ወሒድ ዑመር
ሃሩን ማን ነው?
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
25፥35 *በእርግጥም ለሙሳ መጽሐፍን ሰጠነው፡፡ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ሃሩንን ረዳት አደረግንለት*፡፡ وَلَقَدْ آتَيْنَا مُوسَى الْكِتَابَ وَجَعَلْنَا مَعَهُ أَخَاهُ هَارُونَ وَزِيرًا
ሚሽነሪዎች፦ ቁርኣን ከባይብል ታሪክ ጋር ይጣረሳል” ብለው ሱሪ ባንገት ሊያስገቡ ሲቃጣቸው ይታያል፣ ከሚተቹበት መወዛገብ አንዱ፦ “ቁርኣን የሙሴን ወንድ አሮንን የኢየሱስ እናት የማርያም ወንድም ያደርጋል” የሚል ግራጫ ውሸት ይዋሻሉ፥ ይለቃሉ። በኢስላም ላይ ስትቀጥፉ ህሊናን ከሚያሳድድ ጥያቄ አታመልጡም።
ታላቁ ኢትዮጵያዊ ባለቅኔው ሎሬትዬ ጸጋዬ ገብረ መድኅን፦ “የሰው ልጅ ከሁለት ነገር ይማራል፦ አንዱ “ሀ” ብሎ “በሳር” ሲሆን ሁለተኛው “ዋ” ብሎ “በአሳር” ነው” ይለናል። ሚሽነሪ ሃያሲ ሂስ ከመስጠት በፊት “ሀ” ብሎ “በሳር” ከቁርኣን መማር አሊያም “ዋ” ብሎ “በአሳር” ተነግሮ ከማያልቅ ታፍሶ ከማይዘለቅ ከዲነል ኢስላም ዕውቀት መማር ነው። መዋተቱና መቃተቱን ትታችሁ ጓዛችሁን ሸክፋችሁ ለመማር ኑ። መቆዘም አያዋጣም። ይህ ነጥብ ምን ያህል እንደተወዛገባችሁ ጥልልና ጥንፍፍ ባለ መልኩ እናያለን፣ “ሃሩን” هَارُونَ ማለት በአማርኛችን “አሮን” ተብሎ በቁርኣን የተጠቀሱ ሁለት የተለያዩ ግለሰቦች አሉ፣ እነርሱም አንዱ የሙሴ ወንድም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የኢየሱስ እናት የማርያም ወንድም፣ ይህን ነጥብ በነጥብ እንመልከተው፦
ነጥብ አንድ
“የሙሳ ወንድም ሃሩን”
ሙሳ አንደበተ ኮልታፋ እና ተብታባ ስለነበር ወንድሙ በእርሱ ፋንታ እንዲናገር ወደ አላህ ዱዓ አደረገ፦
20፥29 «ከቤተሰቦቼም ለእኔ ረዳትን አድርግልኝ፡፡ وَاجْعَل لِّي وَزِيرًا مِّنْ أَهْلِي
20፥30 *«ሃሩንን ወንድሜን*፡፡ هَارُونَ أَخِي
20፥32 *«በነገሬም አጋራው*፡፡ وَأَشْرِكْهُ فِي أَمْرِي
28፥34 *«ወንድሜም ሃሩን እርሱ ምላሱ ከእኔ የተባ ነው፡፡ እውነተኛነቴንም የሚያረጋግጥልኝ ረዳት ኾኖ ከእኔ ጋር ላከው፡፡ እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁና*፡፡» وَأَخِي هَارُونُ هُوَ أَفْصَحُ مِنِّي لِسَانًا فَأَرْسِلْهُ مَعِيَ رِدْءًا يُصَدِّقُنِي ۖ إِنِّي أَخَافُ أَن يُكَذِّبُونِ
ሙሳ መልእክተኛ ነው፤ ሃሩን ደግሞ ነቢይ ነው፤ ነገር ግን “በነገሬም አጋራው” ብሎ በጠየቀው መሰረት ተውራት የተባለውን ሪሳላ ስለተጋራ መልእክተኛ ተባለ፤ “ከእኔ ጋር ላከው” የሚለው ይሰመርበት፤ ለዛ ነው አላህ ተውራትን ለሙሳ እና ለሃሩን ሰጠናቸው ያለው፦
21፥48 *ለሙሳ እና ለሃሩንም እውነትንና ውሸትን የሚለይን ብርሃንንም ለጥንቁቆችም መገሰጫን በእርግጥ ሰጠናቸው*፡፡ وَلَقَدْ آتَيْنَا مُوسَىٰ وَهَارُونَ الْفُرْقَانَ وَضِيَاءً وَذِكْرًا لِّلْمُتَّقِينَ
