በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
“(አላህም) «ኢብሊስ ሆይ! በሁለት እጆቼ (በኃይሌ) ለፈጠርኩት ከመስገድ ምን ከለከለህ? (አሁን) ኮራህን? ወይስ (ፊቱኑ) ከትዕቢተኞቹ ነበርክ?» አለው፡፡” (ሱረቱ ሷድ 38፡75)፡፡
በዚህ አምላካዊ ቃል ላይ ከክርስቲኖች በኩል ሁለት ጥያቄ ተነስቷል፡፡ የመጀመሪያው፡- አንቀጹ አላህ እጆች እንዳሉት የሚናገር ነውና፡ እርሱ አካል እንዳለው በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እናንተ አላህ ማንንም አይመስልም የምትሉት ለምንድነው? የሚል ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ፡- በዚሁ አንቀጽ ላይ ጌታ አላህ ኢብሊስን ‹‹ለፈጠርኩት ከመስገድ ምን ከለከለህ? (አሁን) ኮራህን? ወይስ (ፊቱኑ) ከትዕቢተኞቹ ነበርክ?›› ሲለው፡ አላህ ኢብሊስን እንዲህ ሲጠይቀው ፡ ኢብሊስ ኮርቶ ይሁን ወይም ከትእቢተኞች ኾኖ ሁን አላወቀም ነበር ወይ? የሚል ነው፡፡ ጽሑፍን ላለማርዘም እና አንባቢንም ላለማሰልቸት ሲባል፡ የመጀመሪያውን ዛሬ እንመለከተውና፡ ሌላኛውን ደግሞ በአላህ ፈቃድ በሌላ ቀን እንመለስበታለን ኢንሻአላህ፡፡ ምላሹም እንደሚከተለው ይኾናል፡-
1/ አላህ ፈጣሪ ነው፡፡ ከሱ ውጭ ያለው በጠቅላላ ፍጡር ነው፡፡ በመኾኑም ፈጣሪ አምላካችን አላህ ፍጡራኑን አይመስልም፡፡ ከፍጡራኑም እሱን የሚመስል አንድም የለም፡፡ የአላህ ሥሞችና ባሕሪያት በጠቅላላ መለኮታዊ ሲሆኑ፡ የፍጥረታት ባሕሪ ደግሞ ፍጥረታዊ ናቸው፡፡ መለኮታዊ ባሕሪን ከፍጥረታዊ ባሕሪ ጋር ለማመሳሰል መሞከር በፍጹም አይቻልም፡፡ ክህደትም ነው፡፡ ጌታ አላህ እሱ ፈጽሞ አምሳያ እንደሌለው፡ እኛም ለሱ አምሳያ ማድረግ እንደማይገባን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
“ለአላህም #አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡ አላህ (መሳይ እንደሌለው) ያውቃል፡፡ እናንተ ግን አታውቁም፡፡” (ሱረቱ-ነሕል 16፡74
“(እርሱ) የሰማያትና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና ተገዛው፡፡ እርሱን በመገዛትም ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ #ሞክሼን ታውቃለህን?” (ሱረቱ መርየም 19፡65)፡፡
“ሰማያትንና ምድርን ፈጣሪ ነው፡፡ ከነፍሶቻችሁ ሴቶችን ከቤት እንስሳዎችም ዓይነቶችን (ወንዶችና ሴቶችን) ለእናንተ አደረገላችሁ፡፡ በእርሱ ያበዛችኋል፡፡ #የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡” (ሱረቱ-ሹራ 42፡11)፡፡
“«ለእርሱም አንድም #ብጤ የለውም፡፡»” (ሱረቱል ኢኽላስ 112፡4)::
2/ የሥም መመሳሰል የተሰየመውን ነገር አንድነት አያሳይም፡፡ ፈጣሪ አምላካችን አላህ ከመለኮታዊ ባሕሪያቱ መካከል ማየትና መስማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይህ እውነተኛ አምላክ ያያል፡ ይሰማል፡፡ በመስማቱም ሆነ በማየቱ እንከን የሌለበት የምሉእ ባሕሪ ባለቤት ነው፡፡ ይኸው ጌታ ፍጡራኑንም ሲፈጥራቸው ሰሚ እና ተመልካች አድርጎ ነው የፈጠራቸው፡፡ እነዚህ ፍጡራን ያያሉ ይሰማሉ፡፡ ሆኖም በማየታቸውም ሆነ በመስማታቸው ‹‹ሰሚ›› እና ‹‹ተመልካች›› የሚለውን ሥያሜ አገኙ እንጂ፡ መስሚያ እና መመልከቻን ከለገሣቸው ከጌታቸው አላህ የማየትና የመስማት ባሕሪ ጋር ግን ተመሳሰሉ አይባልም፡፡ ምክንያቱም፡-
ሀ/ እነሱ የሚያዩት በተወሰነ ሜትር ርቀት ያለን ነገር ብቻ ነው፡፡ ያ ነገር ከነሱ በራቀ ቁጥር ከእይታቸው እየተሰወረ (እያነሰ) ይሄድና በመጨረሻም ማየት ወደማይችሉበት ደረጃ ይደርሳሉ!፡፡ ታዲያ በየብስና በባሕር ያሉትን፣ በቀን ብርሀንና በሌሊት ጨለማ የሚመላለሱትን፣ በሰማያት ውስጥና ከአፈር በታች የተሸሸጉትን ፍጡራኑንን በጠቅላላ አንድም ሳይሰወርበት ከሚያየው ጌታ ጋር እንዴት ማመሳሰል ይቻላል?
