በኡስታዝ አቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት ይሁን፡፡
“…وَأُنَبِّئُكُمْ بِمَا تَأْكُلُونَ وَمَا تَدَّخِرُونَ فِي بُيُوتِكُمْ إِنَّ فِي ذَلِكَ لَآيَةً لَكُمْ إِنْ كُنْتُمْ مُؤْمِنِينَ” سورة آل عمران 49
“…የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ የምታምኑ እንደሆናችሁ ለእናንተ በዚህ ዉስጥ በእርግጥ ታምር አለበት” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 49)፡፡
ከወገኖቻችን ዘንድ ይህን የቅዱስ ቁርኣን አንቀጽ መሰረት በማድረግ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሁሉን እንደሚያውቅ መረዳት ይቻላል የሚል ድምጽ ይሰማል፡፡ ይህ ግን ፍፁም የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ እንዴት ካሉም፡-
1ኛ/ ሁሉን ዐዋቂነት የጌታ አላህ ብቸኛ መለኮታዊ ባህሪው ነው፡፡ ይህን አምላካዊ ባህሪ ማንም ሊጋራው አይችልም፡፡ “አል-ዐሊም፣ አል-ዐልላም፣ አል-ኸቢር” በሚባሉ መለኮታዊ ስሞቹም የሚታወቀው እሱ ብቻ ነውና፡፡ የአላህ ቃል እንዲህ ይላል፡-
” قُلْ لَا يَعْلَمُ مَنْ فِي السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ الْغَيْبَ إِلَّا اللَّهُ وَمَا يَشْعُرُونَ أَيَّانَ يُبْعَثُونَ ” سورة النمل 65
“በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ ሩቅ ምስጢር አያውቅም፤ ግን አላህ (ያውቀዋል)፤ መቼ እንደሚቀሰቀሱም አያውቁም በላቸው።” (ሱረቱ-ነምል 27፡65)፡፡
” وَعِنْدَهُ مَفَاتِحُ الْغَيْبِ لَا يَعْلَمُهَا إِلَّا هُوَ…” سورة الأنعام 59
“የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው፡፡ ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም…” (ሱረቱል አንዓም 6፡59)፡፡
” عَالِمُ الْغَيْبِ وَالشَّهَادَةِ الْكَبِيرُ الْمُتَعَالِ * سَوَاءٌ مِنْكُمْ مَنْ أَسَرَّ الْقَوْلَ وَمَنْ جَهَرَ بِهِ وَمَنْ هُوَ مُسْتَخْفٍ بِاللَّيْلِ وَسَارِبٌ بِالنَّهَارِ ” سورة الرعد 10-9
“ሩቁንና ቅርቡን ዐዋቂ ታላቅ የላቀ ነው። ከናንተ ውስጥ ቃሉን ዝቅ ያደረገ ሰው፥ በርሱ የጮኸም ሰው፥ እርሱ በሌሊት ተደባቂም፥ በቀን (ተገልጾ) ኺያጅም የሆነ ሰው፥ (እርሱ ዘንድ) እኩል ነው።” (ሱረቱ-ረዕድ 13፡9-10)፡፡
2ኛ/ ጌታ አላህ ለመረጣቸው ነቢያቱና መልክተኞቹ ከዚህ የሩቅ ዕውቀት (ዒልሙል-ገይብ) የፈለገውን ያህል ያሳውቃቸዋል፡፡ የዕውቀት ሁሉ ምንጭ እሱ ነውና፡፡ ይህንንም የአላህ ቃል እንዲህ ይመሰክራል፡-
” عَالِمُ الْغَيْبِ فَلَا يُظْهِرُ عَلَى غَيْبِهِ أَحَدًا * إِلَّا مَنِ ارْتَضَى مِنْ رَسُولٍ فَإِنَّهُ يَسْلُكُ مِنْ بَيْنِ يَدَيْهِ وَمِنْ خَلْفِهِ رَصَدًا ” سورة الجن 27-26