ሃሩን በራሱ መልእክተኛ አይደለም፤ ግን ነቢይ ሆኖ ሙሳን በመልእክቱ በማስተላለፍ ይረዳዋል፤ አላህ ወደ ሕዝባቸው በተዓምራታችንና በግልጽ አስረጅ ላካቸው፦
19፥53 *ከችሮታችንም ወንድሙን ሃሩንን ነቢይ አድርገን ሰጠነው*፡፡ وَوَهَبْنَا لَهُ مِن رَّحْمَتِنَا أَخَاهُ هَارُونَ نَبِيًّا
25፥35 *በእርግጥም ለሙሳ መጽሐፍን ሰጠነው፡፡ ከእርሱም ጋር ወንድሙን ሃሩንን ረዳት አደረግንለት*፡፡ وَلَقَدْ آتَيْنَا مُوسَى الْكِتَابَ وَجَعَلْنَا مَعَهُ أَخَاهُ هَارُونَ وَزِيرًا
23፥45 *ከዚያም ሙሳንና ወንድሙን ሃሩንን በተዓምራታችንና በግልጽ አስረጅ ላክን*፡፡ ثُمَّ أَرْسَلْنَا مُوسَىٰ وَأَخَاهُ هَارُونَ بِآيَاتِنَا وَسُلْطَانٍ مُّبِينٍ
ስለ ነቢዩ ሃሩን በጥቅሉ ይህንን ይመስላል። የሙሳ እና የሃሩን እናት እና አባት አሊያም የቤተሰብ ዝርዝር ስም ሆነ ማንነት ቁርኣን ላይ አልተጠቀሰም።
ነጥብ ሁለት
“የሃሩን እኅት”
አምላካችን አላህ በዒሣ እናት በመርየም ዘመን የነበሩት የመርየም ዘመዶች የዒሣን እናት መርየምን “የሃሩን እኅት” እንዳሏት ተርኮልናል፦
19፥28 *«የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም፡፡ እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም» አሏት*፡፡ يَا أُخْتَ هَارُونَ مَا كَانَ أَبُوكِ امْرَأَ سَوْءٍ وَمَا كَانَتْ أُمُّكِ بَغِيًّا
“አሏት” የሚለው ይሰመርበት፤ ባዮቹ የመርየም ዘመዶች ቢሆኑም አላህ ይህንን ተርኮልናል። የኢሳን እናት መርየም የአባቷ ስም አፖክራፋ በሆነው በያዕቆብ ወንጌል ውስጥ “ኢያቂም” יְהוֹיָקִים በቁርኣን ደግሞ “ዒምራን” عمران ነው፤ የእናቷ ስም አፖክራፋ በሆነው በያዕቆብ ወንጌል ውስጥ “አና” חַנָּה በተፍሲር ደግሞ “ሐናህ” حنة ነው፣ ኢያቄም የማርያም አባት ስለመሆኑ ከቁርአን ማየት ይቻላል፦
3፥35 *የዒምራን ባለቤት (ሐና)* «ጌታዬ ሆይ! እኔ በሆዴ ውስጥ ያለውን ፅንስ ከሥራ ነጻ የተደረገ ሲኾን ለአንተ ተሳልኩ፡፡ ከእኔም ተቀበል አንተ ሰሚው ዐዋቂው ነህና» ባለች ጊዜ አስታውስ፡፡ إِذْ قَالَتِ امْرَأَتُ عِمْرَانَ رَبِّ إِنِّي نَذَرْتُ لَكَ مَا فِي بَطْنِي مُحَرَّرًا فَتَقَبَّلْ مِنِّي ۖ إِنَّكَ أَنتَ السَّمِيعُ الْعَلِيمُ
66፥12 *የዒምራንን ልጅ መርየምንም ያችን ብልቷን የጠበቀችውን ምሳሌ አደረገ*፡፡ በእርሱም ውስጥ ከመንፈሳችን ነፍፋን፡፡ በጌታዋ ቃላትና በመጻሕፍቱም አረጋገጠች፡፡ ከታዛዦቹም ነበረች፡፡ وَمَرْيَمَ ابْنَتَ عِمْرَانَ الَّتِي أَحْصَنَتْ فَرْجَهَا فَنَفَخْنَا فِيهِ مِن رُّوحِنَا وَصَدَّقَتْ بِكَلِمَاتِ رَبِّهَا وَكُتُبِهِ وَكَانَتْ مِنَ الْقَانِتِين