• እነሱ የሚሰሙት በተወሰነ ሜትር ርቀት ያለውን ድምጽ ብቻ ነው፡፡ ከተወሰነ ሜትር በላይ የመስማት ችሎታቸው ርቆ መሄድ አይችልም፡፡ የፍጡራኑን ድምጽ እና ጥርሪ በጠቅላላ መስማት ከሚችለው ጌታ አላህ ጋር በፍጹም አይመሳሰሉም!!
ለ/ እነሱ በአንድ ጊዜ የሚያዩት ፊት ለፊታቸው ያለውን ብቻ ነው፡፡ ከቀኝ ከግራ፣ ከላይና ከታች፣ ከኃላቸው ያለውንም ነገር ለማየት የአይናቸውን አቅጣጫ ካልቀየሩ በስተቀር፡ ማየት የማይችሉ ደካማ ፍጥረት ናቸው፡፡ ታዲያ ሁሉንም በአንዴ ከሚመለከተው የጌታ አላህ ባሕሪ ጋር እንዴት ማመሳሰል ይቻላል?
• እነሱ የሚሰሙት ውስን ቋንቋን ብቻ ነው፡፡ ከተወሰኑ ቋንቋዎች ውጪ መስማት (መገንዘብ) አይችሉም፡፡ አላህ ግን የቋንቋዎች ሁሉ ፈጣሪ በመሆኑ ሁሉንም የባሪያዎቹን ቋንቋ መስማት የሚችል አምላክ ነው፡፡ በመሆኑም እሱን የሚመስለው የለም፡፡
ሐ/ እነሱ እይታቸው ጌዜያዊና ዘለቄታዊ ዋስትና የሌለው ነው፡፡ በዕድሜ መግፋት (እርጅና ሰበብ) ወይንም በህመም ምክንያት የማየት ኃይሉ እየቀነሰ ይሄድና ወደ መታወር ደረጃ ይደርሳል፡፡ ኃይሉም ሲቀንስ የአይን መነጽር ይታዘዝላቸዋል፡፡ በዕለተ-ሞታቸው ጊዜም አብሯቸው ይሞታል፡፡ ታዲያ በባሕሪው ዘላለማዊ ከሆነው የአላህ እይታ ጋር በምን ይመሳሰላሉ?