“(እርሱ) ሩቁን ሚስጢር ዐዋቂ ነው፣ በሚስጢሩ ላይ አንድንም አያሳውቅም። ከመልክተኛ ለወደደው ቢሆን እንጅ (ለሌላ አይገልጽም)…” (ሱረቱል ጂን 72፡26-27)፡፡
“…وَمَا كَانَ اللَّهُ لِيُطْلِعَكُمْ عَلَى الْغَيْبِ وَلَكِنَّ اللَّهَ يَجْتَبِي مِنْ رُسُلِهِ مَنْ يَشَاءُ…” سورة آل عمران 179
“…አላህም ሩቁን ነገር የሚያሳውቃችሁ አይደለም፤ ግን አላህ ከመልክተኞቹ የሚሻዉን ይመርጣል…” (ሱረቱ አሊ-ዒምራን 3፡179)፡፡
3ኛ/ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እሱም ቢሆን ለነቢይነቱና ለመልክተኛነቱ ማስረጃና አጋዥ ይሆነው ዘንድ ከፊል የሩቅ ሚስጥር ከጌታው አላህ ዘንድ ተሰጠው እንጂ፡ ሙሉ የሆነ ዕውቀት የለውም፡፡ ከላይ መግቢያ ላይ የተጠቀሰውም ማስረጃ ይህንኑ ሀሳብ የሚደግፍ እንጂ ሁሉን አዋቂነቱን የሚገልጽ አይደለም፡፤ እንዴት የሚሉ ከሆነም፡-
ሀ/ በአይነቱ የተገደበ መሆኑ፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) እነግራችኋለሁ! እያለ ያለው ስለሚመገቡት ምግብ ብቻ ነው፡፡ ስለሚያስቡት፣ ነገ ስለሚደርሳቸው/ስለሚደርስባቸው፣ ስለሚወለደው/ስለሚሞተው… አይደለም፡፡ ከምግብ ጋር ብቻ የተገናኘ ነው፡፡ ይህም በአንድ ነገር ላይ የተገደበ ዕውቀት ብቻ ነው፡፡
ለ/ በቦታ የተገደበ መሆኑ፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) የምትበሉትን እና የምታደልቡትን እንግራችኋለሁ በማለት እየተናገረ ያለው በወቅቱ የተነበሩትን የሱን ቃል የሚሰሙትን ህዝቦች እንጂ፡ በሌላ የምድር ወለል ላይ የሚኖሩ ህዝቦችን አይደለም፡፡ ስለነሱ ማወቅ አይችልምና፡፡ ስለሆነም ‹‹የምትበሉትን›› አለ እንጂ ‹‹የሚበሉትን›› ብሎ ስለሌላው አልተናገረም፡፡
ሐ/ በጊዜ የተገደበ መሆኑ፡- የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) ሰዎቹ ከዚህ በፊት ስለ ተመገቡት ነገር አውቃለሁ አላለም፡፡ ከዚህም በኋላ እስከመጨረሻው የሚበሉትን አውቃለሁ አላለም፡፡ እሱ ያለው “የምትበሉትንና በቤታችሁ የምታደልቡትንም” ብቻ ነው፡፡ ማደለብ ማለት፡- ለነገ ለከነገወዲያ የሚሆን ምግብን ቀድሞ ማከማቸት ማለት ነው፡፤ ለዕድሜ ልክ የሚል ትርጉም ፈፅሞ አይኖረውም፡፡
4ኛ/ የመርየም ልጅ ዒሳ (ዐለይሂ-ሰላም) በአንደበቱ እንደሚመሰክረው፡- እሱ አላህ ዘንድ ያለውን እንደማያውቅና በተቃራኒው ጌታው አላህ ግን በሱ ዘንድ ያለውን ሁሉ እንደሚያውቅ ነው፡፡ ስለዚህ ዒሳ ሁሉን ዐዋቂ አልነበረም፡፡ አይደለምም፡፤ አይሆንምም፡-
“…تَعْلَمُ مَا فِي نَفْسِي وَلَا أَعْلَمُ مَا فِي نَفْسِكَ إِنَّكَ أَنْتَ عَلَّامُ الْغُيُوبِ ” سورة المائدة 116
“…በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ፤ ግን ዘንድ ያለውን አላውቅም፤ አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና” (ሱረቱል ማኢዳህ 5፡116)፡፡
በተሰማሩበት መስክ የሒዳያ ኢስላማዊ ማዕከል አባል በመኾን ዳዕዋውን ማገዝ ከፈለጉ በሚከተለው ማስፈንጠሪያ የአባልነት ቅፅ በመሙላት ሊቀላቀሉን ይችላሉ፦
የአባልነት ፎርሙን ለመሙላት ይህንን ይጫኑ
ማዕከላችንን የሚሰራቸውን ስራዎች በቀጥታ ለመደገፍ፦
አካውንት – 1000499318212
የአካውንት ስም – Hidaya Islamic Center
በአጭር ቁጥር – 8212 መጠቀም ይችላሉ።


