በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን (አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
ክቡራን ወንድሞቼና እህቶቼ! አሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላሂ ወበረካቱሁ፡፡
ከአንድ እህቴ በኩል የቀረበልኝ ሀሳብ ስለሆነ እንጂ መልስ ለመስጠት ብዙም አስቤበት አላውቅም ነበር፡፡ ይሄን ያህልም ሰዎች ለጉዳዩ ቦታ ይሰጡታል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ጉዳዩ እንዲህ ነው፡- ነቢዩ ሙሐመድ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በወቅቱ የነበሩ ሰዎችን እሳቸው ነቢይ እንደሆኑ ለማሳመን፡ ከአፈር ውስጥ ወተት ፈለቀልኝ የሚልን ሀሳብ በልባቸው ይዘው ወተትን በአፈር ውስጥ ይቀብሩታል፡፡ ከዛም ወደ ህዝባቸው ዘንድ በመሄድ ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ! እኔ ትክክለኛ ነቢይ ለመሆኔ ማስረጃ ከፈለጋችሁ፡ ይኸው ከአፈር ውስጥ በተአምር ወተት ሳፈልቅ ኑ ተመልከቱ! በማለት ሰዎቹን ወደ ስፍራው ይዘው ይጓዛሉ፡፡ ውሻ ደግሞ ከሩቅ የማሽተት ተሰጥኦ አለውና በስፍራው ሲደርሱ ውሻው አፈሩን በእግሮቹ ጣት በመታገዝ እየቆፈረው ወተቱን ቀድሞ በማሳየት አጋለጣቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ውሻ በኢስላም የተጠላው የሚል ነው፡፡
ይህንን የወገኖቻችንን ክስ ድሮ ነበር እንደ ተረት የምሰማው፡፡ ዛሬም ያ ያልበሰለ ጭንቅላት ድጋሚ ያነሳዋል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ መብሰሉ ላይቀር ነገር የሰው ከሰል ይጨርሳል ይባላልና ለማንኛውም ጥቂት ነገር እኔም ላክልበት፡-
1ኛ/ እውነት አፈሩ ውስጥ ወተት ከተቀበረ በምን አይነት መልኩ ነው ተመልሶ ሊፈልቅ የሚችለው? አፈሩ አይመጠውም እንዴ? ወይስ በወቅቱ የነበረው የምድር አፈር ፈሳሽ ነገርን መምጠጥ አይችልም ነበር? እንዴት ሆኖ ሊፈልቅ ይችላል?
2ኛ/ አይ በእቃ (ጀሪካንና መሰሎቹ) ላይ ተቀምጦ ነው ከተባለም፡ ታዲያ ምኑ ላይ ነው ተአምሩ? በጀሪካንም ሆነ በማንኛውም ፈሳሽ መያዢያ እቃ ውስጥ ወተት አኑሮ መቅበር ማንም ሰው የሚችለው ተግባር አይደለምን? ወይስ ከጀሪካኑ ስር ወደ ውጭ መፍለቅ ጀመረ ሊባል ነው?
3ኛ/ ደግሞስ አንድ ነቢይ ነኝ የሚል ሰው ከአፈር ወተት አፈልቃለሁ ብሎ ለህዝቦቹ ከተናገረ፡ እዛው እነሱ ያሉበት ስፍራ ላይ ተአምሩን ያሳያል እንጂ፡ ኑ ብሎ ወደሆነ ስፍራ እንዴት ሊወስዳቸው ይችላል? ይህ ለነሱ የሚጠቁመው ነገር አይኖርምን? የነቢይ ተአምር ከአምላኩ ጋር እንጂ ከተወሰነ የመሬት ስፍራ ጋር አይደለም የሚያያዘው፡፡ ህዝቡስ እንዴት ተጎትቶ ሊሄድ ቻለ? ለምንስ ያ ቦታ ብቻ ተመረጠ?
4ኛ/ በጣም የሚገርመው ደግሞ ውሻው ነው፡፡ እንደተባለው በስፍራው ላይ ውሻው ቀድሞ ከተገኘና ይህንን ነገር በማጋለጥ የበኩሉን ከተወጣ፡ ታዲያ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች እንዴት በሳቸው ነቢይነት ሊያምኑ ቻሉ? ወይስ ውሻውን ከማየት ተጋርደው ነበር?