• እነሱ በአንድ ጊዜ መስማት የሚችሉት ከአንድ አቅጣጫ የሚመጣን ድምጽ ብቻ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች በተመሳሳይ ሰአት በአንድ አይነት ቋንቋ የሆነ መልእክት ቢያስተላልፉላቸው፡ መስማት የሚችሉት ትኩረት ለሰጡት ለአንዱ አካል ብቻ ነው፡፡ ካልሆነም የሁለቱም ይደበላለቅባቸውና ከጫጫታ ውጭ ምንም እንዳልሰማ ይኾናሉ፡፡ ጌታ አላህ ግን በሰማይና በምድር ያለው ፍጡራኑ በጠቅላላ፡ በተመሳሳይ ሰአት በተለያየ ቋንቋ፡ የተለያየ ሀሳብና ጥያቄ ቢያቀርቡለት ሁሉንም በአንዴ የሚሰማ አምላክ ነው፡፡ እንግዲያውስ በምን ማመሳሰል ይቻላል? የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“አላህ የዚያችን በባሏ (ነገር) የምተከራከርህንና ወደ አላህ የምታሰሙተውን (ሴት) ቃል በእርግጥ ሰማ፡፡ አላህም (በንግግር) መመላለሳችሁን ይሰማል፡፡ አላህ #ሰሚ#ተመልካች ነውና፡፡” (ሱረቱል ሙጃዲላህ 58፡1)፡፡
“እኛ ሰውን (በሕግ ግዳጅ) የምንሞከረው ስንኾን ቅልቅሎች ከኾኑ የፍትወት ጠብታ ፈጠርነው፡፡ #ሰሚ#ተመልካችም አደረግነው፡፡” (ሱረቱል ኢንሳን 76፡2)፡፡
3/ ወደ ሱረቱ ሷድ ስንመለስ በዚህ ሱራ አንቀጽ 75 ላይ ጌታ አላህ አባታችንን አደምን (ዐለይሂ-ሰላም) በሁለት መለኮታዊ እጆቹ እንደፈጠረው ይነግረናል፡፡ ይህ ማለት አላህ ሁለት እጆች እንዳሉት መረዳት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ታዲያ ችግሩ ምንድነው? ብለን ወገኖቻችንን ስንጠይቃቸው፡ እኛም እጅ ስላለን፡ ጌታ አላህም እጆች አሉት ከተባለ፡ እኛን ይመስላል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አካል እንዳለው ተጠቅሷልና ይላሉ፡፡ የኛ መልስም፡-
ሀ/ ምነው ከወንበርና ከጠረጴዛ ተሽሎ መገኘት አቃታቹሳ! ብለን እንወቅሳቸዋለን፡፡ እነሱም፡- ተው እንጂ አትሳደቡን፡ መልስ ካላችሁ መልሱን ብቻ ስጡን! ካሉም፡ እኛ አልሰደብናችሁም እውነታውን ነገርናችሁ እንጂ! እንላቸዋለን፡፡ እውነታውም፡- በቤታችሁ በሚገኘው ጠረጴዛ እግር ሥር መጽሐፍን ወይንም ወንበር ሥር ጫማችሁን እንደምታስቀምጡ የታወቀ ነገር ነው፡፡ ይህ ማለት ጠረጴዛና ወንበር እግር አላቸው ማለት ነው፡፡ እናንተም እግር ስላላችሁ፡ ከቤታችሁ ወንበርና ጠረጴዛ ጋር በነዚህ ሁለት ክፍለ-አካላት ትመሳሰላላችሁ፡ ተሸላችሁም አልተገኛችሁም የምንለው ለዚህ ነው! ብለን እናብራራላቸዋለን፡፡
እነሱም በመቃወም፡- እንዴት ሕያው የሆነና የሚንቀሳቀስን እግር ሙት ከኾነውና ከማይንቀሳቀሰው የጠረጴዛ እግር ታመሳስሉናላችሁ? ካሉን፡ እኛም፡- እንዴት እናንተስ የተፈጠረ የኾነውን እጃችሁን፡ አደምን ከፈጠረና ከሠራ መለኮታዊ እጅ ጋር ማመሳሰል ፈለጋችሁ? እንዴት እናንተ ከደምና ስጋ፡ እንዲሁም ከአጥንትና ቆዳ የተሠራውን እጃችሁን ያልተፈጠረና ያልተሠራ እንዲሁም አምሣያ የሌለው ከሆነው መለኮታዊ እጅ ጋር ማመሳሰል ፈለጋችሁ? እንዴትስ እናንተ ፈራሽና ጠፊ፡ ደካማና አቅመቢስ፡ ከሜትር ቁመት ያልዘለለ የኾነውን እጃችሁን፡ ሰማያትን ከጠቀለለ ምድርን ከጨበጠ፡ ፍጡራኑን በጠቅላላ በመዳፉ ላይ እንደጎመን-ዘር ፍሬ በማድረግ ታላቅነቱን ካሳየው መለኮታዊ እጅ ጋር ታመሳስላላችሁ? ብለን ልንወቅሳቸው ይገባል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፡- ‹‹አል-ኢሽቲራኩ ፊል-ኢስሚ ላየዱሉል ኢሽቲራኩ ፊል-ሙሰማ›› (የሥም መመሳሰል፡ የተሰየመውን ነገር መመሳሰል አይገልጽም) የሚለውን እናስታውሳቸዋለን፡፡ የጌታ አላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችንም የሠሩትን ለነርሱ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች ያሏቸው መኾኑን አብስራቸው፡፡ ከርሷ ከፍሬ (ዓይነት) ሲሳይን በተመገቡ ቁጥር (ፍሬዎችዋ ስለሚመሳሰሉ) «ይህ ያ ከአሁን በፊት የተገመብነው ነው» ይላሉ፡፡ እርሱንም ተመሳሳይ ኾኖ ተሰጡት፡፡ ለነሱም በውስጧ ንጹህ የተደረጉ ሚስቶች አሏቸው፡፡ እነሱም በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡25)፡፡