ቁርኣን ላይ የመርየም እናት ስሟ ባይጠቀስም ማንነቷ ተገልጻል። ነገር ግን ባይብል ላይ የመርየም እናት እና አባት ስም ሆነ ማንነት አልተገለጸም።
ስለዚህ ከመነሻው በሌለ ነገር ሁለት የተለያዩ ታሪካትን አዛብቶ ግጭት መፍጠር አይቻልም፣ ታዲያ የዒሣ እናት የመርየም ወንድም ሃሩን ማነው? ስንል የስም ሞክሼ እንጂ እራሱ የሙሳ ወንድም አይደለም። ይህንን ከነብያችን”ﷺ” መረዳት ይቻላል፦
ኢማም ሙስሊም መጽሐፍ 38, ሐዲስ 13
አል-ሙጊራህ ኢብኑ ሹዕባ እንደተረከው፦ *”ወደ ነጅራን በመጣው ጊዜ የነጅራን ክርስቲያኖች፦”የሃሩን እኅት ሆይ! የሚል ቀርተክልናል፤ ሙሳ ከዒሣ ብዙ ጊዜ በፊት የነበረ ነው” ብለው ጠየቁኝ። እኔም ወደ አላህ መልእክተኛ”ﷺ” ስመለስ ስለዚህ ጉዳይ ጠየኳቸው፣ እሳቸውም አሉ፦ “የድሮ ሰዎች ከራሳቸው በፊት ከነበሩት የነቢያቶች ስሞች ከነቢያቱ ህልፈት በኋላ ይጠቀሙ ነበር*። عَنِ الْمُغِيرَةِ بْنِ شُعْبَةَ، قَالَ لَمَّا قَدِمْتُ نَجْرَانَ سَأَلُونِي فَقَالُوا إِنَّكُمْ تَقْرَءُونَ يَا أُخْتَ هَارُونَ وَمُوسَى قَبْلَ عِيسَى بِكَذَا وَكَذَا . فَلَمَّا قَدِمْتُ عَلَى رَسُولِ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم سَأَلْتُهُ عَنْ ذَلِكَ فَقَالَ “ إِنَّهُمْ كَانُوا يُسَمُّونَ بِأَنْبِيَائِهِمْ وَالصَّالِحِينَ قَبْلَهُمْ
ከነቢያችን”ﷺ” ንግግር የምንረዳው የሙሳ ወንድም ሃሩን እና የዒሣ እናት የመርየም ወንድም ኃሩን የስም መመሳሰል እንጂ እራሱ የሙሳ ወንድም አይደለም። ሁለት የተለያዩ ግለሰቦች ናቸው፣ የእሳቸው ዘመድና ባልደረባም ኢብኑ ዐባሥ”ረ.ዐ.” ይህን አንቀጽ ሲፈስረው፦ “አሮን የማርያም ግማሽ ወንድምና የአባቷ ልጅ ነው” በማለት አስቀምጦታል።
ነጥብ ሦስት
“ኢኽወቱን”
“ኢኽወቱን” إِخْوَةٌ ማለት “ወንድማማች እና እህትማማችነት” ማለት ነው፤ አማኞች ደግሞ ወንድም እና እህት ናቸው፦
49፥10 *ምእመናኖች ወንድማመቾች ናቸው*፡፡ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ፡፡ ይታዘንላችሁም ዘንድ አላህን ፍሩ፡፡ إِنَّمَا الْمُؤْمِنُونَ إِخْوَةٌ فَأَصْلِحُوا بَيْنَ أَخَوَيْكُمْ ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ لَعَلَّكُمْ تُرْحَمُونَ
በነብያችን”ﷺ” ሐዲስ የሙሳ ወንድም እና የመርየም ወንድ ሁለት የስም ሞክሼ መሆኑ ተሰምሮበታል፤ ነገር ግን የሙሳ ወንድም እና የመርየም ወንድ አንድ ማንነት ናቸው ቢባል እንኳን አሁንም ችግር የለውም። ምክንያቱም አማኞች ደግሞ ወንድም እና እህት ናቸው በሚል ቀመርና ስሌት መረዳት ይቻላል።