እውነት ወገኖቻችን አስተሳሰባቸው የጤና ነውን? ስብሓነላህ፡፡ በጥላቻ የሰከረ ልብ ምን ያህል የአእምሮን አስተሳሰብ እንደሚገድል ተመልከቱ እንግዲህ፡፡ ለካ ጭንቅላት ለምን ይጠቅማል? ሲባል፡ ኮፊያ ለማስቀመጥ በማለት መልስ የሰጠው ልጄ ‹‹ሀይደር›› እውነቱን ነበር!! ሰው በአእምሮው ካላሰበብትና ነገሮችን ካላመዛዘነበት ምኑን ከእንሰሳ ተለየ? እንግዲውስ ውሻ በኢስላም ለምን ተጠላ? ወደሚለው ጥያቄ በቀጥታ እንግባ፡-
ሀ/ ቅድሚያ ከላይ የቀረበው የካፊሮች ክስ፡ ፍፁም ከእውነታ የራቀ፡ ለህጻናት እንኳ እንደ ተረት ሊነገር የማይገባው ርካሽ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከምን እየቀጣጠፉ እንደሚያቀርቡላቸው ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ከዛ በላይ ደግሞ የነሱ አሜን ብሎ መቀበልና ጭራሽ እኛው ዘንድ ቀርበው ይህን ሀሳብ ለውይይት ማቅረባቸው ምን ያህል (brainwash) እንደተደረጉ አመላካች ነው፡፡ አላህ በእዝነቱ ይድረስላቸው፡፡
ለ/ ውሻ በኢስላም የተጠላ ነው የሚል አንድም ሃይማኖታዊ ማስረጃ፡ ከቅዱስ ቁርኣንም ሆነ ከሐዲሥ ማቅረብ አይችሉም፡፡ ይህም ተራ አሉባልታ ነው፡፡ ኢስላም ውሻን መጥላትን ሳይሆን እያስተማረ ያለው፡ ውሻን ማሳደግን በምን አይነት መልኩ መሆን እንዳለበት በመግለጽና ገደብ በማበጀት ብቻ ነው፡፡ የተፈቀደውም፡-
1/ ለአደን ስራ፡-
ውሻን በማሰልጠን በኢስላም ለመብልነት የተፈቀዱ የእንሰሳት አይነቶችን አድኖ ቢይዝልን እንሰሳው ሐላል ይሆናል፡፡ ስለዚህ ውሻን ለአደን ተግባር መያዝ ይቻላል፡፡ ማስረጃውም ቀጥሎ የሚቀርበው የአላህ ቃልና የመልክተኛው ሐዲሥ ነው፡-
” يَسْأَلُونَكَ مَاذَا أُحِلَّ لَهُمْ قُلْ أُحِلَّ لَكُمُ الطَّيِّبَاتُ وَمَا عَلَّمْتُمْ مِنَ الْجَوَارِحِ مُكَلِّبِينَ تُعَلِّمُونَهُنَّ مِمَّا عَلَّمَكُمُ اللَّهُ فَكُلُوا مِمَّا أَمْسَكْنَ عَلَيْكُمْ وَاذْكُرُوا اسْمَ اللَّهِ عَلَيْهِ وَاتَّقُوا اللَّهَ إِنَّ اللَّهَ سَرِيعُ الْحِسَابِ ” سورة المائدة 4
“ለነርሱ ምን እንደተፈቀደላቸው ይጠይቁሃል፤ በላቸው፦ ለናንተ መልካሞች ሁሉና እነዛ ከአዳኞች አሰልጣኞች ሆናችሁ ያስተማራችኋቸው (ያደኑት) ተፈቀደላችሁ፤ አላህ ካስተማራችሁ ዕውቀት ታስተምሩዋቸዋላችሁ፤ ለናንተም ከያዙላችሁ ነገር ብሉ በርሱም ላይ የአላህን ስም አውሱ አላህንም ፍሩ፤ አላህ ምርመራው ፈጣን ነውና።” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡4)፡፡
በዚህ ትርጉም ውስጥ ‹‹ከአዳኞች›› ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ውሻ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ውሻን ለአደን ተግባር መጠቀም ይቻላል፡፡
عَنْ عَدِيِّ بْنِ حَاتِمٍ رَضِيَ اللَّهُ عَنْهُ، عَنِ النَّبِيِّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ قَالَ: «إِذَا أَرْسَلْتَ كَلْبَكَ وَسَمَّيْتَ فَأَمْسَكَ وَقَتَلَ فَكُلْ، وَإِنْ أَكَلَ فَلاَ تَأْكُلْ، فَإِنَّمَا أَمْسَكَ عَلَى نَفْسِهِ، وَإِذَا خَالَطَ كِلاَبًا، لَمْ يُذْكَرِ اسْمُ اللَّهِ عَلَيْهَا، فَأَمْسَكْنَ وَقَتَلْنَ فَلاَ تَأْكُلْ، فَإِنَّكَ لاَ تَدْرِي أَيُّهَا قَتَلَ… رواه البخاري 5484 ومسلم 5081.