በዚህ የቁርኣን አንቀጽ ላይ የጀነት ሰዎች (አላህ በራሕመቱ ከነሱ ያድርገን) የጀነትን ጸጋ ሲጠቀሙ፡ ከሷ በተመገቡ ቁጥር‹‹ይህ ከዚህ በፊት (በዱንያ) የተመገብነው ነው እኮ! በማለት ሲገረሙ፡ ጌታ አላህም ‹‹ተመሳሳይ ሆኖ ተሰጣቸው›› በማለት፡ ሲሳዩ ምድር ላይ ከነበረው አንጻር የሥም ወይንም የመልክ መመሳሰል እንጂ፡ የጥፍጥናና የይዘት፡ የመንስኤና የውጤት አንድነት እንደሌላቸው ገለጸ፡፡
ታዋቂው የቅዱስ ቁርኣን ተንታኝና ታላቁ ሶሓባ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐብባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ስለዚህ መመሳሰል ሲገልጹ፡- ‹‹ለይሰ ፊ-ዱንያ ሚነል-ጀንነቲ ሸይኡን ኢልለል-አስማእ›› (በምድራዊ ዓለም ያለው ጸጋ በጀነት ካለው አንጻር ሥሙ እንጂ ሌላ የለም›› በማለት አብራርተዋል፡፡ (ተፍሲሩ-ጠበሪይ፡ ጃሚዑል በያን፡ ሱረቱል በቀራህ ቁ. 525)፡፡
የጀነቱም ሆነ የዱንያው ጸጋ ሁለቱም ፍጥረታዊ እና ግኝት ሆነው ሳለ፡ ግን በሥም እንጂ በሌላ ነገር ፈጽሞ የማይመሳሰሉ ከሆነ፡ እንዴት የፈጣሪ አምላካችንን የአላህን መለኮታዊ ባሕሪያት፡ ፍጥረታዊና ጠፊ ከሆነው ሰዋዊ ባሕሪ ጋር ማመሳሰል እንችላለን? (ሱብሓነሁ ወተዓላ ዐምማ የሲፉሁ-ዟሊሙን)፡፡
4/ እነዚሁ ሰዎች ድጋሚ ጥያቄአቸውን በማስተካከል፡- እኛ ‹‹እጅ›› ሲባል በኛው ሰውነት ላይ ያለው እጅ እንጂ፡ ሌላ ትዝ የሚለን ነገር የለምና፡ እንዴት ሌላ አይነት ነገር ነው ብለን ማሰብ እንችላለን? ካሉ ደግሞ፡-
ሀ/ አይዟችሁ አታስቡ! እንላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እኛ የአላህን ባሕሪያት ምንነትና ይዘት (ከይፊያህ) እንድናሰላስል አልታዘዝንም፡፡ የአላህ ቃልም ሆነ የነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሐዲሥ፡ ስለ አላህ ባሕሪያትና ሥሞች ያስተማሩን፡ ባሕሪያቱን በሚገባ መልእክታቸውን በማወቅ ከአላህ ጋር እንድንተዋወቅ እና በነዚያ ሥሞች፡ አላህን እንድንማጸነው ነው እንጂ፡ የባሕሪያቱን ትክክለኛ ገጽታ ተመራምረን እንድንደርስበት አይደለም፡፡
• አላህ መሐሪ ጌታ መሆኑን የተረዳ ሙስሊም፡ በሠራው ኃጢአት ተስፋ ሳይቆርጥ ቶሎ ጌታውን ምሕረት ይለምናል እንጂ፡ የአላህ ምሕረት ሲባል ምን አይነት ነው ብሎ አይፈላሰፍም፡፡
• አላህ ሰሚ መሆኑን የተረዳ ሙስሊም፡ ስሞታውንና በደሉን በጠቅላላ ወደ አላህ ያደርሳል፡ ከሱም ዘንድ መፍትሄን ይፈልጋል እንጂ፡ የሚሰማው በምኑ ነው? ደግሞስ እንዴት ነው የሚሰማው? ብሎ በጥመት ውስጥ አይዋዥቅም፡፡
• አላህ ተመልካች መሆኑን ያመነ ሙስሊም፡ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው አላህ ያየኛል በማለት አላህን ፈሪ ይኾናል እንጂ፡ የጌታው አስተያየት እንዴት ነው? ብሎ በማይወጣው ባሕር ውስጥ ገብቶ አይዋኝም፡፡
ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ‹‹ ላየጁዙ ቂያሱል ጋኢብ ዐለ-ሻሂድ›› በመሆኑ ነው፡፡ በአይን ያልታየን እና የራቀን ነገር በሚታይ ነገር መመሰል አይቻልምና!!
