በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ሥም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምሥጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን(አል-ፋቲሓ 2)፡፡ የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56) ለመላው የአላህ መልክተኞች (አል-ሷፍፋት 181) የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
እኛ የአላህ ባሮች የሆንን ሰዎች፡ አላህ ሲፈጥረን ኃጢአተኛ አድርጎ አልፈጠረንም፡፡ ኃጢአት የሌለበት ፍጹምና ንጹህ ኾነን ነው የተፈጠርነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችን አደምና ሐዋእም (ዐለይሂማ-ሰላም) ሲፈጠሩ ንጹሀን ነበሩ፡፡ ስህተት የተጀመረው በቀንደኛው ጠላታችን ኢብሊስ አሳሳችነትና ጎትጓችነት በጀነት ውስጥ አትቅረቡ! የተባሉትን ዛፍ በመቅረባቸውና ከዛፉም ወስደው በመብላታቸው ነው፡፡ ይህ አለፍጽምና አደምና ሐዋእ በምርጫቸው ያመጡት እንጂ፡ በውርስ ወይንም በተፈጥሮ የተቀበሉት ባሕሪ አይደለም፡፡
በወቅቱ ሸይጧንን ማውገዝና የጌታቸውን ትእዛዝ በማስታወስ ከዛፉ ለመራቅም መብቱና ፈቃዱ ነበራቸው፡፡ ግን ሁሌም ህያው ሆኖ የመኖር ምኞት በውስጣቸው አደረ፡፡ ይህ ምኞትም የተከለከሉትን ዛፍ እንዲቀርቡ አደረገ፡፡ ኃጢአት በሰዎች ውስጥ ሀ ብሎ ጀመረ፡፡ ጌታ አላህም ወቀሳቸው፡፡ ከዚህች ዛፍ እንዳትቀርቡ ብዬ አልከለከልኳችሁምን? ሸይጧንስ ለናንተ ግልጽ ጠላት ነውና ተጠንቀቁት አላልኳችሁምን? አላቸው፡፡ ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
“በማታለልም አዋረዳቸው፤ ከዛፊቱም በቀመሱ ጊዜ እፍረተ ገላቸው ለሁለቱም ተገለጠችላቸው፤ ከገነት ቅጠልም በላያቸው ላይ ይደርቱ ጀመር፤ ጌታቸውም ከዚቻችሁ ዛፍ አልከለከልኋችሁምን? ሰይጣንም ለናንተ ግልጽ ጠላት ነው አላልኩዋችሁምን? ሲል ጠራቸው።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡22)፡፡
ታዲያ የአደምና ሐዋእም ምላሽ ምን ነበር? ጌታችን ሆይ! እኛ አንተ ከከለከልከን ዛፍ ወስደን የበላነው፡ አስቀድመህ እንድንበላው ስለጻፍክብን ነው የሚል ነበርን? በፍፁም አይደለም! ለስህተታቸው ቀደርን (ቅድመ ውሳኔን) አላሳበቡም፡፡ ምክንያቱም ቅድመ ውሳኔ ከሰው ዕውቀት ውጪ የሆነ መለኮታዊ አሰራር ነው፡፡ ማንም የአላህን ቀዳማይ ዕውቀት ሊያውቅ አይችልም፡፡ ለሚሰራው ጥፋትም በቀደር ማሳበብ አያስኬደውም፡፡ ታዲያ እነዚህ መልካም ወላጆቻችን በወቅቱ ያደረጉት ነገር፡ ጥፋታቸውን በትኩሱ አምነውና ተጸጽተው፡ እራሳቸውን እንደ በደለኛ ቆጥረው፡- ጌታችን አላህ ሆይ! እኛ ነፍሳችንን በድለናልና እባክህ ምሕረትህን አውርድልን፡፡ ካልሆነ እንከስራለንና የሚል ተማጽኖ ነበር፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
“ጌታችን ሆይ! ነፍሶቻችንን በደልን፤ ለኛ ባትምር ባታዝንልም በእርግጥ ከከሳሪዎቹ እንሆናለን አሉ።” (ሱረቱል አዕራፍ 7፡23)፡፡
