በኡስታዝ አቡ ሀይደር
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
” وَإِنْ مِنْكُمْ إِلَّا وَارِدُهَا كَانَ عَلَى رَبِّكَ حَتْمًا مَقْضِيًّا ” سورة مريم 71
“ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም፤ (መዉረዱም) ጌታህ የፈረደዉ ግዴታ ነዉ።” (ሱረቱ መርየም 19፡71)፡፡
ወገኖቻችን የዚህን አንቀጽ ትክክለኛ መልእክት መረዳት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ትልቅ ስህተት ላይ ወደቁ፡፡ ጭራሹኑ እንዲህ ሲሉም ተደመጡ፡- በዚህ አንቀጽ መሰረት ሙስሊሞች ሁሉ ጀሀነም እንደምትገቡ ይህ አንቀጽ ይናገራል!! ያሳዝናል፡፡
1ኛ/ አንቀጹ እየተናገረ ያለው በጀሀነም ጀርባ ላይ ስለተዘረጋው ድልድይ (ሲራጥ) እንጂ ሌላ አልነበረም፡፡ ደግሞም ‹‹ከናንተ ውስጥ›› የሚለው አጠቃላይ ከሰዎች ማለትን እንጂ፡ በወቅቱ የነበሩትን ወይም ሙስሊሞችን ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ዝርዝር ሀሳቡን በቀጣዩ ይከታተሉ፡፡
2ኛ/ ይህ የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ ትምህርቱን የሚጀምረው ከአንቀጽ 66 ነው፡፡ እኛም ትክክለኛውን ሀሳብና መልእክት ለመረዳት ከዛው ጀምረን አብረን መከታተል ይጠበቅብናል፡፡ አንቀጽ 66 እንዲህ ይነበባል፡-
“ሰውም፣ በሞትኩ ጊዜ ወደፊት ሕያዉ ኾኜ (ከመቃብር) እወጥጣለሁን? ይላል።”
ይህ ‹ሰው› ተብሎ የተገለጸው አካል ከሞት በኋላ ዳግም ህይወት የለም! መቀስቀስ እና በጌታ አላህ ፍርድ ሚዛን ቀርቦ መመርመር የለም! የሚሉትን ከሀዲያን የሚመለከት ነው፡፡ ሙስሊም ከሞት በኋላ ህይወት መኖሩን አበክሮ ያምናልና፡፡ እንደ ቅዱስ ቁርኣንም የውሙል ቂያምን (የትንሳኤውን ዕለት) አስመልክቶ ሰፊ ቦታ በመስጠት በዝርዝር ያስተማረ አንድም መጽሐፍ የለም!!
እንግዲያውስ ሰው ከሞተና፡ አጥንቶቹና ስጋው በስብሰው አፈር ከሆኑ በኋላ በምን አይነት መልኩ ነው ዳግም ወደ ማንነቱ ተመልሶ ህያው ሆኖ ሊቀሰቀስና ከመቃብር ሊወጣ የሚችለው? ለሚለው የከሀዲያን ጥያቄ የጌታችንም መልስ እንዲህ ነበር፡-
“ሰዉ፣ ከአሁን በፊት ምንም ነገር ያልነበረ ሲኾን፣ እኛ የፈጠርነዉ መኾኑን አያስታዉስምን ?” 67
በዚህ መልኩ ትላንት ካልነበረበት ከኢምንት ዓለም፡ በጥበቡና በችሎታው ያስገኘው ጌታ አላህ መሆኑን በመግለጽ፡ ዛሬም ካለበት መቃብር ውስጥ እሱን ማውጣት ቀላል መሆኑን አስረዳ፡፡ እኛ ሰዎች ከመፈጠራችን በፊት የት ነበርን? ህልውናስ ነበረን? እራሳችንን የምንገልጥበት ምን ማንነት ነበረን? ለዚህ ሁሉ ምላሹ ምንም! የሚል ነው፡፡ ታዲያ ካልነበርንበት ዓለም ወደ ህያውነት ዓለም በጥበቡና በችሎታው ካመጣን፡ አሁን ደግሞ ካለንበት የሙታን ዓለም (መቃብር) በኃይሉ ሊቀሰቅስን ምን ይሳነዋል? እያለን ነው፡፡ ከዛም በመቀጠል እነዚህን ከሀዲያንና መሪዎቻቸውን ሰይጣናትን አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡-
“በጌታህ እንምላለን፣ ሰይጣናት ጋር በእርግጥ እንሰበስባቸዋለን፤ ከዚያም በገሀነም ዙሪያ የተንበረከኩ ኾነዉ፤ በእርግጥ እናቀርባቸዋለን።” 68
‹በጌታህ እንምላለን› በማለት አላህ በራሱ ይምላል፡፡ ነቢዩ ሙሐመድም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) ሆኑ ማንኛውም ፍጥረት ከአላህ ውጭ ሌላ ጌታ የለውምና አላህ እራሱን በእሱነት (third person singular) በመግለጽ በጌታህ እንምላለን በማለት ተናገረ፡፡ የመሃላውም ግብ፡- እነዚህን ከሀዲያን ከሰይጣናቶቻቸው ጋር በመሰብሰብ በጉልበታቸው የተንበረኩ ሆነው ወደ ጀሀነም እንደሚያቀርባቸው በአጽንኦት መግለጽ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠልም፡-
“ከዚያም ከየጭፍሮቹ ሁሉ ከነርሱ ያንን (እርሱ) በአልረሕማን ላይ በድፍረት በጣም ብርቱ የኾነዉን እናወጣለን” 69