ለ/ መላእክት ተብለው የሚጠሩ የሰማይ ነዋሪ የኾኑ መንፈሳዊ ፍጥረታት መኖራቸውን እነዚህ ወገኖቻችንም ያምናሉ፡፡ እነዚህ መላእክት ደግሞ ክንፍ እንዳላቸው የታወቀ ነው (ሱረቱ-ፋጢር 35፡1)፡፡ ታዲያ አንድ ሰው ስለ መላእክት ክንፍ መኖር ሲነገረው፡ እነዚህን መላእክት በአይኑ አይቷቸው ስለማያውቅ፡ ክንፍን ግን በበራሪ አእዋፋት ላይ ስለተመለከተው፡ የመላእክት ክንፍ ሲባል በሰማ ቁጥር፡ ወዲያው ትዝ የሚለው የነዚህ በራሪ አእዋፋት ክንፍ ነውና፡ የመላእክትም ክንፍ ከዚህ አይለይም ቢል፡ አባባሉ ትክክል ይሆናልን? አይሆንም ካላችሁ፡ እንግዲያውስ የመላእክት ፈጣሪና አስገኚ የኾነው ጌታ አላህ አደምን በሁለት መለኮታዊ እጆቹ መፍጠሩን በገለጸልን ወቅት፡ እናንተ ‹‹እጅ›› የሚለውን ስላነበባችሁ ብቻ ለምን ከፍጡራን እጅ ጋር ማመሳሰል ፈለጋችሁ ታዲያ? በማለት እንጠይቃቸዋለን፡፡ ምናልባትም አሁን መሳሳታቸው ሊታያቸው ይችላል፡፤ አላህ ወደ እውነቱ ይምራን፡ ይምራቸው፡፡
5/ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ደግሞ ከዚህ የበዛና ግር የሚያሰኙ በሰው አካላት ላይ የሚታዩ አንዳንድ ክፍለ-አካላት በሥም ለእግዚአብሄር ተሰጥተው እናገኛለን፡፡ ይህንንስ ወገኖቻችን እንዴት ነው የሚረዱት? ለምሣሌ፡-
• እግዚአብሄር ራስና ጸጉር አለው (ትንቢተ ኢሳይያስ 59፡17፣ ዳንኤል 7፡9)
• እግዚአብሄር ፊት አለው (መዝሙረ ዳዊት 43፡3)፡፡
• እግዚአብሄር አይንና ቅንድብ አለው (ትንቢተ ዳንኤል 9፡18፣ መዝሙር 11፡4)፡፡
• እግዚአብሄር ጆሮ አለው (ትንቢተ ዳንኤል 9፡18)፡፡
• እግዚአብሄር አፍንጫ አለው (2ኛ ሳሙኤል 22:9) 1980 ቀላል አማርኛ ትርጉም
• እግዚአብሄር ከንፈር አለው (ትንቢተ ኢሳይያስ 30፡27)
• እግዚአብሄር አፍ አለው (2ኛ ሳሙዔል 22፡9)፡፡
• እግዚአብሄር ምላስ አለው (ትንቢተ ኢሳይያስ 30፡27)
• እግዚአብሄር እጅ አለው (ኦሪት ዘጸአት 31፡18)
• እግዚአብሄር እግር አለው (2ኛ ሳሙዔል 22፡10)፡፡
ምናልባትም ከነዚህ ጥቅስ ተነስተው ይሆን አምላክ ሰውን ይመስላል የሚሉት? ለማንኛውም ጌታ አላህ የራሱ የኾኑ መለኮታዊ ባሕሪያት አሉት፡፡ በነዚህ መለኮታዊ ባሕሪያቱ ፍጡራኑን አይመስልም፡፡ አላህ ትክክለኛ ግንዛቤን ይለግሰን፡፤ ወሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላህ
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