በትውፊት መርየም የሌዊ ዘር ናት፤ ሃሩንም የሌዊ ዘር ነው፤ ስለዚህ ሁለቱም ወንድምና እህት መሆን ይችላሉ፤ “አኽ” أَخ ማለት “ወንድም” ማለት ሲሆን እና “ኡኽት” أُخْت ማለት ደግሞ “እኅት” ማለት ነው፤ ቃሉ የግድ አብራካዊ ወንድምና እህት ብቻ አያመለክትም። ምክንያቱም “ኡኽት” أُخْت የሚለው ቃል “ሚስል” مِثْل ማለትም “ቢጤ” በሚል ይመጣል፦
43፥48 ከተዓምርም አንዲትንም አናሳያቸውም እርሷ *ከብጤዋ* በጣም የበለጠች ብትኾን እንጅ፡፡ ከክህደታቸው ይመለሱም ዘንድ በቅጣት ያዝናቸው፡፡ وَمَا نُرِيهِم مِّنْ آيَةٍ إِلَّا هِيَ أَكْبَرُ مِنْ أُخْتِهَا ۖ وَأَخَذْنَاهُم بِالْعَذَابِ لَعَلَّهُمْ يَرْجِعُونَ
7፥38 አንዲቱ ሕዝብ ወደ እሳት በገባች ቁጥር ያሳሳተቻትን *ብጤዋን* ትረግማለች፡፡ كُلَّمَا دَخَلَتْ أُمَّةٌ لَّعَنَتْ أُخْتَهَا
“ብጤዋ” ለሚለው የገባውን ቃል “ኡኽቲሃ” أُخْتِهَا አንዳንድ የኢንግሊሽ ትርጉም “እህትዋን”its sister” በማለት አስቀምጠውታል፦
43፥48 And We showed them not a sign except that it was greater than *its sister*, and We seized them with affliction that perhaps they might return [to faith]. Sahih International
ማጠቃለያ
ይህንን እንዲህ በእንዲህ ካየን ዘንዳ በዐረቢኛ “መርየም” مَرْيَم ፣ በዐረማይክ “ማርአም” ܡܪܝܡ ፣ በግሪክ “ማርያ” mαρία ሲሆን የስሙ መሰረት የዕብራይስጡ “ሚሪየም” מִרְיָם ነው፤ “ሚሪየም” מִרְיָם የሁለት ቃላት ውቅር ነው፤ “መር” מר ማለት “ጠብታ” ማለት ሲሆን “የም” ים ደግሞ “ባህር” ማለት ነው፤ በጥቅሉ “ሚሪየም” מִרְיָם ማለት “የባህር ጠብታ” ማለት ነው።
በባይብል ማርያም በሚል ስም የሚጠሩ ሴቶች ስምንት ሲሆኑ እነርሱም፦
1ኛ. የሙሴ እህት፦ ዘጸአት 15፥21
2ኛ. የዕዝራ ልጅ፦ 1ኛ ዜና 4፥17
3ኛ. የኢየሱስ እናት፦ ማቴዎስ 1፥18
4ኛ. መቅደላዊት፦ ሉቃስ 8፥2
5ኛ. የአልዓዛር እህት፦ ዮሐንስ 11፥1
6ኛ. የቀለዮጳም ሚስት፦ ዮሐንስ 19፥25
7ኛ. የማርቆስ እናት፦ 12፥12 እና
8ኛ. የሮሜ ማርያም፦ ሮሜ 16፥6 ናቸው።
የኢየሱስ እናት እህት አላት፤ መርየም ለእናቷ አንድና የስለት ልጅ ብትሆንም በአባቷ ግን ወንድምና እህት እንዳላት ነገረ-ማርያም”Marylogy” ይነግረናል፣ ባይብልም ማርያም እህት እንዳላት ይናገራል፦
ዮሐንስ 19፥25 ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ፦ ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ *የእናቱም እኅት*፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።
በታሪክ፣ በፔንታተች ሆነ በታልሙድ መጻሕፍት የሙሴና የአሮን አባት “እንበረም” עַמְרָם ሲሆን እናታቸው ደግሞ “ዮከብድ” יוֹכֶ֤בֶד ናት፣ ይህን ከራሳችሁ መጽሐፍ ቅሪት ማየት ይቻላል፦