ምሕረቱ ጥንታዊ የሆነው አምላክ አላህም፡- አልምርም! አላላቸውም፡፡ ወይንም ከልጅ ልጆቻችሁ ተወልጄ፡ አድናችኋለሁ ልጄቼ! ብሎም ቃል አልገባላቸውም፡፡ መለኮታዊ ባሕሪውን ሳይቀይር የባሮቹን ጥፋት መማርና በይቅርታ ማለፍ የሚችል አምላክ በመሆኑ ምሕረትን አደረገላቸው፡፡ የሱ ምሕረት የዛሬ 2018 ዓመት ሳይሆን የጀመረው፡ ከዘመናት በፊት ጥንትም ከራሱ ጋር ያለ ባሕሪ ነውና፡፡
“አደምም ከጌታው ቃላትን ተቀበለ፡፡ በርሱ ላይም (ጌታው ጸጸትን በመቀበል) ተመለሰለት፤ እነሆ እርሱ ጸጸትን ተቀባይ አዛኝ ነውና፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 37፣ ሱረቱ ጣሀ 122)፡፡
ከዚህ ምሕረት በኋላ የሆነው ነገር፡ ቀድሞውኑ አላህ በወሰነውና ባቀደው ፕሮግራሙ የአላህን ህግና መመሪያ ተቀብለው ወደ ምድር እንዲወርዱና እስከ ዕለተ-ሞታቸው ድረስ ከነ-ልጆቻቸው ጋር አላህን እያመለኩ እንዲኖሩ ሆነ፡፡ አላህ መጀመሪያውኑ ለመላእክት፡ ይህን ሰው የተባለውን ፍጡር በምድር ላይ ምትክ (አንዱ በሞተ ቁጥር ሌላው የሚተካ) እንደሚያደርገው አሳውቋቸው ነበርና፡-
“(ሙሐመድ ሆይ) ጌታህ ለመላእክት፡- «እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ፤» ባለ ጊዜ (የኾነውን አስታውስ፤ እነርሱም) «እኛ ከማመስገን ጋር የምናጠራህ ላንተም የምንቀድስ ስንኾን በርሷ ውስጥ የሚያጠፋንና ደሞችንም የሚያፈስን ታደርጋለህን?» አሉ፡፡ (አላህ) «እኔ የማታውቁትን ነገር አውቃለሁ» አላቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡30)፡፡
በዚህ ቀዳማይ ዕውቀትና መለኮታዊ ውሳኔ መሰረት ወደ ምድር እንዲወርዱና በርሷም ውስጥ የአላህን መመሪያ እየተከተሉ እንዲኖሩ ተደረጉ፡-
“«ሁላችሁም ኾናችሁ ከርሷ ውረዱ፡፡ ከኔም የኾነ መመሪያ ቢመጣላችሁ ወዲያውኑ መመሪያዬን የተከተለ ሰው በነሱ ላይ ፍርሃት የለባቸውም፤ እነሱም አያዝኑም» አልናቸው፡፡” (ሱረቱል በቀራህ 2፡38)፡፡
ይህ ነው ኢስላማዊው አስተምህሮና አምላካዊው እውነታ! ይህን እውነት በአግባቡ ያልተረዱ ወገኖች ግን፡ አደም ከሙሳ (ዐለይሂማ-ሰላም) ጋር ባደረጉት ክርክር (የቃላት ምልልስ) ላይ፡ ጀነት ውስጥ የተከለከለውን ዛፍ እንዲቀርብና ከዛፉም ወስዶ እንዲበላ አላህ ቀድሞ የጻፈበትና የወሰነበት መሆኑን በመጥቀስ፡ እኔ ልወቀስ አይገባኝም ማለቱን፡ በዚህም ሰበብ ሙሳን እንደረታውና እንዳሸነፈው በሐዲሥ ተጠቅሷል የሚል የተንሸዋረረ ምልከታን ያቀርባል፡፡ ይህን ነጥብ ከዚህ በፊትም መልስ ሰጥቼበት ነበር፡፡ ምናልባትም ያላነበቡት ሌሎች ወንድሞችና እህቶችም ካሉ ይጠቀሙበት ዘንድ ዛሬም መልሱን እደግመዋለሁ፡-
عن أبي هريرة قال قال رسول الله صلى الله عليه وسلم: “احتج آدم وموسى فقال موسى يا آدم أنت أبونا خيبتنا وأخرجتنا من الجنة فقال له آدم أنت موسى اصطفاك الله بكلامه وخط لك التوراة بيده أتلومني على أمر قدره الله علي قبل أن يخلقني بأربعين سنة فقال النبي صلى الله عليه وسلم فحج آدم موسى فحج آدم موسى فحج آدم موسى” رواه البخاري وأبو داود.
