አላህ አለን እንጂ፡ አብ ተብሎ የሚጠራ አምላክ የለንም፡፡ አላህ፡- ባሪያና ተገዢ የሆኑ ፍጥረታት ያሉት አምላክ እንጂ ወልድ ተብሎ የሚጠራ ልጅ ያለው አምላክ አይደለም፡፡ ሰው ባላመነው ነገር እንዴት ይከሰሳል?
በመጨረሻም፡- ውድ ወንድሞችና እህቶች እኔንም ጨምሮ በዚህ አንቀጽ ልሰናበታችሁ፡-
” يَا أَيُّهَا الَّذِينَ آمَنُوا اتَّقُوا اللَّهَ وَلْتَنْظُرْ نَفْسٌ مَا قَدَّمَتْ لِغَدٍ وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ خَبِيرٌ بِمَا تَعْمَلُونَ ” سورة الحشر 19
“እላንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ማንኛይቱም ነፍስ ለነገ ያስቀደመችውን ትመልከት፤ አላህንም ፍሩ፤ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጠ ዐዋቂ ነው።” (ሱረቱል ሐሽር 19)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