ዘጸአት 6፥20 *እንበረምም עַמְרָם የአጎቱን ልጅ ዮካብድን יוֹכֶ֤בֶד አገባ፥ “አሮንና ሙሴንም” ወለደችለት*፤
ነገር ግን የሙሴ እህት ማርያም እና የኢየሱስ እናት ማርያም ሁለት የተለያዩ ሴቶች ናቸው። ይህ በቀላለ እንድትረዱት አንድ ናሙና ከባይብል ልስጣችሁ፣ “የጌት ሰው ጎልያድን” የገደለው ማን ነው ዳዊት ወይስ ይሽቢብኖብ?
እዚህ አንቀጽ ላይ የጌት ሰው ጎልያድን ዳዊት እንደገደለው ይናገራል፦
1ኛ ሳሙኤል 17፥4 ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር *የጌት ሰው ጎልያድ*፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ዋነኛ ጀግና መጣ።
1ኛ ሳሙኤል 17፥50 *ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ*፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም።
እዚህ አንቀጽ ላይ ደግሞ የጌት ሰው ጎልያድን ይሽቢብኖብ እንደገደለው ይናገራል፦
2ኛ ሳሙኤል 21፥19 ደግሞም በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፤ የቤተ ልሔማዊውም የየዓሬኦርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን *የጌት ሰው ጎልያድን* ገደለ።
አንዱን ክርስቲያን ተወያይ ይህን ጥያቄ ሳቀርብለት “ወሒድ ምን ነካህ ደህና ሰው አልነበርክም እንዴ? ዳዊት የገደለው ጎልያድ እና ይሽቢብኖብ የገደለው ጎልያድ እኮ በተለያየ ዘመን የኖሩ ሁለት ግለሰቦች ናቸው” አለኝ፣ እውነት ነው የአይሁድ ሆነ የክርስቲያን ስመ-ጥርና ዝነኛ ኮሜንታተሮች በተለያዩ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ግን በአንድ ቦታ በጌት ይኖሩ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን አስቀምጠዋል፣ ታዲያ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ነው ነገሩ፣ በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም ይሉሃል እንደዚህ ነው።
ሲቀጥል ወንድምና እህት የግድ የአብራክ ክፋይ የሚለውን አያሲዝም። ሉጥ የኢብራሂም የወንድሙ ልጅ ሲሆን ኢብራሂም ለሉጥ ደግሞ አጎት ነው፣ ነገር ግን ሉጥ ለኢብራሂም ወንድም ተብሏል፣ ያ ማለት የአንድ ቤተሰብ መሆንን ካሳየ የሙሳ ወንድም አሮንና መርየም የሌዊ ቤተሰብ ስለሆኑ ወንድም አሊያም እህት ቢባሉ ችግር የለውም፦
ዘፍጥረት14፥12 በሰዶም ይኖር የነበረውን *የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥን* ደግሞ ከብቱንም ወስደው ሄዱ።
ዘፍጥረት14፥14 አብራምም *ወንድሙ* እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ በቤቱ የተወለዱትን ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብላቴኖቹን አሰለፈ፥ ፍለጋቸውንም ተከትሎ እስከ ዳን ድረስ ሄደ።
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