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ባስተላለፈው ሐዲሥ የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- “አደምና ሙሳ (ዐለይሂማ-ሰላም) ተከራከሩ፡፡ ሙሳም፡- አደም ሆይ! አንተ አባታችን ነህ፡፡ አዋረድከን ከጀነትም አስወጣኸን አለው፡፡ አደምም፡- ሙሳ ሆይ! አላህ አንተን በቀጥታ በማናገሩ መርጦሀል፡፡ ተውራትንም በመለኮታዊ እጁ ጽፎ ሰጥቶሀል፡፡ ታዲያ አላህ እኔን ከመፍጠሩ ከአርባ ዓመት በፊት ቀድሞ በወሰነብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን? አለው፡፡ ነቢያችንም (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) አደም ሙሳን ረታው (አሸነፈው)፣ አደም ሙሳን ረታው፣ አደም ሙሳን ረታው አሉ” (ቡኻሪይ፣ አቡ ዳዉድ)፡፡
ይህን ሐዲሥ ቡኻሪና ሙስሊም እንዲሁም አቡ ዳዉድና ሌሎች የሐዲሥ መዛግብት በውስጣቸው ያሰፈሩት የሆነ ታላቅ ሐዲሥ ነው፡፡ መልእክቱንም በደንብ ላስተዋለው ሰው በውስጡ፡- ለሚሰራ ጥፋት ቀደርን (ቅድመ ውሳኔን) ማሳበብ ይበቃል የሚል ሽታም እንኳ አያገኝበትም፡፡ እንዴት የሚባል ከሆነም ማብራሪያውን ቀጥለን እንየው፡-
1ኛ. በሙሳና በአደም (ዐለይሂማ-ሰላም) መካከል የተካሄደው ክርክር ከጀነት መውጣትን የተመለከተ እንጂ፡ በጀነት ውስጥ ከተከለከሉት ዛፍ ስለመብላት አልነበረም፡፡ ሙሳም አደምን፡- አንተንም እኛንም ለምን ከጀነት አስወጣኸን? በማለት ጠየቀው እንጂ፡ ከተከለከልከው ከዛፍ ፍሬ ወስደህ ለምን በላህ? አላለውም፡፡ አደም በጀነት እያለ ከተከለከለው የዛፍ ፍሬ ወስዶ መብላቱ ‹መዕሲያህ› (አመጽ) ሲሆን፡ ከጀነት መውጣቱ ደግሞ ‹ሙሲባህ› (ከአላህ የሆነ መከራ፡ ፈተና) ነው፡፡ ውይይቱ የሚያተኩረው ሙሲባው ላይ ነው፡፡
2ኛ. አደም በጀነት እያለ ለፈጸመው አመጽ (መዕሲያህ) በቀደር ሳይሆን ያሳበበው፡ እራሱን በመውቀስ የጌታውንም ምሕረት በመሻት ከባለቤቱ ጋር ተውበት ገብቷል፡፡ አላህም ይቅር ብሏቸዋል፡፡ የኃጢአት ምሕረትንም አግኝተዋል፡፡ ‹አት-ታኢቡ ሚነ-ዘንቢ ከመን-ላ ዘንበ ለህ› (ከኃጢአት በተውበት የሚመለስ ኃጢአት እንደሌለበት ነውና) አደምም ተውበት ባደረገበት ጥፋት ሊወቀስ አይገባም፡፡ ሙሳም (ዐለይሂ ሰላም) ይህን ነገር ጠንቅቆ ያውቃልና ‹ሊማዛ አከልተ ሚነ-ሸጀራህ?› (ከዛፊቷ ወስደህ ለምን በላህ?) በማለት ወቀሳን አላቀረበም፡፡ ያቀረበው ወቀሳ ‹ሊማዛ አኽረጅተና ወነፍሰከ ሚነል-ጀንናህ?› (ለምን እራስህንም እኛንም ከጀነት አስወጣኸን?) ነበር ያለው፡፡ የአደም ከጀነት መውጣት ደግሞ ሙሲባህ ነው፡፡ ሙሲባህ (መከራንና ፈተናን) ደግሞ ሰው በገዛ ፈቃዱ ፈልጎና አቅዶ የሚያመጣው ነገር ባለመሆኑ፡ አደምም፡- ሙሳ ሆይ! አላህ እኔን ከመፍጠሩ ከአርባ ዓመት በፊት ቀድሞ በወሰነብኝ ነገር ትወቅሰኛለህን? በማለት በቀደር በማሳበብ መለሰለት፡፡ ነቢያችንም (ዐለይሂ ሶላቱ ወስ-ሰላም) አደም ሙሳን ረታው በማለት የንግግሩን እውነተኝነት አጸደቁለት፡፡