ዐዲይ ኢብኑ አቢ ሓቲም (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “ቢስሚላህ በማለት ለአደን (ያሰለጠንከውን) ውሻህን ብትልክና አድኖ ቢገድለው አንተም ከአደኑ ብላ፡፡ ውሻው ያደነውን መብላት ከጀመረ ግን አትብላ፡፡ እሱ ለራሱ ነው ያደነውና፡፡ ሌሎች የአላህ ስም ሳይወሳባቸው የተላኩ ውሾችን ከተቀላቀለና እነሱ አድነው የገደሉትን ካገኘህ አትብላ፡፡ የትኛው ውሻ እንደገደለው አታውቅምና…” (ቡኻሪይ 5484፣ 5081)፡፡
በቁርኣኑም ሆነ በሐዲሡ መሰረት ለአደን የምንጠቀመው ውሻ ላይ ሁለት ነገር ማሟላት ይኖርብናል ማለት ነው፡፡ ማሰልጠንና ቢስሚላህ ብሎ መላክ፡፡
2/ ለጥበቃ፡-
ሌላው ውሻን ማሳደግ የሚቻልበት መንገድ ከጥበቃ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ ጥበቃ ሲባል ደግሞ፡-
ሀ/ የጓሮ አዝመራን
ለ/ ለቤት እንሰሳዎች
ለ/ መኖሪያ ቤትን፡-
عن أبي هريرة رضي الله عنه أنَّ النَّبيَّ صلى الله عليه وسلم قال: مَنِ اتَّخَذَ كَلْباً إِلاَّ كَلْبَ مَاشِيَةٍ أوْ صَيْدٍ أوْ زَرْعٍ انْتُقِصَ مِنْ أجْرِهِ كُلَّ يَوْمٍ قِيرَاطٌ. رواه مسلم 4111.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ ነቢይ (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) እንዲህ አሉ፡- “ለበግ/ፍየል እረኝነት ወይንም ለአደን ወይንም ለአዝመራ ጥበቃ እንጂ፡ (ከዛ ውጪ ላላ ነገር) ውሻን የያዘ ሰው በየቀኑ ከአጅሩ ላይ ይቀነስበታል” (ሙስሊም 4111)፡፡
ለአደንና ለእረኝነት ውሻን ማሳደጉ የተፈቀደ ከሆነ፡ ለቤት ጥበቃ ደግሞ ከዛም በበለጠ መልኩ የሚፈቀድ መሆኑን ቂያስ በማድረግ ኢማሙ ነወዊይ ረሒመሁላህ (ሸርሑ ሶሒሕ ሙስሊም 10/340) ላይ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ሸይኽ ሙሐመድ ቢን ሷሊሕ አል-ዑሠይሚን (ረሒመሁላህ) ይህን ሀሳብ ደግፈዋል (አል-ኢስላሙ ሱአሉን ወጀዋብ ቁ. 69777)፡፡
ከዚህ ውጪ ዝምብሎ ውሻን ማሳደግ አልተፈቀደም፡፡ ምእራባዊያን የኛ ምሣሌ አይደሉም፡፤ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ ከአላህ መልክተኛ ፍኖትና መንገድ ያፈነገጡ ሰዎች በመሆናቸው ፍጻሜያቸው ከውሻቸው የባሰ ሆኗል፡፡
ሲጀመር ውሻን እንደ ኖርማል በቤት ውስጥ ማሳደግ ጀመሩ፡፡
ቀጥሎም የትም ስፍራ የጉዞ ጓደኛቸው አደረጉት፡፡
ቀጠለና ደግሞ በቤት ውስጥ አብሮ አዳሪ በመሆን አብሯቸው መኖር ጀመረ፡፡ የሟቾቹንም ንብረት በኑዛዜ የውርስ ተካፋያቸው ሆነ፡፡
በመጨረሻም የትዳር አጋር ሆኖ አንሶላ መጋፈፍ ጀመረ፡፡ ያለምንም እፍረት ሰርግ ሰርገውና ድግስ አዘጋጅተው ውሻን የትዳር አጋሬ ነው ብሎ ማግባት መሰልጠን ወይስ መሰይጠን? እነዚህ ናቸው ለኛ አርአያ የሚሆኑት? አልሐምዱ ሊላህ ዓላ ኒዕመቲል ኢስላም፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