በማለት፡ ከየግሩፖቻቸው (ጭፍራዎቻቸው) በጌታቸው ትእዛዝ ላይ እጅግ አመጸኛ የነበሩትን መንጥሮና አበጥሮ ያወጣቸዋል፡፡ እጅግ የከፋው ቅጣት ከነሱ ይጀመራል ማለት ነው፡፡ ይቀጥልና፡-
“ከዚያም እኛ እነዚያን እነሱ በርሷ ለመግባት ተገቢ የኾኑትን እናዉቃለን።” 70
በማለት ጀሀነም በመግባት ለእሳት ቅጣት የተገባው ማን እንደሆነ አላህ የበለጠ ዐዋቂ መሆኑን ገለጸ፡፡ ይቀጥልና ደግሞ፡-
“ከእናንተም ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም፤ (መዉረዱም) ጌታህ የፈረደዉ ግዴታ ነዉ።” ይላል፡፡ 71
‹ከእናንተም› ማለቱ አጠቃላይ ሰዎችን እንጂ፡ የተወሰኑትን ከሀዲዎች ወይም አማኝ ሙስሊሞችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ከላይ ክህደታቸውን ሲገልጽልን የነበሩትን ከሀዲዎች ብቻ ቢሆን ኖሮ ‹‹ከእነሱም›› በማለት አያይዞ ይነግረን ነበር፡፡ አሁን ግን እያናገረ ያለው ‹‹ከእናንተም›› በማለት እኛኑ ስለሆነ ሁሉንም ሰው የሚመለከት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ታዲያ ከኛ ምን? ብለን ስንጠይቅ፡ አንቀጹም ‹‹ወደ እርሷ ወራጅ እንጂ አንድም የለም›› በማለት ይመልስልናል፡፡
‹‹ወደ እርሷ ወራጅ›› የሚለውን ቃል በደንብ አስተውሉ፡፡ ወራጅ ማለት፡ አላፊ፡ ተሻጋሪ ማለት እንጂ ገቢ ለማለት አይደለም፡፡ ይህም በጀሀነም ጀርባ ላይ በተዘረጋው ድልድይ (ሲራጥ) ላይ የሚሆን ክስተት ነው፡፡ ሲራጥ ምንነቱን በተመለከተ፡ በሐዲሥ ላይ እንደተነገረን ‹ከሰይፍ የሰላ፡ ከጸጉር የቀጠነ› ድልድይ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ሰው ከአደም (ዐለይሂ-ሰላም) እስከ መጨረሻው ድረስ ያሉት ሁሉ በዚህ ድልድይ ላይ ማለፍና መሄድ ጌታ አላህ የወሰነው ነገር ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹(መዉረዱም) ጌታህ የፈረደዉ ግዴታ ነዉ›› በማለት በቃሉ ገለጠው፡፡ ታዲያ ማን በተሳካ መልኩ ይህን ድልድይ ተሸግሮ ያልፋል? ማንስ ተንከባሎ ወደ ጀሀነም አዘቅት ይወድቃል? ለሚለው ጥያቄ፡ በቀጣዩ አንቀጽ እንዲህ በተብራራ መልኩ ምላሹን እናገኛለን፡-
“ከዚያም እነዚያን የተጠነቀቁትን እናድናለን፤ አመጠኞቹንም የተንበረከኩ ኾነዉ በዉስጧ እንተዋቸዋለን።” 72
አዎ! የአምላካችን አላህ ማዳን ለነዚያ ለጥንቁቆቹ (አላህን ፈሪ ለሆኑት) ነው፡፡ በምድራዊ ህይወቱ በቀጥተኛው እምነት ላይ የጸናና ጌታውን የፈራ ሙስሊም፡ ነጌም በመጨረሻው ዓለም በአላህ ሁሉን ቻይነት የሲራጥን ድልድይ ከሚያልፉትና ከሚድኑት ይሆናል፡፡ (አላህ በራሕመቱ ከነሱ ያድርገን)፡፡ በዛው ተቃራኒ ከአላህ ትእዛዝ የወጡ አመጠኞች ደግሞ የተንበረከኩ ሆነው ወደ ጀሀነም ይወረወራሉ ማለት ነው፡፡ (አላህ ከቁጣው ይጠብቀን)፡፡
ታዲያ ሙስሊሞች ሁሉ ጀሀነም ይገባሉ የሚለው ክስ ማስረጃውና ጭብጡ የታለ?
عَنْ أَبِي هُرَيْرَةَ، رضي الله عنه قَال عن النَّبِيّ صَلَّى اللهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ أنه قَالَ أَنَّهُ لَا يَدْخُلُ الْجَنَّةَ إِلَّا نَفْسٌ مُسْلِمَةٌ، وَأَنَّ اللهَ يُؤَيِّدُ هَذَا الدِّينَ بِالرَّجُلِ الْفَاجِرِ» رواه البخاري ومسلم.
ከአቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደተላለፈው የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “እነሆ ሙስሊም የሆነች ነፍስ እንጂ ሌላው ጀነትን አይገባትም፡፡ አላህ ይህንን ዲን (ሃይማኖት) ከፈለገ በከሀዲያንም ቢሆን ያጠናክረዋል (የበላይ ያደርገዋል)፡፡” (ቡኻሪይ 3062.6528፣ ሙስሊም 552-553)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