3ኛ. ሙሲባህ ከአላህ ዘንድ የሚመጣ ነው፡፡ ሰበቡ የሰዎች ኃጢአት መብዛት ሊሆን ይችላል (አን-ኒሳእ 4፡79)፡፡ ወይንም አላህ ባሪያዎቹን ለመፈተን የሚያደርገው ሊሆን ይችላል (አል-በቀራህ 2፡155-156)፡፡ በሁለቱም መንገድ ብናየው እንኳ ሰው በሚደርስበት ሙሲባህ ሳይሆን የሚወቀሰው፡ በሰራው ኃጢአት ነው የሚወቀሰው፡፡ ምክንያቱም ኃጢአቱ ላይ የገዛ ፈቃዱ ስለታከለበትና ፈልጎ ስለሰራው ሲሆን፡ ሙሲባውን ግን ፈልጎ ያመጣው ነገር ስላልሆነ ነው፡፡ አደምና ሐዋእም (ዐለይሂማ-ሰላም) ከዛፊቷ ወስደው ሲበሉ፡ በሸይጧን አሳሳችነት ሁሌም ህያው የሚሆኑ መስሏቸው እንጂ ከጀነት ለመውጣት አቅደው አይደለም፡፡ ለፈጸሙት ጥፋት ተውበት አደረጉ፡፡ አላህም ማራቸው፡፡ ቀድሞ በተወሰነው መሰረት ደግሞ ከጀነት እንዲወጡና በምድር ላይ እንዲኖሩ ተደረጉ፡፡ አላህ አስቀድሞውኑ ሰውን ሳይፈጥር በፊት ለመላእክት፡- እኔ በምድር ላይ ምትክን አድራጊ ነኝ! ብሎ አሳወቃቸው እንጂ፡ በጀነት ላይ አደርጋለሁ አላለም (አል-በቀራህ 2፡30)፡፡
4ኛ. ሁኔታውን ግልጽ ለማድረግ አንድ ምሳሌ እንመልከት፡- ወደ ሌላ ከተማ ለመሄድ ጓዝህን ጠቅልለህ እየተሳፈርክ ሳለ፡ በጉዞህ ላይ የመኪና መገልበጥ አደጋ ቢደርስብህና በሰውነትህ ላይ ጉዳት ቢደርስብህ፡ ቤተሰቦችህ፡- ለምን ወደዚያ ከተማ አቀናህ? እቤት አርፈህ ብትቀመጥ ኖሮ ይህ ሁሉ ጉዳት ሊደርስብህ አይችልም ነበር! በማለት አንተን መውቀስ ይችላሉን? በፍጹም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም፡- አንተ ወደ ከተማው ያቀናኸው ለጉዳይ እንጂ ሰውነትህን አደጋ ላይ ለመጣል አይደለም፡፡ እሱ በመንገድ እያለህ ካንተ ፈቃድ ውጪ ሆኖ የተከሰተ የአላህ ቀደር ነው፡፡ ስለዚህ አንተ ልትወቀስበት አይገባም፡፡ አደምና ሐዋእም ለምን ከጀነት ወጣችሁ? ተብለው እንዳይወቀሱ፡ መች ከጀነት እንውጣ ብለው ከዛፊቷ በሉ? የሚል ጥያቄ ይነሳልና፡፡
5ኛ. እኛም ከዚህ ሐዲሥ የምንወስደው ትምህርት፡- ኃጢአት በሰራን ጊዜ በቀደር ከማሳበብ ይልቅ እንደ ሁለቱ ወላጆቻችን በፍጥነት ተውበት መግባትንና፡ የሆነ ሙሲባ በሚደርስብን ጌዜ ደግሞ ‹‹ቀደረላሁ ወማ ሻአ ፈዐል›› (አላህ ወሰነ እሱ የሻውን ሰራ!) በማለት ቀደርን መጠቀም እንዳለብን ነው፡፡ አላህ የበለጠውን ዐዋቂ ነው፡፡
ይህ ነው እውነታው! እነዚህ ወገኖቻችን ግን ከቅዱስ ቁርኣንም ሆነ ከሐዲሥ ዕውቀት ጡሀራ ስለሆኑና፡ ከመጽሐፍ ወይም ከሆነ ነገር ያገኘትን ብቻ የሚለጥፉ ግልባጭ ስለሆኑ፡ ከህመማቸው እስኪያገግሙ ዱዓ ማድረግ ነው፡፡ ወሰላሙ ዐለይኩም ወራሕመቱላህ
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


